January 20, 2024
ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ እንደማለት አላዋቂነት የለም። የኢዮብ መጽሐፍ ጥናት የገለጠለኝ ያን እውነት ነው። ሁሉን ነገር ለማወቅ ከሚጥር ይልቅ አንድን ነገር በጥልቀት ለማወቅ የሚጥር ሰው ስለሁሉም ነገር ሁሉን ነገር ለማወቅ ከሚጥሩት በላይ የተሻለ ግንዛቤ ይኖረዋል።
በተለይ ለዚህ ዘመን የማህበራዊ ሚዲያ ዜና አጋባሾች ለሆን ይሄ መርሳት የሌለብን ሐቅ ነው። እግዚአብሔርን ለማወቅ ትጥራለህ፣ እርሱን ብቻ ለማወቅ ከጣሩ ቅዱሳን አንዱን ምረጡ፤ የዛን ቅዱስ ሕይወት በጥልቀት መመርመርን የሕይወት ግባችሁ አድርጉት። በእውቀት ውቅያኖስ ላይ በሁሉም አቅጣጫ ለመሄድ የምትጥረው መርከባችሁ፣ የዛኔ ወደቧን ታገኛለች። ወደዛ ቅዘፉ። ወደ-ዛ አንድ አቅጣጫ ብቻ። በሁሉም አቅጣጭ ለመሄድ ከሚጥሩት በላይ ስለውቅያኖሱም ሆነ ስለወደቦቹ የበለጠ እውቀት ይኖራችዋል። በመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት ከውቅያኖሶቹ ወደቦች በአንዱ የደረሰው፣ ከዛም እግዚአብሔርን የመምሰልን ሕይወት በሚገርም ልዕልና ያቀላጠፈው የአራተኛው ክፍለዘመን የኑሲሱ ጻድቁ አባታችን ቅዱስ ጎርጎርዮስ ፤ ስለመንፈሳዊ ሕይወት ምከረን ብሎ ለጠየቀው መነኩሴው ቄዛርያስ እና ከሱ ጋር ለሚኖሩ ጽፎ የላከላቸው ስለሙሴ ሕይወት ነበር። የሙሴን ሕይወት ችክ ብሎ ያጠና ሞኝ፣ በመጨረሻ ያ ጽናት ብልህ ያደርገዋል።
በዚህ ወደ ኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች እንሂድ። የኢዮብ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ መጽሐፎች (በተለይ ከብሉይ ኪዳን) አስጨናቂው እና ከባዱ ነው። ከባድ የሆነው ግን ቀላል ስለሆነም ነው። ማለትም ከባዱ ፈተና በጣም ቀለል ያለ መልስ ያለው ነው። በርግጥ በሕይወት በጣም ከባዱ ነገር መቅለል ነው።
የኢዮብን መጽሐፍ የሚያነብ ሁሉ፤ በተለይ ሁለት ሦስቴ ብቻ አንብቦ የተወ፤ ራሱን የኢዮብ ወዳጆች ጎራ ያገኘዋል። ብዙ ጊዜ ይሄ የሚሆነው ሳናውቀው ነው። በጣም መጥፎ ስለሆነ በዚህ ምድር ላይ የመጨረሻ ከባድ የሆነውን ቅጣት የተቀበለ ሰው ሳይሆን፤ በጣም ጥሩ ስለሆነ የመጨረሻ ክፉ ነገርን የተቀበለን ሰው ነው በኢዮብ መጽሐፍ የምንገናኘው። ያ ነው የመጀመሪያው እንቆቅልሽ። ወለፈንዲዎች ያለመጠፋፋት የተዋሃዱበት ታሪክ። ይሄን ወለፈንዲ በአግባቡ ቢረዱት ኖሮ አይሁዶች ክርስቶስን ለመቀበል ባልቸገራቸው ነበር። የኢዮብ መጽሐፍ በርግጥም ጎልጎቷ ነው። መንስኤ እና ውጤት (cause and effect) ሁልጊዜ ቢሰራ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ቻርልስ ዳርዊን ልክ ነበር። ፍትሕ ቢሆን የዚህ ዓለም ብቸኛ ሕግ ከኢዮብ በላይ የኢዮብ ወዳጆች ጠቢባን ነበሩ። በርባን በነጻ በሚለቀቅበት ዓለም ላይ ነው የምንኖረው፣ ግን የወጣላቸው ክፉ ወንጀለኞችም በጎልጎቷ ተሰቅለዋል። ዓይናችንን ብናምን በመኃከል ያለው የወንጀለኞቹ አለቃ መሆን አለበት። ለቀረበው ግን፣ ወደ መስቀሉ ለተጠጋው ግን ይሄ ዓለም አንዳች እንቆቅልሽ እንደሆነ ይረዳል።
