top of page
Search

ደደብነት

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Apr 13
  • 6 min read




አዋቂው ቻርሊ መንገር እንዲህ ይላል "95% የሚሆነው የስኬት ምንጭ ደደብነትን ከሕይወት በማራቅ የሚመጣ ነው።" ብዙ ሰዎች ስኬት የሚገኘው እጅግ አዋቂ በመሆን ይመስላቸዋል። ባለው የዘር ግንድ ሳይሆን ዓለም ላይ ባሳደረው ተጽዕኖ ምክንያት በዌስት ሚኒስትር ለመቀበር የበቃው ቻርልስ ዳርዊንን ብትጠይቁት እውነቱን ይነግራችዋል። ዳርዊን በሕይወቱ ገና ወጣት እያለ ነበር የIQ መጠኑ ዝቅተኛ እንደነበረ የደረሰበት። ግን ታታሪ ሰው ስለነበረ ከሱ በፊት የነበሩ ሰዎችን ስኬት እና ውድቀት ሲያጠና የደረሰበት እውነት ፥ ስኬት እጅግ ብዙ ጊዜ ደደብነትን በማሶገድ የሚገኝ እንጂ ስማርት በመሆን የሚመጣ እንዳልሆነ ነበር። ስለዚህ በሕይወቱ ሁሉ ደደብ ላለመሆን ብቻ ሠራ። ምንአልባት ዓለም ሁለት ትርክት ቢኖራት ፥ አንዱ ትርክት መሠረቱ የዳርዊን ነው። ደደብነትን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ የዓለም የትርክት አንደኛው ምንጭ ሆነ።



ትዝ ይላችዋል ልጅ ሆነን ወላጆቻችን ደደብ ብለው ለምን እንደሚሰድቡን? ስማርት ስላልሆንን አልነበረም። ፈጽሞ። ደደብነት ስማርት (ጂኒየስ) ያለመሆን አይደለም። ደደብ የሚሉን የነበረው ብዙ ሰው ዓይቶት እኛ ማየት ስለተሳን ነገሮች ነበር። በቀላሉ ግልጽ ሊሆንልን የሚችሉ ነገሮች ከተሰወሩብን ደደብ ይሉናል። እንደ ሮቢንሰን አዳም ትንታኔ ደደብነት ማለት በጣም ግልጽ የሆነን ነገር ችላ ማለት ወይም መካድ ነው።



ሰው ሁሉ ፍቅረኛዋ እየተጫወተባት እና በአፉ ብቻ እየደለላት እንደሆነ እያወቀ ነገር ግን እርሷ ብቻ ይወደኛል ብላ የምታስብ እና “እርሱ እኮ እንዲህ ስለሆነ ነው” እያለች ምክንያት የምትሰጥ ሴትን ደደብ እንላታለን። ምክንያቱም ሁሉም ማየት የቻለውን ነገር እየካደች ነውና። ይህች ሴት በመስታወት ብቻ የሆነ በር ተመልክታ ነገር ግን በሩ ላይ የመክፈቻ እና መዝጊያ መያዣ ያለውን ሳታይ እንደምትጋጭ ሰው ትመስላለች። መስታወቱ ጥርት ማለቱ የበሩን መያዣ እንዳታይ አድርጓታል፤ ምንም እንኳ ያ በግልጽ ቢታይም።



ደደብነት የሚመነጭባቸው ስምንት ዋነኛ ቦታዎችን እንመልከት፤



1) ከየቀን ሁኔታ እና ከምቾት ዞናችን ስንወጣ፤



ለምሳሌ ታዋቂው የጊታር ተጫዋች እና ቦስተን ስቴት የሚኖረው ዮዮ ማ ለኮንሰርት ኒው ዮርክ ከተማ ሲሄድ ታክሲ ውስጥ ጊታሩን ረስቶ ወጣ። ዮዮ ማ ስለሆነ ከከተማው ከንቲባ እስከ ፖሊሲ አለቃው እና የሕዝብ ሬዲዮ ተረባረበ። ይሄን የሰሙ ሰዎችም ሆነ ሌሎች ጊታር ተጫዋቾች “ዮዮ ማ አደንዣዥ ዕጽ (drug) ወስዶ ነበር ወይ ሰክሮ ነበር” እያሉ አሾፉ።


