
በድንገትም ሆነ ታስቦበት የወጣ ቃል ፥ አሸናፊ የማድረግ አቅም አለው። ለምሳሌ ብዙዎቻችን የምናውቀው እና የአሜሪካን የፍርድ ቤት ሥርዓት ወደ ድራማ ትይንት የቀየረው የO J. Simpson ጠበቃ Johnnie Cochran የተናገረው፣ በመጨረሻም O J. Simpson በጁሪው ነጻ እንዲሆን ያደረገው ቃል ይሄ ነበር፦ “If it doesn’t fit, you must acquite” - ፖሊስ በማስረጃነት ስላቀረበው ጓንት ነበር ይሄን የተናገረው። “ልኩ ካልሆነ ልክ አታስገቡት” የሚል አውዳዊ ትርጉም አለው።
የታዋቂው የተከላካይ ጠበቃ የማርክ ገራጎስ ቃልም የብዙ ጠበቆች መስመር ሆኖ ቀርቷል፦ “just because someone says it’s true doesn’t make it true” “የሆነ ሰው እውነት ነው ስላለ ብቻ እውነት አይሆንም።”
የሕግ ሊቀ ሊቃውንት የሰር ዊሊያም ብላክስቶን ቃልስ ፦ “Better that ten guilty persons escape than that one innocent suffer.”። (“አንድ ንጹሁ ሰው ከሚታሰር አስር ወንጀለኛ ነጻ ቢወጣ ይሻላል!”) የሚለው እና የወንጀል ሕግ ሥርዓት መሠረት ሆኖ የቀረው ከዚህ ሊቅ አንደበት የወጣ ነው። ወደ ሀገራችን ስንመጣም ከፈረንሳዩ የሶርባን ዩኒቨርስቲ በሕግ የተመረቀው ልዩ ፍጥረት አክሊሉ ሀብተወልድ እንዲህ የሚለው ቃሉን አንረሳውም።
“አንድ ግብ ብቻ ነው ያለን
ኢትዮጵያ!
አንድ መተባበሪያ አላማ ብቻ ነው ያለን
ኢትዮጵያ!!
አንድ ፕሮግራም ብቻ ነው ያለን
ኢትዮጵያ!!!”
ይሄን የመሰለ ውበት ያለው እና ሁሉን አቃፊ የሆነ መስመርን እንዴት ባለ ጥንቃቄ የሚያፈልቅ፤ ልክ እዚህ ሀገር ባሉ ሊቃውንት ደረጃ ያለ ሰው ነበር አክሊሉ።
ይሄን ያነሳውት ዛሬ ዎልስትሪት ጆርናል የክልሌን ገዢ እጩ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጠ እና ለዛ ያበቃውን ዋነኛ ምክንያት ሲጠቅስ፤ ካሚላ ሀሪስ ባይደንን እንደተካችው፤ ገዢያችን ቲም ዋልዝ ትረምፕን እና ቫንስን “ዊርዶች” ብሎ መግለጹ ነው ይላል። ከዛ በኋላ ሁለቱ ዊርዶች የሚለው ቃል የሊብራል ሚዲያ ቃል ሆነ። ዋልዝንም ለአሸናፊነት አበቃው። ቃላት በዘፈቃድ የሚወጡ አይመስለኝም፤ ጊዜ እና ሁኔታን፤ አውድን እና ሰሚን አስተውሎ እና አጥንቶ የሚለቀቅ ቃል ፥ የቃል ፍጥረትን የሰው ልጅን ይማርኩታል። ቃላት ያድኑናል፤ ቃላት ይገሉናል።
Comments