top of page
Search

ዝምድና

Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew



“የሃማስ አባል የሆነ ሁሉ ሞት ዒላማ አድርጎታል” ይሄን ያለው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢቢ ናታኔሁ ነው። በእስራኤሎች ላይ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም ፳፯ ቀን በሃማስ የተፈጸመው ግፍ አረመኔያዊ ነው። ምንም ጥያቄ የለውም። ይሄን ሰብአዊነት የሚሰማው ሁሉ አምርሮ ማውገዝ አለበት። ጥያቄው ግን እንዴት ነው ሀዘናችንን የምንገልጸው የሚል ነው? ማለትም በሞተው የሰው ቁጥር ብዛት ነው ወይስ በአገዳደሉ ዓይነት ነው ወይስ ለሞት በዳረጋቸው ምክንያት ወይስ ገዳዮቹ የተነሱበትን ዓላማ በመፈተሽ ወይስ በራሳችን የአይዶሎጂ እና የማንነት ትስስር (ክርስቲያን እና ሙስሊም መሆናችንን ለማለት ነው)? ምንድነው ከፍልስጤማውያን የሚሞቱ ልጆች በላይ ለእስራኤሎች ሕጻናት ወይም ከእስራኤላውያን ሲቪሊያን በላይ ለፍልስጤማውያን ሲቪሊያን ለማዘን የዳረገን? ምንድነው የሰብአዊነትን እና የታሪክ እንዲሁም የመብት ጥሰት መከራከሪያ ጽንሰሀሳቦችን አስቀድሞ ፍርድ ለሰጠው ስሜታችን መደገፊያ አድርገን እንድናቀርብ ያደረገን? ምንድነው ለያዝነው አቋም መሰረት?


ለዚህ የሚኖረን መልስ ብዙ ሊሆን ይችላል። ትልቁ ግን ዝምድናችን ነው። ይሄ ዝምድና ያልኩት ምን እንደሆነ ከማስረዳቴ በፊት የጹሁፌን ጭብጥ ልናገር። ከላይ ያነሳውትን ጥያቄ የጠየኩት ለእስራኤሎች ወይም ለፍልስጤማውያን የምትከራከሩ ሰዎች ምን ያህል ምክንያታዊ እንዳልሆናችሁ ለማሳየት አይደለም። የኔ ፍላጎት ይሄን ጦርነት እንዴት ሰዎች እየተረጎሙት እንደሆነ እና ለሞቱት ሰዎች ያሳዩት ሐዘን ፥ የእስራኤል መንግስትም ሆነ ሀማስ የወሰዱት አጸፋ ምን ያህል ስለእኛ ሀገር ሁኔታ የበለጠ እንድገነዘብ ያደርገኛል የሚል ነው።