በሚገርማችሁ ሁኔታ ይሄ እንዴት በራሳቸው ላይ ሊፈጠር እንደሚችል ብዙዎች እምብዛም መፈተሽ አልፈለጉም። እውነታው ግን ኒው ዮርክ ከተማ ውስት ለኮንሰርት ከሚሄዱ ጊታሪስቶች 15% የሚሆኑት ጊታራቸው ከኮንሰርት በፊት ወይ በኋላ ይጠፋባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ከየቀን ውሎህ እና ከምታውቀው ከባቢ ስትነጠል አዕምሮአችን የቱ ጋር መልህቁን እንደሚጥል አያውቅም። አዕምሮአችን የሚደገፍባቸው የልምድ እና የአከባቢ መዘውሮች ይቋረጣሉ። ለዚህም ነው አዲስ ከተማ ሄደን የሆቴላችንን ቁጥር የምንረሳው። ለዚህ ነው አንዳንድ ሰዎች ኤርፖርት ደርሰው ፓስፖርታቸው ግን ኪሳቸው ውስጥ የለም። ለምሳሌ ከክፍላቸው መኪናቸውን እየነዱ ለመሄድ አስበው ወጥተው ፥ የመኪናቸውን ቁልፍ ግን ክፍላቸው ረስተዋል። የመጀመሪያው ይሄን ደደብነት የማሶገጃው መንገድ አዕምሮአችን የልምድ እና የአካባቢ እስረኛ መሆኑን ማወቅ ነው። ለምሳሌ መንገድ የሚሄድ ሰው ፖስፖርቱን ነገ የሚያደርገው ጫማ ውስጥ ቢከት ፥ ይሄን ደደብነት በቀላሉ አሶገደ ማለት ነው። ወይም ቁልፋችንን ሁልጊዜ ተመሳሳይ ቦታዎች ብቻ ማኖር። ሁሉንም ነገር ካላንደር ላይ ማኖር እና የጠዋት የመጀመሪያው ሥራችን ካላንደርን ቼክ ማድረግ ቢሆን


ሰዎች ደደብ ነገር ሲያደርጉ ከማሾፍ እና ከመሳለቅ፤ "እኔ በምን ሁኔታ ብሆን ነው ይሄን የምፈጽመው" ብላችሁ ጠይቁ። ያን ቢጠይቁ ኖሮ ዮዮ ማ የሰራውን ደደብነት ሌሎች ጊታሪስቶች ባልደገሙ ነበር።



2) በቡድን ውስጥ መሆን፤



የናሳ የ1986 ትልቁ አደጋ የዚህ የቡድን (የግሩፕ) ውጤት ነው። በጣም ብዙ ኢንጂነሮች የኦሪንግን (O-ring) ችግር ያውቁ ነበር። ግን በቡድን ስብሰባ ወቅት ሌሎቹ ዝም ስላሉ ሁሉም ፈርተው ዝም አሉ። ምክንያቱም ከላይ ያሉት አለቆቻቸው እና ዋይት ሃውስ የፕሮጀክቱን መሳካት እንዲፋጠን ይፈልጉ ነበር። በሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ሰዎች በግል ቢሆኑ መቼም የማያደርጉትን ነገሮች ያደርጋሉ። ለምን? ምክንያቱም በግሩፕ ሲኮን ደደብነት ይደበቃል። ደደብነት ጀግንነት ተደርጎ ይቆጠራል።


ካስ ሰንስቲን በአንድ መጽሀፉ ለመሪዎች ምክር ሲሰጥ በስብሰባ ወቅት መጀመሪያ መሪው ፈጽሞ መናገር የለበትም፤ ምክንያቱም እርሱ ከተናገረ በኋላ መቃረን ከባድ ነው። ያ ብቻ ሳይሆን መሪው ተናጋሪ ሰዎች መጀመሪያ እንዲናገሩም መፍቀድ የለበትም። ዝምተኞች፣ ሰዎች ባሉበት መናገር የሚፈሩ ሰዎችን መጀመሪያ ሀሳባቸውን መጠየቅ አለበት። እውነትን ለማወቅ እና ለድርጅቱ ታላቅነት የሚተጋ መሪ ከሆነ። እነዚህ ዝምተኞች ብዙ ጊዜ ተመልካቾች ናቸው። ስለዚህ ሲጠየቁ እውነትን የመፈንጠቅ አቅም አላቸው። ግን ተናጋሪዎች ወይም መሪው አስቀድሞ ከተናገረ ግን “እርሱ እና እርሷ እንዳለችው” እያለ ነው ሁሉም ነገር የሚቀጥለው።


