በሊዮ ቶሎስቶይ
ትርጉም በሙሉዓለም ጌታቸው
የመጨረሻ ክፍል
6
ባሽኪርሶች እየተከራከሩ እያሉ በቀበሮ ጸጉር የተሰራ ኮፍያ ያጠለቀ ከተፍ አለ። ሁሉም በአንዴ ዝም አሉ ፥ ወዲያውም ቆሙ። አስተራጓሚውም ይሄው የጎሳችን መሪ አለው።
ፋሆም ወዲያው ምርጥ የሆነውን ልብስና ካባ አምጥቶ ስጦታ ሰጠ ፥ አምስት ፓውንድ የሚመዝን የሻይ ቅጠልም አስረከበ። የጎሳውም መሪ ስጦታውን ተቀብሎ በክብር ቦታው ተቀመጠ። ባሽኪርሶች የሆነ ነገር ይነግሩት ጀመር ፥ መሪያቸውም ዝም ብሎ ከሰማ በኋላ በጭንቅላቱ ዝም እንዲሉ ምልክት ሰጠ። ከዛም በራሺይኛ ለፋሆም ራሱ ይነግረው ጀመር እንግዲያውስ የፈለከውን ያህል መሬት ምረጥ እኛ ብዙ መሬት ነው ያለን አለው።
“እንዴት ነው የፈለኩትን ያህል መሬት የምወስደው?” አለ ፋሆም በልቡ። በውል ካላሰርኩት በቀር ከባድ ነው ፥ ነገ ተነስተው ሰጥተንኻል ያሉትን መሬት ቢነጥቁኝስ።
“ስለመልካም ቃላታቹ ከልብ አመሰግናለሁ።” አለ ፋሆም። “እናንተ ብዙ መሬት ነው ያላችሁ እኔ ደግሞ የምፈልገው ጥቂት ነው። ነገር ግን የትኛው መሬት የኔ እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ። ተለክቶ ሊሰጠኝ አይችልምን? ሕይወት እና ሞት በእግዚአብሔር እጅ ነው። እናንተ መልካም ሰዎች መሬቱን ብትሰጡኝም ልጇቻችሁ ግን ሊወስዱብኝ ይችላሉ።”
“በጣም ልክ ነህ አለ መሪው። ላንተ ለክተን እንሰጥኸለን።”
“አንድ ነጋዴ በዚህ እንደነበረ እና በውል አስራችሁ መሬት እንደሰጣችሁት ሰምቻለሁ። እኔም ልክ እንደሱ እንዲሆንልኝ እመኛለሁ” አለ ፋሆም።
የጎሳው መሪውም እንደተረዳው አሳየ።
“ልክ ነው” አለ ፥ “ያ በቀላሉ ሊደረግ ይችላል። በከተማ ጻሐፊ አለ ፥ ወደሱ ሄደን ውሉ በአግባቡ እንዲዘጋጅ እናደርጋለን።”
“ዋጋው ስንት ነው?” አለ ፋሆም።
“ዋጋችን ሁሌ ተመሳሳይ ነው። በቀን አንድ ሺ ሩብልስ።”
ፋሆም አልገባውም።
“አንድ ቀን? ምን ዓይነት መለኪያ ነው እሱ ደግሞ? ምን ያህል ሄክታር መሬት ነው እሱ?”
