የዚህ ጹሁፍ ብዙ ክፍሉ ከሲ ኤስ ሉዊስ የተወሰደ ነው።
አንድ ኃጢአት አለ በዚህ ዓለም ላይ ያለ ሰው ሁሉ ነጻ ነኝ ብሎ የማይናገርበት። ይሄን ኃጢአት ሁሉም ሰው በሌላው ላይ ሲያየው ይጠየፈዋል፣ ክርስቲያን ካልሆኑ በቀር ይሄ ኃጢአት አለብኝ ብሎ በድፍረት የሚናገር እምብዛም የለም። እንደዚህ ኃጢአት ሰውን የሚያዋርድ የለም ፥ እንደዚህ ኃጢአትም ሰዎች በራሳቸው ላይ የማያስተውሉት የለም። ይሄ ኃጢአት በራሳችን ላይ በብዛት ሲኖረን ፥ በሌሎች ላይ አብዝተን እንጠለዋለን።
እንደ ክርስቲያን መምህራን፣ ይሄ ትልቁ ኃጢአት ፥ ይሄ አቻ የማይገኝለት መጥፎ የነፍስ ጠረን ፦ ትዕቢት ነው። የኃጢአት ጣሪያ ነው ትዕቢት።
በትዕቢት ፊት ፥ አመንዝራነት፣ ቁጣ፣ ስግብግብነት፣ ስካራ እና ሌሎች ሁሉ እንደ ትንኝ ናቸው። ትዕቢት ነው ሳጥናኤልን ሰይጣን ያደረገው። ትዕቢት የሌሎች ኃጢአቶች ሁሉ ድልድልይ ነው። የእግዚአብሔር ተቃራኒ ትዕቢት ነው። የኃጢአት አቻ ሌላ ስሙ ትዕቢት ነው። ምክንያቱም ኃጢአት ማለት ቦታችንን መልቀቅ፣ የማይገባንን ቦታ መያዝ፣ ያልተፈቀደልንን ነገር የራስ አድርጎ፤ የሚገባን አድርጎ መቁጠር ነው። ሰይጣን ሔዋንን ያላት ያን ነበር። “ይሄን ፍሬ መብላት እንደ እግዚአብሔር ያደርግሻል።” ያን ነው ትዕቢት የሚለው። “እንደ...” የመሆን ፍላጎት ፥ ርካታ የሌለው “እንደ..” የመሆን ናፍቆት እና “እንደ...” እነዛ ያለመሆን መጠየፍ ነው ትዕቢት።
1) ትዕቢተኛ ከሌሎች የተሻለ መሆን ይፈልጋል፤
በትዕቢት ጾር ትቸገራላችሁ? ሉዊስ እንዲህ ይላል ትዕቢት ባላችሁ መጠን አብዝታችሁ በሌላ ሰው ላይ ታዩታላችሁ። ምንድነው የሚሰማችሁ ስትናቁ፣ ሰዎች ከቁብ ሳይቆጥሯችሁ ሲቀር ወይም ከላይ ወደታች ሲያዮችሁ? ትዕቢተኛ ከሆናችሁ ሌላ ሰው እንዲህ ከፍ ሲል፣ ሲያሸንፍ በጣም ነው የምትበሳጩት።
የትዕቢት ደስታው የሆነ ነገር ሲያገኝ አይደለም። ነገር ግን ከሌላው ሰው የበለጠ እሱ ሲኖረው እንጂ። ሰዎች ሀብታም ስለሆኑ፣ ጎበዝ ስለሆኑ ወይም ስለሚያምሩ ትዕቢተኛ ናቸው እንላለን። ለዛ አይደለም ሰዎች ትዕቢተኛ የሚሆኑት። ሰዎች ትዕቢተኛ የሚሆኑት ከሌሎች በላይ ሀብታም ስለሆኑ ነው፣ ከሌሎች በላይ ጎበዝ ስለሆኑ ነው ወይም ከሌሎች በላይ ቆንጆ ስለሆኑ ነው። የሆነ ሰው ከኛ እኩል ጎበዝ፣ ሀብታም ወይም ቆንጆ ከሆነ የሚያስታብይ ምንም ነገር የለም። ንጽጽሩ ነው የሚያስታብየው ፥ ከሌላው የተሻለ ሆኖ መገኘቱ ነው የትዕቢት ርካታ።