የኢዮብን መጽሐፍ የሚያነብ ደጋግሞ ራሱን ማስታወስ የሚያስፈልገው፤ ኢዮብ ጻድቅ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ እና ክፋትን ሁሉ ያስወገደ መሆኑን ነው። ይሄን መሰረት የለቀቀ ሰው፤ ያን መጽሐፍ በማንበቡ ምንም የሚጨምረው ነገር የለም። የውሸት የአዋቂነት ስሜትን ካልሆነ በቀር። መጽሐፉ መግቢያውን ያደረገው በዚህ ነው፣ ድምዳሜውም የኢዮብ ቅንነት ነው። ካለዛ በሕይወት ላስጨነቃችሁም ሆነ ለሚያስጨንቃችሁ ጥያቄ ከዚህ መጽሐፍ የተለየ መገለጥን አታገኙም።
የማንኛውም ትንታኔ ዋነኛው አንጓ የትንታኔው መሠረት (premises) ነው። የትንታኔው መሠረት (premises) ውሸት ከሆነ፤ ትንታኔው ሦስት ገጽም ይፍጅ ሦስት መቶ ገጽ ሁሉም ነገር ውሸት ነው። ለዚህ ነው የኢዮብ መጽሐፍን የሚያነብ ሁሉ የዚህ መጽሐፍ መሠረት የሆነውን ፈጽሞ መልቀቅ የሌለበት። ያም ኢዮብ በእግዚአብሔር የተመሰከረለት ጻድቅ እና ክፋትን ሁሉ ያስወገደ መሆኑን ነው።
ለዛሬ ሰይጣን ስለኢዮብ የተናገረውን ልለፈው፤ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ኢዮብ በመጨረሻ በደረሰበት ነገር የተጋፈጠው ከሕይወት ትርጉም ጋር ነበር። ሰባት ቀን ሙሉ በዝምታ ከአሁን አሁን ንስሐ ይገባል፣ ከአሁን አሁን ኃጢአቱን ተናዞ ፈውስ ይለምናል ብለው ለሚጠብቁት ወዳጆቹ፤ ኢዮብ መናገር ሲጀምር እምነታቸውን ነቀነቀባቸው፤ ቲዎሎጂያቸውን ደመሰሰው፣ ስለእግዚአብሔር ያላቸውን ዕይታ አፈረሰባቸው። ከዛ በኋላ ወዳጆቹ ታስሮ እንደተፈታ በሬ የኢዮብን ቃል ሁሉ በእውር ድንብር መተሩ፣ ለማጽናናት የሄዱት ወዳጆቹ ስለሃይማኖታቸው ክርክር ገጠሙ። የሚያምኑት ከሚፈርስባቸው፣ ኢዮብን አሳልፈው መስጠት መረጡ።
“መቃብርን ባገኙ ጊዜ በእልልታ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ ሕይወት ስለ ምን ተሰጠ?
፤ መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፥ እግዚአብሔርም በአጥር ላጠረው ብርሃን ስለ ምን ተሰጠ?” ምዕ 3፥22
ይሄ አይደል የብዙ ሰው ጥያቄ?! መደስት ካልቻልን “ለምን ሕይወት?” አይደለም የምንነው! በውሃ መርካት ካልቻልን ለምን ውሃ? ብርሃን ጨለማን ገፎ ከጥሻ ውስጥ እንድንወጣ ካልሆነ ፥ ምንድነው ጥቅሙ? ልጅ ልጅ ካልሆነ ለምን ሕይወትን ሰጠኸን? ሀብት ካልሰጠኸን ለሀብት የመጎምዠትን ፍላጎት ለምን አሳደርክብን? የምንወደውን ሰው አግኝተን በዛ መርካት ካልቻልን ለምን ይሄን ስሜት በኛ ውስጥ አኖርክ? ይሄ ነው ሌላው የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሽ። መከራ እና ስቃይ ነው ከዚህ የሕይወት ትርጉም ጋር እንድንጋፈጥ የሚያደርገን።
ዮሐንስ በወንጌሉ ብርሃን ያለው ክርስቶስን ነው፤ ኢዮብም የሚጠይቀው ምንድነው ፈጣሪን ማምለክ ከመከራ የማያወጣ ከሆነ (ብርሃን በአጥር ለታጠረው ስለምን ተሰጠ፤ አንተን ማወቅ ከዚህ ዓይነት ስቃይ የማያላቅቅ ከሆነ ምንድነው ፋይዳው?) ነበር ያለው።
