
ይሄ ሕይወት እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የምንኖርበት አይደለም፤ ከኛ በኋላም ብዙዎች እኛ ዛሬ የሚያሳስበን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳስባችዋል። ሞኞች የሕይወትን ውጣ ውረድ ልክ እነሱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ ያህል ይጋፈጡታል። ብልሆች ግን ከሆነው አንዳች ያልሆነ፤ አዲስም የሚሆን ነገር እንደሌለ ይገነዘባሉ። ከንቱ ነው ፥ አይደለም ማለት የሞራል ፍርድ ነው። የዚህ ጹሁፍ ዓላማ የሞራል ፍርድ መስጠት አይደለም። እንደብዙዎቹ የሰንበት ዕይታዎች ሕይወትን እንደሆነው ለማየት መጣር እንጂ። ግን ማበብም መጠውለግም የሕይወት አካል ነው። ሁለቱም ውበት ናቸው። አንዱ ካለአንዱ ትርጉም አይሰጥም።
በተቻለ መጠን ሕይወትን በምልአት ለመረዳት መጣር ከብዙ ድካም ያድናል። ማለትም ሕይወት ፊዚክስ፣ ቦይሎጂ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ሕግ ወይም ሳይኮሎጂ እያለ ተከፋፍሎ አይንቀሳቀስም። በሕይወት ውስጥ እነዚህ ነገሮች ተከፋፍለው የሉም። ሁሉም በአንድነት በሁሉም ቦታ በጥምረት፣ ያለመለያየት በውህደት ነው የሚሰሩት። እኛ ለመረዳት ከፋፈልነው እንጂ።
ስለዚህ ትልልቅ ነገሮችን ልክ ለመሆን ትልልቅ ሀሳቦችን በአግባቡ መረዳት ወሳኝ ነው። ፒተር ካፉማን ሁለት ትልልቅ ሀሳቦችን ያነሳል፦ (1) መልካምነትን ማንጸባረቅ (መልካም ሁን ደግሞ መጀመሪያ አድርገው) (2) ዘላቂ በመሆን ፥ ትንንሽ ድሎችን ሰብስብ። የዘመናት የአሸናፊነት ጥበብ ከእነዚህ የሚመነጭ ነው። ሁልጊዜ መጀመሪያ መልካም አድርግ ከዛ ደግሞ ይሄን ሁልጊዜ አድርገው።
ይሄ ቀላል ይመስላል። ነገር ግን በሕይወት በጣም ከባባድ ነገሮች መፍትሔያቸው ቀላል ነው። ቀሊል መሆንም ነው በጣም ከባዱ ነገር። እስቲ ይሔን ለመረዳት ራሱ ካፉማን ከሚለው እንነሳ። በሕይወት በጣም ወሳኙ ነገር ዘርፈ ብዙ አዋቂ መሆን ነው። ያ ደግሞ መታወርን ይቀንሳል። ማለትም እውነተኛ አሳቢ ማለት ነገሮችን የሚረዳ ነው። ምክንያቱም በተረዳንበት ነገር ስህተት ሰርተን አናውቅም። መረዳት ማለት ደግሞ ማድረግ ያለብንን ነገር ማወቅ ነው። በአንድ ዘርፍ ብቻ አዋቂ መሆን ማለት በኩሬ ውስጥ እንዳለች እንቁራሪት መሆን ነው። ለዚህች እንቁራሪት ውቅያኖሱ ኩሬው ነው። ኩሬው ነው ሁሉ ነገርዋ። እቺ እንቁራሪት የምትወስነው ውሳኔ ሁሉ ከኩሬው የሚሰፋ አይደለም።
በሕይወት ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ማድረግ ያስፈልጋል። የመጀመሪያው ሁልጊዜ መልካም መሆን። ግን እሱ ብቻ ሳይሆን መጀመሪያ መልካም መሆን። ሳንቀደም መልካም ሆኖ መቅደም። ድመትን በጭራዋ ያዟት። የሚከተለውን መገመት ከባድ አይደለም። ለመማር ግን ጥሩ ነው። ሁለተኛ ድመትን በጭራዋ በኩል አትይዟትም። ድመትን በጭራዋ በመያዝ ለድመት የምትነግሯት ነገር ወዳጅዋ እንዳልሆናችሁ ነው። አያያዛችሁ ለጥሩ እንዳልሆነ ነው። ደግሞ አሻሾት። መጀመሪያ በጥሩ ሁኔታ ዳብሷት። ከዛ በምላሷ ልትልሳችሁ ፥ ልትተሻሻችሁ ትጠጋለች። ለምን? አሁን መልካም ሆናችዋል። መጀመሪያ መልካም ሆናችሁ ቀርባችዋል። በመልካምነት ቀደማችሁ። ይሄ በሕይወት እጅግ ሩቅ መንገድ ያስጉዘናል። በመልካምነት ቅደሙ። ለዛ ሰው ምን መልካም ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ። ምን መልካም ላድርግለት ብላችሁ አስቡ። ይሄ ሰው ገንዘብ ይሰጠኛል ወይም ምን አገኝበታለሁ ሳይሆን ምን ልጥቀመው ብላችሁ አስቡ። የምታገኙት ውጤት አስገራሚ ነው የሚሆነው። ብዙ ሰው ግን በተቀራኒው በየቀኑ የሚሰራው በብዙ ሰው ለመወደድ እንጂ ብዙ ሰው በቀን ውስጥ ለመውደድ አይደለም። እስቲ ሌላው ሰው የሚሰማው ስሜት እና ሌላው ሰው የሚፈልገው ነገር ይሁን የመጀመሪያው ግባችን። ያ ሁሉን ነገር ሲለውጠው ታያላችሁ።
ሁለተኛ ዘላቂነትን በሕይወት ውስጥ መለማመድ ነው። የማናቋርጠው ነገር ምን አለ። ታላቅ ሰው አሳዩኝ። በሕይወት ያላቋረጠው ነገር ብቻ እዛ ደረጃ እንዳደረሰው አሳያችዋለው። ውሻችሁን በተከታታይ በሆነ ሰዓት መግቡት ከዛ ደግሞ በሌላኛው ቀን ዝለሉት። የሆኑ ቀናት ተንከባከቡት ከዛ ደግሞ ዝለፉት። ምን እንደሚሰማው ታውቃላችሁ? ምንም ወጥ ባህሪ አታዩበትም። ስለ እናንተ ምንም መገመት ስለማይችል ውሻውም የማይገመት ይሆናል። ኒሮቲክ እና ፍጹም አስቸጋሪ እንዲሁም ፈሪ ስለሚሆን ፈጥኖ መተናኮል ይጀምራል። ይሄ ለሰውም ተመሳሳይ ነው። በመልካም ባህሪው ያልቀጠለ ሰው ከክፉ ሰው በላይ ሰዎች ይጠሙበታል። ምክንያቱም የማይገመት ነገር ለሰው ልጅ አዕምሮ አስፈሪ ነው።
በሞኝነቱ የቀጠለ ሞኝ ጠቢብ ይሆናል ይባላል። ጀምረን ያልቀጠለው ነገር ነው ባብዛኛው የጸጸት ውጤት። የዛሬ ውድቀት ወይም የፈለግንበት ያለመድረስ ምክንያት ጀምረን ያልቀጠልነው ነገር ነው።
እነዚህን የሰንበት ዕይታዎች መጻፍ ለእኔ ወጪ አለው። ዌብሳይት ያስከፍለኛል። ረፈት አልባ የሆነውን የደንበኞቼን ስልክ (ገንዘብ የሚያስገባልኝን) ለጊዜው መግታት ያስፈልገኛል። ከዛ ደግሞ ትርጉም የሚሰጥ እና የታሰበበት ነገር ለመጻፍ መጨነቅ ይሻል። ይሄ ሁሉ ስለሌላው ማሰብን፣ ሌሎች እንዴት ከዚህ ጹሁፍ እንደሚጠቀሙ መጨነቅን እና ያ ከምንም ነገር በላይ ታላቅ ዋጋ እንዳለው ከልብ መገንዘብን ይጠይቃል። ከዛ በላይ ለጊዜው መጎዳትን ይሻል። በመጨረሻም ሰዎች ሲሪየስሊ እንዲወስዱን ፥ አለማቋረጥ እና ዘላቂ መሆንን ማሳየት ይፈልጋል። ይሄ ሁሉ መልካምነትን መጀመሪያ ለማድረግ፣ ቀላል የማይባሉ ሰዎች መጀመሪያ ከንቱ ልፋት አድርገው ሲወስዱ ያን ለመቀበል መዘጋጀት እና መጽናት ይጠይቃል።
ሕይወት ውቅያኖስ ናት። ከኩሬው ካልወጣን በቀር ካለንበት ጣሪያ በላይ እምብዛም ተሻግረን ማሰብ አንችልም። ይሄ ሕይወት ረጅም ነው። ብቻችንን ከሄድን ቶሎ ልንሄድ እንችላለን ብዙ ርቀት ግን አንጓዝም። ሌሎች አብረውን እንዲጓዝ ከፈለግን ደግሞ የሌሎችን ፍላጎት ማስቀደም ይኖርብናል። መልካም መሆን ብቻ ግን አይደለም ከሌሎች በፊት መልካም መሆን እንጂ። ግን ደግሞ ሰዎች በቀላሉ አያምኑንም ስለዚህ በበጎ ባህሪያችን መጽናት ይጠይቃል።
コメント