top of page
Search

ምንድነው የተማርኩት?

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • May 18
  • 2 min read




የሰንበት ዕይታ ዓላማ ሳምንታዊ ግምገማ ነው። “ምንድነው በዚህ ሳምንት የተማርኩት?” የሚል ግምገማ። ረጋ ብሎ፣ ዝግ ብሎ፣ ቆም ብሎ፣ ወደ ኋላ በማየት ስለወደፊቱ የማሰብ አቅምን የማግኘት የሪፍሌክሽን ማዕድ ነው። ዝም ብሎ ላለመሮጥ የመወሰን የመንገድ ጉብታ ነው። ይሄ ለጥ ያለ አስፓልት ላይ ሳምንታዊ እብጠት ነው። ፍሬን ተይዞ ፥ “ምን ያህል መጣው እስካሁን ፥ ቀሪውንስ እንዴት ልጓዝ?” የምልበት ማቀዝቀዧዬ ነው።



ፍጹሙ ሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይቀር ራቅ ብሎ ወደ ተራራ በመውጣት፣ ለአንድ አፍታ ከሰው መንጋ ፥ ከተከታዮች አድናቆት እና ክብር ራቅ ብሎ ፥ እርሱ እና አባቱ ብቻ ወደ ሚነጋገሩበት ርጋታ እና ዝምታ ይሰወር ነበር።



“ምንድነው እያደረኩኝ ያለውት? የት ነው ይሄ የሚያደርሰኝ? ምን አስቤ ነው እዚህ ድረስ የመጣውት? ከዚህስ በኋላ እንዴት ነው ልጓዝ እያሰብኩኝ ያለውት?” የምንልበት የጸጥታ በዓት ያስፈልገናል።



ከተርዕዮ ሱስ ራቅ ብለን ፥ ወደ ውስጥ የምንመለከትበት የርጋታ ጉብታ ላይ መውጣት ያሻል። ለእኔ ያ መጻፍ ነው። ከራሴ ጋር የማወራበት፣ ማደርገውን ነገር በምክንያት የምሞግትበት፣ ከመውቀጥ፣ ከመደለቅ፣ ከመሰልጠቅ ሩቅ ወደ ሆነው የመመሰጥ እና የማሰብ ሀገር የምሄድበት ነው የሰንበት ዕይታ።



“ምንድነው የተማርኩት?” የምልበት። ብሩስ ሊፕተን የእንጀራ አባቱን ሞት ሲገልጽ እንዲህ ይላል። “የእንጀራ አባቴ ለአንድ ሳምንት ኮማ ውስጥ ገብቶ ቆይቶ በመጨረሻ ትንፋሹ ሰዓት ብድግ ብሎ ተነሳ። ከየት አመጣው በሚያስብል በታላቅ አቅም ነበር ብድግ ያለው። ‘በሕይወቴ ሁሉ አንድ ቀን ደስ ብሎኝ አያውቅም’ የሚለውን ቃል ተናግሮ እስከወዲያኛው ጸጥ አለ። ከዛ ቀን ጀምሮ ስሞት እንዲህ ላለማለት ወሰንኩኝ” ይላል ብሩስ ሊፕተን።



ብዙ ሰው በሕይወት ዘግይቶ ይነቃ እና “ለዚህ ነበር!”ይላል። “ከቤተሰቦቼ ጋር ተጋጭቼ የኖርኩት ለዚህ ነበር?” ይላል። “ያንን ሁሉ ሰው ያሳዘንኩት ለዚህ ነበር?” ይላል። “በማይረባውም በሚረባውም ስባዝን እና ስጨነቅ የኖርኩት ለዚህ ነበር?” ይላል። በእስትንፋሱ መጨረሻ ሰዓታት ላይ ይነቃ እና “ለዚህ ነበር!” ይላል።



ከዛ የሚጠብቀን የመንገድ ጉብታ ፥ አስገድዶን ፍሬን የሚያሲዘን እና ቆም ብለን በጥልቀት እንድናስብ የሚያደርገን የማሰላሰያ አዋሻዊ የርጋታ የዝምታ ጉብታ ያስፈልገናል።



እንደ ማርከስ አርሊየስ እያሰብ ከእውነታ ጋር የምንጋፈጥበት ጉብታ። በቅርብ ሁሉን ነገር ትረሳለህ። በቅርብ በሁሉ ትረሳለህ። በዚህ እውነታ ውስጥ ነው ያለነው። በቅርብ የግርግዳ ፎቶ ትሆናለህ። ከዛም ከምንም ነገር ላይ ትወርዳለህ። በዚህ ሳይክል ውስጥ ነው ያለኸው። ስለዚህ ምን እያደረክ ነው?



እየተካሰስክ ነው ወይስ ቢያንስ የአንድ ሰውን ሕይወት በጎ ለማድረግ ጥረት እያደረክ ነው? በዚህ ክፋት በሞላበት ዓለም ፊት ውበትን የማየት አቅም አጥተን ይሆናል። ስለዚህ እንቁም። ጉድለት በበዛበት ሕይወት ውስጥ ያለንን ብዙ ነገሮች ረስተን ይሆናል። ስለዚህ ፍሬን እንያዝ። “ምንድነው ግን የተማርኩት?” እንበል። “ምንድነው በሕይወቴ መድገም የማልፈልገው እና ብደግመው የማፍርበት ነገር? ምንድነው በሕይወቴ እየሰራ ያለ ጥሩ ነገር እና አብዝቼ መቀጠል ያለብኝ? ማቋረጥ የምሻው እና ያላቆምኩት ነገር ምንድነው?” እንበል።



በዚህ ሕይወት በጣም የምፈልገው ነገር ምንድነው? ያን ባገኝ ምንድነው የሚሆነው? ምን ላደርግበት ነው ያን ነገር የምፈልገው? ሳላገኘውስ ይሄ ሕይወት ቢያበቃ እንዴት ነው ሕይወቴን መኖር ያለብኝ?



መቀበል የቸገረኝ ነገር ምንድነው? ለምንድነው የከበደኝ?



ምንድናቸው ዓይኖቼ የታወሩባቸው ነገሮች? ማየት የተሳኑኝ?



ዛሬ ትላንት የጓጓህለት ወይም የፈራኸው ነገ ነው። ትላንት የተደሰትክበት ወይም ያዘንክበት ዛሬ ነበር። ነገም ዛሬ ይሆናል። ከዛ ትላንት። ለዚህ ነው ዘይትህን ቆም ብለህ ለመፈተሽ ወይም ለመቀየር መወሰን ያለብህ። ካለዛ አንድ ቀን ኢንጅነህ ተበላሽቶ ትነቃለህ። ኢንጅንህ እስከወዲያኛው ላለመስራት ሆኖ ትደርሳለህ። ብትረግጠው፣ ብትገፋው፣ ብታስገፋው - Too Late! ይልሃል።





 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page