- Mulualem Getachew
- Oct 6
- 3 min read

አላን ዋትስ ስለ ካርል ዩንግ በጻፈው መጣጥፍ ላይ ከራሱ ጋር የታረቀ ሰው በዚህ ዓለም ላይ ካርል ዩንግ ነበረ ይላል። ዩንግ ራሱ ላይ ያሉትን ሕጸጾች እና ድካሞች በይሁንታ ያለማፈር የተቀበለ ሰው ነበር። በተለይ በ1950ዎቹ ሲዊዘርላንድ ላይ ለቀሳውስት ያደረገው ንግግሩ ዩንግ የሰውን ተፈጥሮ በጥልቀት መረዳቱን የሚያሳይ ነበር።
ሰዎች ለራሳቸው ጥቅም እንደሆነ እስካወቁ ድረስ ምንም ክፋትን በሰዎች ላይ የማድረግ አቅም አላቸው። የሰው ልጆች በጎ ላደረገላቸው እና መልካሙን ነገር ለሰጣቸው ሳይቀር የእነሱ ሕይወት የሚሰምር ከመሰላቸው ወይም በጣም የሚፈልጉት ነገር እንዲሆንላቸው የወደዱ እንደሆነ ክፋትን ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው። ለዚህ ነው ለክርስቲያኖች የክርስቶስ ሕይወት አስገራሚ የሆነው። ምክንያቱም በበርባን ምትክ ንጹሁ ክርስቶስ ለመሞት ፈቅዷልና። በቅርብ አንድ ወዳጄ ስለ ልጁ ነገረኝ። ልጁ ገና አራት እና አምስት ዓመቷ ነው። በቤቱ ውስጥ እርሷ ነበረች እንደ እንቁ የምትታየው። ነገር ግን አዲስ ልጅ ሲወለድ የቤተሰቡ ትኩረት ሁሉ ወደ ሕጻኑ ሆነ። ከዛ ይህች ሕጻን ልጅ አዲስ የተወለደውን ልጅ ጠላችው። መምታት ጭምር ፈለገች። እኔን በጣም የገረመኝ የአንዲት ነፍስ ያላወቀች ልጅ ሪያክሽን ራሱ ከፍቅር ይልቅ ቅናት መሆኑ ነው። በዚህ ዓለም ላይ ገና ክፍትን ያልተማረች ሕጻን ልጅ ተፈጥሮዋ የነገራት አዲስ የመጣው ልጅ ትኩረቱን ስለወሰደ ጠላትሽ ነው የሚል ነው። ይሄ የሚነግረን የሰው ልጅ ጠባዩ እንስሳዊነት ሲሆን፤ ተፈጥሮውም እስካልተገራ ድረስ ከበጎነት ይልቅ ለክፋት የተመቸ መሆኑን ነው።
ለዚህ ነው ሰው የራሱን ጥቅም ከሚያጣ፤ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት እና መጉዳት ምርጫው የሚሆነው። ይሄን ለክፋት የተመቸን ማንነታችንን እውቅና ካልሰጠነው እና በፍጹም ሰብአዊ አስተሳሰቦች እና ክርስትናዊ ፍቅር ካልገራነው በቀር ሰው አውሬ ነው። ክርስቶስን የተለየ የሚያደርገውም ይሄ ነው። ተፈጥሮ ለመልካም ነገሮች ያደላ ነው። ፍጹም ስለራሱ ሕመም ብቻ ማሰብ በሚገባው የመስቀል ሰዓት ያሰበው ከራሱ ይልቅ ስለ ሰቀሉት ምህረትን ነበር። ከዛም ለሚወዳት እናቱ ልጅ እና ተንከባካቢን መስጠት ነበር። ከዛም በዛ መራራ ሰዓት አንተም እንደኛው ወንጀለኛ ነህ እያለ በሚከሰው አላዋቂ ከመናደድ እና ከመራገም ይልቅ በሌላኛው ጎኑ ሆኖ አንተ ልዩ ነህ ያለውን ያን ሰው የገነት ቁልፍን መስጠት ነበር ሥራው ያደረገው። ለክፋት ፈጽሞ አልመለሰም። ከክፋት ጋር ድርድር ውስጥ አልገባም። ፍርድን ሊሰጥ ከማይችል ከጲላጦስ ፊት አለፈለፈም። ሦስቴ የከሰሰውን ሰው ከሰስከኝ ብሎ አላወራውም። ይሄ ሁሉ ክፋት ምንም አላስደነቀውም።
የበሰሉ ሰዎች የሚደርሱበት ደረጃ ያ ይመስለኛል። በሰው ክፋት አለመደነቅ። ከሰው ልጆች ሞራል እና ከፍታን አለመጠበቅ። የሰው ልጅ ተፈጥሮ በሆኑ ጉዳዮች ጉድ አለማለት። ያ ብቻ ሳይሆን እነርሱም ለዛ ክፋት ብቁ መሆናቸውን ማወቅ። ለጴጥሮስ መመለስ ትልቁ አስተዋጽኦ ክርስቶስ በርሱ መክዳት አለመደነቁ ነው። የሰው ልጅ የሚድን ከመሰለው ሁሉን ትቶ የተከተለውን መልሶ ይክደዋል።
