
ምንአልባት በብሉይ ኩዳን ወደ እርሷ ተመልከቱ ከተባልነው ፍጥረት መካከል ጉንዳን ብቸኛዋ ሳትሆን አትቀርም። ከልጅነቴ ጀምሮ በጉንዳኖች እደነቃለሁ። በጣቶቼ ጨፍልቄ እስከምገላቸው ድረስ ተስፋ ሳይቆርጡ መንገድ እየቀየሩ የሚጓዙ ነበሩ። ፍጥነታቸውን ለመግታት በእነሱ ዓይን የሰማይ ስባሪ የሚያህል ጣቴን በመንገዳቸው ላይ ስደቅን ወዲያው በጣቴ ወደ አልተዘጋው ቦታ አቅጣጫ ቀይረው ለመጓዝ ይጥራሉ። መድከም፣ መቆም አላይም። ከእነሱ በመጠን ፍጹም ከሚበልጠው ጣቴ ጋር እምብዛም ሲላተሙ እና ጉልበት ሲጨርሱ አላይም። ወደ አልተዘጋው፣ ወደ ሌላው ክፍተታ ያለብዙ ጊዜ መግደል ይነጉዳሉ እንጂ።
“አንተ ታካች ፥ እስከ መቼ ትተኛለህ?” “ወደ ጉንዳን ሂድ ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን።” ይለናል ጠቢበኛው ሰሎሞን። (ምሳ 6፥6)። ዝንብን ደግሞ በተቃራኒው ተመልከቱ። የእናንተን ትዝታ አላውቅም፤ የእኔ የዝንብ ትልቁ ትዝታ ግን ልጅ ሆኜ በክፍሌ ተኝቼ ሳለው ከመስታወት መስኮት ጋር እየተጋጩ የሚፈጥሩት ድምጽ እና አላስተኛ የሚሉኝ ነገር ነው። ወደ ውጪ ለመውጣት ከመስታወት መስኮት ጋር እየሄዱ ሲላተሙ እና ከዛ ደግሞ መውጣት ሲሳናቸው የሚፈጥሩት ድምጽ፣ በመጨረሻም ከመስታወቱ ጋር አብዝተው በመላተም ከታች ወድቀው ሲሞቱ ነው የማስታውሰው።
ትንሽ ዞር ቢሉ ሰፊ በር ነበር ወደ ውጪ የሚያወጣቸው ግን በቀለማት የሸበረቀችው ዝንብ ይሄ መች ታይቷት። ከመስታወት ጋር መላትም እና የማታሸንፈውን መግጠም ነው ተግባሯ። ምንአልባትም ያ የሚመር እንቅልፍ የሚነሳ ድምጽ የዝንብ ማማረር ይሆናል።
ወደ ጉንዳን ተመልከቱ ይለናል ታላቁ ንጉስ ሰሎሞን። በዙሪያው ካሉ ግዙፍ ነገስታት በላይ፣ ከሚቀድሙት ታላላቅ አበው በላይ፣ በጫካው ንጉስ ተብሎ ከሚያጎራው አንበሳ በላይ ፥ ትንሻ ነፍስ፣ እጅግ ትንሻ ፍጥረት የጥበብ ጅረት ሆና እየታየችው።
አስቂኝ ፍጥረት ነን። ዓለምን እንደሆነው ለማየት እና ለማወቅ የምንጥር ሳንሆን በአይዶሎጂ እና በቲዎሎጂ መነጽር አጥበን ለማየት የምንፈልግ፣ እውነትን ላለመጋፈጥ ሩቅ መንገድ የምንሄድ ነን። ዓለም ያልሆነችውን በፍልስፍና ዓይን እናያታለን። ቻርልስ ኬተሪንግ ከ300 በላይ የፈጠራ ውጤቶችን በማግኘት ለሁሉም የፓተንት መብት ያገኘ አስገራሚ ሰውነበር። ኬተሪንግ እንዲህ ይላል “ሰዎች በተማሩ ቁጥር ይደድባሉ።” (ይሄ የዩኒቨርስቲ ትምህርትን ሲያመለክት ነው)።
“ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩን አንድ ትልቅ ትምህርት ውድቀትን መፍራት ነው” ይላል ኬተሪንግ። ውድቀትን መፍራት ደግሞ የፈጠራ ጠላት ነው። ስለዚህ ማነብነብ ይሆናል እውቀት፣ መሸምደድ እና ሌሎች የሄዱበትን መንገድ ማጥናት ይሆናል እውቀት።