ይሄ በአንድ ቅዱስ የቀረበ ታላቅ ጥያቄ ነው። የብዙ ሰው ጥያቄ። በተለይ ኢዮብ በምዕራፍ 21 ላይ በጣም ግልጽ በመሆን የምናየውን እውነት ይጋፈጣል፤ ይሄን የየዕለት እውነት መጋፈጥ ፈርተው ኢዮብ ላይ “ጽድቅ በረከት እንዲሁም ኃጢአት መርገምን ሁልጊዜ ይወልዳል” ለሚሉ ወዳጆቹ ይሄ ውስልትና ነው ይላቸዋል። “አታዩም እንዴ ኃጢአተኞች ሆነው እስከ እርጅና ድረስ በደስታ፣ በብልጽግና፣ በልጆች በረከት የሚደሰቱትን፤ ልጆቻቸው ላይ ግፍ ይደርሳል ትሉኛላችሁ፤ ‘የክፋታቸውን መጠን ያውቁ ዘንድ ለምን ለራሳቸው አይከፍልም?’ ፥ ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ ዘንድ ምን ይጠቅመናል ብለው በተድላ ዕድሜ ጠግበው ሞቱ። ኃጢአተኞች ይጠፋሉ ትላላችሁ፤ ስንቱ ኃጢአተኛ ነው የጠፋው?” እያለ ኢዮብ ባልተለመደ መልኩ ብዙ ሰው መልስ የለውም ብሎ ስለሚያስብ አይቶ እንዳላየ የሚያልፈውን፣ ለህሊና ጥያቄም የራሱን እንቶ ፈንቶ እንደሚመልሰው ሆኖ ኢዮብ አላለፈም፤ እውነትን ፊት ለፊት ተጋፈጠው እንጂ።
የአክስቴ ልጅ በቅርብ አንድ መጽሐፍ አንብባ እንደሁልጊዜው የመጽሐፍ ግምገማዋን ላከችልኝ። በዚህ ውስጥ ቀልቤን የሳበው እንዲህ የሚለው አገላለጿ ነበር “በዚህ ዓለም እውነትን በፍጥነት ከተጋፈጥካት ፥ የደረሰብኅን ነገር በፍጥነት ማከም ትችላለ፤ ያን በፍጥነት ካደረክ ደግሞ ጉዳቱን መቀነስ ትችላለ።” ኢዮብ ያደረገው ያን ነበር፤ መራራውን እውነት በሰው ቲዎሎጂ እና ፍልስፍና ሳያለባብሰው ፊት ለፊት ተጋፈጠው፣ የወዳጆቹን ኑፋቄ እና የፍልስፍና መጋረጃ ቀደደው። መራራውን እውነት ተጋፈጠው። ያም ፍትሕ ማለት በጎ ለሠራ በዚህ ምድር ሁልጊዜ በጎ ክፋያ እንዳልሆነ፣ ክፉንም ላደረገ መከራ ሁልጊዜ እንደማይዘንብለት ነበር።
የኢዮብ ወዳጆች ይሄን ነው መታገስ ያቃተቸው። ልክ እንደ ኢዮብ ወዳጆች በዚህ መሠረታዊ የሕይወት ትርጉም ጥያቄ ፊት ብዙ ሰዎች ሲበረግጉ፣ በዚህ ጥያቄ ፊት የጥቅስ መዓት ሲያዥጎደጉዱ አይቻለሁ።
“ጽድቅ ትሰራለህ ከዛ እግዚአብሔር ለጽድቅህ በረከት ይሰጠኸል የሚለው ትምህርት ነው” ስንቱን ከእውነተኛው ሃይማኖት ነቅሎ የወሰደው። ሌላም ትምህርት አለ። በንጽሐ ባህሪው በእግዚአብሔር ፊት “የአንተ መልካም ሥራ ምንም ነው፣ በመልካም ሥራ ለእርሱ ምን ትጨምርለታለህ?” የሚል፤ እግዚአብሔር ኃያል ስለሆነ ብቻ ተገዛለት ብሎ የሚያስተምር፤ ሰውን በእርሱ ፊት ትርጉም አልባ የሚያደርግ አፍራሽ አመለካከት። ኢዮብ መልስ የጠየቀው ለዚህ ነው። የዚህን እንቆቅልሽ ፍቺ ነው ከወዳጆቹ ማግኘትን የወደደው።
የዚህ መጽሐፍ አስደናቂው ነገር፣ ከኢዮብ ይልቅ እግዚአብሔር ስለኢዮብ የተናገረው ልክ ነበረ። ምንም እንኳ የዘሩትን የማሳጨድ ፍትሕ (retributive justice) አተገባበሩ ግር ቢለውም፤ ከዚህ ፍትሕ የሚጋጭ እውነትን በየቀኑ ቢያስተውልም፤ በመሠረቱ ግን የኢዮብ እምነት “ሰው ሁሉ የዘራውን ያጭዳል” ከሚለው የወዳጆቹ እምነት እምብዛም አይለይም ነበር። ያልዘራው መከራ እስከሚወረው ድረስ። ለዚህ ነው “እናንተ የምታውቁትን