
አውግስጢኖስ በ'City of God" መጽሐፉ ስለዚህ ዓለም ደስታ እና ስቃይ እንዲህ ይላል ፥ "የዚህ ዓለም ደስታ ለኃጥዕም ለጻዲቅም ይሰጣሉ፣ ዝናቡን ለሁለቱም እንደሚያወጣ፣ ፀሐይንም ለኃጥዑም ለጻድቁም እንደሚያቆማት። ይሄን ያደረገው የዚህ ዓለም መልካም ነገር ምንም አለመሆኑን ለመረጡት እና ለወደዱት ሲነግራቸው ነው፤ ይሄ ብቻ ግን አይደለም በመግቦቱ ቸርነት ኃጥአን ወደእሱ እንዲሳቡም እንጂ።
መከራም በኃጥዕሙ በጻድቁም ላይ ይመጣል፤ ጻድቁን ግን እንደወርቅ እያነጻው ፥ በመከራ እሳት ሲያልፍ ያበራል። ኃጥዕን ግን በጻድቃን ላይ የደረሰው መከራ ቢደርስባቸውም ያ ወርቅ የሆነውን ጻድቅ ያነጻ እሳት ፥ ገለባ የሆነውን ኃጥዕ ግን ያጨሰዋል። ያ እሳት ለአንዱ ውበት ለሌው ጭስ ይሆናል።
አንዱ መስቀል በቀኝ ለተሰቀለው የገነት መግቢያ ቁልፍ ሲሆን ፥ ያው መስቀል በግራ ለተሰቀለው የሲዖል ሩጫውን አፋጠነው። በክርስቶስ ለሆኑት በዚህ ዓለም ደስታ እና መከራ መካከል አንዳች ልዩነት የለም።
ሁለቱም የምስጋና ምንጮች ናቸው። አጥንታችንን ሰብሮ ሲጠግነን ፥ ያን የምህረት ፏፏቴ ነፍሳችን ታሸተዋለች። በበረክት ሲሞላንም ያን የቸርነት ምንጭ ፥ ነፍሳችን ትጠጣዋለች።
ለኃጥዓንም እንደዚሁ። በዚህ ዓለም ደስታ እና መከራ መካከል ምንም ልዩነት የለውም። ሲያገኙ በትዕቢት የአምላክን መኖር ረስተው፣ በደሃው ላይ ይረማመዳሉ፣ በሆዳምነት እና በትዕቢት ወደ ጥልቁ ይሰምጣሉ።
በመከራ ደግሞ አፋቸውን በአምላካችን ላይ ይከፍታሉ፣ ይረግሙታል፣ አንተ ብትኖር ይሄ ሁሉ ይደረጋል ይላሉ፣ እስቲ ካለህ አሳየን እያሉ አምላካችንን እኩያቸው ያደርጉታል ፥ በዝምታው የፍቅርን በር ቢከፍትላቸውም እነሱ ግን በመታወራቸው የሲዖልን በር በርግደው ከውስጥ በራሳቸው ላይ ይቀረቅሩታል።"
በሌላም ጎኑ በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ነገሮች በኛ አጠቃቀም ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እኔ ቢላዋ መጀመሪያ ለምን ጉዳይ እንደተፈጠረ አላውቅም። ግን አንዳንድ ሰዎች መልካሙን ምግብ ለማዘጋጀት ቢላዋን ለመክተፊያነት ይጠቀማሉ። አንዳንዶች ግን ይሄንኑ ተመሳሳይ ነገር ምትክ አልባውን የሰውን ልጅ ሕይወት ለማጥፋት ቢላዋን ይጠቀሙታል። በዚህ ዓለም ያለ አብዛኛው ነገሮች እንደ ቢላዋ ናቸው። የኛ እጆች ናቸው ውጤቱን የሚወስኑት። ለአንዱ የገነት መግቢያ የነበረ መስቀል ፥ ለአንዱ የሲዖል ድልድይ ይሆናል። መስቀልነቱ አይደለም የተቀየረው። በመስቀሉ ላይ የሰፈሩት ራሶች እንጂ።
ለአንዱ ክፉ የሆነውን አጋጣሚ፣ አንዱ ግን ያንኑ መሳሪያ የበረከት ውሃ ለማፍለቅ ይጠቀምበታል። በዚህ ዓለም ትልቁ ጦርነት የሚካሄደው በውስጣችን ነው። በስሜት እና በእውቀት መኃል። ስሜት ፈጽሞ በእውቀት፣ በቁጥር፣ በማስረጃ እና በምክንያት መመራት አይወድም። ግን እንደዛም ሆኖ እጅግ ኃይለኛ ነው። ማንም ከስሜቱ ጋር ፊትለፊት ጦርነት ገጥሞ አያሸንፍም። ቅዱስ ጳውሎስ ሳይቀር “ማድረግ የምወደውን ሳይሆን ማድረግ ያልፈለኩትን፣ በብልቶቼ ላይ ግን የሰለጠነውን ያንን አደርጋለሁ” አለ። የምክንያት ክፍላችን ደግሞ በማስረጃ እና ምክንያት፣ በቁጥር እና በማመዛዘን ይመራል።
ይሄ ክፍላችን ስሜትን በጥበብ የረታ ቀን ፥ በኛ ፊት ውድቀት ፀሐይ የለውም። ያን ለማድረግ ግን ይሄን ጦርነት በጥልቀት መገንዘብ ያስፈልጋል። ያለረፍት ሪፍሌክት ማድረግ የሕይወት አንኳር ተግባራችን መሆን አለበት። እውነትን ማወቅ እና ማግኘት የሚያስደስተን መሆን አለበት። የዛኔ ለአንዱ ክፉ የሆነው ነገር ለኛ ጥቅሙ ይታየናል። ራሳችንን ከእውነት ጋር አስታርቀን መጓዝ አይቸግረንም። የዛኔ እኛ የያዝነው ቢላዋ የሌሎች መጥገቢያ እንጂ መቅጠፊያ አይሆንም። የነካው ሁሉ ይባረክለታል የሚለው ይሄን እጅ ነው። እንደ ኢዮብ ያለ እጅን። በመጥገብም ሆነ በመጉደል በፊቱ እና በአንደበቱ አምላኩን በድሎ የማያውቅ ሰው የያዘው ቢላዋ ማንንም አያስፈራም።
ያ ሰው ስሜቱን ለምክንያት ያስገዛ ነው። ያ ሰው በውስጡ ያለውን ጦርነት ያሸነፈ ነው። ያ ሰው ሀገርን ከሚገዛ በላይ ገዢ ነው። ሀገር ገዢው ፈጽሞ ሊገዛ ያልቻለውን የውስጡን የስሜት ፈረስ በቀጭን የማስተዋል ክር ወደ ፈቀደው ይስበዋልና።
Comments