
የሃርፐር ሊን To Kill a Mockingbird እያነበብኩኝ፤ እንዲህ ይላል “ከዛ ሰው የእይታ አድማስ ነገሮችን ለመረዳት እስካልሞከርክ ድረስ ፈጽሞ ሰውን ልትረዳው አትችልም።” ... “በቆዳው ላይ እስካልወጣህ ድረስ ፥ በዛ ቆዳ ውስጥ እስካልተራመድክ ድረስ መረዳት አትችልም።”
በዚህ ምድር ላይ የአንዱ ሰው የሕይወት ታሪክ በተወሰነ ደረጃ እና መልኩ ብቻ ነው ለኛ ትምህርት እና ጥቅም የሚኖረው። ሕይወት ለያንዳንዳችን ልዩ ናት። እኛን የሚመስል ሰው ፈጽሞ አልተወለደም። አይወለድምም። በመልክ እና በቅርጽ ወይም በማንነት እና ባስተዳደግ ብዙ ብንመሳሰል እንኳ ፥ አሁንም ልዩ ነን። የኛን ልምድ እና ያን ልምድ የመገንዘቢያ ውቅራችንን የሚመስለው የለም። በሚገርም ሁኔታ ልዩ ነን።
ሁለት መንታ ልጆችን ብትወስዱ፣ በተመሳሳይ ወላጆች ያደጉ፣ ተመሳሳይ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት እየበሉ፣ ተመሳሳይ የልጅነት እና የዕድገት ሂደትን ያለፉ፣ ከተመሳሳይ የመጽሐፍ መደርደሪያ መጻሕፍትን ያነበቡ ሁለት ልጆችን ብትወስዱ እንኳ የተለያየ ስብዕና ታገኛላችሁ። አንዱ የሕይወት ውጣ ውረድ አውጠልጥሎት ሲወድቅ አንዱ ደግሞ እነዛን መከራዎች እንደመሰላል ከፍ ላለ የሕይወት ልዕልናዎች መወጣጫ ሲጠቀመው ታገኙታላችሁ። አንዱ በትንሽ ነገር ሲደሰት እና ሲዝናና ስታገኙት አንዱ ደግሞ ሲጨነቅ ታዩታላችሁ። በመልክ መመሳሰላቸው ሕይወት ለእነሱ በምትሰጠው ግብረ መልስ እንዲመሳሰሉ አያደርጋቸውም።
በመንታዎች መኃል ይሄን ያህል ልዩነት ካየን ደግሞ በዚህ ሕይወት ውስጥ ብዙ የሚለያይ የሕይወት ልምዶች ያሉን ሰዎች እንዴት ዘርፈ ብዙ ማንነቶች እንደሚኖሩን ገምቱ። ለዚህ ነው ካርል ዩንግ ሰዎችን መርገም እና መተቸት እምብዛም ረብ የለውም የሚለው። ሰዎችን ከመረዳት እና ከመቀበል ውጪ ብዙም ዕድል የለንም።
ብዙ ጥረታችን እና ልፋታችን የሚባክነው ግን ለመረዳት እና ለመቀበል ሳይሆን ሌሎችን ለመለወጥ ነው። የብዙ ማህበረሰብ ትልቁ ኢንቨስትመንቱ ሰዎችን የማረሚያ እና የመለወጪያ ተቋሞችን መገንባት ነው። የራሱ ሕይወት ተገልጦ ቢታይ ፈጽሞ በሰው ፊት ሊቆም የማይችለው ሰባኪ ፥ የተሰባኪውን ሕይወት ለመለወጥ የጥቅስ እና የተግሳጽ ናዳ ያወርዳል።
ትልልቅ ወንጀል እየሰሩ ሕዝብን የሚያስተዳድሩ ዘራፊ ፖለቲከኞች ቀላል የማይባል የሀገሪቷን ገንዘብ የሚመድቡት ለማረሚያ ተቋሞች ነው። በብዙ ማህበረሰብ ውስጥ የወላጆች ተቀዳሚ ሥራ ልጆችን ማረም ይመስላል። ትምህርት ሳይገባን ሲቀር ወይም የማስተማር ዘይቤው ሳይጥመን ሲቀር በምናሳየው ባህሪ የሚቀጡን መምህራን ነበሩን። ቅጣት እና ዱላ የአዕምሮን በሮች ይከፍት ይመስል።
በፍርድ እና በብየና የተዋቀረ ስነልቦና ነው ብዙዎቻችን ያለን። ግን ሁላችንም፣ ቀጪዎቹ እና ፈራጆቹ ሳንቀር የምንፈልገው አንድ ነገር ቢኖር እንዲሁ እንዳለን የሚቀበለን ሰው ነው። ምንም ምንም ፍርድ ሳይሰጥ፣ምንም ምንም በውስጡ ስለእኛ አሉታዊ ነገር ሳይቋጥር እንዳለን የሚቀበለን ሰው ነበር የሁላችን መሻት። ከተራራ ላይ ስናይ ከታች ያሉ ቤቶች ያረጀው ክፍላቸው ሳይቀር ሊታየን ይችላል። ግን የቆምንበት ተራራ ነው ያን ሁሉ የሰው ጉድ ያሳየን እንጂ የኛ ከፍታ አይደለም። እኛ ከቆምንበት ተራራ በላይ ቆሞ የሚያየን ደግሞ የኛን ዝገትን ያያል። በዛ ተራራ ላይ ቆሞ የሚያየን ሁሉ ያ ዝገት የሕይወት ጉዞአችን የውጣ ውረድ ውይብና እንደሆነ እንዲቀበለን ነው የምንፈልገው።
ለዛ ዝገት ላለው ሕይወት ክብር ነው የሚገባው።ለውጣ ውረዳችን እና ለሕይወት ልምዳችን ፍርድ ሳይሆን መረዳት፣ ነቀፋ ሳይሆን መቀበል፣ ውግዘት እና ምክር ሳይሆን ግንዛቤን ነው ይምንሻው።
ትችት አይለውጥም ይጨቁናል እንጂ። ነቀፋ ከክፉ ባህሪ ነጻ አያወጣም ለሀፍረት ያስገብራል እንጂ። የሚተቹ እና የሚነቅፉ ሰዎች ለጎሰቆለው ሕይወት ወዳጅ እና አጋር ሳይሆኑ ጨቋኞች እና አስገባሪዎች ናቸው። የራሱን ጨለማ ክፍል ማየት ያልቻለ ሰው ግን ረጋሚ እና ጨቋኝ ነው የሚሆነው። በርሱ ውስጥ ያለውን የክፋት ጥግ እና የእንክርዳድ ማሳ ማስተዋል ያልቻለ ሰው ፥ ሌላውን ሰው መቀበል ይቸግረዋል።
ለዚህ ነው የመምሰል ሕይወት አሰልቺ እና አድካሚ የሚሆነው። ፍጹም ልዩ የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በሌላው ሰው ቁመት እና ወርድ ሲለካ እና ያን ለመሙላት ሲጥር ይባክናል። ይሄ ሕይወት ስጦታ ነው። በተለያዩ ሰዓቶች የተጠሩ ሰዎች ሕይወት በተባለ ማሳ ላይ ተሰማርተዋል። ማንም በርሱ ያለው መልካም ማንነቱ እና ውብ ስብዕናው እንዲያድግ እና እንዲለመልም እንደሚፈልገው፤ በወቀሳ በሚወቅረው ዓለም ፊት ግን ሕይወት ራሱ የፍትሕ እጦት ፍሬ ሆና ነው የምትታየው።
Comments