በዓለማችን ብዙ አይሮፕላን የተከሰከሰበት ኤርላይንስ የደቡብ ኮርያው ነበር። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በባህላቸው አለቃን ወይም ከፍ ያለን ሰው መቃረን በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ነበር። ስለዚህ ጥፋት እንደሆነ እያወቀ እንኳን ኮ-ፓይለቱ (co-pilot) የፓይለቱን ስህተት ዝም ብሎ ያልፋል። አሜሪካን ማናጀሮች መጥተው የደቡብ ኮሪያን ኤርላይንስ ባህል እስከሚቀይሩት ድረስ ይሄ ትልቅ ፈተና ሆኖ ነበር።



3) በሙያ እና በእውቀት ከሚበልጠን ሰው አጠገብ መሆን (ወይም ራሳችን በሙያ ፍጹም ከፍ ስንል)፤



አዲስ ተቀጣሪው የኤክስፐርቱን ግልጽ ስህተት እያየ ዝም ይላል። ምክንያቱም እርሱ ከእኔ የተሻለ ያውቃል ብሎ ያስባል። ዶክተሩ ያውቃል ብሎ ስለሚያስብ ፥ ደደብ የሆነ ነገር በሰውነቱ ላይ ሲደረግ እያየ በሽተኛው ዝም ብሎ ያልፋል። በ2008 የነበረው የአሜሪካ የፋይናስ ውድቀትን ብዙ ሰዎች ያስተዋሉት ቢሆንም ኤክስፐርቶች ስለ ኢኮኖሚው ውብ ስዕል መሳላቸውን ስለቀጠሉ እየመጣ የነበረውን ውድቀት ችላ አሉት። በሃይማኖት ውስጥ ያሉ ሰዎች ፥ "እንደዚህ ያሉ የተመራመሩ እና አዋቂ ሰዎች ይሄ ሃይማኖት ልክ ነው ካሉ ፥ ልክ ነው" ብለው ሲቀበሉ አላያችሁም?


 እኛም በእውቀት እጅግ የሚያንሰን ሰው በጣም ተራ የሆነ ስህተታችንን ሲያሳየን ፥ መቀበል ይከብደናል። ለምን?


ምክንያቱም እውቀታችን አደድቦናል።



4) እጅግ ትኩረት የሚፈልግ ነገር ስንሰራ፤



ቼዝ የምትጫወቱ ሰዎች ታውቃላችሁ፤ በራሳችሁ ስትራቴጂ ላይ በጣም ትልቅ ትኩረት ከጣላችሁ ከየት መጣ የተባለ የተቀናቃኝ ጦር ቼክ ሜት ይለናል። በራሳችን ምርጥ ስትራቴጂ ስለተወሰድን የተቀናቃኛችንን ወደ እኛ መጠጋት ፈጽሞ ማየት ይሳነናል። ይሄ ማለት መነጽሩን አድርገን መነጽሩን መፈለግ ማለት ነው። ልክ አናጺዎች እርሳሱን ጆሮአቸው ላይ አድርገው እርሳሱን እንደሚፈልጉ። ወይም ስልኩን እያናገሩበት ስልኩን ራሱ የት አስቀመጥኩት ብለው እንደሚፈልጉ ሰዎች ማለት ነው። በሕይወት እጅግ ብዙ ደደብ ሥራ የምንሰራው ፥ የራሳችንን ብቻ ነገር ስናይ ነው። ይሄ ዓለም ሌሎችም የሚኖሩበት ነው። የሌሎች ተግባር ለኛ ሕልውና ልክ እንደኛው ተግባር የመጥፊያ ምክንያት ሊሆን ይችላል። የአንተ መስመር እና የትራፊክ ሕግ አክብረህ መሄድ በራሱ ከመጥፎ የትራፊክ አደጋ አይጠብቅህም። ለዚህም ነው የሌሎችን አነዳድ እንድናይ መስታወቶች የተገጠሙሉን። እኛ በጣም ጠንቃቃ ብንሆን ሌላው ጠንቃቃ ካልሆነ ሞታችን ቅርብ ሊሆን ይችላል። በዚህ ዓለም የሌሎችንም ተግባሮች ለሕግ እና ለሥርዓት ለማስገዛት መስራት ተገቢ ነው።



