
የየቀን ትግሌ ይሄ ነው። ተዋጊ መሆን። በርግጥ የእንግሊዘኛው ቃል ነው የሚገልጽልኝ። Survivor መሆን። victimhood እኔ ጋር የለም። ሌሎች ላይ ከሆነው የባሰ ነገር በእኔ ምንም ሆኖ አያውቅም። ግን በሕይወቴ እጅ ለመስጠት እና ለማማረር ከበቂ በላይ የሆነ ነገር ውስጥ አልፌያለሁ። ከልጅነት እስከ እውቀት። ግን ሁልጊዜ survivor ነኝ።
በእኔ ውስጥ እንዲሰለጥን የማልፈልገው አስተሳሰብ አለ። እጅ መስጠት። ተበዳይ መሆን። ተፈጥሮ በድላኛለች፣ አምላክ ትቶኛል ብሎ ማሰብ። በእኔ ይሄ አስተሳሰብ ቤቱን ሰርቶ አያውቅም። የሆነውን ለመቀበል ነው የምቸኩለው። በሆነው ውስጥ የተሻለውን እና ማግኘት የምችለውን ነገር ለማግኘት ነው የምሰራው። ልቤ አንበሳ እንዲሆን ነው የማደርገው። አላውቀውም ፥ አልችለውም ብዬ አልቀመጥም። ዛሬ ባላውቀው፣ ዛሬ ባይኖረኝ፣ ዛሬ ባልችለው ነገ ግን እንደሚለውጥ እና ያንንም እንደምለውጥ አምናለሁ። እንደዛ ዓይነት ታሪኮች እንጂ የመበደል እና ሌሎችን ሰይጣን አድርጎ የመሳል ታሪክ እና ትርክት እኔ ጋር ብዙ ቦታ እንዲኖረው አልፈቅድም። በእኔ ላይ የተፈጠሩ ብዙ ነገሮችን የምቆጣጠረው ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ከሁኔታዎች በታች ራሴን ለማድረግ ፈቅጄ አላውቅም። ዊል ስሚዝ እንዳለው “በትሬድ ሚል ላይ መሞት ከሆነም ለመሞት ዝግጁ ነኝ ፥ ግን አላቋርጥም።” እርዳታ ቢስ እና ተስፋ የሌለኝ ሆኜ ለመታየት አልፈቅድም። ለራሴ ሌላ ትርክት ነግረዋለሁ እንጂ። ሰዎች ወደ እኔ መጥተው “ልጅ ሆኜ አባቴ እንዲህ ስላረገኝ ነው፣ እናት አባቴ እንዲህ ስላረጉኝ ነው፣ ልጅ ስለሆንኩኝ ነው፣ ወይም አስተዳደጌ ይሄ ስለሆነ ነው” ሲሉኝ ፥ እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት በእነሱ ላይ ለተከሰተ ነገር ምን ያህል ራሳቸውን ባሪያ አድርገው እንደሰጡ ነው የማየው። አሁን ያ የሚሉት ስቃይ እና ማነቆ ባይኖር እንኳ ፥ አዲስ ማንነት ፈጥሮ ፥ አዲስ ማንነት ሰርቶ ከዛ ለመውጣት ፈቃደኞች አይደሉም። ነገር ግን የትላንት ባሪዮች ሲሆኑ ሳይ አዝናለሁ። ዛሬን እና ነገን ለትላንት ማስገበር።
የሰው ልጅ ልዩ ባህሪው ፈጣሪ መሆኑ ነው። የመፍጠር ችሎታችን ነው ከሌሎች ሁሉ የለየን። የማንፈጥር ካልሆንን ፥ የጎደለ ስብዕና ነው ያለን። መፍጠር የሚጀምረው ደግሞ ራስን ለዛሬ እና ለነገ በድጋሚ በሚስማማ መልኩ በመፍጠር ነው። ልክ ነው ብዙ መከራ ደርሶብን ይሆናል፤ ግን ዓይናቸውን፣ ጆሮአቸውን፣ እንደውም ተጨማሪ አካላቸውን አጥተው እኛ ፈጽሞ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ሰርተን የማናውቀውን ነገር የሚሰሩ እና ያሳኩ ፥ ዓለምን ጉድ ያሰኙ ሰዎች አልገጠሟችሁም?
