top of page
Writer: Mulualem Getachew
Mulualem Getachew
7 hours ago
3 min read


 የሶረን ኪከርጋርድን የፍቅር ሥራ(works of love) የሚለውን ድንቅ እና ከባድ መጽሐፍ እያነበብኩኝ ነው። ማንበብ በዚህ ደረጃ በሰው ልጅ ባህሪ ላይ ተጽዕኖ ማምጣት እንደሚችል የሚያሳይ መጽሐፍ ነው።




 


ስለ ፍቅር መጻፍ ከባድ ነው። ስለ ሮማንቲክ ፍቅር አይደለም የሚናገረው። ወደድኩሽ፣ ሞትኩልሽ ብሎ ስለ ሚገለው ፍቅር አይደለም። ወይም ካላንቺ መኖር አልችልም ብሎ ከዚች ሴት የት አባቴ ልጥፋ ብሎ ስለሚጠናቀቀው ፍቅር አይደለም የጻፈው።


 




ያ የገጣሚዎች ፍቅር ነው። የዘፋኞች ፍቅር ነው እርሱ። ለገቢ የሚሆን። በተዘዋዋሪ ራስን መውደድ ነው እርሱ። የሚያፍን ፍቅር ነው እርሱ።


 




ዛሬ የምፅፍላችሁ ፍቅር፥ የሕግ አዋቂው ጌታን ፈትኖ ያገኘው ፥ ሊቅ አራቆ የተረከውን ፍቅር እንጂ።


 




ስለሁለተኛው ትእዛዝ፣ ከመጀመሪያው ትእዛዝ እግዚአብሔርን ከመውደድ ቀጥሎ ስላለው ፍቅር።


 




ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ።


 




ባልንጀራ ማነው?





ጌታ ይሄን በምሳሌ አስረዳ። ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ ባልንጀራ ማለት የቤትህን በር ከፍተህ የምታየው ሰው ነው ይላል። ልክ በርህን ከፍተህ የምታየው ሰው፣ ያ ሰው ነጭ ይሁን ጥቁር፣ አማራ ይሁን ኦሮሞ ፣ ትግሬ ይሁን አፋር ፣ ወይም ቻይናዊ ይሁን አረብ ፥ ያ ሰው ነው ባልንጀራህ ይላል። እግዚአብሔርን የመውደድህ ምልክት። እርሱን መውደድህ ነው።


 


 




“ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?”” 1ኛ ዮሐ 4፥20።


“ያየውን ወንድሙን” ሲል “የምናየውን፣ በር ከፍተን፣ ዓይናችንን ልክ ስንከፍት የምናየው ሰው ፥ ያ ነው ባልንጀራ” ነው እያለን ነው።





ተመልከቱ ባልንጀራን እንደ “ራስ መውደድ” ውስጥ ራስ መውደድ የሚባል ሳጥን አለ። ያንን ሳጥን ከፍታችሁ ሁሉን ካስገባችሁበት ራስን መውደድ የሚባል ነገር ፈጽሞ ይጠፋል።


 




ምሳሌ፦ አንድ የእኔ የምትሉት ቤት አለ። ያ ቤት ውስጥ ማንም ሰው እኩል ስልጣን እና እኩል መብት ካለው ፥ ያ ቤት የማነው? የማንም። ሁሉም እኩል መብት ካለው ያ ቤት የሁሉም ነው። የሁሉም የሆነ ነገር ደግሞ ሁሉን የሚሰጥ ብቻ የተለየ መብት ይኖረዋል (only the one who gives everything has a better right)። ሁሉን የሚሰጥ ካለ። ካለዛ ግን የማንም አይሆንም።


 




የማንም ያልሆነ ነገር ደግሞ ምንም ጥበቃ አይኖረውም። ግን የባልንጀራ ፍቅር ጥበቃ አለው። ጠባቂው “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ያለው ነው። ስለዚህ ሰው አምላኩን ካልወደደ ራሱንም አይወድም። ራሱን ያልወደደ ደግሞ ሌላውን እንደ ራሱ ይጠላ ይሆናል እንጂ መውደድ አይችልም። ምክንያቱም ራሱንም በአግባቡ አይወድምና።