“እኛ መለካቱን አናውቅበትም። የምንሸጠው በቀን ነው። በእግርህ በቀን ውስጥ መራመድ እስከቻልክበት ድረስ ያንተ ነው እናም ዋጋው አንድ ሺ ነው በቀን።”
ፋሆም ተደነቀ።
“ግን በቀን ውስጥ እጅግ ብዙ መሬት ማዳራስ ይቻላል።” አለ።
የጎሳው መሪ ሳቀ።
“ያንተ ነው እንደዛ ከሆነ። ነገር ግን አንድ ቅድመ ሁኔታ አለ ፥ በዛው ቀን ፥ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ወደተነሳህበት ቦታ ካልመጣክ ገንዘብህ ባክኖ ነው የሚቀረው” አለው።
“እንዴት ነው የተነሳውበትን ቦታ ማስታወስ የምችለው።”
“ለምን እኛ መነሳት የፈለክበት ቦታ አብረንህ አንሄድም? ከዛማ ከዛ ቦታ ትነሳለህ ፥ መቆፈሪያ ከራስህ ጋር ትወስድ እና ምልክት እያኖርክ ትቀጠላለህ። አስፈላጊህ ሲመስልህ ምልክት አኑር፣ በመታጠፊያ ላይ ቆፍር እና ሣር ከምርበት ፥ እኛም ማረሻ ይዘን ከአንዱ ጉድጓድ ወደ ሌላኛው እንሄዳለን።”
ፋሆም በደስታ ፈነደቀ። በሌሊት ለመጀመር ተስማሙ። ከዛም ትንሽ አወጉ፣ ወተት ጠጡ፣ የበጉን ሥጋ በሉ፣ በጋራም ሻይ ጠጡ ከዛም ማታው ሲመጣ ለፋሆም ከላባ የተሰራ አልጋን ለቀቁለት ፥ ባሽኪሮችም ወደየ ድንኳናቸው ተበተኑ ፥ ፀሐይ ሳትወጣ ለመገናኘት ተቀጣጥረው።
VII
ፋሆም በላባ አልጋው ቢጋደምም እንቅልፍ ግን ሊወስደው አልቻለም ፥ ስለመሬቱ ማሰቡን ቀጠለ።
“ምን ያህል ብዙ መሬት ላይ ምልክት ማኖር እችላለሁ?” ብሎ አሰበ። “አምስት ኪሎሜትር እንደሄድኩኝ ውሃ ሊጠማኝ ይችላል። ቀኑ በዚህ ወቅት ረዥም ነው ግን ደግሞ በ35 ኪሎሜትር ውስጥ ምን ያህል መሬት ሊኖር ይችላል። የማይረባውን መሬት ለገባሮቹ ሸጬ አሪፍ የተባለውን ለራሴ አስቅርና አርሳለሁ። ሁለት በሬ ገዝቼ እና ሁለት የጉልበት ሠራተኞችን ቀጥሬ ወደ መቶ ሃምሳ የሚጠጋ ሄክታሩን አርሳለሁ ቀሪውን ደግሞ ከብቶች አረባበታለሁ።”
እልቅልፍ እስከሌሊት ድረስ በዓይኑ ሳይዞር ቆይቶ ሊነጋጋ ሲል ብቻ ትንሽ ጋደም አለ። ወዲያውም ዓይኖቹ ሳይከድኑ ሕልም ማለም ጀመረ። ቅድም በነበሩበት ድንኳን ውስጥ ሆነው ሰዎች ከውጭ ሲያስካኩ ይሰማል። ማን እንደሆነ ለማየት ብድግ ብሎ ሲወጣ የባሽኪሮቹ መሪ በድንኳኑ ፊት ለፊት ተቀምጦ አንድ ጎኑን በአንድ እጁ ተደግፎ ይስቃል። ወደ መሪው ቀረብ ብሎ ፋሆም ጠየቀ ፥ በምንድነው የምትስቀው። ሲጠጋው ግን የበሽኪሮች መሪ አልነበረም ይልቁስ ያ በቤቱ ያለፈው እና ስለበሽኪሮች መሬት የነገረው ነጋዴ ነበር። እዚህ ምን ያህል ቆየክ ብሎ ሊጠይቀው ሲል ወዲያው ሰውዬው ነጋዴው ሳይሆን ፥ ከቮልጋ ወደ አሮጌው ቤቱ የመጣው ያ ጢሰኛ ነበር። ወዲያው ግን ጢሰኛው ሳይሆን ሰይጣን ከነጥፍሮቹ እና ቀንዶቹ ሲያሽካካ እንደሆነ አየ ፥ ፊትለፊቱም አንድ ሱሪ ብቻ የለበሰ ከላዩ የተራቆተ ሰው በመሬት ላይ ተነጥፎ አየ።
