
“ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ? ስለ ምንስ ያረጃሉ? በባለጠግነትስ ስለ ምን ይበረታሉ?
ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥ ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው።
ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ ነው፥ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።”
መጽሐፈ ኢዮብ 21፥7
ይሄ የኢዮብ ቃል። ኢዮብ ለዚህ ምክንያት እና መልስ አልተሰጠውም። አንድ ነገር ግን ተደረገለት። ተፈጥሮን እንዲያይ ተደረገ። እግዚአብሔር ለኢዮብ የነገረው ነገር ፥ ስለፍጥረቱ ነው። ፍትህ እና የሰጥቶ መቀበል ሕግ የዚህ ሥርዓት ምሰሶ አልነበረም። አይደለምም።
ብዙ ሰዎች በየቀኑ የሚሉት ነው።
ለምን እኔ?
ይሄ ፌር አይደለም (This is not fair)?
ለምን ይሄ ሁሉ ስቃይ በእኔ ላይ?
ሌሎች በዚህ መጠን አልተሰቃዩም ወይም ወዳጆቼ ሲደሰቱ ለምን ይሄ በእኔ ላይ ደረሰ?
ዙሪያችን ያሉትን በማየት እና የሌሎችን ሕይወት አጮልቀን በመመልከት ፥ ይሄን ሕይወት እናማራለን። ሃይማኖተኛ ካልሆንን ደግሞ እንደ Luigi Mangione የካፒታሊዝም መሪዎችን በአደባባይ በሽጉጥ እንዘርራለን። የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ሕይወት እንደ እኛ የፍትሕ መስፈርት ስለማትሰራ ነው። በየቀኑ የማያማርን ሰው አለመስማት በጣም ከባድ ነው። ከዛ ለዚህ ምራሬ የሃይማኖት ደጅ መጥናት፤ የጸናበት ደግሞ ይሄን የሚረሳበት ማደንዘዣ መውሰድ የተለመደ ነው።
ግን አንድ መራራ ሀቅ አለ። እርሱም ይሄ ሕይወት ፈጽሞ ፍትሐዊ መሆን እንደማይችል ማወቅ ነው። በተገነባ፣ በተሰራ እና በሚንቀሳቀስ ዓለም ላይ ነው የተፈጠርነው። ብዕራችንን አንስተን ከምንም ዲዛይን ሰርተን የምንገነባው ዓለም ላይ አይደለም ያለነው። በሃይማኖት ለምናምን ይሄ ዓለም ድንቅ በሆነ ሠሪ ከብዙ ሺ ዓመት በፊት የተገነባ ነው። በሃይማኖት ለማናምን ይሄ ዓለም ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በፊት በዝግመታዊ ለውጥ ሂደት አሁን ያለንበት ደረጃ የደረሰ ነው። በሁለቱም ብንሄድ የኛ ድርሻ ኢምንት ነው። በኛ አቅም ወይም በአንድ ትውልድ ዘመን የሚፈርስ ሆነ የሚገነባ ምንም ነገር የለም። የሚለወጥም መሠረታዊ አሰራር አይኖርም።
ማንንም የማታውቁበት ሰዎች ወደ ተሰበሰቡበት ታላቅ ድግስ ተጠራችሁ እንበል። ስለ ድግሱ ዓላማማ ሆነ የመርሐ-ግብር ይዘት እምብዛም እውቀት የላችሁም። መቅረት አትችሉም። ስለዚህ በዚህ ድግስ መኃል ራሳችሁን ብታገኙ ምንድነው የምታደርጉት? አቅማችሁ በፈቀደ መጠን ስለድግሱ ለማወቅ ነው የምትጥሩት። በድግሱ ስላሉት ሰዎች፣ ስለመርሐግቡር ይዘት፣ ስለምግቡ እና ስለእናንተ ቦታ፣ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ እና በዛ ድግስ ውስጥ ስለሚኖራችሁ ዕድል ነው አብዝታችሁ የምትጨነቁት።
ሕይወትም እንደዛ ናት። ራሳችንን በዚህ የሕይወት ድግስ መኃል አግኝተነዋል። ድግሱ እንዲህ መሆን አለበት ማለት ሳይሆን ይሄ ድግስ እንዴት ነው የሚሰራው የሚለው ነው ታላቁ ጥያቄ።
