top of page
Search

ሴቶች ቤትን እንዴት ያፈርሳሉ?

Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew

March 23, 2024


ወንድ ስለሆንኩኝ ስለወንዶች ባህሪ ከሴቶች በተሻለ አውቃለሁ። በተለይ ወንዶች ምን ቢደረግላቸው የተሻለ ባል እና ቤታቸውን የሚወዱ ማድረግ እንደሚቻል ሴቶች መገንዘብ አለባቸው ባይ ነኝ። በማንኛውም ጥምረት ውስጥ ችግር ካለ የአንዱ ችግር ብቻ ነው ብሎ የሚቀበል ሰው ስህተት እየሰራ ነው። ቢያንስ በኛ ዘመን የግዳጅ ጋብቻ የለም። ስለዚህ አሁን የሚማረርባትን ሴት ለጥምረት በመምረጥ ቢያንስ የወንዱ ኃላፊነትም አለ። ስለዚህ ስለሴቶች ስጽፍ ሴቶች ብቻ ናቸው ጥፋተኛ ለማለት ወይም ደረጃ ለማስቀመጥ አይደለም። የማውቀው ላይ ማተኮር የተሻለ ነው በሚል ነው።

በዴል ካርኒጌ የ1936 መጽሐፍ እትም ላይ የነበረ ቀጥሎ ባሉ እትሞቹ ላይ ግን ያልተካተተ (ምክንያቱን አላውቅም) ስድስተኛው ምዕራፍ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ነው።


 ሴቶች ቤትን የሚያፈርሱበት 7 መሳሪያዎች አሉ፤


1) ጭቅጭቅ


ወንዶች መታገስ የማይችሉት ነገር የምትጨቃጨቅ እና የምታኮርፍ ሴት ነው። ወንድ የምትጨቃጨቅ እና የምታኮርፍ ሚስት ያለችበትን ቤት እንደ ሲዖል ነው የሚቆጥረው። ከዛ ነጻ ለመውጣት ሞትን ሳይቀር ይመኛል። ጭቅጭቅ ግን የብዙ ሴቶች በትር ነው።

 በመልኳ ውብ፣ በዘሯ ስመጥር፣ ልጃገርድ እና ሁለመናዋ ድንቅ የነበረችውን ማሪ ዩጄኒክ ኢግናስ ናፖሊዮ ሦስተኛ (የናፖሊዮ ቦናፓርቴ የወንድም ልጅ) ያገባታል። በውጫዊ ውበቷ ከንፎ ነበር ያገባት። ብዙም ግን አልቆየም። ማሪ በቅናት የምትደብን፣ ናፖሊዮንን ሥር ሥሩ የምትከታተል፣ በማልቀስ እና እሱ ላይ በመጮኽ መከራ የምታሳየው ሆነች። እረፍት ነሳችው። በትልቅ በትንሹ መነዝነዝ ሆነ የፍላጎቷ ማሳኪያ መንገዷ።


“የምፈራው ነገር ደረሰብኝ!” እንዳለው ኢዮብ፤ ናፖሊዮን ይሄን መቋቋም ተሳነው። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከቤት መራቅ፣ በሳቅ እና በደስታ ወደ ሚቀበሉት ሴቶች መሸሽ፣ ከጓደኞቹ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍን ሥራው አደረገ። ምስኪን ሴት ማሪ ፥ ናፖሊዮንን አቃናለሁ ብላ የዘየበችው የመጨቃጨቅ መላ ጭራሽኑ አጠፋው። ጭቅጭቅ እንደ ኮብራ እባብ ነው ፥ የትዳርን ሕይወት ይገላል።


የሊዮ ቶልስቶይ ሚስት ይሄ የገባት ቆይቶ ነበር። ባሏ በመጨረሻ እሷን ከማየትስ ልጥፋ ብሎ፣ አድራሻውን ሳያሳውቅ ሁሉን ትቶላት ጠፋ። The Last Station በጣም ጥሩ ፊልም ነው፣ ይሄን የቶልስቶይን ታሪክ በደንብ መዝግቦታል። ከሚስቱ ሽሽት ከቤቱ አጠፋው፣ በባቡር ጣቢያ ላይ ወድቆ ፥ ሞቱን በመንገድ እንዲሆን አደረገው። ጠቢበኛው ሰሎሞን እንዳለው “ከጠበኛና ከቍጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል።” ምሳ 21፥19። ይሄ የቶልስቶይ ትዳር በሁሉ ዘርፍ ስኬታማ የሚባል ነበር፣ የቶልስቶይ ጹሁፎች ቁጥር ስፍር የላቸውም። ሁለቱ መጽሐፎቹ እስከዛሬ በዓለም ላይ ከታተሙ ምርጥ አስር መጽሐፍት ውስጥ በቁጥር አንድ እና ሦስት የሚቀመጡ ናቸው። ይሄን ሁሉ ያሳካው ከሚስቱ ጋር እና በርሷ ትብብር ነበር። ቶልስቶይ ግን ሥራን አንዱ ከሚስቱ የመራቂያ መንገድ ነበር ያደረገው። ለዚህም ነው ከማንም በላይ የሰራው። ውጫዊው ስኬት የውስጣዊው ሰላም እጦት ምክንያት ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ይሄ ስኬት በቂ አልሆን አለው። መታገስ አቃተው። ጠቢበኛው ሰሎሞን እንዳለው ከቁጡ ሚስቱ ይልቅ ፥ ቤት አልባ ሆኖ ጎዳና ላይ መኖርን መረጠ። ሞቱ አፋፍ ላይ ሆኖ እንኳን ሚስቱ መጥታ እንዳታየው ከባብሩ ጣቢያ ተሸክመውት ለሄዱት ሰዎች አሳሰባቸው። ከሞተ በኋላ “ለቶልስቶይ ሞት ምክንያቱ እኔ ነኝ!” ብላ ለመጀመሪያ ልጇ በማልቀስ ነገረቻት፤ አብራት ከማልቀስ በቀር ሴት ልጇ ግን ምንም ልትላት አልቻለችም። ሁሉም የሚያውቀው እውነት ነበርና።