ይሄን ስለእስራኤላውያን አይደለም የምለው። ወይም ስለፍልስጤማውያንም አይደለም። ስለእኛ እና እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር የአይዶሎጂ ወይም የሌሎች ተዛማጅ ግንኙነት ስላለን ሰዎች እንጂ። የፈረንሳይ የሕግ እና የታሪክ ሊቅ ፈርናንድ ብሮዴል በአንድ ወቅት እንዳለው “ወደ እንግሊዝ ሀገር ለአንድ ዓመት ሄደ ብትኖር፣ በዛ አንድ ዓመት ውስጥ ስለእንግሊዝ ማወቅ አትችልም። ነገር ግን ወደ ሀገርኽ ስትመለስ ከመልመድኽ የተነሳ የተሰወረብኽ ነገር ግልጥ ሆኖ ይታይሃል። በአዲስ ጮራ በልምድህ የተሰወረብህ ይገለጥልሃል” ይላል። በሌላ አነጋገር የሌሎችን ነገር የምታጠናው የበለጠ ስለራስሕ ለማወቅ ነው ማለት ነው። ያንተ ቆዳ በሌለበት ጦርነት (skin in the game) ውስጥ በዜና እና በንባብ (intellectually) ያገኘኸው ነገር ያን ጦርነት ወይም ሀገር ያሳወቀኸ ከመሰለህ ከትዕቢት ውጪ ያተረፍከው ምንም የለም። አንድን ነገር በእውቀት ማወቅ እና በዛ ውስጥ ራስኽ ማለፍ ምን ያህል ልዩነት እንዳለው ለማወቅ መከራ የገጠማቸውን ሰዎች ለማጽናናት ያነጎድከው ዲስኩር በአንተ መከራ ወቅት ከሸንበቆ የቀጠነ ደካማ ምርኩዝ እንደነበረ ማስታወስ ብቻ ይበቃኸል። ያ ዲስኩር ሊያጽናናኽ ይቅርና ተመሳሳይ ነገር ሊነግሩኽ እና ሊያጽናኑ የሚፈልጉትን እንኳ እንዴት እንደምትጠየፋቸው ታውቃለኸ። ቲኤስ ኤሊኦት እንዳለው “ስለሌሎች ለማወቅ መባዘናችንን ማቆም የለብንም። ነገር ግን የዚህ የማወቅ አሰሳ መጨረሻው መነሻችን ጋር መድረስ መሆን አለበት። የአሰሳው ፍጻሜ መነሻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ አጥርተን ለማወቅ ነው።”

አሁን የድጋፎቻችን መሠረት ስለሆነው ዝምድና ለመናገር ልመለስ። የስጋ ዘመዱን በሞት የተነጠቀ ሰው ሀዘኑን በማሰብ ወይም በምክንያት እንዲያደርግ መጠየቅ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። እናቱ የሞተችበትን ሰው ፥ “ይሄ ሁሉ ሕጻን በግፍ በሚገደልበት ሀገር ምን ይሄን ያህል ለእናትህ ያስለቅሰሃል” ማለት ፥ ስለሀዘን የመረዳት አቅማችን ምን ያህል ደካም እንደሆነ ብቻ ነው የሚገልጸው። ሕይወት እንኳ በአልአዛር ሞት ለሞት እንባን አፍሷል። ስለዚህ የቅርብ ወገኑን የተነጠቀ ሰው እንዲያመዛዝን መጠበቅ ጅልነት ብቻ ነው።


ለምን?


ጅልነት የሚሆነው ማመዛዘንን ስለጠበቅንበት አይደለም። ይልቁንስ አንዱ ከአንዱ ጋር ተሳስሮ የሚኖረው ፥ እርስ በእርሳችን በፈጠርነው የዝምድና ገመድ እንጂ ፥ የሰው ልጅ የሰው ልጅን ሁሉ መውደድ አለበት በሚል ፍልስፍናዊ ትርክት ስላልሆነ ነው። ለወገንህ ያለህ ፍቅር እና ያ ፍቅርህ በሚወልደው ኃላፊነት ብቻ ነው ለሌላው የሚተርፍ ሰብአዊነት በውስጥኽ የሚያቆጠቁጠው።

ከዚህ ውጪ ለሀገርህ እና ለወገንሕ የተሻለ ነገር ለመመኘት እና ያን ወደ ድርጊት ለውጠኽ ስትንቀሳቀስ ለምን ስለራስኽ ብቻ ታስባለኽ፣ ለሌላውም መቆም አለብህ፤ ካለዛ ግን ዘረኛ ነህ ብሎ የሚከስኽ ፥ አንተ ለራስህ ወገን ያደረከውን ለዛ ሰው ወገን የራስህን ትተኽ ብታደርግለት ግን በዘረኝነት እና በጨካኝነት አይከስህም። ለምን? ምክንያቱም ከመጀመሪያው ያን ክስ ያቀረበብኽ እሱም ለራሱ ወገን የበለጠ ሳስቶ እንጂ አንተን ከከሰህ ለዝምድና ከማድላት ሰብአዊነት ተላቆ አይደለም።