ፍልስፍና ይዘን፣ ሕይወት እንዲህ እና እንዲያ መሆን አለበት በማለት ወደዚህ ሕይወት ወደ ተባለ ውቅያኖስ መግባት ብዙም አዋጪ አይደለም። ይሄ የማርክሲስት ውድቀት ነው። ሕይወትን ፍትሐዊ እናደርጋለን ብለው ሁሉን ድሃ አደረጉት። ካፒታሊዝም ከገደለው እና ካሰቃየው በላይ ብዙ ገደሉ አሰቃዩ። ስለ ፍትሕ እጨነቃለሁ የሚለውም Luigi Mangione ሦስት ልጆችን ያለ አባት አስቀረ። ሶሻሊዝምን ድጋሚ እና ድጋሚ ብትሞክሩትም ፥ ፍትሕ እኛ በምንለው መልኩ ሊመጣ አይችልም።
ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ አመት በፊት የነበረው ዲሞስትኒስ “ሰው የሚመኘውን ነገር ያምነዋል” ይላል። በሌላ አነጋገር እውነት እንዲሆን ስለምንፈልግ ፥ እውነት ነው ብለን እናምናለን።
ማን ነው በዚህ እንቅፋት ያልተመታ? ማማረር ማለት ይሄ ነው። ምኞታችን እውነት ሳይሆን ሲቀር ፥ የሚመጣ ንጭንጭ ነው።
በየቀኑ የምሰማው ይሄ ፌር (fair) አይደለም የሚል ማማረርን ነው። ግን ማነው ፌር (fari) ይሆናል ብሎ ቃል የገባልን? ማነው ፍትሐዊ ሕይወት እንደምናገኝ ቃል የሰጠን? ማንም ዋስትና የሰጠን የለም። በሆነ በሚሰራ እና የራሱ አሰራር ባለው ዓለም ውስጥ ተወርውረናል። ስለዚህ ያን ተቀብሎ እና እንዴት እንደሚሰራ አጥንቶ መጓዝ እንጂ ዓለም ያልሆነውን እንዲሆን መመኘት ቅዠት ነው።
እንደ ፍቺ የሕግ ጠበቃ ፥ የትዳር መፍረስ መሠረቱ ይሄ ነው። ሲጋቡ አንዱ አንዱን ለመቀየር ይጋባሉ። ሁለቱም ግን በልባቸው ሌላኛው ሰው እንደ ሆኑት እንዲቀበሏቸው ነው የሚመኙት። ሁሉም ጋብቻ በሚባል መልኩ የሚፈርሱት ጋብቻው ሲመሰረት በነበረ ባህሪ ነው። ሁለቱም ያን ባህሪ ገና ወደ ጋብቻ ውስጥ ሲገቡ ያውቁታል። ግን እለውጠዋለሁ ብለው አመኑ።
በተመሳሳይ ከዚህ ሕይወት ጋር ያለን ትግል ይሄ ነው። መሬት ላይ የተቀበረ ድንጋይ እንቅፋት ቢመታን ፥ ሕጻን ካልሆንን በቀር እንቅፋት ከመታን ድንጋይ ጋር ድብድብ አንገጥምም። ይልቁንስ ድንጋዩን ባለማየታችን ራሳችንን እንወቅሳለን። በዚህ ሕይወት ከጠበቅነው ውጪ ስናገኝ ፥ ያላየነው እና ያልተረዳነው ነገር እንዳለ ነው ማወቅ ያለብን እንጂ የምናማር ከሆነ ከድንጋዩ ጋር እየተደባደብን መሆኑን ማወቅ አለብን።
ራሳችሁን ይሄን ጠይቁ። ይሄን ነገር የማምነው ምኞቴ ያ ስለሆነ ነው ወይስ በርግጥም እውነት እንደዛ ስለሆነ ነው? እንደዚህ እየሰራው እና እየሆንኩኝ ያለሁት ምኞቴ ስለሆነ ነው ወይስ እውነቱ እንደዛ ስለሆነ ነው? የማታውቁ ከሆነ አላውቅም በሉ። እዛ አቁሙ። ይሄ ሁሉ ፍልስፍና እና እምነት እንደ እንጉዳይ ዓለምን የሞላው ዓለም አላውቅም ማለት ፈርቶ እና አፍሮ ነው። ስለዚህ እውቀት አልባነትን ከምኞት በሚመጣ ፍልስፍና ሞላው። የትንትኔ እና የዲስኩር መዓት የከደነን ፥ አላውቅም የሚሉ ሰዎች ስለሌሉን ነው።
ዓለም ግን እርሷን ለማወቅ የሚጥርን እና ከማማረር ይልቅ ነገሮች እንዴት እንደሚሰሩ አውቆ ራሱን ከዛ ጋር ለማስማማት የሚጥርን ሁልጊዜ ትሸልማለች። ቢያንስ የሚያማርበት ጊዜ አይኖረውም።
ጥያቄ፦እግዚአብሔር እኮ ፍፁም ፍትሐዊ አምላክ ነው ወደድንም ጠላንም ይህች ዓለም ምትጓዘው እግዚአብሔር እስከፈቀላት ድረስ
ስለእውነት የሚሞተውም ስለጥቅሙ የሚገለውም ፍፁም ፍትሐዊ ከሆነው አምክ ፊት የተሸሸጉ አይደሉም...ይህ ደግሞ ፍፁም ፍትሐዊ በሆነው አምላክ ፊት ያለ እርሱ ፍቃድ የማይሆኑ ከሆነ
"አንድ መራራ ሀቅ አለ።እርሱም ይሄ ህይወት ፈፅሞ ፍትሐዊ መሆን እንደማይችል ማወቅ ነው።" አልክ
እንዴት?
ashenafikebatu9@gmail.com