top of page
Search

እጥረት እንሁን

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Nov 3, 2024
  • 3 min read




“ፍላጎት ገደብ የለውም ፥ ሀብት ግን ገደብ አለው” ወይም “demand is unlimited but all resources are scarce” የሚለው የእንግሊዘኛ ዓረፍተ ነገር የኢኮኖሚክስ ክላስ ሁሉ ሀ ሁ ነው። እጥረት ማለት አንድን ፒዛ ለመቶ ሰው ለማከፋፈል እንደመጣር ነው። በኢኮኖሚክስ እጥረት ማለት ብዙ ሰው የሚፈልገው ነገር በተመጠነ ቀጥር ብቻ ሲኖር ማለት ነው። በተመጠነ ቁጥር ያለ ግን ብዙ ሰው የማይፈልገው ነገር ዋጋው በጣም ዝቅተኛ ወይም ርካሽ ነው። በተመሳሳይ ብዙ ሰው የሚፈልገው ነገር ፥ ግን በብዛት ያለ ነገርም ዋጋው ርካሽ ነው። እጥረት የሰዎችን የመወሰን አቅም ይቀርጻል። ማለትም በሆነ ጊዜ በጣም ያጠረን ነገር ዘወትር ባህሪያችንን ሊመራው ይችላል። ለምሳሌ በልጅነቱ በጣም ደሃ የሆነ እና የተቸገረ ሰው ፥ በኋላ ላይ ገንዘብ ቢኖረውም አላስፈላጊ የሆነ ስግብግብነት ወይም የገንዘብ ስስት ሊያሳይ ይችላል። ምክንያቱም ወደ ዛ ችግር እመለሳለው የሚለው ፍራቻ አሁን ላይ ተትረፍርፎት ቢሆን እንኳ አላስፈላጊ የተጋነነ ቁጠባ ውስጥ ራሱን ሊከት ይችላል።



በሚገርም ሁኔታ ግን እጥረት በራሱ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። ይልቁንስ መትረፍረፍ የበለጠ ሊጎዳን ይችላል። በዓለም ላይ በረሃብ ከሚሞተው በላይ በውፍረት ከሚመጣ በሽታ የሚሞት ሰው ይበዛል። የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ በነበረኝ የስደተኞች ጉዳይ ጥናት ባህር እየተሻገሩ የሚሰደዱ እና የሚሞቱ ሰዎች ድኇች እንዳልሆኑ የደረስንበት ጥናት ነው። ምክንያቱም በሰዓ ያንን ስደት ለማድረግ ከሰባት ሺ እስከ አስራ አምስት ሺ የአሜሪካ ዶላር ያስፈልግ ነበር። ያ ገንዘብ የኢትዮጵያ ድሃ ኖሮት አያውቅም። ስለዚህ ድህነትን ተላቀው የወጡ ሰዎች ነበ ይሄን ስደት የሚመርጡት። ምክንያቱም ሀብታም ለመሆን። ድህነትን ለማምለጥ ሳይሆን።


የብዙ ስህተቶች ምንጭ ከእጥረት በላይ መትረፍረፍ ነው።



የዚህ ጹሁፌ ዓላማ በዚህ የኢኮኖሚክስ ጽንሰ ሀሳብ ላይ አተኩሬ መጻፍ አይደለምይልቁንስ እንዴት እጥረትን እኛ መጠቀም እንደምንችል እና እኛ ራሳችን እጥረት መሆን እንደምንችል ማሳየት ነው።


እጥረት የፈጠራ ምንጭ ነው። የገንዘብ እጥረት ነው ለብዙ መፍትሔዎች መሰረት። ነጋ የሆነ ነገር እንደምናጣ ስናስብ ነው ሰውን በአግባቡ መጠየቅ፣ መልካም መሆን የምንጀምረው። ነገ ገንዘብ ሊያጥረን እንደሚችል ስናስብ ተጨማሪ ሙያ መማር እንጀምራለን። ነገ ብቸኛ ልንሆን እንደምንችል ስናስብ እና ስንሰጋ ወደ ትዳር፣ ልጅ ወደ መውለድ ወዳጆቻችንን ወደ መጠየቅ እንገባለን። እጥረትን በሆነ መጠን ስንቀምሰው ወዲያው ባህሪያችንን መቀየር እንጀምራለን። ጤና የተትረፈረፈ ነገር እንዳልሆነ የምናውቀው የጤና እጥረት ሲገጥመን ነውከዛ ስለጤናችን ማሰብ፣ ጥሩ ምግብ መብላት እና ስፖርት ወደ መስራት እንሄዳለን። “በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል" እንላለን። ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ያሉ ሰዎች ድንገት ሲለዩን ፥ እነሱ በሕይወት እያሉ ያሳየነው መዘናጋት እንደ እግር እሳት ይለበልበናል። ብዙ ሰው ግን በመትረፍረፍ ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚቻል አያውቅም። ስለዚህ እጥረትን እስከሚቀምስ ድረስ ማሰብ አይችልም።