2) ትዕቢተኛ ሰው መቼም አይረካም፤
ከሌሎች ጋር መፎካከር ሁልጊዜ የትዕቢት ምልክት አይደለም። ለምሳሌ የሪሶርስ (የሀብት) እጥረት ሲከሰት ሰዎች የድርሻቸውን ለማግኘት ይፎካከራሉ። ትዕቢተኛ ግን የበለጠ ለማግኘት ይጥራል ምንም እንኳ በቂ ቢኖረውም። ብዙ ኃጢአቶች የትዕቢት ልጆች ናቸው። ለምሳሌ ስግብግብነት እና ራስ ወዳድነት። ለምሳሌ ገንዘብን ውሰዱ። ያለጥርጥር ስግብግበነት ሰዎች ብዙ ገንዘብ እንዲፈልጉ ያደርጋቸዋል ምክንያቱም የተሻለ ቤት፣ የተሻለ ምግብ እና መጠጥ ወይም ብዙ የእረፍት ቀን ስለሚፈልጉ። ግን እስከሆነ ነጥብ ድረስ ብቻ ነው። እነዚህን ሁሉ የሚያስገኝ ገንዘብ ካገኙ በኋላ አሁንስ ገንዘብ የምትፈልገው ለምንድነው? ትዕቢት ነው - ከሌሎች የተሻለ ሀብታም የመሆን ትዕቢት፣ ከዛም ስልጣንን መፈለግ።
3) ትዕቢተኛ ሰው ስልጣን ይጠማል፤
ትዕቢት በጣም የሚረካው በስልጣን ነው። ትዕቢተኛ ሰው ከሌሎች የበላይ ለመሆን ያለው ምኞት ወደር የለውም። ስልጣን ደግሞ ይሄን የበላይ የመሆን የትዕቢት ተክል ውሃ ያጠጣዋል። ይሄን የስልጣን ፍላጎት በሁሉም ቦታ እናየዋለን። አድናቂዎች በመሰብሰብ የስልጣን ጥማቷን ከምታረካው ቆንጆ ሴት ፥ ተደማጭነቱን ለማስፋት ስልጣን እስከሚቋምጠው ፖለቲከኛ ድረስ።
ትዕቢተኛ ሰው ከሆንኩኝ ፥ ከኔ የሚበልጥ ሰው በዓለም ላይ አንድ ቢቀር እንኳ እረፍት የለኝም። ያን ሰው እስከምበልጠው ድረስ ጠላቴ ነው (ሰይጣን አንድ የቀረውን ጻድቅ ኢዮብን እንኳ ላለመተው የሄደበትን ርቀት ያስታውሱ። ዓለምን ሁሉ የራሱ ማድረጉ አላረካውም ፥ ትዕቢቱ የኢዮብን አለመንበርከክ መታገስ አልቻለም)።
ትዕቢት ዓለም ከተጀመረ ጀምሮ ትልቁ የመከራ ምንጭ ነው። ለሀገራትም ሆነ ለቤተሰቦች። እንደ ስካራ ያሉ ሌሎች ኃጢአቶች አንዳንዴ ሰዎችን ሲያቀራርቡ ትዕቢት ግን ሁልጊዜ ሰዎችን እንደለያየ ነው። የሰናዖር ግንብ አርቲቴክት ትዕቢት ነበር በዚህም የትዕቢት ልጅ የሆነውን መለያየትን የሰው ልጆች ታቀፉ። ኦ ትዕቢት ፥ ስምን፣ ዝናን፣ ክብርን የመትከል ፥ ለትውልድ የማስቀረት ናፍቆት።
4) ትዕቢት የእግዚአብሔር ጠላት ያደርግኸል፤
ትዕቢት ከሰዎች ጋር ብቻ አይደለም ጠላት የሚያደርገን ከእግዚአብሔርም እንጂ። እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ከልኬት በላይ ከእኛ የበላይ ነው። እግዚአብሔርን በዛ መነጽር እስካላየኸው እና አንተ ከሱ ግዙፍ ልኬት-አልባ ማንነት አንጻር ምንም እንደሆንክ ካላወክ በቀር ፥ እግዚአብሔርን አታውቀውም።