ይልቁንስ እንዳልኩት እናቱ የሞተችበት ሰው ብዙ ሕጻናት ስለሚሞቱ እናቱን በማጣቱ የመረረ ሀዘኑን ከመግለጽ ከተቆጠበ የዛኔ ማህበረሰብ አደጋ ውስጥ ይገባል። ሰው ከሰውነት ጎራ ይወጣል። ኃላፊነት ላለመውሰድ እና ከተጠያቂነት ለማምለጥ በር ያገኛል። ለጭካኔያችን ጠንካራ አመክንዮ ይኖረናል። ምን እያልኩኝ ነው? እያልኩኝ ያለውት “ሕይወት እንዴት እንደሚሰራ እንወቅ ፥ ሕይወት እንዲህ እንዲሰራ የፈቀደው ለምክንያት ነውና” ነው። ማለትም ሺዎች በሚራቡበት ሀገር ውስጥ “ለዚህ አጠገቤ ላለው ሰው የዕለት እንጀራውን ብችልለት ምን አመጣለሁ” የሚል ሰው ጭካኔን እና አረመኔነትን በምክንያት የሚተክል ነው። ልክ ነው። በሀገሪቷ የተንሰራፋውን ድህነት እና ችጋር ጎረቤቱ ያለውን ድኋ በመርዳት የሚቀርፈው አይደለም። ይሄ ድህነትን ስታስቲክስ ፥ ረሀብን ዴታ (ቁጥር) ስናደርገው ነው። የሰው ልጅ ቁጥር ሲሆን ፥ በዚህ ምድር የከፋው አረመኔ ነገር የሚከሰተው የዛኔ ነው። ከባህር ማዕበል የሚተፋቸውን በመቶዎች ከሚቆጠሩ አሣዎች መካከል በእግሩ ሥር የወደቁትን በማንሣት መልሶ ወደ ባህር ለመመለስ እና ለማትረፍ የሚጥር ሰው ፥ በአንድ የኔቢጤ እንዲይ ይባላል “አብደኸል፣ ምን ሊረባኽ ነው የምትደክመው? ተመልከት ማዕበሉ ከቁጥር የሚልቁትን ነው እየተፋ ያለው አንተ ደግሞ በጣት የሚቆጠሩትን ነው ለመመለስ የምትጥረው። ምን ለውጥ አመጣ ብለህ ይለዋል? ያ ሰው ግን ወደ እጁ ወዳለው አሣ እያመለከተው “የማደርገው ነገር ለዚህ አሣ ትርጉም አለው” አለው።


የእስራኤል መንግስት ኃላፊነት ለእስራኤሎች ነው። የሀማስም ፍቅር ከፍልስጤማውያን ጋር ነው። ጠንካራ የኔ የምትለው መንግስት ሲኖርህ የእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ዋጋ ይኖረዋል። መንግስትህ አንተ ሞተ ዝም እንደማይል ስታውቅ ፥ ያን መንግስት የኔ ፥ ሀገሪቷን ደግሞ እንደእናት ትቀበላታለህ።

ከዚህ ውጪ ግን ለዝምድናህ ባሳየኸው ቅናት እና በወገንህ ላይ በደረሰ ጥቃት የምታነሳውን በትር ፥ ሊያሸማቅቅህ የሚሞክር ሁሉ አይዶሎጂ ነው። ይሄ አይዶሎጂ እንዴት በሀገራችን እንደተተገበረ ላሳይ።


