
“የሰው ሕይወቱ ብርቱ ሰልፍ ነው” ይላል የዚህ ሰልፍን ትርጉሙን አጥብቆ የጠየቀው ጻዲቁ ኢዮብ። ጥበበኛ ወዳጆቹ የሰጡት መልስ ዛሬ ከሃይማኖት ሰዎች የምትሰሙትን ነው። ኢዮብ ከወዳጆቹ እንደ አንዱ ነበር። የሚለየው እውነትን ለመጋፈጥ ደፋር በመሆኑ ነበር። ግን መከራ ብቻ ነበር ያን ድፍረት የገለጠው። የሚያጣው ምንም ነገር ሳይኖር ሲቀር ፥ እንደ ሰነፍ መሳደብን ገንዘብ ማድረግ ባይፈቅድ እንኳ ፥ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ያለውን ጥበብ ግን ጠየቀ። ማለትም የጽድቅ ፍጻሜው በረከት ነው የሚለውን ሁልጊዜ እውነት ያልሆነውን ፍልስፍና ጣለ። የዚህን ፍልስፍና ውሸት ከኢዮብ በቀር ማንም ሊያሳየን አይቻለውም ነበር። ምክንያቱም በእግዚአብሔርም በሰይጣንም እኩል ሊመሰከርለት የቻለ ሰው ኢዮብ ብቻ ነበር። ስለ ጽድቁ። ስለ ፍጹምነቱ። የኢዮብን ፍጹምነት የጥርጥር አባት ራሱ ሰይጣን አልተጠራጠረም። ምን አልባት ሰይጣን ከወደቀ በኋላ ያመነው ነገር ቢኖር ይሄ ብቻ ይሆናል።
ይሄ ፍጹም ሰው ብቻ ነበር “ስለ ኃጢአቴ አይደለም ይሄ ሁሉ መከራ የደረሰው” ብሎ ሊናገር የሚችል። ስለዚህ የመከራን እውነተኛ መልክ ኢዮብ ነበር ያሳየን። የሕግ ሰዎች ሳይቀር በአጭር መሞትን በወላጆች መረገም ጋር ያያይዙት ነበር። ረዥም ዕድሜን ደግሞ ወላጅን ከማክበር ጋር። ኢዮብ ግን መከራ ከጽድቅም ከኃጢአትም ነጻ ሆኖ መኖር የሚችል መሆኑን በማሳየት መልኩን ገለጸልን። የኢዮብ መጽሐፍን አይሁዶች ቢረዱት ኖሮ ያን ከሚያክል ስህተት እና ግፍ በጠበቃቸው ነበር። ግን ችግሩ የኢዮብን መጽሐፍ ከክርስቶስ የመስቀል ሞት በኋላ ራሱ እኛም እንደ አይሁድ አልተረዳነውም።
“ስለ ሕይወት መልስ አለኝ” ከሚል ሰው በላይ መጥፎ ሰው ወዴት ይኖር ይሆን። መጥፎ በክፋት ሳይሆን መጥፎ ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር ማለቴ ነው። እስቲ የትኛውንም የሚዲያ ዓይነት ከፍታችሁ ስሙ። መልስ የሚፈልግ እኮ ጥቂት ነው። መልስ የሚሰጥ እንጂ። ሕይወትን በምልዓት ያለፈባት ሰው ደግሞ በእነዚህ ሰዎች ይቆስላል። ምክንያቱም ከርሱ የሕይወት ልምድ በተቃራኒ ቆመው ስለርሱ ሕይወት ይነግሩታል። የኢዮብ ወዳጆች በዚህ ጨለማ ውስጥ ያሉ ናቸው። “እውቀትን መጨመር ሕመምን መጨመር ነው” ይላል ጠቢበኛው፤ ግን እውቀትን የጨመረ ሰው ሌላ ሰውን የማሳመም አቅሙ እና ዕድሉ እየቀነሰ ነው የሚመጣው። እውቀት የሌላቸው ሰዎች እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ነው የሚሆኑት። ሁሉም ስለድርጊታቸው እየታመመ እነሱ ግን ጤነኛ ነው የሚሆኑት።
መጽሐፈ ኢዮብ ጽድቅ በራሱ ግብ እንደሆነ የተገለጸበት መጽሐፍ ነው። ምንአልባት ሌሎች መጽሐፎችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አካሎችን ሳይቀር ውድቅ ያደረገ ነው። ሰይጣን ይሄ የቆየ ፍልስፍናን ስለሚያምን እንዲህ አለ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን?” “ሰው በጎ ነገር በመስራቱ አንዳች ክፍያ ማግኘት አለበት” አለ ሰይጣን። ጽድቅ በራሱ በቂ አይደለም በማለት። ኢዮብ የዚህ ውርርድ ተያዥ ነበር። የጽድቅ ክፍያ ራሱ ጽድቅን መስራት እንደሆነ ኢዮብ ነገረን።
