
ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ ነው ይሄ ሩጫ የፍጽምና ሩጫ ነው ያለው። መጨረሻው የሌላ ነገር መጀመሪያ እንጂ በርግጥም መጨረሻ አይደለም ያለው። በዚህ ሕይወት እስካለን ድረስ እያንዳንዱ ግብ ፥ የሌላ ሕይወት መጀመሪያ ነው። እያንዳንዱ መጨረሻ ፥ የሌላ ሕይወት መነሻ ነው።
ቻርልስ ቢኮወስኪ “ይሄ ሕይወት፦ ያሁኑ፤ ያለፈው ሁሉ ያንተ ነው” ሲል ፥ በዚህ ሕይወት ለውድቀትህም ሆነ ለድልህ ከአንተ በላይ ተጠያቂ የለም እያለህ ነው። ያንተ እና ያንተ ብቻ ነው። ያነሰ ኃላፊነት አትውሰድ። ለዚህ ነው በዚህ ሕይወት በሌሎች ፍልስፍና፣ በሌሎች አረዳድ እና በሌሎች የመገንዘብ ችሎታ የራስን ሕይወት መምራት ሕይወትን ማባከን ነው። ሰው ምን ይለኛል ብለህ ይሄን አንድ ሕይወት፣ ይሄን ያንተ የሆነውን ስጦታ ሕይወት ለማህበረሰብ አትስጥ። “ለምን ይሉኛል” ባርነት አትንበርከክ። በዚህ ዓለም የመኖሪያ ማብቂያ ሰዓት ላይ እንዴት ያለ ጅል እንደነበርክ የሚገባህ ፥ ስለራሱ እንጂ ስለአንተ ግድ ስለማይሰጠው ዓለም ስትጨነቅ ህልምህን አለመኖርህ ሲገለጥልህ ነው።
ቆም ብለህ አስብ። የትኛው ኢንዶክትርኔሽን ነው ጨፍልቆህ ያለው? ደስተኛ ያልሆነ ሕይወት እና ኑሮ ውስጥ የነከረ? ለምን? ምንአልባት ያለህበትን ሁኔታ መቀየር አትችል ይሆናል። በርግጠኝነት ግን ላለህበት ሁኔታ ባሪያ አለመሆን ትችላለህ። በሚዲያ፣ በማጉያ፣ በቲዎሎጂ፣ በፖለቲካ፣ በቡና ወሬ አንተን የስብስባቸው ቁጥር፣ የእነርሱ ህልውና ማስረጃ፣ የእንጀራቸው ማብሰያ ከሚያደርጉህ ተላቀ፤ በማፈር እና በፍርሃት የሸመቀቃትን ነፍስ ነጻ ስታወጣት ብቻ ፥ የፍልስፍናቸው ኦናነት ይገለጥልሃል። ለራስህ እውነተኛ ስትሆን ፥ ብዙዎችን ትማርካለህ። ከዘመንህም መሻገር ትችላለህ።
Comentarios