ቀላል የማይባሉ ሰርጅኖች ኦፕራሲዮኑ ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርጉ መቀስ ሆድ ውስጥ ጥለው ይወጣሉ። ለዚህ ነው ክፍል ውስጥ የገባውን እቃ እያንዳንዷን ከኦፕራሲዮኑ በፊት ቆጥረው ልክ ያንን ሰርጀሪ ሲጨርሱ መልሰው የሚቆጥሩት። መርሳት የሰው ልጅ ባህሪ ነው። ስለዚህ በራሳቸው የማስታወስ ብቃት አይደገፉም።



5) የመረጃ መብዛት፤



ብዙ መሪዎች መጥፎ ውሳኔ የሚወስኑት ከመረጃ እጥረት ሳይሆን ከመረጃ ብዛት ነው። ስለ ጦርነት እየወሰነ ያለ መሪ ስለኢኮኖሚው፣ ስለትምህርት ጥራት፣ ስለጤናው ዘርፍ በተመሳሳይ ሰዓት ሪፖርት እንዲቀርብለት ከፈቀደ ፥ መጥፎ ውሳኔ የመወሰኑ ነገር ርግጥ ነው። ወላጆች ከሥራ መጥተው ልጆችን የሚገርፉት ወይም ያለሆነ ውሳኔ የሚወስኑት አዕምሮአቸው በመረጃ ቀኑን ሙሉ ደክሞ አሁንም ሌላ መረጃ ሲመጣለት የውሳኔ ባላንሱን ስለሚያጣ ነው። ኢንቬስተርስ በግልጽ የሚታየውን የኢኮኖሚውን ውድቀት የሚስቱት ብዙ መረጃዎችን ስለ ኢኮኖሚው ስለሚሰሙ ነው። ስቶክ ትሬደሮች ቀዩን መስመር ሳያዩት ይቀራሉ ፥ ምክንያቱም እጅግ ብዙ መረጃዎችን በየቀኑ እንደጎርፍ ይቀበላሉ።



ታላቁ ኢንቬስተር ዋረን ባፌት ይሄን ስላወቀ ነበር ከስቶክ ትሬድ ማዕከል ከሆነችው ኒው ዮርክ ጭር ወዳለችው ኦማሃ ከተማ የሄደው። ምክንያቱም የመረጃ ብዛት አይደለም የጥሩ ውሳኔ ምንጭ። ጥቂት ግን ጥራት ያላቸውን መቀበል ነው የጥሩ ውሳኔ አንዱ ምሰሶ።


6) ድካም፤ ሕመም እና የስሜት ውጥረት፤



ከደከመኝ የደንበኞቼን ስልክ አላነሳም። ካነሳውም በጣም ስለደከመኝ ካስቀይመኳቹ የድካሜ ውጤት ነው ብዬ ማስጠንቀቂያ እሰጣለሁ። የደከመው ዶክተር በጣም ግልጽ የሆነውን መረጃ አሳስቶ አንብቦ ለበሽተኛው ያልሆነ መድኋኒት ሊያዝ ይችላል። ዳንኤል ኮነመን እና ካስ ሰንስቲን በጻፉት ኖይዝ በተባለው መጽሐፍ አሜሪካ ውስጥ ያሉ ዳኞች የከተማቸው የእግር ኳስ ወይም የባስኬት ቦል ቲም ተሸንፎ በማግስቱ ለፍርድ ፊት ለፊቱ ከቀረባችሁ ፥ መጥፎ ውሳኔ የመወሰኑ ዕድል በእጥፍ ይጨምራል። የጨወታው የሽንፈት ንዴቱ የፍትሐዊ ሚዛን አቅሉን ያስተዋል። ወላጆቻችን በማያስገርፍ ጥፋት ደብድበውን ያውቃሉ፤ በሌላ ነገር ተናደው ወይም ደክሟቸው ካገኙን።