 





ሲጋራ የሚያጨስ ሰው ራሱን እየጎዳ ነው። ይሄ ሰው ባልጀራውን ውደድ ቢባል (እንደ ራሱ)፤ ምንአልባት ሲጋራ ነው የሚሰጠው። ምክንያቱም ራሱን መውደድ ምን እንደሆነ ራሱ አያውቅምና።


 





ወደ ቤቱ ምሳሌ እንመለስ። ቤቱ ያንተ ነው። ቤቱን አብክተኸዋል። ጠረኑ፣ ንጽህናው፣ እቃዎቹ ተሰባብረዋል፣ ሽንቱ ቤቱ አይሰራም፣ ጣሪያው ያፈሳል። አቧራ ያስገባል። ወደ እዚህ ያንተ ወደ ሆነው ቤት ሌላ ሰው አስገብተህ እኩል መብት ልትሰጠው ትችላለህ። ግን ወደ እዚህ ወደ ጎሰቆለ ቤት መግባት ባልንጀራህን ይጠቅመዋለ ወይስ ይጎዳዋል? መልሱ ባልንጀራህ ካንተ የባሰ ቤት ውስጥ ይኖር ካልነበረ በቀር ይጎዳዋል። ካንተ የባሰ ቤት ውስጥ ቢኖር ራሱ ያ ካንተ የባሰ ቤት ውስጥ መኖር ይሻለው ይሆናል። ምክንያቱም ብዙ ላያተርፍ ነገር፣ ያንተ ባለውለተኛ ነው ያደረከው። ያንተ ቤት ውስጥ በመግባቱም ትንሽም ቢሆን የባይተዋርነት ስሜት ይሰማዋል። ስለዚህ አንድ ሰው ራሱን በትክክለኛው መንገድ ከወደደ ብቻ ነው ሌላውን መውደድ የሚችለው። ትክክለኛ ያልኩት፥ በዛ በጎሰቆለ ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው ምንአልባት ምርጥ ቤት ውስጥ እየኖረ ሊመስለው ይችላል። የቤቱን መጎስቆል የማስተዋል አቅም ከሌለው።


 




ግን ሰዎች ደግሞ በጊዜ የተገደብን ነን። ይሄ ምን ማለት ነው? ይሄ ማለት ዛሬ ጥሩ የመሰለን ነገር፥ ነገ ወይም ከዓመታት በኋላ መጥፎ ሆኖ እናገኘዋለን። ለምሳሌ የአስር ዓመት ልጅ ጥናቱን ትቶ ሙሉቀን መራገጥ እና ኳስ መጫወት ጥሩ ሊመስለው ይችላል። ኳሱን አቁመህ አጥና የሚለውን ሊጠላ ይችላል። ለጊዜው። ከዓመታት በኋላ ነው እርሱ ጥሩ የመሰለው “ሙሉ ቀን መራገጥ” መጥፎ እንደሆነ የሚገባው። ይሄ በአዋቂዎችም ዘንድ ያለ ነው። አዋቂዎች ብንሆን እንኳን በአንዳንድ ጉዳዮች ከዓመታት በኋላ ነው ልክ እንዳልሆንን የሚገባን።


 





ስለዚህ ሰዎች ሁልጊዜ ትክክለኛው የቱ እንደሆነ አያውቁም ማለት ነው። ስለዚህ ትክክለኛ ፍቅር አለን ብለው ግን ጥላቻ ወይም ጎጂ ስሜት ሊኖራቸው ይችላል። ለጊዜው እየወደዱ ሊመስላቸው ይችላል። ለጊዜው ትክክለኛ ፍቅር ሊመስላቸው ይችላል። ለዚህ ነው ይሄ ፍቅር ሁልጊዜ ትክክለኛ ነገር በሆነ መሠረት ላይ መቆም ያለበት።


 




ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ሌላ ከርሱ ውጪ ያለ ሁልጊዜ ትክክለኛ የሆነ ፍቅር (ፍጹም የሆነ ፍቅር) ላይ መጽናት ካልቻለ፣ ባልንጀራን እንደ ራስ መጥላት ሆኖ ሊቀየር ይችላል። ለዚህ ነው ፈጣሪውን “በፍጹም ልቡ በፍጹም ነፍሱ በፍጹም አሳቡ መውደድ” ያልቻለ ሰው፤ ባልንጀራውን እንደ ራሱ መውደድ የማይችለው። እንደ ራሱ ግን ሊጠላው ይችላል። ምክንያቱም ፍቅርን ራሱ አያውቀውምና።



ይቀጥላል።


 
 
 
Writer: Mulualem Getachew
Mulualem Getachew
Aug 30
3 min read




የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የፓርኪንግ ጠባቂ ሆነው አሜሪካ እየሰሩ መታየታቸው ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ አነጋግሮናል። ብዙዎች ያን የሚያክል ትልቅ ክብር ያለው ሥራ ላይ የነበረ ግለሰብ ዝቅ ብሎ፣ ሥራ ሳይንቅ መሥራቱ አስገርሟቸዋል። ለእኔ ገዱ የብዙዎቻችንን የአዕምሮን ጓዳ ጉድ ያደረገ ነው የሚመስለኝ። ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንደያዝን ነው የገለጠው። ምን ማለቴ እንደሆነ ላብራራ።



የሥራ ዓላማ ግን ምንድነው?



“አዳምንም አለው። የሚስትን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤” ዘፍ 3፥17።



በድካም ሠርቶ መብላት እንግዲህ የሚጀምረው ከዚህ ነው። እኛ የሠሪው፣ ሥራውም መልካም የሆነለት የአምላካችን እግዚአብሔር የእጆች ሥራ ነን። አዳም በገነት ውስጥ እንደማይሰራ አልተነገረንም። እንደውም ከውድቀት በፊት አዳም ሥራ ነበረው። እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት መግዛት። ዘፍ 1፥28። ሥራ የውድቀት ውጤት ነው የሚል ትምህርት ለዚህ ነው ስህተት የሚሆነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያን አይነግረንም። ነገር ግን በላቡ እና በድካም ሠርቶ መብላት የጀመረው ከውድቀት በኋላ ነው። ልጆቹም የሥራ ዘርፍ ተከፋፍለው መሥራት ጀመሩ። ከመሬት ጋር መታገል ፥ ከተፈጥሮ ጋር መታገል ጀመሩ። ፍጥረትን ያለ ችግር የሚገዛው አዳም አሁን ሁሉ ነገር በድካም ብቻ የሚሆንለት ሆነ።




ሥራ ውድቀትን ቢቀድመውም፤ ከውድቀት በኋላ ግን የሰው ልጅ ሳይሠራ መብላት እንደማይችል ተነግሮታል።




ስለዚህ መብላት የሚወድ ሁሉ መሥራት አለበት። ቢያንስ መሥራት ከልቡ መፈለግ አለበት። ቅዱስ ጳውሎስ ለዚህ ነው “ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና።” ብሎ የተናገረው። 2 ኛ ተሰሎንቄ 3፥10። ሊሠራ የማይወድ አይብላ ተብሏል።



በዚህ ምድር ሊሠራ የማይወድ ቢኖር ምግብ መስጠት እንደሌለብን ተነግሮናል። አዎ። ሊሠራ የማይወድን ምግብ እንድንከለክለው የብሉይ ኪዳን ሕግ ብቻ አይደለም የአዲስ ኪዳን የፍቅር ሕግ አዞናል። ግን አስተውሉ ሊሠራ የማይወድ ነው የሚለው። ሊሠሩ እየወደዱ በተለያዩ ምክንያቶች መሥራት የማይችሉትን ግን የመርዳት ግዴታ አለብን።