ኢትዮጵያው ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት የሞቱት አማሮች በአይዶሎጂ ጭካኔ ታውረን ቁጥር ነበር ያደረግናቸው። ቁጥሮች ነበሩ በኢትዮጵያ ስም ለተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች እነዛ ምስኪን አማሮች። ለመንግስትም ቁጥሮች ነበሩ ምክንያቱም ዙፋኑ የሚጸናለት የአማራ መንግስት እንዳልሆነ ለብሔር ብሔረሰቦች ሲነግራቸው ነው። ኢትዮጵያ ማለት ሀማስ መንግስት የሆነባት ሀገር ማለት ናት። ሀማስ ክፉ ነው ደግ ነው የሚል ግልብ ድምዳሜ ላይ መድረስ አልፈልግም። የፖለቲካ እምነቱ ግን እስራኤል የምትባል ሀገር በዛ አካባቢ መኖር የለባትም የሚል ነው። ይሄ ብቻ ግን አይደለም እስራኤሎች በዘመናት ሂደት ውስጥ ታሪካዊ ሀገራችን ባሉት ቦታ ሀገራቸውን አጽንተው ለማቆየት ብዙ ግፉ ፈጽመዋል። ይሄ ደግሞ ለሀማስ የፖለቲካ አቋም ፥ ሕዝብ የማሰባሰቢያ እና ግፍ የመፈጸሚያ ጥሩ ቤንዚል ሆነለት። ሀማስ ከተፈጠረበት መነጽር ውጪ እስራኤልን ማየት ይከብደዋል። ከአይዶሎጂው በሚነሳ የማጥፋት ተግባሩ የእስራኤልን መንግስት ግፍ ዘወትር ይጋብዛል። ይሄ ማንም ለወገኑ ከሚሰማው የተቆርቋሪነት ስሜት የሚመነጭ እልህ ነው። ማለትም አንድ ኃይል በተመሳሳይ ጊዜ ግፈኛ እና ተጠቂ ይሆናል። ተጠቂ እና ግፈኛም እንደዚሁ። ይሄን ወደ ፍጹም ፍትሐዊ ወደ ሆነ ሚዛን አምጥቶ ሁሉም በሰላም የሚኖርበት ሀገር መፍጠር አይቻልም። ግን ወደ አንጻራዊ ፍትሕ ማስጠጋት ይቻላል። ያ የሚሆነው ግን ፍልስጤማውያንም የሚጮህላቸውን እና መጠቃታቸው የሚያበሳጨው ኃይል ራሳቸው ሲፈጥሩ ብቻ እንጂ ፥ ከእስራኤልም ሆነ የፖለቲካ ኃይልን እያየ ከሚፈርድ ዓለም አይደለም።

በተመሳሳይ ማንነቴን አማራ በሚባል ብሔር ተነጥቄያለው፣ ግፍ እና መከራም ይሄ ብሔር አድርሶብኛል ብሎ በሚያምን ድፍን የኢትዮጵያ ብሔር ባለበት ውስጥ ፥ በገፍ የሚገደለው አማራ ከሌላው ፍትህ እና መቆርቆርን አገኛለው ብሎ ካሰበ ፖለቲካን አለመረዳት ብቻ አይደልም ፥ የሰው ልጅ እንዴት እንደሚያዝን እና እንደሚቆረቆር፣ ከሀዘን የሚፈልቀው ለተገፉት የመቆም ስነልቦና እንዴት እንደሚሰራ አለመገንዘብም ነው።


