
የኢዮብ መጽሐፍ የተከታታይ የሪፍሌክሽኔ ነጥብ ነው (it is my constant reflection point)። ይሄንመጽሐፍ እና ታሪክ ሳነብ፣ ሳጠና እና ሳስበው አዕምሮዬ እንዳይጠይቅ የማልፈቅድለት ጥያቄ የለኝም።የኢዮብ ነጻነት ለእኔም ነጻነት ነው። ምንም እንኳ እርሱ የሚያውቀውን እግዚአብሔርን እኔ ባላውቀውም። ኢዮብ ስለእግዚአብሔር የሚያውቀውን እኛ የምናውቅ አይመስለኝም። የተጻፈው ግን ለእኛ ስለሆነ የኢዮብ መጽሐፍ ያን የመጠየቅ ነጻነት ያጎናጽፋል። ይሄን ሕይወት በጥልቀት መጠየቅ። ከዚህ ሕይወት ጀርባ ያለውን ጥበብ በነጻነት መጣል ማውረድ።
የኢዮብ መጽሐፍ ልክ እንደ ቻት ጂፒቲ ጥሩ መልስ ለማግኘት አይደለም የሚጠቅመው፤ ጥሩ ጥያቄ ለመጠየቅ እንጂ። አንዱ ጥያቄ የኢዮብ መጽሐፍ ሲጠናቀቅ ኢዮብ ከቁስሉ ስለመፈወሱ የሚነግረን ምንም ነገር የለም። ከጸጉሩ ጫፍ እስከ እግሩ ጥፍር በቁስል የተመታው፣ ከቁስሉ የተነሳ ጽድቁን ጠንቅቀው የሚያውቁ ወዳጆቹ ሳይቀር ኃጢአተኛ ነህ ያሉት እና ያስባለው ያ ቁስል መጠገጉ፣ መፈወሱ አልተነገረንም።
ምን አልባት ኢዮብ ከነቁስሉ ለብዙ ጊዜ ቀጥሎ ይሆናል። ምንአልባት የኢዮብ ቁስል ተፈወሰ ማለት ኢዮብን ማዋረድ ይሆናል። ምክንያቱም ሌሎች ልጆች ቢመጡም የሞቱትን ግን የሚተካ አይደለም። ያን ማሰብ ጭከና ነው። ግን ከዛ በላይ ስለ ሕይወት የሚነግረን ነገር ይኖራል። በሕይወት ብዙዎቻችን እንቆስላለን፤ ግን እነዛ ቁስሎች ሲፈወሱ ጠባሳ ይሆናሉ እንጂ የድሮውን፣ ከቁስሉ በፊት የነበረውን ቆዳችንን አናገኘውም። ስለ ጽድቁ የቆሰለውን ኢዮብ ከቁስሉ ተፈወሰ ማለት ለዚህ ነው ልክ የማይሆነው። የልጆቹ ሞት ጠባሳ፣ ኃጢአተኛ ተብሎ የደረሰበት ግፍ እና ፍርድ ጠባሳ፣ ከዛም የውጫዊው ቁስል ጠባሳ ሁልጊዜ ፥ ሐዋርያው ቶማስ እንደነካው የጌታ ቁስሎች በኢዮብ ሕይወት ቀጥለዋል።
ሰዎች ካቆሰሉን በኋላ ይቅርታ ማድረጋችን ያደረጉብንን ነገር ስለመርሳት አይደለም። ይቅርታ ማለት መርሳት ስላልሆነ። ጠባሳ ሆኖ ይቀጥላል። እንደ ትላንት አይደለም። አንሆንምም። በሕይወት ከውጣ ውረድ ቆስለን ስንወጣ ዓላማው እንደ ትላንት መሆን አይደለም። ዓላማው ከቁስላችን ጋር የመኖር ችሎታን ማግኘታችን ነው። ለዚህ ነው ላለማቁሰል አስቀድመን መጠንቀቅ ያለብን። አንዴ ካቆሰልን በኋላ ግን እንደ ትላንት ሊሆን አይችልም። ይቅርታ ማለት ከቁስላችን ጋር ማደግ ማለት ነው። ጠባሳው የዚህች ምስኪን ሕይወት ታሪክ ነው። ዓላማው ሌላ ሰው መሆን ነው። ግን የተሻለ ሰው ፥ ከቁስል አልባው ሰው ይልቅ ለሰዎች ጉስቁልና ሀዘኔታ የሚሰማው፣ የሌሎች ሕመም እና ችግር የሚገደው ከፍ ያለ ሰው መሆን ነው። እንጂማ ሕይወት ወንዝ ነው። አንዴ የረገጥነውን ውሃ ደግመን አናገኘውም።
Comments