ሸክላ ሠሪው ሸክላውን የመስበር መብት እና ሲፈልግ ተንደገና የመጠገን መብት አለው ፥ የለውም አይደለም የኢዮብ ጥያቄ። ሲሰብርም ሆነ ሲጠግን አንዳች ምክንያት ሊኖረው ይገባል እንጂ። “የዚህ ዓለም ውበት አንድ ኃያል አምላክ አለ በመጨረሻ ለኃጢያተኛው በረከትን የሚነፍግ ለጻድቁ በረከቱን የሚያለብስ” አሉት ወዳጆቹ። በሌላ አነጋገር “የእግዚአብሔር አምላክነት ኃይለኝነቱ ነው” አሉ የኢዮብ ወዳጆች። ስለዚህ እውነትን ሳይቀር ለኃይል አስገዟት። በምንም በማይረታ ኃይል ፊት ፥ እውነት መናገር ከባድ ስለነበር ብዙ የሚያጡት ነገር ያላቸው የኢዮብ ወዳጆች ፊት ለፊታቸው ካለው ግራ መጋባት ይልቅ ለኃይል ተንበረከኩ። ፍጻሜያቸው ታናሽ እንደሆነ የሞቱ ከአቤል ጀምሮ ያሉ ንጹኃንን ረሱ። ስለዚህ ብቻ ንስሃ ግብ “ጅማሬ ታናሽ ቢሆን እንኳ ፍጻሜ ታላቅ ይሆናል” አሉት። ዓለምን ከዚ በላይ ያቀለለ ፍልስፍና ከየት ይኖራል። ይሄ ዓለም ግራ የገባው ሰው ማሰብ ጀምሯል። ለዚህ እንቆቅልሽ ወጥ የሆነ መልስ የሰጠ ሰው የማሰብ እንጥፍጣፌ ያልቀረለት ነው።
በሬናይሰንስ ፍልስፍና ውስጥ ለማይታጣው the Songs of Ronland ለተባለ ጥንታዊ መጽሐፍ በ1916 ድጋሚ መታተም መግቢያ የጻፈው ጄ ኬ ቼስተርተን፤ በዚህ መጽሐፍ ላይ ያን ቅዱስ እና ታላቅ ጦርነት አሸንፎ፣ ሰላማዊ አገዛዝን አስፍሮ እፎይ ብሎ ስለተኛው ንጉሱ Charlemagne ይነግረናል። ንጉሱ ያን ቅዱስ ጦርነት አጠናቀኩኝ፣ አገዛዜ ሰላም ሆነ ብሎ መልካም እንቅልፍ ተኝቶ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ቀሰቀሰው። እርሱ እና ሠራዊቱ ሌላ ሩቅ ቦታ ለአዲስ ጦርነት እንደሚፈለግ ነገረው። ንጉሱ ከእንቅልፉ ነቅቶ አለቀሰ። ኢዮብን እያስታወሰ መራራ ለቅሶን አለቀሰ። ረፍት የማይሰጥ ሕይወት ፥ የማያልቅ ጦርነት ፥ የማያባራ ጠላት ሲሆንበት አለቀሰ። ገና አረፍኩኝ ሲል መልአኩ ቀሰቀሰው። ሩቅ እና አዲስ ለሆነው ሠልፍ።
የማያልቅ ምዕራፍ ነው ይሄ ሕይወት። ጥቂት እንደተኛን የምንቀሰቀስበት። ለአዲስ ትግል። ለአዲስ ምዕራፍ። ምንአልባትም ለዚህ ይሆናል ኢዮብ ከቁስሉ እንደተፈወሰ መጽሐፍ ቅዱስ ያነገረን። ኢዮብ ያገኘው ጥበብ ከቁስሉ ጋር መኖር ስለሆነ ሊሆን ይችላል። ቁስሉን መቀበል ስለሆነ። በዛ ጉድለት፣ በዛ አለማወቅ ውስጥ መጽናናትን አገኘ። ከሰው መልስ ይልቅ የእግዚአብሔር ጥያቄዎች እረፍት ሰጡት። ምንአልባትም የሰው ልጅ ሞተር ይሄ ያልተፈታ እና የማይፈታ እንቆቅልሽ ነው። ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ እንዳለው በጽድቅ ጉዞ ውስጥ ፍጽምና የለም። በዚህ ጉዞ መርካት ላይ የደረሰ ሁሉ የክፋትን እና የጥፋትን ጉዞ ጀምሯል። ፍጻሜ የሌለውን ነገር ፍጻሜ መስጠት ተቃራኒውን ነገር መጀመር ማለት ነው። ያረፋችሁ የመሰላችሁ እስክትቀሰቀሱ ነው። የምትዋጉም ለመጨረስ ሳይሆን የማያልቀው ይሄ እንደሆነ እወቁ ሕይወት ማለት። በዚህ በማያልቅ ጦርነት ውስጥ መቀጠል ነው ሕይወት።
Comments