
ጥንታውያን የቼዝ ጨዋታን እንደ ጦር ስትራቴጂ እና የሕይወት ትምህርት ለመቅሰም ይጠቀሙበት ነበር። በቼዝ ጨዋታ የሁለቱም ተጫዎቾች ዓላማ ንጉሱን መጠበቅ ነው። (በአንዳንድ ሀገሮች ንግስቲቱን ሚኒስትር ንጉሱን ደግሞ ንግስቲቱ ብለው ይጠራሉ)። ወታደሮች፣ ፈረሶች፣ ቢሾፖች፣ ዘቦች እና ንግስቲቱ ዓላማቸው የራሳቸውን ንጉስ ጠብቀው የሌላኛውን ንጉስ መፈናፈኛ ማሳጣት ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ተልዕኮ የላቸውም። የራስን ንጉስ ከጥቃት መጠበቅ፤ የሌላኛውን ንጉስ በማጥቃት መሄጃ ማሳጣት።
ከዚህ ውጪ ያለው ሁሉ የጌሙ (የጫወታው) ውበት እንጂ ዓላማ አይደለም። በዚህ ጫወታ ውስጥ ሁሉንም ነገር አጥተህ ንጉስህን አስጠብቀህ ማሸነፍ ከቻልክ ድል ነው። ወታደሮች፣ ፈረሶችህ፣ ካህናትህ ሳይነኩብህ ንጉስህ ጥቃት ደርሶበት ልትሸነፍ ትችላለህ። ከሩቅ ለሚያየው ሁሉ ነገር ስላለህ የተሸነፈክ ላይመስል ይችላል። ከቅርብ ለሚያየው እና የጌሙን ሕግ ለሚረዳ ግን የንጉስህን ሁኔታ ተመልክቶ እንዳለቀልህ ሊገባው ይችላል። ስለዚህ ብዙ ፍሬዎች (pieces) አሉ ወይም የሉህም አይደለም ቁምነገሩ፤ ዋናው ነገር “ንጉስህ እንዴት ነው?” ነው።
ልክ እንደቼዝ የትኛውም ሕይወት አንድ ንጉስ ነው ያለው። ሕይወታችን በጫወታው የሕግ ብዛት፣ በውስብስብ ማህበረሰባዊ ጥልፍልፍ መዋቅሮች እና መጠብቆች (expectations) ንጉሱ ካልተሰወረበት በቀር ንጉሱ አንድ ነው። የሰው ልጅ የዚህ ምድር ግብ ደስተኛ መሆን ነው። በግለሰብም ሆነ በቡድን የምናደርጋቸው ትግሎች መሠረታዊው ምሰሶ ደስታ ነው። ልክ እንደ ቼዝ የማሸነፊያ መንገዶች ሺ ዓይነት እንደሆኑ ሁሉ፣ በሕይወትም ሰዎች ደስተኛ የሚሆኑበት እሱም በዘላቂነት ደስተኛ የሚሆኑበት መንገድ ለየቅል ነው።
ለምሳሌ በጎግል በአንደኛ ደረጃ በዓለም ዙሪያ የተጠየቀ ጥያቄ “ምን ልመልከት?” (what to watch) የሚል ነው። ይሄ ሰዎች ራሳቸውን ለማዝናናት (ደስተኛ ለመሆን) የሚያነሱት ጥያቄ ነው። ሲ ኤስ ሉዊስ ሕመም ትልቁ “የእውነት ገላጭ መሳሪያ ነው” “Pain exposes reality” ይላል። ሰው ሲታመም ከምንም ነገር በላይ ምን ወሳኝ እንደሆነ ይገባዋል። በዛ የሕመም ወቅት የሕይወት ጥያቄ ሁሉ ተሰብስቦ አንድ ብቻ ይሆናል። እሱም ከዛ ሕመም ለጥቂት ጊዜ እንኳ ረፍት ማግኘት።
ይሄ ማለት ግን ምቾት እና ድሎት ነው ሰውን ደስተኛ የሚያደርገው ማለት ላይሆን ይችላል። ሰዎች ትርጉም የምንፈልግ ፍጥረት ነን። ይሄ ማለት ሌሎች እንስሳት ትርጉም አይፈልጉም ማለት ላይሆን ይችላል። እኛ በብዙ መንገድ በዓይናችን ከምናያቸው ፍጥረታት በላይ ውስብስብ ነን። ከዛ በተጨማሪም ነገሮችን የምንረዳበት መንገድም ደስተኛ በመሆን ላይ የራሱ ገጽታ አለው። በተለይ ሕይወትን በንጽጽር ብቻ መገንዘብ መቻላችን፤ ምቾትን፣ ጤናን፣ ረፍትን፣ እፎይታን ያለ ድካም፣ ሕመም እና ተግዳሮት ማጣጣም እንዳንችል አድርጎናል።
