ክፍል ሦስት

ኮምፕሌክስ ኮሜርሻል ሊቲጌሽን ብቻ የሚሰራ የጠበቆች ቢሮ ሰርቼ ነበር። ሥራው እጅግ ከባድ ነበር። አለቃችን የነበረችው ሴትዮ ከባድ የሕግ ክስ ሲኖርብን ፥ ስለ ኬዙ እንዴት እንደምታስብ ስትነግረን ፥ “እኔ እንደዚህ ከባድ ክስ ሲገጥመኝ ለጁሪው (ፍርድ የሚሰጡት አስራ ሁለቱ የማህበረሰቡ አካላት) ከሚነበበው ትዕዛዝ ነው የምጀምረው” ትል ነበር። ይሄ ማለት ዋናው ቁም ነገር “ምን ተብሎ ነው ጁሪው ሊፈርድብን የሚችለው” የሚለውን የመጨረሻ ትዕዛዝ ማየት ማለት ነው። ከመጨረሻው የጀመረ ሰው ፥ በመኃል በሚወረወርለት ነገር ትኩረቱን አያጣም። በርግጠኝነት የምነግራችሁ ማንኛውንም ነገር ለማሳካት ተነሱ ፥ እጅግ አስተዋይ ካልሆናችሁ በቀር ግባችሁን በቀላሉ የሚያስረሱ አዕምሮአችሁን የሚቆጣጠሩ ጥቃቅን ነገሮች በመኃል እንደ እንጉዳይ ይፈለፈላሉ። በመቀጠል እነዚህ በመኃል የተፈጠሩትን ነገሮች በመፍታት የተነሳችሁበትን ዓላማ ፈጽሞ ትረሳላችሁ። ከዛ ሲጀምር ይሄን ነገር ለምን እንደጀመራችሁት ራሱ ነው ግራ የሚገባችሁ።
አሁን የምነግራችሁ በቅርብ ከአንድ ጠበቃ ወዳጄ ጋር የተወያየንበት ክስ ነው። ከፍተኛ ሽያጭ የነበረው ሰውዬ ተጨማሪ ዕቃ ለማስገባት ካሽ (cash) ያጥረዋል። ደንበኞቹን ላለማጣት ደግሞ ዕቃው የግድ ያስፈልገዋል። ከዛ ወዳጁ ጋር ሄደ ብድር ጥየቃ። ወዳጁን $90 ሺ የአሜሪካ ዶላር እንዲያበድረው ጠየቀው። ይሄ ወዳጁ ጓደኛውን ለመርዳት ተስማማ። ነገር ግን የቤቱ ታይትል ላይ ሊን (የባለቤትነት ድርሻ ወይም (interest)) አኖረ። በአንድ ዓመት ውስጥም እንደሚመልስለት ቃል ገባለት። በአንድ ዓመቱ ግን ጓደኛው መመለስ አልቻለም። የመክፈያ ጊዜውን እንዲያራዝምለት ጥያቄ ቢያቀርብለትም እንቢ አለው። ከዛ ቤቱን ለሽያጭ በማቅረብ ብድሩን ለመመለስ ተካሰሱ። ፍርድ ቤቱ “ቤቱ ለሀራጅ ሽያጭ እንዲቀርብ” ወሰነ። የሁለቱ ሰዎች ወዳጅነት ወደ ጠላትነት ተቀየረ።
ተመልከቱ። የጓደኛው ግብ ወዳጁን መርዳት ነበር። ወዳጅነቱን የበለጠ ማጠንከር ነበር። በብድሩ መጨረሻ ላይ ጓደኛውን እንደሚያጣ ቢያቅ ኖሮ አያበድርም ነበር። እርሱ ያሰበው የጓደኛውን የአሁን ችግር መፍታት እንጂ ነገ ጠላት እየፈጠረ እንደሆነ ፈጽሞ አልገባውም። ምክንያቱም የዚህ መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል ፈጽሞ አልገመተም። ሌሎች ሰዎች በተመሳሳይ ምክንያት ከወዳጅነት ወደ ጠላትነት እንደተቀየሩ ቢያቅም ይሄ ግን በእነርሱ ላይ አይደርስም ብሎ አሰበ። የእነሱ ወዳጅነት ከዚህ ነጻ እንደሆነ ገመተ። ከመጨረሻው ለመጀመር አለመፈለግ ማለት ይሄ ነው።
በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ያለን ሰዎች ከመጨረሻው ቀን ብንጀምር ብዙ ነገር የሚቀየር ይመስለኛል። ምንአልባት ብዙዎቻችን ቀላል የማይባለውን ጊዜ ምንም ከዚህ ትዕዛዝ ጋር በማይገናኝ መልኩ እያሳለፍን መሆኑን ይገባን ነበር። የመጨረሻው ትዕዛዝ ይሄ ነው “ማነው ተርቤ ያበላኝ፥ ማነው ተጠምቼ ያጠጣኝ፥ ማነው እንግዳ ሆኜ የተቀበለኝ፥ ማነው ታርዤ ያለበሰኝ ፥ ማነው ታምሜ የጠየቀኝ ፥ ማነው ታስሬ የጎበኘኝ።” “የተራበ ማነው ያበላው” ተባብለው ክርስቲያኖች ሲጣሉ እስካሁን አላየንም። በብዙ በዚህ ቀን መለኪያ ባልሆኑ መስፈርቶች ግን ክርስቲያኖች በየቀኑ በሁሉም ቦታ ይከራከራሉ። ይጣላሉ። የጁሪው ትዕዛዝ በመኃል ተዘንግቷል። ሁሉን ነገር ትቶ ይሄ የመጨረሻው ቀን መጠይቅ (checklist) ላይ ያተኮረ ሰው በመጨረሻው ቀን ከማንም በቀደመ በቀኙ ለመቆም የበቃ ይሆናል።
ከመጨረሻው አለመጀመር። በቅርብ በጣም በሥራ ተወጠርኩኝ። በመኃል በየቀኑ ሥሰራ የነበረውን የአካል እንቅስቃሴ በዚህ ውጥረት ምክንያት ተውኩኝ። የሆነ ሰዓት ባነንኩኝ። ምንድነው የዚህ ሥራ ግብ? ጤናዬን እና ዘላቂ አዕምሮአዊ እና አካላዊ ማንነቴን አሳልፌ የምሰጥ ከሆነ። የሥራ መጨረሻ ለማረፍ ከሆነ፤ ይሄን እረፍት ማግኘት የምችለው ጤናዬ እስካለ ድረስ ብቻ ነው። ስለዛ ግቡን እየዘነጋው ነው። ቅድመ ተከተሉ ጠፍቶኛል።
ከመጨረሻ ቢጀምሩ ኖሮ ዛሬ በሀገራችን ያሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች የሚካሄዱ ይመስላችዋል? ግቡ የተማሩ፣ ጤናማ የሆኑ፣ አስተዋይ እና ክብራቸው የተጠበቁ ማህበረሰቦችን ለመፍጠር ከሆነ ፥ የተራዘመ የእርስ በእርስ ጦርነት ይሄን ግብ ሲያሳካ አይታችሁ ታውቃላችሁ? አሁን ግቡ ተረስቷል። ምክንያቱም በመኃል ብዙ ደም ፈሷል። ብዙ ሰው እና ንብረት እንዳይሆን ሆኗል። አሁን ግቡ ግለሰባዊ እና ጀብደኝነት ሆኗል። ዛፉን እንዳታዩ ትፈልጋላችሁ ፥ ደን ውስጥ ደብቁት።
