
ከሰባት ዓመት በፊት በጂኒቫ ስዊዘርላንድ በአንድ ዓለም አቀፍ የጠበቆች ቢሮ ውስጥ እሰራ ነበር። አንድ ጀርመናዊ ስማርት ጠበቃ በዚህ ቢሮ ውስጥ አብራን ትሰራ ነበር። በሰዓቱ አብሮን ከሚሰሩት መካከል ሕንዳዊውን ፕራሳድ አንድ ጥያቄ ጠየቀችው። ፕራሳድ ሲበዛ ሊብራል ነው። ግን የሂንዱ እምነት ተከታይ ነው። ጀርመናዊቷ ሕንድ ውስጥ ስላለው የካስት ሥርዓት ጠየቀችው። የሕንድ የካስት ሥርዓት አንድ ሰው በተገኘበት ቤተሰብ መሠረት በማህበረሰብ ውስጥ በዘላቂነት ስለሚኖረው ቦታ የሚወስን ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ከሆነ ዘር፣ ጎሳ እና ቤተሰብ በመወለዱ ምክንያት ብቻ ፥ ሌላው ሰው ፈጽሞ ሊገዛለት እና ዝቅ ሊልለት ይገባል። ጀርመናዊቷ በዚህ ግራ በመጋባት ነበር ይሄን እንዲያስረዳት የጠየቀችው። በተለይ የPHd ዲግሪዋን ስትማር ከሕንድ የመጣ ሌላ የPHd ተማሪ የነበረ ወዳጅ ነበራት። ይሄ ሰው ከእነሱ ጋር በአቻነት ቁጭ ብሎ የሚጫወት እና የሚበላ ነበር። ነገር ግን ከሌላ ካስት የሆነ ሕንዳዊ መጥቶ ሲቀላቀላቸው ፥ ቆሞ ይሄን ሕንዳዊ ማስተናገድ እና ለእርሱ መታዘዝ ጀመረ። ምክንያቱን ተገርመው ሲጠይቁ ያገኙት መልስ “አዲስ የመጣው ሕንዳዊ ከፍ ካለ ካስት እንደሚወለድ ነበር።” ይሄን ልትረዳው አልቻለችም። በተለይ አንድ የPHd ተማሪ የሆነ፣ በትምህርት ችሎታው እና አስተሳሰቡ ምርጥ የሆነ ሰው እንዴት እንደዚህ ዓይነት ስህተት ወይም ጅል እምነት እንደሚይዝ ግራ ተጋብታ ነበር። ፕራሳድም ይሄን በጥልቀት ሊያስረዳት አልቻለም። ምንአልባት እርሱም ያምንበት ይሆናል።
እናንተስ ገጥሞአችሁ አያውቅም? እንዲህ ያለ ግራ መጋባት። እዩ ጭፉን የመሰለ አታላይ ሰውዬን ከልብ አምነው እና የክርስቶስ አገልጋይ ብለው የተቀበሉ በብዙ ነገሮች ምርጥ አዋቂ የሆኑ ሰዎች ገጥሞአችሁ አያውቅም? በብዙ የእውቀት ዘርፍ የማትነቅፏቸው ሰዎች በጅል እምነት ታስረው እና ሁላችን ልክ እንዳልሆነ በምናየው አታላይ ላይ እምነታቸውን ጥለው ተመልክታችሁ አታውቁም? ለምን?
ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ የሚለው አለው። በአካዳሚሽያን እና በኢንቴሌክቿል መካከል ልዩነት አለ ይላል። አካዳሚሽያን ስለአንድ ነገር ያለው እውቀት እጅግ ጥልቅ ነው። ስለሌሎች የሕይወት ጉዳዮች ያለው እውቀት ግን ከመኃይምናን የሚያስመድበው ነው። ኢንቴሌክቿል ግን ስለሕይወት ለመረዳት ነው ዘወትር የሚጥረው። አለማወቅ እና እርግጠኛ አለመሆን አያስፈራውም። ባይሎጂን ብቻ በመረዳት ጥሩ ሕይወት መኖር እንደማይቻል ያውቃል። ስለዚህ ሕይወት ባይሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ጂኦግራፊ ወይም ኬምስትሪ እያለች የምትከፋፍል አይደለችም። በምልዓት ሁሉን ነገር ትተገብራለች እንጂ። እኛ የመረዳት ችግር ኖሮብን የከፋፈልነው ነገርን እንደ ሕይወት መረዳት ስህተት ነው። ለዚህ ነው በሆነ ነገር ምጡቅ የሆኑ ሰዎች በሌሎች ነገሮች ሲጃጃሉ የምናየው። ምክንያቱም እነዚህ ግርግዳ ላይ አንድ ሕይወት የተባለችን ትልቅ ስዕል ለመስቀል ከተቦረቦሩት አንዱ ቀዳዳዎች መካከል ናቸው። ወይም ቀዳዳ ውስጥ የሚገቡ ብሎኖች። ስዕሉን አረጋግቶ ለማቆም ከአንድ ቀዳዳ በላይ፣ ከአንድ ብሎን በላይ ያስፈልጋል።
ሕይወትን በተሻለ የተረዷት እና የተጠቀሙባት እጅግ ብሪሊያንት ያልናቸው ሰዎች አይደሉም። ይልቁንስ በየቀኑ የአስተሳሰብ ጉድለታቸውን እየሞሉ የሚያድሩ እና የዘወትር ተማሪዎች የሆኑ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ለረዥም ጊዜ ሲጃጃሉ አታይዋቸውም። ዘወትር ራሳቸውን ይፈጥራሉ። ራሳቸውን ይሰራሉ። አዲስ ማንነት በመፍጠር ፥ ራሳቸውን የተሻለ ቦታ ላይ ያስቀምጣሉ። ዕድልን ይጠቀማሉ። ዕድልን ይፈጥራሉ፣ ከባከነ ዕድል ይማራሉ።
ግሩም እይታ ነው። በርታልን!
ለምሳሌ የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ስማርት ከሚባሉት ናቸው የተጠቀሙበት ግን ለችግር መፈልፈያ የሆነ ህገ መንግስት ነው ሌሎች የእሳቸው ዘመን ተጋሪዎችም እንዲሁ በተንኮል ይጃጃላሉ ሀሌ ለምን እላለሁ ይሄ ፅሁፍ በሙሉም ባይሆን የተወሰነውን መልሶልኛልና አመሰግናለሁ በርታ እውቀትህን በቀላሉ እንድንረዳ አውርደህ ነውና የምታካፍለን በርታ ወንድማችን የእኔ ጥያቄ ግን ለምንድን ነው በጥቅሉ ስማርት የምንላቸው ሰዎች በአፍራሽ ሚና ላይ የሚሳካላቸው?