ትዕቢተኛ እስከሆንክ ድረስ እግዚአብሔርን አታውቀውም። ትዕቢተኛ ሁልጊዜ ሌሎችን ዝቅ አድርጎ እንዳየ ነው። ሁልጊዜ ዝቅ አድርጎ የሚያይ ደግሞ ከፍ ያለውን ሊያይ አይችልም። ይሄ ከባድ ጥያቄ ያስነሳል። “ታዲያ እንዴት ነው ትዕቢተኛ ሆነው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሰዎች ያሉት?” እኔ እንደሚመስለኝ እነሱ በአዕምሮአቸው ለቀረጹት ሌላ እግዚአብሔር ነው የሚንበረከኩት። ሀሳብ ወለድ የሆነውን እግዚአብሔርን እያመለኩት በህሊናቸው የሚያስቡት እንዴት ከተራው ሰው የተሻሉ እንደሆኑ ነው ፥ ከዚህ የውሸት የትህትና አምልኮ እጥፍ ትዕቢትን ይሰበስቡበታል።
እንደሚመስለኝ ጌታ ያለው እነዚህን ነው ፥ “በስሜ ይሰብካሉ፣ ድንቅም ነገርን ያደርጋሉ ፥ አጋንትንም ያወጣሉ፤” ይሄ ሁሉ ግን የሚደመደመው ፈጽሞ አላውቃችሁም በሚለው የሱ የመጨረሻ ቃል ነው። ምንአልባትም አንዳንዶቻችን በዚህ የሞት ወጥመድ ውስጥ ነው በዚህ ሰዓት ያለነው።
5) ትዕቢት ለሰይጣን አሳልፎ ይሰጠናል፤
ብዙ ጾሮቻ በስጋችን በኩል ከዳይብሎስ የሚሰነዘሩብን ናቸው። ትዕቢት ግን መንፈሳዊ፣ በጣም ድብቅ እና ገዳይ ነው።
ሰይጣን አንዱ የሚያደርገው ትዕቢትን በመቀስቀስ ሌሎች አነስተኛ ኃጢአቶችን እንድናሸንፍ ያደርገናል። ለምሳሌ መምህሮች ተማሪዎቻቸው ጎበዝ እንዲሆኑ ወይም መልካም ባህሪ እንዲኖራቸው ትዕቢቱን (በነሱ አጠራር ራስን የማክበር ስሜቱን) ይቀሰቅሱበታል። ብዙ ሰዎች ፍርሃትን፣ ዝሙትን፣ ቁጣን ማሸነፍ ችለዋል። እንዴት? እነዚህ ከእኔ ክብር በታች ናቸው ፥ ለእኔ ክብር አይመጥኑም በማለት። ሰይጣን በዚህ እንደሚደስት በምንም አይረካም። ሰይጣን አንተ ንጹሁ በመሆንህ፣ ታጋሽ በመሆንህ ወይም ጀግና በመሆንህ በጣም ደስተኛ ነው ፥ በላይህ ላይ ትዕቢትን እስካነገሰ ድረስ። ካንሰር እሰከሰጠ ድረስ ከቁስልህ መፈወስኽ ሰይጣንን ግድ አይሰጠውም። ትዕቢት መንፈሳዊ ካንሰር ነው፣ ፍቅርን ጨርሶ የሚበላ እና የሰው ልጅ ያለውን አስተውሎት የሚያጠፋ ነው።
6) በራሳችን ትዕቢት እንታወራለን፤