ስለዚህ ሥራ አንዱ ትልቁ ተልዕኮ ለመብላት ነው ማለት ነው።



ቅዱስ ጳውሎስን ተመልከቱ። ሊቁን ጳውሎስን። በዚህ ምድር የእውቀት ጥግ ያለውን። በመንፈሳዊ ሕይወት ደግሞ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያሉትን ሁሉ እግዚአብሔር እስከ ሦስተኛው ሰማያት ድረስ ወስዶት ያሳየውን ድንቅ ሰው። 2ኛ ቆሮ 12፥4።



 ክብርን ቢሆን የእርሱን ያህል የከበረ ከመካከላችን ማን ይኖር ይሆን?! ይሄ ታላቅ ሐዋርያ ግን በሰው ላይ ሸክም ላለመሆን ማታ ማታ ድንኳን እየሰፋ ነበር የሚተዳደረው። ሐዋ 18፥4። ጳውሎስ ሥራን የመዘነው በሰው ላይ ሸክም ላለመሆን ነበር። ከሰው ሸክምነት ነጻ እስካወጣው ድረስ ፥ ሥራን አልናቀም። የወገብ በሽታ እያለበት፣ ቀኑን ሙሉ ወንጌል የመስበክ ግዴታ እያለበት ፥ ባለችው ጊዜ ግን በሰው ላይ ሸክም ላለመሆን ድንኳን እየሰፋ ራሱን ያስተዳድር ነበር።



ሌላው ፈጣሪያችን ሠራተኛ ነው። የሚበላው ጎድሎት አይደለም። እንደ እኛ አይበላም። ሌላው ላይ ሸክም ላለመሆን አይደለም። እርሱ ሁሉን የተሸከመ ነው እንጂ። ውበት እና ሞገስ አጥሮት አይደለም። እርሱ የውበት ፏፏቴ ነው።



ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲይ ይላል፦ “ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።” ዮሐ 17፥5። ምንም ሳያስፈልገው፣ ማንም የሚከሰው ሳይኖር፣ ምንም ሳይጎድለው እግዚአብሔር ይሠራል። የእጆቹም ሥራ ውብ ናቸው። መልካም እና እጅግ መልካም ናቸው። እርሱ ብቻ መልካም የሆነው አምላካችን ፥ መሥራት የእርሱ መገለጫ ነው። አብ ይሠራል። ኢየሱስ ክርስቶስም ይሠራል። ያለማቋረጥ። እኛም እንድንመስለው ተጠርተናል። ስለዚህ እንሠራለን።



ለዚህ ነው የሰው ልጅ ከውድቀትም በፊት እንዲሠራ የሥራ ዘርፍ የተሰጠው። እርሱም የእግዚአብሔርን ፍጥረት ማስተዳደር እና መግዛት ነበር። ሥራን የርግማን ውጤት አድርጎ ማስተማር ምንፍቅና ነው። ስሁት ትምህርት ነው።



አሁን ወደ ገዱ እንመለስ። ኢትዮጵያኖች ያለምክንያት ድሃ እንዳልሆንን አሁን እንወቅ። ያለ ምክንያት የዓለም ጭራ እንዳልሆንን አሁን ይግባን። ሥራ ክቡር ነው። በሰዎች ላይ ሸክም እንዳንሆን የሚያደርገን የእጃችን ሥራ ክቡር ነው። ለመብላት የምንሠራው ሥራችን ክቡር ነው። ከዛም እንደ ፈጣሪያችን መልካም የሆኑ ሥራዎችን ሳይቸግረን እና ሳይርበንም ጭምር የምንሠራው ክቡር ነው። ፈጣሪያችን ሠሪ ነው። እኛም እንሠራለን።



በኢትዮጵያ ግን ሥራ ሌላም ዓላማ አለው። ይሄ ግን መንፈሳዊ አይደለም። ይልቁንስ ሰይጣናዊ እንጂ። እርሱም ትዕቢት ነው።



ኢትዮጵያው ውስጥ ሥራ ስታተስ ነው። ሥራ ከባልጀራ ከፍ ማለታችንን መግለጫ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ራስን ከፍ ከፍ ማድረጊያ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው እየተራበ ራሱ ፥ ሥራ ክቡር ሆኖ ሳለ የማይሰራቸው ሥራዎች አሉ። ከሊስትሮ ወይም ከቀን ሠራተኛ በብዙ እጥፍ ዝቅተኛ ገንዘብ የሚከፍል የቢሮ ሥራ ላይ መሰማራት ለኢትዮጵያውያን የተሻለ ነው። የተሻለ የሚከፍሉ እና የሰው እጅ ላይ እንዳንወድቅ ከሚያደርጉ ሥራዎች ይልቅ ዝቅተኛ እየከፈሉን የቤት ኪራይ እንኳን መሸፈን የማይችሉ ሥራዎች ላይ ተቀጥረን መቆየትን እንመርጣለን። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ትዕቢትም ነው። ሥራ ከወንድማችን የመብለጫ ማሳያ ነው። በዚህም ኢትዮጵያችን የሥራችን እርሱም የትዕቢት ውጤት ናት። አሁን ያለንበት ደረጃ የዚህ የትዕቢት ማሳያ ነው።



ትዕቢት ደግሞ ሁልጊዜ ውድቀት ይከተለዋል። ትዕቢት ባለበት ሁሉ ውድቀት ጠፍቶ አያውቅም። የዛሬይቷ ኢትዮጵያ የዚህ ውጤት ናት።



ገዱ አንዳርጋቸው ሥራዓተ መንግስቱን ብቻ አይደለም የተቃወመው። እኛን ኢትዮጵያኖችንም እንጂ። የኛንም ትዕቢት፣ የውድቀታችን መሠረትንም ጭምር ነው የገለጠው።



ወገኖቼ ማንም ራሱን በትህትና ዝቅ ለማድረግ ካላሰበ በቀር ከፍ አይልም። ትልልቅ ስኬቶች ባሉበት ቦታ ሁሉ ትህትና አለ። ይሄን ቃል ፈትኑት። ሳትቸኩሉ፣ ሳትጣደፉ ፈትሹት። ትህትናንን ከፍታ ይከተለዋል።


 
 
 
Writer: Mulualem Getachew
Mulualem Getachew
Aug 16
4 min read





ከምቸገርበት ነገር አንዱ ባህሪዬ ነው። የሆነ ሰሞን በፈጣሪ አምናለሁ። ፈጽሞ ከእርሱ ውጪ ልሰጠው በማልችለው ማዳን ከራሴ ጉድጓድ ጎትቶ ያወጣኛል። በዛ ሰሞን እንደእኔ በእርሱ የሚያምን የሌለ እስኪመስል ድረስ በእርሱ እደገፋለሁ። የሌሎችን ጥርጣሬ እና እንደ እኔ የእርሱን የማዳን እጅ ያላዩትን መኮነን ጭምር ያምረኛል። የሰከረ ሰው ዓይነት ባህሪ።



ከዛ ደግሞ ይመጣል። ኖርማል ቀኖች። አሁን አይምሮዬ ምክንያት ይፈልጋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያነበብኳቸው ዓይነት ተአምሮችን አለማየቴን በማሰብ የእርሱን መኖር እጠራጠራለሁ። በዚህ ዓለም በእኔ ዓይን ክፋት እና አደጋ ሊደርስባቸው አይገባም በምላቸው ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና ግፈኛ ላይ በእኔ የጊዜ ሰሌዳ ምንም እርምጃ አለመወሰዱን ስመለከት ደግሞ እምነቴ ተንሸራቶ ለጥርጥር እጅ ይሰጣል። ምንም እንኳን እንደ ሙሴ ባህር በበትር ተከፍሎ ባላይም ዝንጀሮ በዝግመተ ለውጥ ሰው ሲሆን ባላየውበት የዳርዊን ሳይንስ ለማመን ይቃጠኛል። በሁለቱ መካከል በማየት ዙሪያ ለውጥ ባይኖረውም።