መሬት ላይ የተጋደመው ሰውዬው ማን እንደሆነ በአትኩሮት ሲያይ ፥ ሰውዬው መሞቱን አስተዋለ ፥ ያ ሰውም እሱ ነበር። በዚህ ሰዓት ነው ብድግ ብሎ ባኖ ከእንቅልፉ የተነሳው። በድንጋጤ በላብ ሰምጦ ነበር የተነሳው።
"ሰው ስንት ነገር ያልማል? አለ።
በቀዳዳው አሾልኮ ሲያይ ፥ መንጋት ጀምሮ ነበር።
“ልቀሰቅሳቸው ይገባል ፥ አሁን ልንጀምር ይገባል” አለ።
ተነሳቶ ፥ በጋሪው ላይ የተኛውን አገልጋዩን ቀሰቀሰው። ከዛም ወደ ባሽኪሮች አመራ ፥ ሊቀሰቅሳቸው።
"ወደ አውላላው ቦታ የመሄጃ እና መሬቱን የመለኪያ ሰዓቱ ነው" አላቸው።
ባሽኪሮች ተነሱ ፥ አለቃቸውም ተገኘ። እርጓቸውን እና ሻያቸውን ጠጡ ፥ ለፋሆም ቢያቀርቡለትም እሱ ግን የሚያስረፍደው ስለመሰለው መሄድን መረጠ።
“የምንሄድ ከሆነ እንሂድ ፥ ቀኑ ሳይረፍድ” አለ።
VIII
ባሽኪሮች ብድግ ብለው ተነሱ፤ ሁሉም ተዘጋጁ ፥ አንዳንዶቹ በፈረስ ፥ ገሚሶቹ በጋሪ ላይ ተሳፈሩ። ፋሆም ከረዳቱ ጋር በትንሿ ጋሪው ላይ ተሳፈረ ፥ መቆፈሪያም ይዞ ነበር። በሜዳው ሲደርሱ የጠዋቷ ፀሐይ ደም መስላ ቦግ ብላ ነበር። ባሽኪርስ ሺኪያን የተባለው ጉብታ ላይ ወጥተው ከጋሪያቸው እና ከፈረሶቻቸው ወርደው ፥ ሁሉም በአንድ ቦታ ላይ ተሰባሰቡ። መሪያቸውም ወደ ፋሆም ተጠግቶ ተመልከት ይሄ ሁሉ የኛ ነው አለው እጆቹን ዘርግቶ እያሳየው ፥ የፈለከውን መጠን ለራስህ ማድረግ ትችላለህ አለው።
የፋሆም ዓይኖች እንደ ባትሪ አበሩ። መሬቱ እንደ እጆቹ መዳፍ የተዘረጉ ፥ እንደ ሀባብ ፍሬ የጠቆረ አፈር ያለባቸው ነበሩ። የተለያዩ ዓይነት ሣሮችም መሬቶቹ ላይ በቅለው ነበር።
መሪውም በላባ የተሰራውን ካባውን አውልቆ መሬት ላይ በማነጠፍ ፥ ይሄ የመነሻ ምልክትህ ይሁን። ከዚህ እንደጀመርከው ፀሐይ ሳትጠልቅ ከዚህ መድረስ አለብህ። የረገጥከው መሬት ሁሉ ያንተ ይሆናል እዚህ በሰዓቱ ከደረስክ አለው።
ፋሆምም ገንዘቡን አውጥቶ በካባው ላይ አኖረ። ከዛም የውስጥ ሸሚዙ ሲቀር ኮቱን አውልቆ በወገቡ ላይ አጥብቆ አሰረው። ቁራሽ ዳቦም በኮቱ ኪስ ውስጥ ወሸቀ ፥ የኮዳም ውሃን ከቀበቶው ጋር አያይዞ አሰረ። የተሸበሸበውን የቦቲ ጫማውን ወደ ላይ ሳበው። መቆፈሪያውን ከረዳቱ ተቀብሎ ለመሄድ ዝግጁ ሆነ። ለደቂቃ በየት በኩል መጀመር እንዳለበት አሰበ ፥ በሁሉም በኩል ለመሄድ ያጓጓ ነበር።