በውዳሴ መደሰት ትዕቢት አይደለም። ከእውነት እስከሆነ ድረስ ሰዎችን በማመስገን ማስደስት ስህተት የለውም፣ ችግሩ የሚጀምረው በውዳሴው መደሰት አቁመኸ በራስኽ መደሰት ስትጀምር ነው። ዋነኛው፣ ሰይጣናዊ ትዕቢት ያለው ሌሎችን ዝቅ አድረገ መመልከት ስትጀምር እና ሰዎች ስለሚሉት ነገር ግድ ሳይሰጥኽ ሲቀር ነው። ስለሰዎች ሀሳብ ምንም አለመጨነቅ አንዳንዴ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታችን ነው ፥ ያ ግን በትክክለኛው ምክንያት ሲሆን ነው። ማለትም እግዚአብሔር ስለእኛ ያለው ሀሳብ ሲበልጥብን።
ትዕቢተኛ ግን የማይጨንቀው ለሌላ ምክንያት ነው። ትዕቢተኛ እንደዚህ ይላል “የማደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የማደርጋቸው ለማንነቴ ነው፣ ፍላጎቴን ለማርካት ፥ መጠራቴን ለማስደሰት ነው ወይም ለቤተሰቤ ክብር ስልነው ወይም እኔ እንደዛ ስለሆንኩኝ ነው በቃ። መንጋው ቢወደኝ ይሁን ፥ ካልወደደኝም የራሱ ጉዳይ። እነሱ ለእኔ ምንም ናቸው።”
ትዕቢተኛ ስትሆን የሆኑ መጽሐፍትን በማንበብኽ ትኮፈሳለ ፥ የጻፉት ሰዎች እኮ በመጽሐፉ መደሰት አቁመዋል። (የቶልስቶይን War and Peace እና አና ካሪኒና በማንበቤ እኮፈስ ነበር። ቶልስቶይ ግን በሕይወቱ መጨረሻ እነዚህን መጽሐፎቹን ይጠየፋቸው ነበር)።
7) ትሁቱ ትዕቢተኛ፤
የሆኑ መንፈሳዊ ፍሬዎች ሰይጣንን ምንም አይረብሹትም። የትኞቹ? እንዳለኽ የምታውቃቸው መንፈሳዊ ማንነቶችኽ። በተለይ ለትህትና ይሄ በጣም ትክክል ነው። በጣም ትሁት እንደሆንክ ይሰማኸል ፥ ይሄ ስሜት ከተሰማ በርግጠኝነት ትዕቢተኛ ነህ።
በጣም ትሁት ሳለን፣ በመንፈሳችን መጻጉ ሆነን ሲያገኘን፤ ከዛ በአዕምሮአችን ውስጥ “ዋው! እንዴት ትሁት ነህ እኮ” የሚል ሀሳብ ያሰርጋል። ወዲያው በትህትና ትዕቢት ይመጣል። አዋቂ ሆነን ሳለን “ደድብ ነኝ እኮ እኔ” እንድንል ያደርገናል፣ ለታይታ ወንበር ያስለቅቀናል፣ ወገባችንን ሰብረን ሰው ሰላም እንድንል ያደርገናል፣ አንተ እኮ እንደዚህ ነህ ሲለን “አረ እኔ ፈጽሞ” እያልን የአፍ፣ የከንፈር ጫወታ እንድንጫወት ይጋብዘናል። በዚህ የሰይጣን ጫወታ ሺዎች ትህትና ማለት ቆንጆ ሴት “መልከ ጥፉ ነኝ” ብላ ማመን፣ ጎበዝ ሰው “ደደብ ነኝ” ብሎ ማሰብ፣ ጀግና “ፈሪ ነኝ” ብሎ መቀበል እንዲመስላቸው አድርጓል። እነዚህ ሰዎች መቼም ይሄን በልባቸው እውነት ነው ብለው ስለማይቀበሉ ከእውነተኛው ትህትና ይቆርጣቸዋል። ይልቁስ አዕምሮአቸው ዘወትር በራሳቸው ዙሪያ እንዲሽከረከር ያደርጋል። ሰይጣን በክፋት ከሚያሸንፈን በላይ በበጎ ባህሪያት የሚያሸንፈን ይበልጣል። ለሰዎች ቸርነት ማድረጋችንን ዘወትር ያስታውሰናል፣ ለሰው ስንነግር ደግሞ “መንገር ፈልጌ አይደለም ግን” ብለን ትህትና ጣል እንድናደርግበት ይጋብዘናል። ምክንያቱም ክፋታችንን ካየን ልንታረም እንችላለንእና። ስለዚህ በበጎ ተግባራችን ራሱን ይደብቃል። ትዕቢት እሰከሰጠን ድረስ፣ ቀኝ እጃችን ያደረገውን መልካም ነገር ለግራው በየጊዜው እስካስታወስነው ድረስ ፥ በበጎ ምግባራችን ሰይጣን ተከፍቶ አያውቅም።
ሉዊስ ስለትዕቢት የጻፈውን ደጋግሜ ካነበብኩኝ በኋላ ራሴን ጠየኩት “ለምንድነው ይሄን ጹሁፍ ደጋግመኸ ያነበብከው?” ብዬ። መልሴ አጭር ነበር። “እንደነዛ ትዕቢተኞች ላለመሆን።” ጹሁፉን ደጋግሜ ካነበብኩ በኋላ ራሱ በትዕቢት ምክንያት እንደማነበው ያወኩት በመጨረሻ ነበር። “እንደነዛ ላለመሆን!” አሁንም ያ የመለየት፣ ልዩ የመሆን የትዕቢት መሠረት ነበር ስለትዕቢት መጥፎነት ራሱ የሚያስነብበኝ።
የትህትና ግቡ ትዕቢተኛ አለመሆን ነበር የመሰለኝ፤ ያውም እንደነዛ ትዕቢተኛ አለመሆን። ሰይጣን በእጅጉ ነበር የተሳካለት ምክንያቱም ስለትዕቢት በመማር በትህትና ወደ እግዚአብሔር መቅረብን ሳይሆን የተማርኩት ፥ ስለትዕቢት በማወቅ ወደ ሚበልጠው፣ ከእኔ እንኳ ወደተሰወረው ትዕቢት ነበር የተመነደኩት።
ትሁት እንዴት መሆን እንችላለን?
የመጀመሪይው ደረጃ ትዕቢተኛ እንደሆንን ማወቅ ነው። ትዕቢተኛ እንደሆንክ ካላወክ ፥ እንግዲያውስ በጣም ትዕቢተኛ ነህ። ትዕቢት እንደመጥፎ የአፍ ጠረን ነው። ከአንተ በቀር ሁሉ ሰው አፍህ እንደሚሸት ያውቃል እንዴት ግን ለአንተ ይንገሩኽ? ከነገሩኹ አሁንም አፍህን ከፍተኸ ልትናገር ነው። በዛም መጥፎ ጠረንኽ ሊረብሻቸው። ለዚህ ነው ትዕቢት አፍኖ የሚገለን።
ትሁት ሰው ደስተኛ ነው፣ ስማርት ነው፣ በሚያወራቸው ሰዎች ልዩ ፍላጎት ያሳያል፣ ሰዎች ከሱ ጋር ሲያወሩ የእሱ ጠቢብነት እና አስተዋይነት ሳይሆን የእነሱ ጠቢብ እና አስተዋይ መሆናቸው ነው የሚታያቸው። ከትሁት ሰው ጋር የሚያወራ ሰው ምንም በደለኛ ቢሆን ያ ሰው እየፈረደበት እንዳልሆነ ቆዳው ስለሚነግረው ምቾት ይሰማዋል። ይሄን ሰው የማንወደው ስለምንቀናበት ነው ምክንያቱም ሕይወትን በቀላሉ ይደሰትባታል። ስለትህትና ፈጽሞ ሲያስብ አታዩትም ፥ አረ እንደውም ስለራሱ ሲያስብ አታገኙትም።

Comments