ቅዱስ ቶማስ አኩዋይነስ እንዳለው “ልክ ጸጥታ የዝማሬያችን ውበት እንደሆነው ፥ መከራ ነው፣ ስቃይ ነው፣ ክፋት ነው የበጎ ነገርን እውቀት የሰጠን።” ያለ ክፋት በጎነት ለሰው ልጆች አዕምሮ ግልጽ አይደለም። ያለ ሕመም ጤናን የሚረዳው አይኖርም ነበር። ደስተኛ ለመሆን ከደስታ ተቃራኒ የሆኑ የሕይወት ክፍሎች የግድ ያስፈልጉናል። ረፍትን ያለ ድካም ማጣጣም አይቻልም። የጤና ትርጉም ከሕመም ነው የሚመነጨው።
ይሄን የምዘረዝረው “የሰው ልጅ ንጉስ የሆነው ደስታ እንዲው በቀላሉ የሚጠበቅ አይደለም” የሚለውን ለማሳየት ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን ለመከራ እና ስቃይ ያልተጋለጠ ሕይወት ደስታን ማግኘት አይቻለውም። በምቾት ውስጥ ካለ ሰው ይልቅ ከመከራ ወደ ምቾት የመጣ ሰው በሕይወት የበለጠ ደስተኛ ነው። ለዚህም ይመስላል እንደ ፊንላንድ ያሉ በHappiness Index እንዴክስ እና በምቾት ከፍተኛ ደረጃ ያስመዘገቡ ሀገሮች በተመሳሳይ ራስን በማጥፋትም (suicide rate) ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገቡት።
በቼዝ ውስጥ ከሁሉም በላይ ደካማው ንጉሱ ነው። ግን ደግሞ ንጉስ ነው። ከሁሉም በላይ ራሱን መጠበቅ የማይችለው ንጉሱ ነው። ከሁሉም በላይ ቀርፋፋው ንጉሱ ነው። በኛ ሕይወትም በሁሉም አቅጣጫ በቀላሉ ሊጠቃ የሚችለው ደስታችን ነው። መቼም ርግጠኛ የማንሆንበት ነገርም ደስታችን ነው። ከደቂቃዎች በፊት እየሳቀ የነበረ ሰው ሊያለቅስ ይችላል። ይሄን ከመፍራት የምስራቁ ዓለም ደስታን መግለጥ ላይ ገደብ ያኖራል። የምስራቁ ዓለም ማህበረሰባዊ ስለሆነ (በንጽጽር ለማስቀመጥ እንጂ ሁሉም ማህበረሰባዊ ነው)፤ ደስታው በቀላሉ ሊታጠፍ እንደሚችል ስለሚገባው የሚያስፈነድቀው ነገር ሲኖር ራሱ ያን በገደብ ነው የሚገልጸው። በዚህም በኋላ ከሚመጣ ማህበረሰባዊ ሀሜት ራሱን ይጠብቃል።
በቼዝ ሁሉም ፍሬዎች (pieces) እያሉህ፤ ንጉስህ ቼክ ተብሎ ከጫወታ ልትወጣ ትችላለህ። በተመሳሳይ በሕይወት ሁሉም ነገር እያላቸው ግን ፍጹም የሆነ ስቃይ ውስጥ የሚኖሩ አሉ። በተቃራኒው አብዛኛውን ፍሬዎች (pieces) አጥተው የቼዝን ጫወታ የሚያሸንፉ አሉ። ልክ እንደ ቼዙ ብዙ የቁስ ክምችት ያላፈናቸው ሰዎች ግን አስገራሚ ደስታ እና ርካታ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ የሕይወት ስትራቴጂስቶች ናቸው። በሕይወት ውስጥ ንጉሳቸውን እንዴት አድርገው መጠበቅ እንዳለባቸው የተረዱ እና ለራሳቸው የሚስማማ እና ራሳቸውን የሚመስል የጌም ፕላን አውጥተው የሚጫወቱ ሰዎች ናቸው። እስቲ ሪፍሌክት አድርጉ። እያደረጋችሁት ያለው ነገር በረዥም ጊዜ ውስጥ ደስተኛ ሕይወትን እንድትመሩ የሚያደርጋችሁ ነው? ወይስ ምንን በዚህ ሕይወት መጠበቅ እንዳለብን አስበንበት አናውቅም።
Comentarios