በሕይወታቸው ላይ በደረሰ አንድ ሁለት ሦስት ክስተቶች ምክንያት ሙሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ሰዎችን ተመልከቱ። እነዚህ ሰዎች እነዚህን አጋጣሚዎች ወደ ዕድል ለመለወጥ አለመቻላቸው አስገራሚ ነው። በእኔ ላይ በራሴ ጥፋትም ሆነ ያለ እኔ በደል የደረሱብኝን ክፉ አጋጣሚዎች ሁሉ አፈቅራቸዋለሁ። እነዚህ ራሴን በጥልቀት እንዳውቅ እና ነጥሬ በአዲስ ማንነት እንድነሳ ያደረጉኝ ናቸው። ራሴን በድጋሚ የፈጠርኩባቸው ክስተቶች ናቸው። ያለእነሱ እኔ አይደለሁም።
ከ100% በታች ኃላፊነት በሕይወት የሚወስዱ ሰዎች፣ ለደስታቸውም ሆነ ለሐዘናቸው እነሱ ብቻ ተጠያቂ እንዳልሆኑ የሚገልጹ፣ መቆጣጠር ስለማይችሉት፣ መለወጥ ስለማይችሉት ነገር በማሰብ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ፣ ወደ ፊት መሄድ ሳይሆን ከጊዜ ማዕበል ጋር መጋፋት የሚወዱ ቪክተሞች አሉ። አሉ ደግሞ እሱ ነው፣ እሷ ናት፣ እከሌ ነው፣ ሚስቴ ናት፤ እርሱ በሕይወቴ እስኪመጣ ድረስ ሰላማዊ ነበርኩኝ፤ እከሌ እስኪቀላቀለን ድረስ ሀሴት ነበር ሕይወታችን የሚሉ ፥ የሚደፈድፉበት ነገር የሚመስጣቸው፤ ክርስቶስን ሰቃዮች ፥ በበጉ ደም መፍሰስ እነርሱ የሰሩት ኃጢአት እንዲደመሰስ የሚሹ ፥ ከሳሾች አሉ። አሉ ደግሞ በሕይወታቸው የተፈጠረውን ነገር ከሥሩ ከመፍታት ይልቅ ፥ ትንሽ በማልቀስ፣ ትንሽ በመተንፈስ፣ ትንሽ በማማረር ወይም ችግራቸውን የሚረሱበት ከNetflix እስከ ሲጋራ በመሳብ ለጊዜው እፎይ ማለት ብቻ የሚመርጡ ቪክተሞች። በጣም የሚገርመው እነዚህ ቪክተሞች ሁሌ ልክ ናቸው። ሌላው እና ሌሎች እንጂ እነርሱ ሁልጊዜ ልክ ናቸው። ስለዚህ ለውድቀታቸው ከሳሾች ናቸው። ቪክተሞች መሆናችሁን ለማወቅ ቀላሉ መንገድ የተቀየማችሁት ሰው እንዳለ እና እንደሌለ መጠየቅ ነው። ካለ የቪክተም አስተሳሰብ ተጠቂዎች ናችሁ። ይቅር ማለት የማይችል ልብ ያለው ሰው ፥ መፍጠር አይችልም። ሁሉን ነገር ሲሪየስሊ መውሰድ የሚቀናው ሰው ፥ አዕምሮ የመፍጠር ችሎታውን የተነፈገ ነው። ምክንያቱም በራሱ ላይ በተፈጠረው ነገር መሳቅ የማይችል ሰው የመማር አቅሙን አጥቷል።
ማማረር እና ማሳበብ ልጆች ከወላጆቻቸው የሚማሩት ነው። እንደ እኛ ሀገር ባለ ፖለቲካ ደግሞ ማማረር የአጭር ጊዜ እንጀራ ነው። ቪክተም መሆን ለጥቂቶች የስልጣን ኮርቻ ነው። ትውልድ ግን ይሞታል። የትውልድ አዕምሮ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናል። ትላንት ኦሮሞ ነበር። ዛሬ ደግሞ አማራ ሆኗል ይሄን የቪክተም ስነልቦና የሚጋተው። እስቲ አንድ የተሳካለት፣ ሕይወቱ ያማረለት፣ በፈጠራ ችሎታው እና በአገልግሎቱ አንቱ የተባለ ግን የቪክተም አስተሳሰብ የሚያራምድ አንድ ሰው ጥቀሱልኝ? አንድ ማምጣት አትችሉም። አንድ!!!
ለምን? መልሱ ግልጽ ነው። ቪክተም ስነልቦና መጀመሪያ የሚያደርገው የመፍጠር ችሎታችን መንፈግ ነው። 100% ስለሕይወቱ ኃላፊነት የማይወስድ ሰው መፍጠር አይችልም። ጥርጣሬ የሌለው ሰው፣ ሕይወትን ከሌሎች መነጽር አንጻር ለማየት የማይችል ሰው፣ ሌሎችን ይቅር ለማለት የማይፈቅድ ሰው ፥ አንቱ ሊባል አይችልም።
አዎ፦ በየቀኑ ተዋጊ ነኝ። ከሕይወት ጋሪ ጋር ወደ ፊት በመሮጥ የምተባበር፤ የኋላዬን እየረሳው ወደፊት የሚጠብቀኝን ለማየት እና ለመያዝ የምዘረጋ ነኝ። Survivor ነኝ። የደረሰብኝ ሁሉ ከትምህርት የዘለለ ትርጉም የለውም። በሕይወቴ መጨረሻ “የተሰጠኝን አበዛውት፣ በብዙ እጥፍ አድርጌም ለሰጪው ሰጠውት” ለማለት የምዘረጋ እንጂ የምጎተት አይደለውም።
I found this somehow it's so motivational script. Your contributions to our people are so invaluable. We are so grateful for all that you do. Your hard work and dedications are truly admirable. And we are so fortunate to have you person like you. And thank you!
እይታህን በጣም አደንቃለሁ፤ ሳንከፍል ሰለምታስነብበንም አመሰግናለሁ ። አንተም እንዳልከው ኹሌም ከችግር መማር እና ከገጠሙን ፈተናዎች መውጫው መፈልግ እንጂ በችግሩ ተስፋ ቆርጦ መቆዘም እና ማማረር እንደሌለብን አምናለሁ። ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ሁሌም የሚያሳስበኝን ጥያቄ ልጠይቅህ? ፈቃደኝነትክን በመተማመን ነው።
ሀገራችን በአዙሪት ጦርነት እና ችግር ውስጥ ነች። ለዚህ ዋና ምክንያት ምንድን ነው? እንዴትስ እንወጣለን? አኹን ላይ ያለው "መንግስትስ" በታሪክ ከየትኛው መንግስት ጋር ይመሳሰላል? የትጥቅ ትግል መፍትሄ ነው ብለህ ታምናለህን?