April 20, 2023
ጥሩ ሕይወት የጥሩ ውሳኔዎች ድምር ውጤት ነው። ግን ማነው ጥሩ ውሳኔ መወሰን የማይፈልግ? ማነው የመጥፎ ውሳኔዎች ባለሙያ መሆን የሚሻ? ይልቁስ በሙያችን ተቀጥረን የምንሰራ ወይም ሙያችንን የምንሸጥ ሰዎች ፥ ቀጣሪዎቻችን ስለውሳኔያችን አይደል እንዴ የሚከፍሉን? እንደ ጠበቃ ደንበኞቼ የሚከፍሉኝ ስለ ጥሩ ውሳኔዎቼ እንደሆነ አውቃለሁ። ስለዚህ የዘወትር ሥራዬ ጥሩ ውሳኔዎችን እንዴት ነው መወሰን የምችለው የሚለውን ጠንቅቄ ማወቅ ነው። መጥፎ ውሳኔዎቼ የእኔን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ሰዎች ሕይወት ይጎዳል።
ነገር ግን አይደለም ብዙ የማናውቃቸው ነገሮች ባሉበት ጉዳዮች ቀርቶ ብዙ እውቀት ባለን ጉዳይ ራሱ ጥሩ ውሳኔ መስጠት በጣም ከባድ ነገር ነው። በርግጥ አንዳንዴ አንዳንድ ውሳኔዎችን በቀላሉ በፍጥነት ስንሰጥ በሌሎች ጉዳዮች ደግሞ መዘግየት እና ሪስክን ለመቀነስ መጣር ይገባል።
የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞ ውሳኔዎችን እንደ በር ወይም እንደ መንገድ ነው የሚያያቸው። የሆነ ነገር ሲገጥመው መጀመሪያ የሚጠይቀው ይሄ ነገር አንድ አቅጣጫ በር ነው ወይስ ሁለት አቅጣጫ (one way route or two-way route)? ምን ማለት ነው? ምንድነውስ ልዩነቱ?
በተለይ በሃይዌይ ላይ የምትነዱ ከሆነ ይሄ በቀላሉ ይገባችዋል፤ በአንድ አቅጣጫ መንገድ ውስጥ ከገባችሁ ወደ ኋላ መመለስ የለም። አንዴ ከገባችሁ ገባችሁ ነው ፤ ሌላ መውጫ አግኝታችሁ በሌላ መንገድ እስከምትሄዱ ድረስ። ሁለት አቅጣጫ ከሆነ ግን፤ ከሳታችሁ እዛው መንገዱን አቋርጣችሁ መታጠፍ ትችላላችሁ። ጄፍ ለሼር ሆልደሮቹ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፤ “አንዳንድ ውሳኔዎችን ማጠፍ እና መለወጥ አይቻልም። እነዚህን ውሳኔዎች በጥንቃቄ፣ በጣም ቀስ ተብሎ፣ ከፍተኛ ጊዜ ወስዶ እና ብዙ ምክክር አድርጎ መወሰን ያስፈልጋል። እነዚህን ውሳኔዎች አንድ አቅጣጫ ውሳኔ እንላቸዋለን። ነገር ግን ብዙ ውሳኔዎች እንደዛ አይደሉም። በቀላሉ ማጠፍ፣ መለወጥ እና መቀየር እንችላለን። እነዚህን ባለሁለት አቅጣጫ ውሳኔዎች እንላቸዋለን። እነዚህ መመለስ የምትችሉባቸው በሮች ናቸው። በሩን እንዳለፋችሁ፣ ልክ ካሎናችሁ፣ በሩን መልሶ ከፍቶ ወደ መጡበት መሄድ ነው። ትልቁ ጥፋት ለደረጃ አንድ የሚገባውን ዓይነት ውይይት፣ ክርክር እና ጊዜ ለሁለተኛው፣ ማለት መመለስ ለምንችልበት ውሳኔዎች ስንሰጥ ነው። ስለዚህ ጥበቡ የትኛው ነው ባለአንድ አቅጣጫ? የትኛው ነው ባለሁለት አቅጣጫስ? የሚለውን ማወቅ እና ለአንዱ የሚያስፈልገውን ጊዜ እና ትኩረት ለሌላው አለመስጠት ነው።
ለምሳሌ አዲስ የጥርስ ቡርሽ ለመሞከር የሚፈልግ ሰው፣ ስለዛ ጉዳይ ከአንድ እና ሁለት ደቂቃ በላይ ማሰብ አይገባውም። ካልተመቸው መቀየር ይችላል። ባለሁለት አቅጣጫ መንገድ (ውሳኔ) ነው። ይሄ ግን ቤት ለመግዛት ወይም የትዳር አጋሩን ለመምረጥ ለሚፈልግ ሰው የሚጠቅም አይደለም። ምክንያቱም ያ ባለ አንድ አቅጣጫ መንገድ ነው። አንዴ ከገቡበት በኋላ ፥ መዘዙ እስከ እለተ ሞታችን ሊከተለን ይችላል። ስለዚህ ከፍተኛ ጊዜ መውሰድ፣ መወያየት፣ ማጥናት፣ ምክር መጠየቅ እና ሌሎች ተጨማሪ ማስረጃዎችን መሰብሰብ ሊያስፈልገን ይችላል። ውሳኔዎችን በዚህ ዓይን ማየት ከጀመራችሁ ፥ ሁሉ ነገር ይቀየራል።