የትኛውም ያው ነው ብሎ ወሰነ። ወደ ፀሐይ መውጫ በኩል እሄዳለው።
ፊቱን ወደ ፀሐይ መውጫ መለሰ ፥ ጥቂት ተሳበ እና ፀሐይዋ በራሱ ላይ እስከምትሆን ጠበቀ።
ሰዓት ማባከን የለብኝም ሲል አሰበ። ደግሞ ፀሐዩ ሳይከር መጀመር ይሻላል ብሎ ተነሳ።
የፀሐይዋ ጨረር ገና ወደ ፋሆም አልደረሰም ነበር ፥ መቆፈሪያውን በትከሻው ላይ አኑሮ ወደ ሜዳው አቀና።
ፋሆም ሳያዘግምም ፥ ሳይፈጥንም መጓዙን ቀጠለ። ወደ ዘጠኝ መቶ ሜትር እንደሄደ ጉድጓድ ቆፍሮ ሰርዶ ደራረበበት ፥ በግልጽ እንዲታይ። ከዛም ቀጠለ፤ አሁን ሰውነቱ ስለተሟሟቀ እርምጃውን ጨመረ። ከዛም አሁንም ጉድጓድ ቆፈረ።
ፋሆም ወደ ጀርባው ተመለከተ። ጉብታው በግልጽ ይታይ ነበር ፥ ሰዎች በላይ ቆመው ፥ ከአንጸባራቂ የጋሪ ጎማዎች ጋር። በግምት ወደ አራት ኪሎሜትር እንደመጣ ደመደመ። መሞቅ ስለጀመረ ፥ ኮቱን ፈቶ በጭንቅላቱ ላይ አኖረ። ከዛም ጉዞውን ቀጠለ። ከበፊቱ የበለጠ መሞቅ ስለጀመረ ፥ ቀና ብሎ ፀሐይዋን ተመለከተ። አሁን የቁርስ ሰዓት ነው።
“የመጀመሪያው ዙር ተጠናቋል ነገር ግን በቀን ውስጥ አራት ዙሮች አሉ። ለመመለስ በጣም ገና ነው ፥ ነገር ግን ቦቲዬ አወልቃለው” አለ ለራሱ።
“ሌላ አራት ኪሎሜትር ሄድ እና ወደ ግራ እታጠፋለሁ። ይሄ ቦታ በጣም አስገራሚ ነው ፥ ፈጽሞ ማጣት የለብኝም። በሄድኩኝ መጠን መሬቱ የሚያስገርም ነው እየሆነ” አለ።
ጥቂት ወደፊት እንደተራመደ ዞር ብሎ ሲያይ ጉብታው በችግር ነው የሚታየው ፥ በሱ ላይ የቆሙት ሰዎች ጉንዳን ነው የሚመስሉት ፥ ከፀሐዩ ጋር የሆነ የሚያንጸባርቅ ነገር ይታያል።
“አሃ!” አለ ፋሆም ፥ “በዚህ አቅጣጫ ብዙ ሄጃለሁ ማለት ነው ፥ አሁን የመታጠፊያ ጊዜ ነው። ደግሞም ብዙ አልቦኛል ፥ ውሃም ለጉድ ጠምቶኛል።”
ቆሞ መሬቱን በመቆፈር ሰርዶ ከመረበት። ከዛም የውሃውን ኮዳ ከቀበቶው በማላቀቅ ከጠጣ በኋላ ፥ እንዲሁ ወደ ግራ ታጠፈ። መራመዱን ቀጠለ ፥ ጉዞውን ቀጠለ። ሣሮቹ በጣም ያደጉ፣ ሙቀቱ ሐሩር ነበር።
ፋሆም ጉልበቱ መድከም ጀመረ። ፀሐይዋን ሲመለከት እኩለ ቀን ነው ብሎ ገመተ።
“እንግዲያውስ ፥ የግድ ማረፍ” አለብኝ አለ።
ተቀምጦ ትንሽ ዳቦ በላ ውሃም ጠጣ። ነገር ግን መጋደም አልፈለገም ፥ እንቅልፍ ይወስደኛል ብሎ ስለሰጋ። ትንሽ እንደተቀመጠ ፥ ጉዞውን ቀጠለ። መጀመሪያ በቀላሉ ተራመደ የበላው ዳቦ ጉልበት ስለሆነው ፥ ግን ሙቀቱ እጅግ ስለጨመረ ፥ እንቅልፉ መጣ። መሄዱን ግን አላቋረጠም ፥ ለራሱም “ለሰዓታት መሰቃየት ከዛ በሕይወት ሁሉ መደሰት።” አለ።