በተያያዘ ደግሞ እጥረት ያላቸው ነገሮች እና ሰዎች የሚፈልጉት ነገር ዋጋው ውድ ነው። ለምሳሌ ወርቅን ተመልከቱ። በየቦታው እንደ ልብ ያለ ቢሆን በዚህ ደረጃ ዋጋው አይወደድም ነበር። እጥረት ነው ዋጋውን ያስወደደው። ለዚህ ነው አንዳንድ ኩባንያዎች ምርታቸውን በጣም ትንሽ ብቻ በማድረግ ዋጋውን ሰማይ ይሰቅሉታል። ለምሳሌ እንደ ሬንጅ ሮቨር ያሉ መኪኖች ከቶዮታ አንጻር ጥንካሬያቸው እና የመገልገያ ዘመናቸው በጣም ያነሰ ቢሆንም ኩባንያው ግን በጣም ትንሽ ቁጥር ያለው ሬንጅ ሮቨር በማምረት ፥ ዋጋውን ሰማይ ይሰቅሉታል፤ በዚህም የክላስ ጉዳይ ያደርጉታል። ይሄ ለሰውም ይሰራል። እጅግ ጥሩ እና መልካም ብትሆኑንም ዘወትር ካላችሁ፣ በቀላሉ የምትገኙ ከሆነ ግን ሰዎች ዋጋችሁን ዝቅ ያደርጉታል። ሁሌ እንደምትገኙ ካሰቡ ላቀረባችሁት መልካምነት የሚሰጡት ዋጋ እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል።



ለዚህ ነው እጥረት በራሱ መጥፎ ያልሆነው። ለምሳሌ ታማኝ ናችሁ፣ በዚህ ላይ ጠንካራ ሰራተኛ እና እጅግ ስማርት ናችሁ እንበል። በዚህ ዓለም ላይ እነዚህን ሦስት ባህሪዎች ገንዘብ ያደረገ ሰው በጣም ጥቂት ነው። ታማኝ ሰው ስታገኙ ሥራ አይችልም። ነገር አይገባውም። ነገር የሚገባው ብሩህ አዕምሮ ያለው ሰው ስታዩ ደግሞ ጥቂት ጠጋ ብላችሁ ስትፈትሹት ጠንካራ ሰራተኛ አይደለም። ወይም ታማኝ አይደለም። ስለዚህ እነዚህን ሦስት ማንነቶች ታማኝነትን ከብሩህ አዕምሮ ጋር ፥ ብሩህ አዕምሮን ከትጋት እና ዲሲፕሊን ከሆነ ሰራተኝነት ጋር አዋህደን ከያዝን በዚህ ዓለም ላይ መቼም ሥፍራ አናጣም። የኛ ዋጋ ሁልጊዜ ከፍ ያለ ነው። እንደ እንቁ ውድ ነን። በአንድ ነገር ላይ ምርጥ መሆን ብቻ አይደለም ግን ብዙ ነገሮችን አዋህዶ መያዝን እንጂ። ለዚህ ነው “እጥረት እንሁን” ያልኩት። ምርጥ አይደለም፤ የማንተካ እንሁን። የኛ መጉደል ትልቅ ክፍተት የሚፈጥር ይሁን። ያን በተንኮል ሳይሆን በብቃታችን እንፍጠር። የኛ መጉደል በነካነው ቦታ ላይ ሁሉ በጎ ትውስታን የሚፈጥር ከሆነ የዛኔ እጥረት ነን ማለት ነው።



ጻድቁ ኢዮብ እጥረት ነበር። ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። እነዚህን ሦስቱንም የሆነ ሰው አልነበረም። ፈሪያ እግዚአብሔር የሌላቸው ግን ቅን ሰዎች አሉ። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ግን ከክፋት መራቅ ያልቻልን አለን። ኢዮብ ግን እጥረት ነበር። ሦስቱንም አካቶ የያዘ።



እጥረትን በጥልቀት እናስብበት። ለኛ ጥቅም እናውለው። በእጥረት ግን እንዳንነዳ እንጠንቀቅ። ምክንያቱም አንዳንድ እጥረቶች የውሸት፣ ሆን ተብለው የተፈጠሩ ወይም አሁን ላይ የሌሉ ናቸው።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page