መኪና በጂፒየስ ስትነዱ ምንድነው የምታደርጉት? የመጨረሻውን፣ መዳረሻችንን አድራሻ እናስገባለን። ያ ምን ይሰጠናል? የተዘጉ መንገዶችን ትቶ ትራፊክ ያልበዛባቸውን አማራጮች ያሳየናል። በመኃል መንገድ ጀምረን ሳይቀር፣ መንገዱ ከተጨናነቀ ሌላ አቅጣጫ ይጠቁመናል። መጨረሻውን ስላስገባነው፣ አማራጮችን ማሳየት አይከብደውም። መንገድ ስንስት ሳይቀር በቶሎ ወደ መዳረሻችን አቅጣጫ ይመልሰናል። ለምን ታዲያ ይሄን በሕይወት፣ በኑሮአችን አንጠቀምም? ከመነሳታችን፣ ምንም ነገር ከማረጋችን በፊት መዳረሻችንን ማየት፣ የት መድረስ እንደምንፈልግ በግልጽ ማወቅ። በየመኃሉ ለመዳረሻችን ምን ያህል እየቀረብን እንደሆነ መመልከት፣ ልክ እንደ ጂፒየሱ መዳረሻችንን ፈጽሞ ከእይታችን አለማራቅ። ዘወትር ምንድነው ግን ማሳካት የምፈልገው ብሎ መጠየቅ። ንግግር ጀምሩ ፥ እንዴት በፍጥነት ያ ንግግር ሊያሳካው ካለመው ዓላማ ስትወጡ በመኃል ራሳችሁን ታገኙታላችሁ። ጂፒየሱን የሳተ ንግግር ማለት ይሄ ነው።
በትዳር ውስጥ፣ በጓደኝነት ውስጥ ያላችሁ ሰዎች ታውቃላችሁ። አንደኛው አካል በክርክር እና ነገሮችን በማስረዳት እንዲሁም በቋንቋ አጠቃቀም በጣም ጎበዝ ይሆናል። ከዛ ልክ የሆነ ችግር ተፈጥሮ ማውራት ስትጀምሩ ፥ ያ ሰው አፍ አፋችሁን እየመታ ዝም ያሰኛችዋል። ክርክሩን ሁልጊዜ ይረታል። በዚህም ለጊዜው አሸናፊ ሆኖ ይወጣል። ግን የተሸነፈውን፣ ብዙ ያላወራውን ሰው ልብ ፈጽሞ አላሸነፈውም። ጭራሽ ያ ሰው በውስጡ እየመረረው ነው። ወይ ያን ሰው የሚያስመርር ነገር ይሰራል ወይም ይሄን ወዳጅነት ቀስ እያለ ይርቀዋል። ፍቺውን ይጀምራል። ግን ግቡ ይሄ ነበር? የዛ ክርክር እና ውይይት ግቡ አንዱ አንዱን መገነዛዘብ እና ልባቸውን ማሸነፍ ነበር። ያን ወዳጅነት፣ ያን ትዳር እና ግንኙነት ወደ በለጠ ጥልቀት መውሰድ ነበር። ግን በመኃል የራስን ልክነት ማሳየት ሆነ ግቡ። ግቡ ክርክሩን ማሸነፍ ሆነ። ውጊያውን አሸንፎ ጦርነት ላይ መረታት (wining the battle but losing the war) ይለዋል ስትራቴጂስቱ ሰን ዙ። ከመጨረሻው የማይጀምር ሰው ሁልጊዜ ችግር ያልሆነንን ነገር ሲፈታ ጊዜውን ይጨርሳል።
እስቲ አስቡት ዘወትር መጨረሻችንን ብናስብ። እሱም እንደምንሞት። በጣም በቅርቡ ዓለምን እንደምንረሳ ፥ በጣም በቅርቡ እኛም በዓለም ፈጽሞ እንደምንረሳ ብንገነዘብ እና ያን በየቀኑ ብናስብ የሚኖረንን ውሳኔ አስቡ? ይሄ ፈጽሞ የማይቀር መጨረሻ ነው። ስለሚቀጥለው ነገር ባናውቅ እንኳ ሁሉም ስለሚደርስበት መጨረሻ ሞት ግን እናውቃለን። ያ ዕለታችንን የምንኖርበትን መንገድ ይለውጠዋል። ለሚወረወርብን ሁሉ መልስ የምንሰጥበት ምንም ጊዜ አይኖረንም። በጣም አንኳር የሆኑ ነገሮች ብቻ የኛን ትኩረት ያገኙ ነበር። ያ ደግሞ የብዙ ችግር፣ እጅግ የብዙ ችግር መፍቻ ቁልፍ ነው።
Comments