ይሄ ነኝ እኔ። ምን አልባት ብዙዎቻችን።



መጽሐፉ ቅዱስ ግን አንድ አስገራሚ ነገር ይነግረናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመረጣቸው ሐዋርያት። በዚህ ውስጥ ጴጥሮስ አለ። በዚህ ውስጥ ቶማስ አለ። በዚህ ውስጥ ይሁዳ አለ። በዚህ ውስጥ ያዕቆብ እና ዩሐንስ አሉ። በዚህ ውስጥ ፊልጶስ አለ። በዚህ ውስጥ ናትናኤል አለ። በዚህ ውስጥ ቀራጩ ማቲዎስ አለ። ቀናተኛው ስምዖን በዚህ ውስጥ አለ።



ከአስቆሮቱ ይሁዳ በቀር በእነዚህ መሠረቶች ላይ ነው ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የገነባው። የሁሉም አለቃን ደግሞ ሐዋርያው ጴጥሮስን አደረገ።



ሐዋርያው ጴጥሮስ የክርስቶስን ዋነኛ ሰው የመሆን ዓላማ የተቃወመ በዚህም ሰይጣን የተባለ፣ ለማመንም ለመካድም የሚቸኩል፣ ከማሰቡ በፊት የሚናገር፣ ሰይፍ አንስቶ የሰው ጆሮ የቆረጠ የነበረ ነው። ከሁሉም ግን ክርስቶስን ሁሉም ቢክድህ እንኳ እኔ አልክድህም ባለበት አንደበቱ ፥ ጌታችን በእርኩሶች እጅ ምራቅ እየተተፋበት እያየ ሦስት ጊዜ አላውቀውም ያለ ሐዋርያ ነበር። እነዚህን ተራ ክህደት አድርጋችሁ አትዩት። ቅዱስ ጴጥሮስ ውሃ በእንስራ ሞልቶ ወይን ሲሆን ያየ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን በውሃ ላይ ሲራመድ አይቶ እርሱም የተራመደ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ሙሴ እና ኤልያስ መጥተው አብ ከሰማያት ስለ ጌታችን ሲመሰክሩ የተመለከተ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ በሰይፍ የቆረጠው ጆሮ በሰከንዶች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ ተተክቶ እንደ ድሮ ያለ ጆሮ ሲሆን ያየ ነው። ዓይን ከጭቃ እንደገና ጌታችን ሲሰራ ያየ ነው። የሞተው አልአዛር ሲነሳ ያየ ነው።



ይሄን ሁሉ ያየ ሐዋርያው ጴጥሮስ ነው የካደው።



ግን በመጨረሻ የቤተክርስቲያን አለቃ ተደረገ። ማናችንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ያየውን ያህል አላየንም። ጌታችን የሰራቸው ሥራዎች ባህር ቀለም ቢሆን ምድር ብራና አይበቃውም ብሎ ሐዋርያው ዮሐንስ የተናገረለት ነው። ያንን ሁሉ ተዓምራት አይቶ ነው ፍርሃቱን ማሸነፍ አቅቶት የካደው። የፍቅርን ጌታ በመሰቃያው ሰዓት አላውቅህም አለው። ሐዋርያውን ለመክሰስ አይደለም። ይልቁንስ ይሄን ሁሉ ድካም የጻፈለን ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንዱ አስደናቂ ባህሪው የሰዎችን ድካም ላለመጻፍ መጠንቀቁ ነው።



ለምሳሌ ዩሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት ላይ ያለችው ሴት ብዙ ድካም ያላት ሴት እንደሆነች ይጠቁመናል። ግን ከመጠቆም ውጪ ድካሞቿን ዘርዝሮ አልነገረንም። እርሷ እና ጌታዋ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መግባባታቸውን ከመንገር ውጪ። ይሄ እጅግ ብዙ ቦታ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምታዩት መገለጫ (feature) ነው። የመረጣቸውን ሰዎች ድካም ግን በግልጽ ይዘረዝራል። እነሱን በአደባባይ ያሰጣቸዋል። ምክንያቱም ማንም ሊደርስበት ከማይችለው የክብር ማማ ላይ አስቀምጧቸዋልና። ከዛ በላይ እነሱ ለእኛ የመዳን ምልክቶች ናቸው። የሐዋርያው ጴጥሮስ ታሪክ እኔ ነኝ። ብዙዎቻችን ነን።