ሲ ኤስ ሉዊስ የሰይጣን የመጀመሪያው ሥራ እንስሳነትህን ማስረሳት ነው ይላል። እስቲ እንስሳ ሲበላ ምግቡን ቀማው። እንደሚነክስህ እርግጠኛ ነህ። አንተ ጌታው ብትሆን እንኳን። ሰውም እንደ እንስሳ ነው። ሲደክመው ወይም ሲታመም ወይም ሲበሳጭ ከሚገባው እና ከሆነው በላይ ይጮሃል።



7) መሮጥ እና መፍጠን፤



ይሄን አባባል ብዙዎቻችሁ ታውቁታላችሁ። ፈጥኖ ለመድረስ ቀስ ብሎ መንዳት። በፍጥነት የጫማችሁን ማሰሪያ ስታስሩ የበለጠ ትፈቱታላችሁ። 600 ሰው የሞተበት የ1977 የTenerife Airport Disaster በታሪክ ትልቁ የአውሮፕላን አደጋ የደረሰበት እና ሁለት ፓይለቶች አይሮፕላናቸውን ፈጥነው ወደ መውረጃ ማዕከሉ ጣቢያ ለማስጠጋት ሲሞክሩ የደረሰ ነበር። ይሄ የቼክ ሊስት (checklist) አለመከተል ችግር አልነበረም። ቼክ ሊስትን ብቻ የመከተል ችግር እንጂ። አንዱ የአንዱን ፍጥነት ለመመልከት ሳይሆን ፥ ቼክ ሊስታቸውን ለሟሟላት ነበር የፈጠኑት። መፍጠን እና መቸኮል የደደብ ውሳኔዎች እና ውጤቶች ሥር ነው።



8. ፍቅር እና ጥላቻ፤


ፍቅርም ጥላቻም ያሳውራል። ሁላችንም ከዚህ ከሚያሳውር ስሜት ነጻ አይደለንም። በአንድ ነገር ላይ ፍጹም ስናምን ከኛ የሚቃረኑ ሰዎችን ለመስማት እንጨክን። ለመማር በማሰብ። ዓለሙ ሁሉ እንደሞተ ያመነውን ጦር ሜዳ የሄደውን ልጇን ፥ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ ከዓመታት በኋላ እንኳን እናት ልጇ እንደሚመጣ ትጠብቃለች። የልጅ ፍቅር እውነትን የመቀበል አቅሟን አሳጥቷታል። ልጅሽ እየተበላሸ ነው ሲሏት የእናት የመጀመሪያ ምላሽ መካድ ነው። ምክንያቱም ፍቅሯ መስማት የሚፈልገው በጎ በጎውን ብቻ ነው። የምትጠሉትም ነገር ተመሳሳይ ነው። ሂትለር ለልጆች ልዩ ፍቅር እንዳለው ፈጽሞ ማመን አንፈልግም።ስለእሱ የሚታየን ያን ሁሉ አይሁድ እና ሌላውን ማህበረሰብ በግፍ መጨረሱን ነው። ግን የሂትለርን የልጆች ፍቅር ውሸት አያደርገውም።


ሴትን ያፈቀረ ወንድ እንከኗን መስማት አይፈልግም። ዘወትር ምክንያት ይሰጣል (justify ማድረግ)። ከሁሉም በላይ የምንወደው ደግሞ ራሳችንን ነው። ራሳችንን ዘወትር መከላከል (defend ማድረግ) ነው የምንፈልገው። ሰዎች አንዴ ቢሰርቁን የእነሱ ነገር በቃን ለማለት ፍጥነታችን። እራሳችንን ግን ሺ ዕድል ለመስጠት፣ መልሰን እና መላልሰን ለማመን ዝግጁ ነን። ለዚህ ነው ሰዎች አሉታዊ አስተያየት ስለ እኛ ሲሰጡን ይሄ የደደብነት ምንጭ የሆነውን የፍቅር መታወር ለጊዜው ያዝ ማድረግ ያለብን።



አሉታዊ (negative) አስተያየት ለመስማት እንፍቀድ። ቢያንስ ሰዎች ተናግረው እስከሚጨርሱ እንታገስ። ከዛ ደግሞ ይሄን አስተያየት ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን እንበላቸው (ልክ ቢሆኑም ባይሆኑም)። ያን የመቀበል እና ያለመቀበል ፈንታ የራሳችን የቤት ሥራ ነው።


 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page