top of page
Search

የአሜሪካ ጥበብ

Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew



 “በሮም ሳላችሁ እንደሮማውያን ፥ when in Rome do as Romans do” የሚባል አባባል አለ። ለባለፉት ዓመታት የምጥረው ነገር ቢኖር የምኖርበትን ሀገር በጥንቃቄ መረዳት ነው። ብዙ ቅዠት ውስጥ ገብቼ አላውቅም። ምን ማለቴ ነው? እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደ ዘመነኞቹ ምዕራባውያንን እየሰደብኩኝ እና ስለክፋታቸው እየተናገርኩኝ ፥ ሕይወቴን ለማትረፍ ግን በመጨረሻ ወደ እነሱ የመጣው አይደለውም። ይልቁንስ ጥቂት ጥሩ ነገር ባይኖራቸውም በብዙ ከኛ እንደሚሻሉ በማመን እና ባለማፈር ምርጫዬ የማደርገው ስልጣኔ እንደሆነ በመናገር ነው። የስልሳዎቹ ትውልዶች ኢምፔሪያሊዝም ይውደም እያሉ ምዕራባውያንን እስኪበቃቸው ካወገዙ በኋላ ግን ሁሉም በመጨረሻ የተጓዙት የሰው ልጆች መብት በአንጻራዊነት ወደ ተከበረባቸው የምዕራብ ሀገራት እንጂ አንዳቸውም ወደ ራሺያ እና ኩባ ወይም ወደ ማኦ ሀገር ቻይና የሄዱ አልነበሩም። ከዚህ በላይ hypocrisy ወዴት ይኖር ይሆን። ሰለሞን ደሬሳ የሚለው አለው “ለሀገሬ የምመኘው ለራሴ የምመኘውን ነው።” ብዙዎቻችን የምንታዌ (dual) ሕይወት መኖር ነው ምርጫችን። ማለትም የምናምነው፣ የምንተገብረው እና የምንናገረው ተዋህዶልን አያውቅም። የምዕራባውያንን ስልጣኔ ሲያወግዝ እና ሲደሰኩር የምታዩት የሃይማኖት መምህር ፥ ተሰዶ በመጨረሻ የምታገኙት የምዕራባውያን ሀገር ነው። የትኛውን ፈጣሪ ሊያስደስት ያን ሁሉ እንደደሰኮረ እርሱ ይወቀው። የእርሱ ምርጫ ግን አልነበረም። የምንታዌ ሕይወት ማለት ይሄ ነው። አንደበት እና ተግባር ያልተዋሀዱበት ሕይወት። ይሄን ረጋ ብለው የሚያስቡ ሰዎች እንዲህ ብለው ይገልጹታል unintegrated life።



ወደ ርዕሴ ልምጣ እና ምንድነው ግን የአሜሪካ ጥበብ? ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፎክስ ሚዲያ አንከር ከነበረው ተከር ካርለሰን ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ስለአሜሪካኖች ፍልስፍና ሲናገር “እነርሱ (እናንተ) የተግባር ሰዎች ናቸው፤ እኛ ደግሞ ፍልስፍና (ሀሳባዊነት) እና መንፈሳዊነት የሚማርከን ነን” አለ። አሜሪካውያን ፕራግማቲስት ይባላሉ። ሁሉ ነገራቸው ምንድነው የሚሰራው፣ ምንድነው የተሻለ ውጤት የሚያመጣው ከሚለው ሀሳብ የሚመነጭ ነው። ለዚህም በሁለት ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት እና አስገራሚ የስልጣን (power) ባላንስ በሚታይባቸው የአራቱ መዋቅሮቻቸው (ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው፣ ሕግ ተርጓሚው እና ሚዲያው) በመመራት ይሄ የፕራግማቲስት ሳይክል ሀገሪቷን የሚጠሏት ሰዎች ሳይቀር በመጨረሻ ለመጠለል የሚመጡባት እና የምርጦች ምርጥ መናኸሪያ እና የእንቁ አዕምሮዎች መጠራቀሚያ አድርጓታል። ይሄን ፍልስፍና የሚገልጽ አንድ ጸሎት አላቸው። “እግዚአብሔር ሆይ መለወጥ የማልችለውን ነገር እንድቀበል መረጋጋትን ፥ መለወጥ የምችለውን ነገር እንድቀይር ጀግንነትን ስጠኝ፤ ጥበብን ግን ስጠን የሁለቱን ልዩነት ለማወቅ።” “God, grant me the serenity to accept the things I cannot change, the courage to change the things I can, and the wisdom to know the difference.”