ኑ አይዟችሁ። የቤቴን መሠረት ይሄን ሁሉ በፈጸመ ግን በመጨረሻ በተመለሰ ላይ ነው የገነባውት እያለን ነው።



ትላንት ድንቅ ተደርጎልን፣ ከምንም አንስቶን ዛሬ ግን በሰው ፊት በአደባባይ እንክደዋለን። ዛሬ አዋቂ ስንባል እርሱ ማፈሪያችን ይሆናል። ዛሬ ምክንያታዊ ስንባል እርሱ እንደ ተረት ዝቅ አለብን። ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ኑ ይለናል። ጌታችን ዛሬ በስም እየጠራ “ትወደኛለህ ወይ?” ይለናል። ምክንያቱም እርሱ ፍቅር ነው።



ሐዋርያው ቶማስንም ተመልከቱ። ሌላ የቤተክርስቲያን መሠረትን። ቶማስ መጠራጠር ሃይማኖቱ ጭምር ነበር። የአልአዛርን ከአራት ቀን በኋላ ከሞት መነሳት ያየ ሐዋርያው ቶማስ አልአዛርን ከሞት ያስነሳው ጌታን ትንሳኤ ግን አላምንም አለ። ባይም አላምንም አለ። መንካት መዳሰስ አለብኝ አለ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ እርሱ እና ሌሎች ባሉበት ተገኝቶ “አሁንስ አታምንም?” አላለውም። ይልቁንስ ቶማስ እንደፈለገው “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።” ዮሐ 20፥27።



እኛ እንደዚህ ዓይነቱን ተጠራጣሪ የመታገስ አቅም ይኖረን ይሆን?



እጅግ ብዙዎቻችን ወይም ሁላችንም ሐዋርያው ቶማስ ካየው አንድ ፐርሰንቱን ተዓምር እስከዛሬ አላየንም። ይሄን ሁሉ ያየ ሐዋርያው ቶማስ ግን አስሩ የነገሩትን ትንሳኤ አላምንም አለ። ነገር በሁለት ምስክር ይጸናል ይባላል። እርሱ ግን የአስር ሐዋርያ ምስክር አልቀበልም አለ። የሚነገረው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆን እንኳ። የጠራን፣ እንድንከተለው ያዘዘን ሐዋርያው ቶማስን ለቤተክርስቲያን መሠረትነት የመረጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።




ከዚህ በላይ የሚያጽናና ምን ነገር ይኖር ይሆን?



መጠራጠራችን እርሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር አይረታውም።



ሐዋርያው ያዕቆብ እና ዮሐንስንም ነጎድጓዶች ይላቸዋል መጽሐፍ ቅዱስ። ምክንያቱም የእነርሱን አለማመን የታገሰውን ጌታችንን ሳያስተውሉ ፥ የእነርሱን ስለ ጌታችን ትምህርት ያላመኑትን ሰዎች ከሰማይ እሳት ወርዶ እንዲያጠፋቸው በቅናት ስለጠየቁ ነበር። እነርሱ እኮ ጌታ በምድር ሊነግስ ይችላል ብለው በእናታቸው በኩል በቀኝ እና በግራ ለመንገስ ያስጠየቁ ሐዋርያት ነበሩ። እነዚህ ደመ ቁጦዎች ሐዋርያት ናቸው ብዙዎችን ወደ ጌታ እንዲስቡ የተመረጡት።



ቀራጩ ሐዋርያው ማቲዎስስ። ከሮማውያን ጋር የሚተባበር እና በአይሁድ ማህበረሰብ የክፋት፣ የስግብግብነት መጠሪያ የሆነ የታክስ ቀራጭነት ሥራን የሚሰራ ሰው ነው ለቤተክርስቲያን መሠረትነት የተመረጠው። ይሄ ቀላል ከመሰላችሁ ፥ “ዛሬ ቤተክርስቲያን ኮሚቴ ሥራ ውስጥ እነዚህ ሰዎች በሰው ቢጠቆሙ ማነው የሚመርጣቸው?” የሚለውን ብቻ አስቡት። እነዚህን አይደለም ለቤተክርስቲያን ሐዋርያነት ለተራ አገልግሎት የሚመርጥ ክርስቲያን ይኖራል? በፍጹም።