ለእናትህ ሞት ላለማዘን በሌሎች ላይ የምታየው ሰቆቃ መጽናኛ ከሆነኽ ፥ ለሌሎችም የሚሆን ሀዘኔታን እንዳጣ ተረዳው። ለራስህ እና ለወገንህ ያለህ ፍቅር ብቻ ነው ለሌሎች ርሕራሔ እንዳለህ የሚነግረኝ። ያንተ የምትላቸውን ላለማስደፈር የምታደርገው ጥረት ነው ፥ ሌሎች ለራሳቸው ወገን ያላቸውን ስነልቦናዊ ትስስር እንድትገነዘብ የሚያደርግህ። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዙ ራሱ “ባልንጀራህን ውደድ” የሚለው ፥ ሰውን ውደድ ከማለት ይልቅ። ጎረቤትህን ስትወድ ብቻ ነው ፥ የሰውን ልጅ መውደድ የምትጀምረው። ዓለሙን ሁሉ እንድንረዳ አልተጠራንም። ዓለምን በችግር መዓበል እያናወጠ ፥ ባልጀራህ ላይ ዓይንህን እንድታደርግ የታዘዝከው የፍቅርኽ ትከሻ መሸከም የሚችለውን ቀንበር ስለሚያውቀው ነው። ይሄ የፍቅር ክንድን አሰራር የተረዳው ሙሴ ነው ግብጻዊውን በክርኑ ጉልበት ገድሎ የዕብራዊውን ስቃይ ያስታገሰው።


 “ሀገሪቷ እንዳትፈርስ” በማለት ዛሬ እስራኤልን በፍልስጤም ላይ እንድትዘምት ካደረጉ ብዙ እጥፍ በላይ የሚሆኑ አማሮች ሲገደሉ አፋቸውን የሚለጉሙ ፥ “ፖለቲካ ማለት” በማለት በሐዘን ቤት መጥተው ዲስኩር የሚያሰሙ ሰዎች ፥ ኢትዮጵያን ከመውደድ የሚናገሩ አይደሉም። የአንተ ሞት እና ስቃይን የመረዳት አቅም ስለሌላቸው እና ያንተ ሞት ከቁጥር እንዳይሻገር ለዝምድና የመቆም እና የመቆርቆር፣ ከዛ የሚመነጭ ፖለቲካን ማራመድ ባለመቻልህ ነው። የእኔ እናት ለሌላው እንደማንም ሴት አንዲት ሴት ናት። ለእኔ ነው እናትነቷ። ያን ባለማፈር በመግለጽ፣ እናቴ ይገባታል ብዬ ለማምነው መብት እና ክብር መቆም ያለብኝ እኔ ነኝ። ይሄን የተለየ ስሜት እኔ መግለጽ ካልቻልኩኝ ግን ዘፋኟ እንዳለችው “እናቱን የማይወድ ሰው ሰው ነው አልለውም አውሬ ነኝ ባይ ነኝ።” ሌላውን ራሱ የመውደድ አቅም እንደሌለኝ ይናገራል።


 እነዚህ ሰዎች የአማራን ሞት እንደራሳቸው ባይሰማቸው ለእኔ የፍልስጤማውያን እና የእስራኤላውያን ሞት ከቁጥር በላይ ሰላም እንዳነሳኝ እነሱንም እረዳቸዋለሁ። ነገር ግን ለኢትዮጵያ ብለን ነው ብለው ሀዘኔን አሳንሰው የእነሱን ጭካኔ እና የሰዎችን የሀዘን ስብራት በተራ የፖለቲካ ዲስኩር ሊያጣጥሉት ሲሞክሩ ግን ይሄን ድራማ ከዚህ በፊት አይተነዋል ማለት ያስፈልጋል። ይሄን ድራማ አሌክሳንደር ሶልዦኒስተን በሦስት ተከታታይ ቅጽ መጽሐፉ ጽፎልናል። ያ ድራም ሁሉም ጋር አንድ ጭብጥ (theme) አለው። አይዶሎጂ ነው። ሶልዦኒስተን እንዳለው አይዶሎጂ መጀመሪያ ከሰብአዊነት ያወጣኽ እና ዓለም አቀፋዊ ያደርግሃል። ከዛ እግዚአብሔርን ያስረሳኸል።


