
መምህር ብርሃኑ አድማስ በቅርብ እዚህ አሜሪካ በሚኒሶታ ግዛት ላይ በነበረው የልጆች አስተዳደግ ላይ ባተኮረ ውይይት እንዲህ ብሎ ነበር። “ልጆችን አደጋ ላይ የሚጥላቸው የማወቅ ፍላጎት ነው። የማወቅ ፍላጎት ነው ለብዙ ክፉ ነገር የሚዳርጋቸው” አለ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ይሄን አባባል ብዙ ሳስብበት ነበር።
በዚህ ሳምንት ከአሜሪካዊ ዳኛ ጋር ለነበረን ወራዊ የመጽሐፍ ውይይት To Kill a mocking bird by H. Lee የሚለውን እና ከአርባ ሚሊዮን በላይ ኮፒ የተሸጠውን መጽሐፍ ላይ ነበር ውይይታችን። ይሄ መጽሐፍ ለልጆች አስተዳደግ እጅግ ምርጥ መጽሐፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በዚህ መጽሐፍ ላይ ወላጅ አባት እና ትልልቅ ሰዎች በአንድ ሁሉን ነገር በምትጠይቅ እና ለማወቅ በምትፈልግ ጂን ፊንች በተባለች የስድስት ዓመትልጅ ሲጨነቁ እናነባለን።
ለስድስት ዓመት ልጅ መግለጽ የሚከብዱ ነገሮች ስትጠይቅ እና ብዙ አዋቂዎች ለመመለስ ሲጨነቁ፤ በሜዬኮም ካውንቲ ጠበቃ የሆነው አባት ብቻ ለዚህ መፍትሔ ሲሰጥ እና የሰጠው መፍትሔ የታሰበበት እንደሆነም እናነባለን። እሱም ግልጽነት ነው። "ልጆች" ይላል ፊንች "ከማንም በላይ መልስ ሳይመለስላቸው ወይም የማታለል ወይም የመሸሽ መልስ ሲሰጣቸው ያውቃሉ። ስለዚህ ግልጽነት ብቻ ነው ለዚህ መፍትሔው" ይላል አቲከስ ፊንች።
በተቃራኒው መምህር ብርሃኑ አድማስ እንዳለው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የማወቅ ፍላጎት ነው የትልልቅ ችግሮች ሥር። ሔዋን እና አዳምን የማወቅ ፍላጎት ነበር እጸ በለስን ያስበላቸው።
አልበርት አንስታይን ደግሞ እንደሚለው የማወቅ ፍላጎት ነው በቁም ያለመሞታችን መስካሪ። ግን ደግሞ ያለ ዓላማ ያለ የማወቅ ፍላጎት አደገኛ የመሆን ዝንባሌ አለው። ለምሳሌ ስለሰዎች የግለሰብ ሕይወት ለማወቅ፣ ካወቅን በኋላ ከራሳችን ሕይወት ጋር ለማስተያየት ጥያቄ እናዘንባለን። እንደዚህ ዓይነት የማወቅ ፍላጎት የርካሽ ስብዕና መገለጫ ይመስለኛል። ይሄ ማለት ግን ከሰዎች ስኬት እና ውድቀት ለመማር ስለሰዎች ጥልቅ ማንነት ጥያቄዎችን መጠየቅ የለብንም ማለት አይደለም።
ስለዚህ መጀመሪያ ለራስ እውነተኛ መሆን ያስፈልጋል። ለምንድነው እነዚህ ጥያቄዎችን የምጠይቀው? ለምንድነው ማወቅ የምፈልገው? ለምን ዓላማ? ለመማር እና የሰዎችን ግለሰባዊ ሕይወት በመጠየቅ ለማውራት የሚጠይቁ ሰዎችን በሂደት ማወቅም ከባድ አይደለም። እነዚህ ሰዎች እኛን እነዚህን ጥያቄዎችን ከመጠየቃቸው በፊት በኛ ፊት ስለሰዎች ካወሩልን፤ ስለእኛም የሚጠይቁን ለሌሎች ለማውራት መሆኑ ድብቅ አይደለም።
የማወቅ ፍላጎት በዓላማ ካልታነጸ ፥ አጥፊያችን ሊሆን ይችላል። አዋራጅ ስብዕናም ሊሆን ይችላል። ያለማወቅ ፍላጎት ደግሞ በሕይወት እያለን የሞትን ሰዎች ሆንን ማለት ነው። የማወቅ ፍላጎት ነው ለብዙ የፈጠራ እና የለውጥ እርምጃዎች መሠረት። ለዚህ ነው "ማወቅ ለምን?" የሚለውን መመለስ የሚያስፈልገው።
ሰላም ጤና ይስጥልኝ ወንድም ሙሉዓለም እንዴት ነኽ?
በግለ ታሪክ ዙሪያ የተጻፉ የሀገረኛ(በአማርኛየተጻፉ)፣ ትርጉሞች(ከ...ወደ አማርኛ የተተረጎሙ) መጸሐፎችን ብታጋራን!
እናመሰግናለን!!!