ጭፈራ ቤት ያለው ሰው መጥቶ ቀን ቀን ቤተክርስቲያንን ላገልግል ቢል ብዙ ምዕመን አያጉረመርምም? ማነው ይሄን ግለሰብ የሚታገሰው? ጭፈራ ቤትህን ሳትዘጋ አትችልም አይደል የምንለው?



ቅዱስ ጳውሎስንም ተመልከቱ። እስጢፋኖስን በማስገደል የተባበረ፣ ክርስቲያኖችን ያሳደደ ነበር። ቢያንስ የቅዱስ ጳውሎስ የሚለየው ለሐዋርያነት ከመጠራቱ በፊት ያደረጋቸው ተግባሮች ስለሆኑ ነው። ግን ደግሞ ሐዋርያ ከሆነ በኋላ ሳይቀር በትዕቢት እንዳይቸገር የወገብ ከባድ ውጋት ተሰጠው። በዚህም ከትዕቢት ነጻ እንዳልሆነ ራሱ ነገረን። ጥላው ሌሎች በሽተኞችን የሚፈውሰው ቅዱስ ጳውሎስ ፥ እርሱ ግን በከፍተኛ የወገብ ውጋት በሽተኛ ነበር። ፈውስም አይደረግልህም ተባለ።



በመጨረሻ የምትረዱት ነገር ቢኖር ክርስትና የየዕለት ሕይወት እውነት ነው። ጌታችን ያቀናል። ደካሞች እንደሆንን ያቀናል። እኛ በራሳችን እንደምናፍር እርሱ ልጆቼ ብሎን በመጥራቱ አያፍርም። እግዚአብሔር ሆን ብሎ ነው እኛ ደካሞቹን የጠራን።



 ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤” 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፥27። የኛ ድካም የእርሱን ቸርነት አያስቆመውም። ትላንት ወድቀን ለምነነው ከተቀበልን በኋላ ዛሬ ከርሱ ርቀን ብንሄድም እርሱ እንደ ሰው አይደለም። እርሱ እንደ እኛም አይደለም። ለእኛ እራሱ ይሄ ባህሪያችን አሳፋሪ እና ራሳችንን ይቅር ለማለት ልንቸገር እንችላለን። እርሱ ግን ተጎሳቁለን መምጣታችንን አይቶ ከሩቅ ሮጦ ይቀበለናል። በዚህ እርግጠኛ ሁኑ።



የይሁዳም የሚነግረን ነገር አለ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገ በሠላሳ ብር አሳልፎ እንደሚሸጠው እያወቀ ነው ይሁዳን የመረጠው። ከክህደቱም እንደማይመለስ እያወቀ ነው ከአስራ ሁለቱ አንዱ ያደረገው። እግሩን ያጠበው። ከማዕዱ አንስቶ ያጎረሰው። ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ የቀረብን የመሰለን ሰዎች ይሁዳን እናስብ። ከይሁዳ በላይ ማናችንም አልቀረብንም። የይሁዳን ያህል ጌታችንን አናውቀውም። በሁሉም ረገደ እርሱ ቅርብ ነበር። ቅርበቱ ግን ጌታችንን በገንዘብ አሳልፎ ላለመስጠት አልጠበቀውም። ቅርበቱ ከመጥፋት አላዳነውም።



ያልጠፋነው በምህረቱ ብዛት መሆኑን እናስተውል። በኃይለኛው በእግዚአብሔር እጅ እንዳንወድቅ ምህረቱን አናሹፍበት። ግን ደግሞ ኃጢአታችንም ወደ እርሱ ላለመምጣት እንቅፋት እንዲሆንብን አንፍቀድለት። እርሱ በድካማችን የሚሰራ ኃያል ነውና።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

​

Designed and built by Abel

​

bottom of page