አይዶሎጂ ፦ የፖለቲካ እና የማህበረሰብ አስተዳደር የጭካኔ ፍልስፍናችንን በእኛ እና በሰዎች ፊት ደግነት ያስመሰለ፣ ነውረኝነታችንን ለሀገር የተከፈለ፣ ለለውጥ ሲባል ለማህበረሰብ የተሰጠ ቸርነት ያስመሰለ ነው አይዶሎጂ። አይዶሎጂ ክርፋት ብልግናችን ውግዘት ሳይሆን ጭብጨባ እና አድናቆት ያላበሰው ነው። አይዶሎጂ ሕዝብ ሲቀነስ መደመር ነው ያለን፣ ረሀብ ሲገርፈን መበልጸግ ነው ያለን፣ የምስኪኖች ቤት ሲፈርስ ከተማ ማስዋብ ነው ያለን ነው። ወንድምን አለመውደድን፣ ለቤተሰብ እና ለወገንህ አለመቆምን፣ ፍቅር የሞተበት ልብህን ዓለማቀፋዊ ወዛደርነት፣ ለጭቁን ብሔሮች የቆመ፣ አርቆ አሳቢ በማለት ሊፒስቲክ ይቀባዋለ።


ይሄን ሂፖክራሲ “የዓለም ጭቁን ሰራተኞች፣ የዓለም ጭቁን ሕዝብ፣ የዓለም ጭቁን ብሔር” በማለት ለአውሬነት ስብዕናችን ፍልስፍና ሰጥተን ሁሉን ድኋ፣ ሁሉን አሽከር፣ ሁሉን ጭሰኛ በመጨረሻ ያደረገውን ፍልስፍናዊ ድራማ አይተነዋል። በአይዶሎጂ ተሸብበኽ ለሚሞተው ወገንሕ መታገል ካልቻልክ ፥ አንተን ነክቶ ሌላው በሰላም መኖር እንደማይችል ካላሰየኸ የሰው ልጅ ስነልቦና አልገባንም ማለት ነው።


ይሄ ማለት ግን የኔ ፍትህ በሌሎች ውረደት እና ስቃይ ይከበር እያልኩኝ አይደለም። “ለእኔ እና ለወገኔ መብት እና ክብር የማልታገል ከሆነ ለማንም የመቆም አቅም የለኝም” እያልኩኝ እንጂ። ለባልጀራው ቁራሽ እንጀራ ላለመስጠት የሰው ልጆችን ረሀብ እንደምክንያት የሚያነሳ ሁሉ ፥ ለማንም የሚሆን ፍቅር በውስጡ እንዳይበቅል የፈቀደ ነው። አስመሳይ እና ውሸታም ነው። ያንተ ለሆኑት ኃላፊነት አለብህ። ሰውነትን እንጂ አምላክነትን ከኛ አይጠብቅም ፥ አይፈልግምም። በቁጥር፣ በማነጻጸር፣ በመደመር በመቀነስ እንድናስብ አልተጠራንም። እንደዛም አናስብም። እንደዛ እንድናስብ የሚነግረን ሁሉ ሀዘናችንን የመካፈል አቅም የሌለው ብቻ ነው። ይልቁንስ እኔ እና ቤቴ ብለን ስለራሳችን ኃላፊነት እንድንወስድ እና የወገናችን መሞት እረፍት እንዲነሳን ነው የተጠራነው። በሞት ፊት ሕይወት እንባውን ካፈሰሰ ፥ የወገኑ ሞት ቁጥር የሆነበት ሁሉ በውስጡ ሕይወት የሌለው ነው።

277 views0 comments

Recent Posts

See All

የሰንበት ዕይታ - 16

እንቢ ማለትን በምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው።...

የሰንበት ዕይታ - 14. የኢዮብ መጽሐፍ እንቆቅልሾች

January 20, 2024 ዊሊያም ብሌክ እንዳለው “በሞኝነቱ የጸና ሞኝ ጠቢብ ይሆናል።” “ያለጽናት አይደለም ጥሩ አማኝ፤ ጥሩ ኢአማኒም መሆን አይቻልም” እንደሚባለው ማለት ነው። አንዴ ያየኸውን ነገር አውቃለሁ...

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page