እውነት ነው የቶልስቶይን ታሪክ ላነበቡ ሰዎች የሚስቱን መጨቃጨቅ ተገቢ ነው ብለው ሊወስዱ ይችላሉ። ቁም ነገሩ እሱ አይደለም። ጭቅጭቅ ምን ለውጥ አመጣ ነው? ምን መለወጥ ቻለች ነው ጥያቄው?! ምንም። ጭራሽ እንድታንገሸግሸው ሆነች። ተጠየፋት። በመጨረሻም ሀብቱን ሁሉ ለበጎ ድርጅቶች አከፋፍሎ ፥ ራሱን ብቻ ይዞ ጠፋ።


የአሜሪካ የአንድነት መሪ የሚባለው አብርሃም ሊንከን በስቃይ የኖረ ሰው ነው። ስቃዩ ግን ሚስቱ ነበረች። የሊከን ሚስት አንድም ቀን አመስግናው፣ ሰላም ሰጥታው፣ ትክክል ነህ ብላው አታውቅም። ለርሷ ሊንከን ማለት ዘወትር የሚሳሳት ፍጥረት ነው። በአለባበሱ፣ በአነጋገሩ፣ በአረማመዱ ሁሉ ትወቅሰዋለች። አንዱ ጆሮው ከሌላው በመብለጡ ትፎግረዋለች። እርሱን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ሥራዋ ነበር። ሜሪ ቶድ የባሏ ምንም ነገሩ አይጥማትም። “ሁለት ተቃራኒ ሰዎች” ይላቸዋል ዴል ካርኒጌ። ሴናተር አልበርት ጌ ሜሪ ቶድን “ጩኸቷን ጎረቤቱ ሁሉ ያውቀዋል፣ የማያቆመው ንዝነዛዋ ከማንም የተሰወረ አይደለም” ይላል።


ይሄ ቁጣ እና ጭቅጨቃ ሊንከንን ቀየረው? በደንብ። እርሷን ያገባበትን ቀን እንዲረግም አደረገው። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሩቅ መንገድ መሄድን፣ በሥራ አሳቦ ከቤት መጥፋትን፣ ከርሱ ጋር ዳኛ ዴቪድ ዳቪስን ተከትለው የሄዲ ጠበቆች በእረፍት ቀን ቤታቸው ለመሄድ እና ከሚስቶቻቸው ጋር ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ሲጥሩ፤ ሊንከን ግን አጋጣሚውን ተጠቅሞ ከቤት መራቅ ነበር ምርጫው።

ማሪ ዩጄንክ፣ የቶልስቶይ ሚስት እና ሜሪ ቶድ የሊከን ሚስት በመጨረሻ ቤታቸውን በቁጣ አፈረሱት። ወንድ ቢሆኑ ባሎቻቸውን መደብደብ ማለት ነው ጭቅጭቅ። ብዙ ሴቶች ቤታቸውን ትልቅ መቃብር አድርገውታል በየቀኑ በጭቅጭቅ መቆፈሪያ በሚቆፍሩት ጉድጓድ። ወንድን ለምንጊዜም ለማሸነፍ የመጀመሪያው ሕግ፦ ጭቅጭቅ እና ቁጣን ማሶገድ ነው።


ቀሪዎቹ ስድስት ነጥቦችን በዚህ ሳምንት በቴሌግራም ፔጄ ላይ ማንበብ ትችላላችሁ።



46 views1 comment

Recent Posts

See All

የሰንበት ዕይታ - 16

እንቢ ማለትን በምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው።...

የሰንበት ዕይታ - 14. የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች

January 20, 2024 ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ...

1 comentario


berheyared89
15 jun 2024

perfectly said

Me gusta
  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page