top of page
Search

ሞኝ የመሆን ድፍረት

Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew

መንገድ ላይ የሚለምኑ ሰዎችን ሳይ፣ ብዙ የማስባቸው ሀሳቦች ቢኖሩኝም፤ አንደኛው ግን አድናቆት ነው። እነዚህ ሰዎች በስንፍናም ይሁን ያለእነሱ ጥፋት በመጣ ድህነት ችግር ላይ ወደቁ። ግን ከመስረቅ፣ ነፍሰ ገዳይ ሆኖ ግፍን በመፈጸም ችግራቸውን ከማባረር ይልቅ አንድ ነገር መረጡ። ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ፥ የመለመንን ድፍረት ተላበሱ። መለመን ቀላል የሚመስለው ይኖራል። ግን መለመን ይቅርና ለመማር የገባንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ራሱ ደደብ ተብሎ ላለመቆጠር ስንት ሰው ነው ጥያቄ የማይጠይቀው ወይም መልስ የማይመልሰው። እንግዲህ መሳሳት መብታችን በሆነበት የትምህርት ዞን ውስጥ የሰው ፍርድን ፈርተን ራሳችንን ከእውቀት ከገደብን፤ ክብርን አዋርዶ መለመን ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል አስቡ። በርግጥ ለጥቂቶች ይሄ ሱስ እና ቢዝነስ ሆኗቸው ይሆናል። አንዳንዶችም የአዕምሮ ጤናቸው ስለተቃወሰ ይሄን ያደርጉ ይሆናል። ግን ብዙዎች ችግር ነው ያወጣቸው።

 

የዛሬ የሰንበት ዕይታ በሰዎች የስኬት ጉዞ ውስጥ ቁልፍ ስለሆነው ስነልቦናዊ እንቅፋት ነው የሚዳስሰው። ታላቁ አሳቢ ሾፐንሀወር “የሰው ልጅ ትልቁ ፍርሃት ደደብ ተደርጎ መቆጠር ነው” ይላል። በእውነትም ትልቁ የስኬታማ ሕይወት እንቅፋት ደደብ ተደርጎ ለመቆጠር አለመፍቀድ ነው።

 

ሕጻናት ለመውደቅ ፍቃደኛ ባይሆኑ ኖሮ መቼም መራመድ አይችሉም ነበር። ግን ያን የመረዳት ስነልቦናዊ አቅማቸውስላላደገ፤ መውደቅን ሳይፈሩ መራመድን ተለማመዱ። እንደ እኔ ሥራችሁ ከብዙ ሰዎች ጋር የሚያገናኛችሁ ሰዎች ከሆናችሁ፤ ሰዎች የሆነ ትምህርት ወይም ሥራ ለምን እንደማይጀምሩ ስትጠይቋቸው የሚመልሱት መልስ “በዚህ ዕድሜዬ” የሚል ነው።

 

ለምን ዕድሜ ተጽዕኖ ፈጠረባቸው?

 

ትልቁ ምክንያት በዚህ ዕድሜያቸው ተጠያቂ እንጂ ጠያቂ፣ አስተማሪ እንጂ ተማሪ፣ ከፍ ብሎ እንጂ ዝቅ ብሎ ለመታየት አለመፍቀዳቸው ነው።

 

ስናድግ ሕጻናትን መራመድ ያስተማራቸውን ትልቁን የስኬት ስነልቦና አውልቀን እንጥለዋለን። እሱም በሰዎች ፊት ለመውደቅ መፍቀድን ነው። ሞኝ መስሎ ላለመታየት መፈለግ የእውቀት መዝጊያ ቁልፍ ነው።

እውነተኛ ጅል ለመሆን ትፈልጋላችሁ? አዋቂ መስሎ ለመታየት ጥረት አድርጉ። ያልገባችሁን ነገር እንደገባችሁ እለፉ።ከንግግራችሁ አላውቅምን አሶግዱ። ሁሉ  እንደገባችሁ ነገር ጭንቅላታችሁን ነቅንቁ። ጥያቄ መጠየቅን ሳይሆን ለማስረዳት እና ለማስተማር ቸኩሉ።

 