በጣም ርቆ ከሄደ በኋላ ወደ ግራ ሊታጠፍ ነበር ፥ ርጥብ ለጥ ያለ መሬት ያየ ስለመሰለው "ይሄን'ማ መተው የለብኝም ፥ በተለይ ለተልባ የተመቸ መሬት ነው" አለ። ስለዚህ ወደ ስፍራው ሄዶ ጉድጓድ በመቆፈር ምልክት ካኖረ በኋላ ታጠፈ። ወደ ጉብታው ሲመለከት ፥ ዓየሩ ብዥ ብሏል። የሚንቀጠቀጥ ይመስላል በዚህም ምክንያት ምንም የሚታይ ነገር አልነበረም።
“አሃ! ይሄ ማለት በዚህ በኩል ብዙ መጥቻለው ፥ በዚህ አቅጣጫ ግን ብዙ መሄድ የለብኝም” አለ። ስለዚህ በሦስተኛው መታጠፊያ በፍጥነት ተራመደ። ወደ ፀሐይ ሲመለከት ከአድማሱ ግማሽ ሆኗል ፥ በዚህ መስመር ገና ሦስት ኪሎሜትር ራሱ አልሄደም። የሱ ግብ እስከ አስራ አምስት ኪሎሜትር ለማካለል ነው።
“አይሆንም" አለ፤ "ይሄ መሬቴን በአንድ አቅጣጫ የተጣመመ ያደርገዋል ግን ወደ ኋላ ቀጥታ በፍጥነት መመለስ አለብኝ። ብዙ ርቀት መጥቻለው ፥ እንዲሁ እንዳለ እንኳን በጣም ብዙ መሬት ነው ያለኝ።"
ስለዚህ ፋሆም ቶሎ ቶሎ መቆፈር ጀመረ ፥ ወደ ጉብታው በቀጥታ መመለስ ጀመር።
11
ፋሆም ወደ ጉብታው ቢመለስም ጉልበቱ ግን በጣም ታዳክሞ ነበር። በሙቀቱ ሰውነቱ ዝሎ ነበር ፥ እግሮቹ ተበሳስቶ እና ተቆራርጧል ፥ ሰንበር በሰንበር ሆኗል ፥ እግሮቹ አልታዘዝ ማለት ጀመሩ።
ለማረፍ ጓጓ ነገር ግን ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት መድረስ ከፈለገ ማረፍ የማይታሰብ ነው። ፀሐይ ማንንም አይጠብቅም ፥ ቀስ በቀስ ወደ መጥለቂያዋ እያጋደለች ነበር።
“ኦ ጌታ ሆይ ፥ ብዙ ለማግኘት ስል ጊዜዬን ባላጠፋ ኖሮ” አለ ፥ “አርፍጄ ይሆን?” ሲል ሰጋ።
ወደ ጉብታው ከዛ ደግሞ ወደ ፀሐይ መጥለቂያ ተመለከተ።ፀሐይዋ ወደ መግቢያዋ ቦታ ደርሳለች።
ፋሆም ተራመደ ፥ አሁንም ተራመደ ነገር ግን መራመድ ከባድ ነበር። ለመፍጠን ፥ ለመራመድ ቢጥርም።
ተጫነው ራሱን ፥ ነገር ግን አሁንም ከጉብታው በጣም ሩቅ ነበር። መሮጥ ጀመረ፣ ኮቱን ወረወረ፣ ቦቲውን ጣለ፣ ኮዳውን ተወው ፥ እንደ መደገፊያም ያገለገለውን መቆፈሪያውን ብቻ በትከሻው አስቀርቶ።
ምን ማድረግ ይሻለኛል ሲል በድጋሚ አሰበ፣ ብዙ ሰበሰብኩኝ እና ሁሉን አበላሸውት። ፀሐይ ሳትጠልቅ መድረስ አልችልም።
