
አልበርት አንስታይን የህሊና አድማስ (ኢማጅኔሽን) የሌለው ሰው እና የሞተ ሰው እኩል ነው ይል ነበር። የእናንተን አላውቅም የእኔ አዕምሮ ግን በሆነ ነገር ላይ ሲመሰጥ ራሱን የዛ አካል አድርጎ በምልዓት ጠልቆ ይገባል። በዚህ ሳምንት በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ 6 ከቁጥር 1 ጀምሮ ያለው ታሪክ የህሊና አድማሴን ይዞት ሄዷል።
ረጅሙ እና ከፍ ያለው ዙፋን ላይ የተቀመጠው አምላክ። ፍጹም አስፈሪው ግን ፍጹም ውበት ያለው፤ ያ የተፈራው ዖዝያን ከሞተ በኋላም እርሱ ግን በረዥሙ እና ከፍ ባለው ዙፋን ላይ ተቀምጧል። ይሄን የሚናገረው ስለዙፋን እና ንጉሶች እነሱን በማገልገል እውቀት የነበረው ነቢዩ ኢሳይያስ ነበር። ከዛ ትልቁ እና ውቡን ዝማሬን ሰማ። “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” የሚለውን። እንደሚዳሰስ ፍቅር፣ እንደሚነካ የምህረት ፏፏቴ አምላካቸውን በማየት የረኩ ከልብ ደስ ብሏቸው “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያሉ ከዙፋኑ ሥር ወደቁ። ፍጹም ፍቅር ያለበት ግን ፍርሃት ያልተለየው ያ ምስጋና።
“የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ።” ይሄ ክብር የሰው ልጅ ክብር ነው። ነቢዩ ይሄን ሲያይ የጠፋ ነበር የመሰለው። ነገር ግን ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እርሱ መጥቶ ፥ የዚህ ደስታ አካል እንዲሆን ተመኝቶ በፍሙ አነጻው።
ተመሳሳይ ደስታ የምናየው በራዕይ ላይ ነው። ራዕይ ምዕ 4። ሃያ አራት ሽማግሌዎች ዙፋኑን ከበውት ፥ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሚለውን የምስጋና ጅረት ሲሰሙ ወድቀው “አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።” ይሉታል።
ይሄ ውበት፣ ይሄ ሞገስ፣ ይሄ ከፍታ የሰው ልጅ የሕሊና አድማስ ነው። ይሄን የውበት ወንዝ እየሳልን ፥ የተጠራነው ከዚህ ፍጹም ሞገስ ጋር አንድ ለመሆን እንደሆነ እንድናውቅ ነው።
ሲ ኤስ ሉዊስ “ሰይጣን ሥርዓት ያለው ዘፈን ሳይቀር ይረብሸዋል” ይላል። እስቲ ሂዱ እና እነዚህ ሰማያዊ መዝሙሮችን ተመልከቱ። ስሜት አልባ እኮ አይደሉም። ድምጽ፣ እሳት፣ ነጎድጓድ አላቸው። ግን ደግሞ ፍጹም ሥርዓትም አላቸው። የመሬት መናወጥ አላቸው ግን ረጋ ብሎ መደፋት እና ሞገስ እና እርከንም (hierarchy) አላቸው። ዙፋኑን የከበቡበት መንገድ፣ ቤቱ በጢስ መሞላቱን ስታዩ ምን ያህል ሕይወት ያለው መዝሙር እና የዛ አካል መሆንን የሚያጓጓ እንደሆነ ታያላችሁ። በተቃራኒው የትህትናው ብዛትን ተመልከቱ። ዓይናቸውን፣ እግራቸውን እየሸፈኑ ግን ደግሞ እየበረሩ የሚያመሰግኑ ነበሩ። ት ህትና ብቻ ነው ወደ ላይ ከፍ የማለት ክንፍ ያለው። ራሱን የሚሸፍን ብቻ ነው የተገለጠውን የሚያየው። ግን ደግሞ ባዶን ነገር መሸፈን አይቻልም። የእውቀት ዓይኖች ፥ የጽናት እግሮች ሲኖሩን ብቻ ነው የሚሸፈን ነገር የሚኖረን። መኖሩ የታወቀ ገንዘብ እንደሚበዘበዝ፣ እንደሚመነዘር ፥ የተደበቀው ግን ወደ በለጠው ክብር ይበራል።
ዙፋኑ ያን ትህትና በሚያሳይ መልኩ ነበር የተዘጋጀው። ረጅም እና ከፍ ያለ ነበር።
ሲ ኤስ ሊዊስ “እንስሳት መሆናችንን ማስረሳት ነው የሰይጣን ተልዕኮ” ይል ነበር። ማለትም ትህትና ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር ይመስለናል። በፍጹም። ትህትና በየቀኑ ትንሽነታችንን በሚያስታውስ ነገር ራሳችንን ካልከበብን እየራቀን ይሄዳል። ከድንኮች ጋር ከዋልን ከትዕቢት ውጪ አማራጭ የለንም።
ሌላ ደግሞ ሽማግሌዎችን እዩአቸው። በዘመን አርጅተዋል። በልምድ ሸብተዋል። ከዚህም የተነሳ ነጭ ለብሰው፣ ከወርቅ የተሰራ አክሊል አጥልቀው እንዲቆሙ ሳይሆን እንዲቀመጡ ነበር የተፈቀደላቸው። ነገር ግን የዙፋኑ መሠረት ኃያል በሆነ ድምጽ ሲመታ እና የምስጋናው ድምጽ ሲሰማ እነዚህ ሃያ አራት አባቶች በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ፥ የሰው ልጅ ቋንቋ የማይገልጸው ውበት ለተላበሰው ወደቁ ፥ ተንበርክከውም ፈቃዱን አደነቁ።
ሥርዓት፣ ሕይወት ያለው ምስጋና፣ ፍጹም ትህትና፣ ንጽህና እንዴት ባለ ገመድ ተሳስረው በሰማያዊው ቤተመቅደስ እንደተገለጡ ተመልከቱ። በዚህ ምድር ላይ እነዚህን ነገሮች ገንዘብ ያደረገ ተቋም የማይበገር ነው። ሥርዓት ያለ ሕይወት (passion) ድብርትን ይጋብዛል። ስሜት (passion) ያለ ትህትና ውድቀትን ይስባል። ንጽህና ደግሞ የዚህ ውበት እና ደስታ ተካፋይ እንድንሆን ያደርጋል። አካል፣ ተካፋይ እንድንሆን ያደርገናል። ይሄን አዕምሮዬ ተመሰጠበት። ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ፥ የሚለው ዖዝያንም ሞቶ ይቀጥላል። ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በፊቱ ወድቀው ፥ አክሊላቸውን ለርሱ አኖሩ።
በመጨረሻም ዖዝያን ይሞታል። ግድ የላችሁም ፥ እርሱን ግን ነገም በዛ ረዥም እና ከፍ ባለ ዙፋኑ ላይ እናየዋለን።
Comments