የሰው ልጅ ውድቀት ሲጀምር፤ ከውድቀት የመውጫውን መንገድ ፈጣሪ ለአዳም ጠቁሞታል። አዳም ሆይ ፥ “ወዴት ነህ? የሚለው ያላዋቂዎች ጥያቄ በአዋቂው በእግዚአብሔር ተጠቆመው። ሁሉን አዋቂው ከመፍረዱ በፊት አላዋቂ ሆኖ ለመቆጠር ፈቀደ። ምንም ምንም በፊቱ ያልተሰወረበት እርሱ ፥ ሁሉ ነገር የተሰወረበትን ጠየቀ። “ወዴት ነህ?” እያለ። በዚህ ምድር በእኛ አቅም የጥበብን ጥግ ማግኘት ከፈለግን እናውቀዋለን የምንለውን ነገር ሳይቀር እንደ አላዋቂ በመጠየቅ እንጀምር። ብዙ አውቀናል የምንላቸው ነገሮችን ፈጽሞ እንደማናውቃቸው የዛኔ ይገባናል።

 

በሕይወት እጅግ ብዙ ነገር የሚገኘው ሞኝ ሆኖ ለመወሰድ ባለ ድፍረት ውስጥ ነው። ሼን ፓሪሽ እንደሚለው “የላቀ ውጤት ለማግኘት ሞኝ ሆኖ የመቆጠር ብቃት ላይ መድረስ አለብን። ምክንያቱ ይሄ ነው። ሁሉም ሰው የሚሰራውን ሥራ ከሰራችሁ ሁሉም ሰው የሚያገኘውን ውጤት ነው የምታገኙት። ከጅምላው ለመለየት የተለየ ዕይታ ያስፈልጋችዋል።” በሀያ ዓመታችን ዓለም ሁሉ ስለኛ የሚጨነቅ ይመስለናል። በአርባ ዓመታችን ስለዓለም ወይም ስለ ሰው አንጨነቅም ማለት እንጀምራለን። በስልሳ ዓመታችን ግን ማንም ስለኛ ተጨንቆ እንደማያውቅ ይገባናል።

 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለጻድቃን ሲናገር በመውደቀቻው በማፈር አይደለም፤ በመነሳታቸው ተደስቶ እንጂ። የሰው ልጅ ትልቁ ክብረ በዓሉ ያለመውደቅ በዓል አይደለም ፥ ከውድቀት የመነሳቱ ትንሣኤው እንጂ። ሁለቱ ነገሮች በአንድ ጊዜ ሊኖሩን አይችሉም፤ ወይ ደደብ ሆኖ የመቆጠር ድፍረቱን እንመርጣለን አልያም የውሸት አዋቂ ሆነን እንኖራለን።

 

ኖህ ለሀያ ዓመታት ሞኝ ሆኖ ለመቆጠር ባይፈቅድ ኖሮ መርከብን ባልገነባ ነበር። ሰማዩ በጠራ ሰዓት፣ ፀሐይዋ መውጣት ባላቋረጠች ወቅት፣ ጉምጉምታ እና ነጎድጓድ በሌለበት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰዎች ሁሉ ምርጥ የተባለውን የዓየር ንብረት እየተዝናኑ ባለበት ፥ ከጎርፍ የሚጠብቅ መርከብን ለመገንባት ሞኝ ሆኖ ለመቆጠር መድፈርን ይፈልጋል። ዝናቡ እስከሚዘንብ ድረስ ኖህ ነበር ሞኙ።

 

ታስታውሳላችሁ ስንቶች ትላንት ሞኝ ይሏችሁ እንደነበር? ያኔ ሞኝ ይሏችሁ የነበሩ ዛሬ ግን የት ናቸው? ዛሬም ያን መራመድን ያስተማረንን “በሰው ሁሉ ፊት መውደቅን የመፍቀድ ስነልቦና” መልሰን እናለምልመው።



378 views0 comments

Recent Posts

See All

የሰንበት ዕይታ - 16

እንቢ ማለትን በምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው።...

የሰንበት ዕይታ - 14. የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች

January 20, 2024 ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ...

Comentarios


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page