እኔ ደግሞ አውቃለሁ፣ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም”፤ “የምትናገሩት ነገር እኮ እኔ የምናገረው ነገር ነው፤ የምናገረውን’ማ አምኜ፤ እሱም ለሰዎች ቅን ሆንኩኝ፣ እግዚአብሔርን ፈራውኝ፣ ክፋትን አሶገድኩኝ ግን የደረሰብኝ ነገር፣ የተሰጠኝ ነገር እናንተ የምትሉት አይደለም። በበረከት ፈንታ መርገንም፣ በእረፍት ፈንታ ስቃይን፣ በደስታ ፈንታ ሐዘንን አከናነበኝ፤ ስለዚህ መልሱልኝ የዚህ ፍቺው ምንድነው?” ነበር ያላቸው።
በሚገርም ሁኔታ ግን ይሄን ጥያቄ የሚጠይቀው ኢዮብ በአምላኩ ላይ ያለው እምነት ፍንክች አላለችም ነበር። ይልቁስ “ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤” ይላል። (ኢዮ 13፥15)። ፍጻሜው ሞት ቢሆን እንኳ ከእግዚአብሔር ውጪ ለእርሱ የተሻለ ተስፋ እንደሌለ አመነ። የዚህ መጽሐፍ አጠቃላይ መሠረት አንድ ይሄ ነው። “እግዚአብሔርን እንዲሁ ሊወድ የማይፈቅድ እና ያልወሰነ ሰው የመከራን ባህር አይሻገርም” የሚል ነው። እንዲሁ መውደድ።
ጄ ኬ ቼስተርትሮን “ኢዮብ ቧሏን ከምትወድ ሚስት ማብራሪያ እንደምትጠይቅ ሚስት፣ ከእግዚአብሔር ማብራሪያ ጠየቀ” ይላል። ምክንያቱም ከአንደበቱ በላይ ውስጡ “እግዚአብሔር ሁልጊዜ ልክ ነው!” ብሎ አምኗልና።
የዚህ መጽሐፍ ትልቁ እንቆቅልሽ ግን የእግዚአብሔር መልስ ነው። በልጁ ድል አድራጊነት በሰው ሁሉ ፊት ቀና ብሎ በደስታ እንደሚሄድ አባት፤ በኢዮብ ጽድቅ ፍጹም የተደሰተው እግዚአብሔር “ይህ ማነው ፥ ያለ እውቀት በሚነገር ቃል ምክርን የሚያጨልም?” በማለት ተገለጠ። ለኢዮብ የሕይወት ትርጉም መልስ፣ ለስቃዩ ምክንያት (ቢያንስ እኛ በምዕራፍ አንድ እና ሁለት የምናውቀውን የሰማይ ቤት ጉባኤ) ይነግረዋል ብለን ስንጠብቅ፣ ስለፍጥረቱ ገለጸለት። ጥልቀቱ የማይመረመረውን የሰማያዊውን የፍርድ አሰራር ከመጠየቅህ በፊት፤ በተለይ ሞኝ ስለሚመስሉ ፍጥረታቱ፣ “ትልቅ ክንፍ ኖሯት መብረር ስለማትቸለዋ ሰጎን፣ ስለፍጹም ሰላማዊው ግን ማንም የቤት እንስሳ ስለማያደርገው የበርሃ አህያ፣ ጉልበቱ ኃያል ስለሆነው ግን ማንም ስለማይጠምደው ጎሽ፣ በላይ በደመናት ተቋጥሮ ስለሚፈሰው ዝናብ” ይገባሃል ፥ ትረዳዋለ ብሎ ጠየቀው?
ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል፣ ከሰው ጉልበት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል። ይሄ ሞኝነት ጥበብ ከሆነብን፤ ይሄ ከረቀቀብን፤ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበብ በላይ የሚልቀው የማዳኑ ጥበብማ እንደምን ይርቀቅብን? ይሄ ሞኝነት የሆነለት ጥበቡን ካልተረዳን፣ ጥበቡ የሆነውን የሕይወት ትርጉም እንደምን ያስረዳን?
ለእኛ እንጂ ለእርሱ የፍጥረቱ በኩር የሆነው ቤሂሞስ፣ ሌቫያተን እንደማያስፈራው ነገረው። ለእኛ እንጂ ኃያልነቱ ለእርሱ በጣቶቹ የሚጫወትበት ፍጥረቱ መሆኑን አሳወቀን።
ኢዮብ ግን በመጨረሻ ተጽናና። የፈለገው እግዚአብሔርን ነበርና አገኘው። ይቀጥላል።
Comments