ፍርሃቱ ደግሞ ትንፋሹን አቆራረጠው ፥ ፋሆም አሁንም መሮጡን ቀጠለ ፥ ሸሚዙ በላብ ሰመጠ፣ ሱሪው በላብ ከሰውነቱ ጋር፣ አፉ ከከንፈሩ ጋር በድርቀት ተጣበቀ። ጡቶቹ እንደ ቀጥቃጭ ወናፍ ሆኑ ፥ ልቡ እንደ ከበሮ ይመታ ጀመር ፥ እግሮቹ የሰውነቱ አካል እንዳልሆኑ ነገር ይክዱት ጀመር። ፋሆም የሚሞት ስለመሰለው በድንጋጤ ተዋጠ። ነገር ግን የሚሞት ቢመስለውም ከመሮጥ ግን አልቆመም።
ይሄን ሁሉ መጥቼ እዚህ ደርሼ ከቆምኩማ ፥ ጅል ነው የሚሉኝ። ሮጠ ፥ ራሱን እየገፋ ቀጠለ። የባክሺሮቹን ጩኸት እና ድምጽ ሲሰማ ፥ ልቡን የበለጠ አሞቀው። ያለውን የመጨረሻ ጉልበት ሰብስቦ ሮጠ።
ፀሐይዋ ወደ መጥለቂያዋ ደረሰች ፥ የከበባት ደመና ጨመረ ፥ ልክ እንደ ደም ቀይ መሰለች። “አሁን ፥ አዎ! አሁን ፥ የመግቢያዋ ሰዓት ደረሰ ፥ እሱም ግን ወደ ግቡ ቀርቦ ነበር። ፋሆም በጉብታው ላይ ያሉ ባሽኪሮች እንዲፈጥን እጃቸውን ሲወዘውዙ ይታየዋል። መሬት ላይ የተዘረጋው ያ የላባ ካባ ፥ በሱ ላይ የተቀመጠው ገንዘብ ይታየዋል፤ መሪው ወገቡን ይዞ መሬት ተቀምጦ ይታየዋል። ፋሆም ህልሙን አስታወሰ።
"በጣም ብዙ መሬት አለ" ሲል አሰበ "ግን እግዚአብሔር እንድኖርበት ይፈቅድልኛል?" ሲል አሰበ። ሕይወቴን አጣው ፥ ሕይወቴን አጣው ፥ በፍጹም እዛ ጋር አልደርስም።
ፋሆም ፀሐይን ቀና ብሎ አያት ፥ ግማሽ ጎኗ ብቻ ቀርቷል። በቀረው ጥንካሬ ሁሉ ፥ ግማሽ አካሉን ወደፊት ዘርግቶ ሞከረ ፥ ወገቡ ታጠፈ ፥ አብረውት ሊጓዙ ያልቻሉትን እግሮቹን ትቶ ይሄድ ይመስል ተውተረተረ። ወደ ጉብታው ሲደርስ ፥ ጨለመ። ወደ ፀሐይ ሲመለከት ፥ የለችም።
አለቀሰ ፥ ልፋቴ ሁሉ በከንቱ ነበር አለ ፥ ሊቆም ሲል ከላይ ያሉት ባሽኪሮች አሁንም እየጨውለት ነበር። የሆነ ነገር ትዝ አለው ፥ “ከዚህ ታች ፀሐይ የጠለቀች ብትመስልም ለእነሱ ከላይ ግን አሁንም ገና ትታያቸዋለች።” በረዥሙ ተንፍሶ ወደ ላይ ሮጠ። ከላይ ገና ብርሃን ነበር። ጫፍ ላይ ሲደርስ ካባውን አየው። ከፊት ለፊቱ ፥ መሪያቸው ተቀምጦ ወገቡን ይዞ ይስቃል። ፋሆም በድጋሚ ህልሙን አስታወሰ ፥ የሲቃ ድምጽ አወጣ ፥ ወደፊት በመውደቅ ካባውን በእጆቹ ነካቸው።
“አሃ! ፥ ይበቃል ወዳጆቻችን” አለ በኃያል ድምጽ መሪው ፥ “እጅግ ብዙ መሬት አግኝቷል።”
የፋሆም ረዳት እየሮጠ መጥቶ ሊያነሳው ሞከረ፣ ነገር ግን ደም ከአፉ መውጣት ጀመር። ፋሆም ሞተ።
ባክሺሮች በምላሳቸው ድምጽ በማውጣት ሐዘናቸውን ገለጡ።
የፋሆም ረዳት መቆፈሪያውን አንስቶ ለፋሆም የሚበቃ ጉድጓድ ቆፈረ ፥ በዛም ውስጥ ቀበረው። ከራሱ እስከ እግሩ መቶ ሰማንያ ሴንቲሜትር ብቻ ነበር ያስፈለገው።

コメント