በመጨረሻ ግን ሕይወት ማለት ይሄስ አይደል። ይሄ ጥበብ። በእውነትስ የጥበብ ትርጉምስ ከዚህ ውጪስ ነውን? መለወጥ የማንችለው እና መለወጥ የምንችለው የቱ እንደሆነ ማወቅስ አይደል ትልቁ ጥበብ። ጀርሚ ጎልድበርግ እንዳለው “ጀግንነት ማለት እንደምንጎዳ እያወቅን ማድረግ ማለት ነው። ደደብነትም ግን ተመሳሳይ ትርጉም ነው ያለው። ለዛም ነው ሕይወት ከባድ የሆነው።” የደደብነት እና የጀግንነት ትርጉሙ ተመሳሳይ ስለሆነ ነው ሕይወት ከባድ የሆነው። ምክንያቱም ተመሳሳይ ተግባር ደደብነትም ሊሆን ይችላል ፥ ጀግንነትም ሊሆን ይችላል። ምን ጊዜ ደደብነት ፥ ምን ጊዜ ጀግንነት እንደሆነ ለማወቅ ግን ጥበብ ይፈልጋል።


 ተቀጥረን የምንሰራውን ሥራ ትተን የራሳችንን መሞከር ደደብነትም ሊሆን ይችላል ፥ ጀግንነትም ሆኖ አንድ ቀን ያን ውሳኔ ልንኮራበት እንችላለን። ጥበብ ብቻ ነው “መቼ” የሚለው የሚያውቀው። የአሜሪካ ብቃት የሚመስለኝ ይሄ ነው። አንድ ሰው ብቻውን፤ አንድ ግለሰብ ብቻውን የዚህ ጥበብ ሁልጊዜ ባለቤት እንደማይሆን ማወቅ እና አጠቃላይ ሥርዓተ መንግስቱን እና አስተዳደሩን እንደ ቤተሙከራ በሚያይ ፕራግማቲስት አስተሳሰብ ማዋቀራቸው። ለአንድ ፍልስፍና እና ለአንድ ወጥ ለሆነ ዶግማ ያልተገዛ ሀገረ መንግስት ማዋቀራቸው። በነጻ ገበያ ሥርዓት የሰዎች ፍጹም የሆነ መልካምነትንም ሆነ ክፋት እንዲገለጥ የሚያስችል ውቅር መስራታቸው። ከዛም ዘወትር ነገሮችን ለማሻሻል እና የተሻለ ምርጥ አድርጎ ለመስራት የሚጥር አስተሳሰብን መትከላቸው። ለዚህ ደግሞ መጠበቂያው የጥሎ ማለፍ ሥርዓትን ማስቀመጣቸው ነው። እስካልተለወጥክ ድረስ ፥ የተሻለ ነገር ማምጣት እስካልቻልክ ድረስ በአሜሪካ ውስጥ ርህራሄ አታገኝም። ስለዚህም ሕይወት በፍጥነት የሚሄድ ሳይክል ነው። በዚህ ፈጣን ሳይክል ላይ ለመቀጠል ዘወትር ፔዳሉን መምታት ያስፈልጋል።



አሜሪካኖች የሚሉን እንቁላል ጥብስ መብላት ከፈለክ እንቁላሉን መስበር ግድ ነው። ጥሩ ነገሮችን መስራት ትፈልጋለህ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ለመስራት መድፈር አለብህ። ያን ደግሞ ማድረግ የምትችለው ሕይወት እንደ ሆነችው መመልከት ስትችል ብቻ ነው። በፍልስፍና እና በማንኛውም ዶግማ መነጽር የምታይ ከሆነ ያልተዋሀደ ሕይወት ይገጥምሃል። የምትናገረው እና የምትሰራው ተቃራኒ ይሆናል።



የአሜሪካኖች ጥበብ ይሄ ነው። “በዚህ ዓለም ለውጥ ማምጣት ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ግልጽ የሆነ ፥ ጭጋግ የሌለበት ዕይታ ሊኖርህ ይገባል። ይሄ ዕይታ በፍልስፍና ያልታወረ፣ በዶግማ ግራ ያልተጋባ እና ነገሮች እንዴት እንደሚሰሩ የሚገነዘብ፣ ሰዎችን የሚመሩ ድብልቅ ፍላጎቶች (mixed motives) የሚረዳ እና አንዳንድ ሰዎችን የሚያስተዳድሩ ዝቅተኛ ስሜቶችን (base interests) የሚገነዘብ ነው።” ይሄን ዓለም እንዳለው እና እንደሆነው ለመረዳት የሚደረግ ጥበብ ነው ይሄ ጥበብ። ነገሮችን በግልጽ፤ ራቆታቸውን ለመረዳት የሚጥር ፥ ጥበብ ነው ይሄ ጥበብ።

403 views1 comment

Recent Posts

See All

የሰንበት ዕይታ - 16

እንቢ ማለትን በምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው።...

የሰንበት ዕይታ - 14. የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች

January 20, 2024 ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ...

1 comentario


yohannesaweke2010
11 ago 2024

thanks for sharing us your views and thoughtful ideas.

Me gusta
  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page