ጉንዳንን የጥናቱ ተልዕኮ ያደረገው ጠቢበኛው ሰሎሞን ከታካች ሰው በተሻለ ወቅቶችን በማጥናት ለነገ ሳይቀር እንዴት እንደሚሰበስቡ ይነግረናል። በተለይ ድህነት እንደ ወንበዴ ፥ ችግርም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ጠላት የሚመጣበትን ሰው እየተመለከተ ፥ “አምላክ ሆይ ምን አደረኩ” በማለት "ዕድሌ ነው፣ ምኔ ነው” እያለ ከጉንዳን አንሶ ሲያየው ፥ “ተነስ አንተ ታካች ወደ ጉንዳን ሂድ፣ ጉንዳንን ተመልከት” ይለዋል።
ጉንዳኖች ከሁሉም በላይ የሚያውቁት የሚመስለኝ ነገር ይሄ ዓለም ከእነሱ በኋላም እንደሚቀጥል ነው። ከሁሉም በላይ የሚረዱትም እነሱ ጉንዳን እንደሆኑ ነው። ይሄን ዓለም እኛ አልፈጠርነውም። ይሄ ዓለም ፍትሐዊ ላይሆን ይችላል። ይሄ ዓለም ብዙ የማንፈልጋቸው እንቅፋቶች ሊኖሩበት ይችላል። የምታመልኩትም ፈጣሪ ይሄን በማድረጉ ልትወቅሱት ትችላላችሁ። ግን ማወቅ ያለብን ነገር ይሄ ዓለም የእኛ ብቻ አይደለም። ስለዚህ እኛ እንደምንፈልገው የመሆን ግዴታ የለበትም። ይሄ ዓለም የእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር በራሱ መንገድ ነገሮችን ይሰራል። እኛ የተሻለ መንገድ ሊኖረን ይችላል። እኛ ግን የራሳችን ዓለም የለንም።
የኛ ድርሻ ይሄን ዓለም መረዳት ነው። ማወቅ በምንችለው መጠን ይሄ ዓለም እንዴት እንደሚሰራ መገንዘብ ነው። የዛኔ ብቻ ነው ዝንብ ከመሆን ጉንዳን ወደ መሆን የምንለወጠው። ከዚህ ዓለም ጋር ከመላተም ይልቅ አጋራችን የምናደርገው። አሁን ላለንበት ኃላፊነት በመውሰድ ፥ ከተዘጋው ጋር ከመደባደብ የተከፈተውን ለማማተር እልፍ የምንለው።
ጠቢበኛው በጉንዳኖች የተደነቀባቸው ሌላኛው “አለቃና አዛዥ ፥ ገዢም” ሳይኖራቸው ሥርዓትን አለማጣታቸው ነበር። “መሪ ስለሌነን ነው ወይም መሪ ነው የጎደለን” የሚለው መነዛነዝ የታካች ሕዝቦች መገለጫ ነው። የሌለው ነገር እንዲገልጸው የሚፈልግ ሁሉ ፥ ውድቀት እና ሽንፈት መጎናጸፊያው እና ዘውዱ ናቸው። ስለሌለን ነው ለማግኘት የታገልነው። ተፈጥሮ ካደረገችልን ትልቁ ውለታ ውስጥ ብዙ ጉድለትን መስጠቷ ነው። ጉድለት ነው፣ ማጣት ነው የሕይወት ጉዞ ውበት። ሕይወትን መተኛት ብቻ ያላደረግናት፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥምረት ያስፈለገን፣ መደራጀት እና መማር፣ መሰልጠን ያሻን ፥ ጉድለት የሚባል ትልቅ ስጦታ ስለተሰጠን ነው። ሕይወት ከዋለችልን ትልቁ ውለታ ውስጥ ማጣትን፣ መጉደለን፣ እንከንን የሚያህል ነገር ያለ አይመስለኝም። ሕመም ነው የጤና ውበት። ረብሻ ነው የሰላም ጌጥ። ረሀብ ነው የማግኘት ፈንጠዝያ። ጉንዳኖች ታካች ለሆንን የሚያስተምሩን ይሄን ነው። “ተነስ አንተ ታካች ፥ ወደ ጉንዳኖችም ሂድ። ተመልከታቸውም።”
Comments