ተመልከቱ አሜሪካ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጉድ። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ክርስትናን የሚያራምድ ነው። አሜሪካ ውስጥ በባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ እንደዚህ ጊዜ ስደተኞች ባይተዋርነት ተሰምቷቸው አያውቅም። ጥቁር እና ስደተኛ ፍጹም ወደ ሆነ ባይተዋርነት እየተገፉ ያለበት ዘመን ላይ ነን። አንገታቸው ላይ መስቀል ያደረጉ እና የቻርሊ ከርክን መገደል አስመልክቶ ወደ ቤተክርስቲያን እየጎረፈ ያለ የትረምፕ ደጋፊዎች ናቸው ስልጣን ላይ ያሉት። ከክርስትና በላይ ለስደተኞች መጨነቅ ያለበት ሃይማኖት መኖር ያለበት አይመስለኝም። ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰደደ ነበር። ለስደተኞች ፍጹም ርህራሄ እንድናሳይ የተጋበዝንበት ሃይማኖት ነበር። ክርስትና መሠረቱ፣ ምሰሶው፣ ጣሪያው ሁሉ ምስኪኖችን እና መሄጃ የሌላቸውን በመቀበል ላይ የተመሰረተ ነው። ቤተክርስቲያን ለዚህ ነው የስደተኞች ቤት የምትባለው። ተሰደው የመጡ ሰዎች የሚጠለዩት የክርስቶስ ቤት ውስጥ ነው።
አሁን ግን ክርስትና የሰው ክፋትን ሊገራው ይቅርና የመጨቆኛ መሳሪያ ሆኖ መጥቷል። ኃጢያተኞች ቤት እየሄደ በአመንዝራዋ እንባ እግሮቹ የታጠበ፣ በቀራጩ ቤት እራት የበላ፣ ከወንበዴው ጋር ንግግር ያደረገ፣ ባል እየቀያየረ ከኖረች ሴት ጋር ለማውራት በጠራራ ፀሐይ ወንዝ ዳር ቁጭ ብሎ የጠበቀን አምላክ የምናመልክ እና የምንከተል ሰዎች ፈጽሞ ልንሆን አንችልም፤ አሁን የምናደርገውን እያደረግን። ይሄ የክርስትና ተቃራኒ ነው። ይሄ ፖለቲካ እንጂ ክርስትና፣ ሃይማኖት ሊሆን አይችልም። ለባህሪያችን የሚስማማ ነገር እያደረግን ክርስቲያን ተብለን ልንጠራ አንችልም።
ለዚህ ነው ዩንግ በዚህ ስብከቱ ለእነዛ ቀሳውስት የክርስትና መሠረቱ በራሳችን ውስጥ ያለውን በርባንን፣ ያን ወንበዴ፣ ያን ዘረኛ የሆነውን እና ቡድነኝነት የሚስማማውን ተፈጥሮአችንን መቀበል ነው ያለው። በርሱ ማፈር ሳይሆን መቀበል፣ በውስጣችን እንደሚኖር ማወቅ ነው ያለብን። ምክንያቱም ሰዎች እንደዛ ነን። ያንን በውስጣችን ያለው የክፋት ጥግ ስናውቅ ሌላው ላይ የመፍረድ አቅም አይኖረንም። ሌሎችንም ከፍ ወዳለ ስብዕና እና እርከን ማውጣት እንችላለን። ያኔ ብቻ ራሳችንን ወደ ማወቅ እና ክርስቶሳዊ ፍቅርን ወደ መላበስ ማደግ እንችላለን።
አረመኔያዊ ነገሮች ሊደርሱብን የፈቀድን ካልሆንን የክርስቶስን ፍቅር መሸከም የምንችል አይመስለኝም። ምክንያቱም መልካም ካልሆንን የሰዎች ክፋትን መቋቋም እንችላለን። የሰዎች ክፋትን ስናውቅ ነው ደግሞ እውነተኛ መልካም መሆን የምንችለው። ምክንያቱም በጎ እንደሚሰጠን እያመንን መልካም ካደረግን’ማ ከተፈጥሮአችን ተቃራኒ የሆነን እምነት አልተከተልም። ክፋት እና መከዳት እንደሚጠብቀን አምነን መልካምነትን የመረጥን ከሆንን ብቻ ነው በመርህ እየተጓዝን ያለነው። በሰው ልጆች እንደምንጎዳ አውቀን ነው ፍቅርን የመረጥነው። ባጎረስን እንደምንነከስ በፍጹም ጠብቀን ነው እጃችንን በክፋት አፍ ውስጥ የከተትነው። ለምን? ይሄ ምርጫ ነው። ምርጫችን በጨለማው ዓለም ውስጥ ጨለማ ላለመሆን ነው። በጨለማው ዓለም ውስጥ ላለመታየት የፈለገ ሰው እርሱም ጨለማ ነው መሆን ያለበት። ከጨለማው ጋር የተባበረ በጨለማው አይጎዳም። የጨለማውን ጨለማነት በመልካም ባህሪ እና በፍቅር ለመለወጥ የፈለጉ ሰዎች ብቻ በዚህ ዓለም ክርስቲያን ተብለው ይጠራሉ። ከዓለም እና ከተፈጥሮአችን ግብዣ ውጪ ክፋትን በክፋት ላለመመለስ ወስነዋልና። እንደሚጠቁ እና እንደሚከሰሱ እያወቁ ራሳቸውን ለሚበልጠው የስብዕና ማማ አሳልፈው ሰጥተዋል። ከርሱ የመከዳት የውስጥ ሕመም እና የሀሰት ክስ ስቅላት ቁስል ጋር አሁን ተባብረው ፥ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ለመተባበር የመርህ ውሳኔ አድርገዋል። በስም ሳይሆን በተግባር ክርስቶስን ለመምሰል መጣር የእነዚህ ራስን እና ሰውን የመረዳት ጉዞ እና ከዛ ተፈጥሮአችን በተቃራኒ የመጓዝ ውሳኔ ነው።