አንድ አቅጣጫ ባለው ውሳኔዎች ጉዳይ ላይ የሚያስቸኩሏችሁ ሰዎች አጭበርባሪዎች ወይም አላዋቂ ናቸው። ከእነዚህ ተጠበቁ። ሁለት አቅጣጫ ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚያዘገዩአችሁ ሰዎች ደግሞ ፈሪዎች ናቸው፣ እነዚህ ኋላፊነት የሚሸሹ እና ምንም ነገር እንዳትፈጽሞ ማነቆ የሚሆናችሁ ስለሆነ ፥ ይሄን አውቃችሁ ፍጥነትን ገንዘብ አድርጉ።
ሁለት አቅጣጫ ባላቸው ውሳኔዎች ዙሪያ ውሳኔዎችን በፍጥነት ወስኑ። መሪነት ማለት ያ ነው። አንድ አቅጣጫ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ግን ዘግዩ። አማክሩ። ተማከሩ። ማስረጃ ሰብስቡ። ሪስኮችን ዳሱ። ራሳችሁን ብቻ አትመኑ።
አንድ አቅጣጫ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ትልቁ አደጋ ስህተት መስራት ነው። ስለዚህ ጊዜ በመውሰድ የምታባክኑት እንደኪሳራ አትቁጠሩት።
የዛሬ ስምንት ዓመት የሕወኃትን ሥርዓት በመሳሪያ የሚታገለውን ግንቦት ሰባት የተባለ ድርጅትን ኤርትራ ድረስ ሄደው ለመቀላቀል የወሰኑ የሦስት ሰዎችን ታሪክ በቅርበት አውቃለሁ። እነዚህ በትልልቅ ቦታዎች ላይ የነበሩ ጓደኛሞች በሰዓቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ኋላፊነት ላይ የነበሩትን የድርጅቱ አመራሮች በስልክ ተገናኝተው፣ የሚሄዱበትን አቅጣጫ ሁሉ አውርተው፣ ወደ ኤርትራ ጉዞ የሚጀምሩበትን ቀን ቆርጠው ነበር። ከመኃከላቸው አንዱ ከጉዞው ጥቂት ቀናት በፊት የመንፈሳዊ አባቱን አማከረ። እኛም አባት በጣም ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቁት። በተለይ ድርጅቱን እንዴት እንዳመኑት፣ እርስ በእርስ እንዴት እንደተማመኑ፣ ስለድርጅቱ ስለሚያውቁት መረጃዎች ሁሉ በጥልቀት ጠየቁት። ልጁ በኢሳት ከሚሰማው ውጪ ስለድርጅቱ ምንም ጠንካራ የሦስተኛ ወገን መረጃ እንዴለለው ተገለጸለት። ስለጓደኞቹም ጽኑ አቋም ከእነሱ ከሰማው ውጪ በምንም እርግጠኛ እንዳልሆነ ገባው። ከዛም እኛ አባት የልጁን ውሳኔ ፊት ለፊት ከመቃወም ይልቅ፣ ለስድስት ወራት እንዲያራዝመው ብቻ ጠየቁት። ተስማማ።
በሦስት ወር ውስጥ ብዙ ነገር ተፈጽሞ ጠበቀው። ከመካከላቸው አንዱ ወደ ትዳር ዓለም ገባ። ከዛ በተባለው ጊዜ ውስጥ ስለግንቦት ሰባትም ብዙ መረጃዎች አገኘ። ትግሉም መስመሩን መለወጥ ጀመረ።
ያኔውኑ እንደወሰኑ ተነስተው ቢሄዱ ኖር፣ ዛሬ ላይ የጸጸት ሕይወትን ሊኖሩ እንደሚችሉ አስቡት። ጊዜያዊ ስሜታቸው እንጂ ሁሉም ለትግል ከምርም ዝግጁ እንዳልነበሩ የጥቂት ጊዜ መራዘም ነገሮችን ግልጥ አደረገ። ከዛም በላይ ያ መስመር ፍጹም የተሳሳተ እና የተባለውን ውጤት ያላመጣ፣ በዛ ትግል ውስጥ ያለፉም ሰዎች ታሪካቸው ራሱ የማይዘከር ወይም ዛሬም በሌላ ማለቂያ የሌለው ትግሉ ውስጥ እንዳሉ ተመልከቱ። “ለአንቺ ነው ኢትዮጵያ” ብለው ስንቱን ወጣቶች ለትግል እና ለሞት የዳረጉ የግንቦት ሰባት አመራሮችም ሆነ የኢሳት ባልደረቦች ዛሬ ላይ ያሉበትን ሁኔታ ስትመለከቱ የአንድ አቅጣጫ ውሳኔን ባህሪ ተረድተው ፥ በጥበብ ያዘገዩት እኛ መንፈሳዊ አባት ለወዳጄ ታላቅ ባለውለታ እንደሆኑት ታያላችሁ።
በሕይወት የአንድ አቅጣጫ ውሳኔን ስትወስኑ ምራቅ የዋጡ፣ ብዙ ታሪኮችን ያዩ፣ እውቀት እና ልምድ ያላቸው፣ ከስሜት የራቁ ሰዎችን ማናገር እና ማወያየት ከዘላለም ጸጸት ያድናል።
በተቃራኒው ደግሞ ልብስ ለመግዛት፣ ዕቃ ለመቀየር ወይም ሠራተኛም ለማባረር በፍጥነት ልትወስኑ ትችላላችሁ። ነገር ግን የሕይወት አቅጣጫችሁን ለሚቀይር ነገር፣ የባለ አንድ አቅጣጫ ውሳኔ ግን ልብ ግዙ።

Commentaires