top of page
Search
Writer's picture: Mulualem GetachewMulualem Getachew

እስከዛሬ ከጻፍኳቸው ጉዳዮች ሁሉ በጥልቀት የማውቀው ይሄን የዛሬን ጉዳይ ነው። ይሄን በተግባር አውቀዋለው።በየቀኑ ኖሬዋለው። ማንም በዚህ ጉዳይ በልምድ እና እውቀት ማነስ አይከሰኝም። ሌሎች ሰዎች እንዳለኝ ካላስተዋሉት፣ስለሌለኝ ሳይሆን የበለጠ ፥ ከእነሱ ግምት በላይ ስላለኝ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ስጽፍ ከራሴ ነው። ከውስጤ ነው። ከጥልቅልምዴ ነው። ጄ ኬ ቼስተርተን “በዚህ ምድር ላይ አንድ ስብከት ብቻ ስበክ ብባል ስለእሱ ነው የምሰብከው” ያለለት ነው።

 

ግን እሱን የለኝም የሚሉት የበለጠ አላቸው። አለኝ የሚሉትም ምን አልባት የበለጠ እንዳላቸው ለመደበቅ ይሆናል። ያለንሰዎች ያላቸውን ሰዎች በቀላሉ እና በፍጥነት እናውቃለን። ከዛ እንጠላቸዋለን። እንደማያውቁት ለሚክዱት ከማንም በላይ ይታመንላቸዋል።

 

ትዕቢት። አዎ ፥ ስለ ትዕቢት ነው የማወራችሁ።

 

ትዕቢት ብቸኛ ዳይብሎስን የሚቀድመው ኃጢአት ነው። ትዕቢት ነው ሰይጣንን ሰይጣን ያደረገው። (ኢሳ 14፥13)። ቅዱስ አውግስጢኖስ እንዳለው ትዕቢት መላዕክትን ሰይጣን አደረገ ፥ ትህትና ደግሞ የወደቀውን የሰው ልጅ መላዕክ አደረገ። ለዚህ ነው ጠቢበኛው “ትዕቢት ጥፋትን ፥ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድመዋል።” ያለን። ምሳሌ 16፥18። የወደቀ ስልጣኔን አሳዩኝ ፥ ያን ስልጣኔ እንዴት ትዕቢት እንደቀደመው በርግጠኝነት አሳያችዋለው። መለያየት ያለበት ቦታንአሳዩኝ ፥ ያን መለያየት ምን እንደቀደመው ነግራችዋለው። ትዕቢት የለንም በሚሉት ዘንድ አብዛታ አለች።  የወደቁ ሥርዓተ መንግስታትን ዘርዝሩልኝ ትዕቢት ዙፋናቸው እንደነበረ በርግጠኝነት አሳያችዋለው። ታላላቅ ስህተቶችን ንገሩኝ ፥ የእነሱ ሁሉ ሥር ትዕቢት ነበረ። ትዕቢት ባለበት ምንም ነገር ጸንቶ አይቆምም።

 

ወድቆ የቀረን ሰው አሳዩኝ ትዕቢትን አሳያችዋለው። “ትዕቢት ነው ለምን ወደኩ? እንዴት ወደኩ?” ብሎ የሚያላዝነው። ትህትና ግን መቆም ራሱ በእግዚአብሔር እርዳታ እንደሆነ ስለሚያውቅ ለመነሳት እጁን ይዘረጋል፣ “ጠላቴ ሆይ ብወድቅ ደስ አይበልሽ እነሳለሁ ፥ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው” ብሎ በአምላኩ ይመካል። ትዕቢት ግን ከመነሳት ይልቅ መውደቁን ለመሸፈን አቅሙን ያባክናል።

 

 

በትዕቢት ፊት እግዚአብሔር ዝም አይልም። ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለን “ትዕቢተኞችን ይቃወማል” 1ጴጥ 5፥5።ምክንያቱም ትዕቢት ከውስጥ፣ ከሰው ልብ ነውና የሚፈልቀው። ማርቆስ 7፥21። ትዕቢት ፍጹም የእግዚአብሔር ተቃራኒ ነው። “የትዕቢት መርዝ እጅግ መርዛማ ከመሆኑ የተነሳ የመንፈስ ፍሬዎችን ብቻ አይደለም የሚመርዘው ፥ ክፋትን ሳይቀር ይመርዛል (Pride is a poison so very poisonous that it not only poisons the virtues; it even poisons the other vices)።” ትዕቢት ዕውርነትን ሳይቀር የበለጠ የሚያሳውር ጨለማ ነው።

 

በጣም የምትጠሉት ነገር ምንድነው?

 

እኔ በጣም የምጠላውን ነገር ነግራችዋለሁ። ከተራ ነገር ልጀምር። የቦካ ቅቤ እና የቦካ ቅቤ የገባበት ምግብ በጣምነው የምጠላው፣ መጥላት ብቻ አይደለም ሽታውን ካሸተትኩኝ ራሱ ያቅለሸልሸኛል። ያለበት መቅረብ አልፈልግም። ይሄግን የግል ምርጫዬ ነው። ሌላው ግን ለልጆቹ ግድ የሌለው አባት ሳይ ደሜ ይፈላል፣ ወደዚህ ዓለም ወዶ አምጥቶአቸውፍቅርን የማይሰጣቸው፣ ወደ ቀናው መንገድ ልጆቹን ለመምራት ጊዜ እንደሌለው አባት የሚያናደኝ ነገር የለም።

 

በሚገርም ሁኔታ ግን እኔም ሆነ እናንተ እግዚአብሔር ትዕቢትን በሚጠላበት መጠን ምንም ነገር ጠልተን አናውቅም።በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ትዕቢትን በሚጠየፍበት መጠን የተጠቀሰ ምንም ሌላ ኃጢአት የለም።“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል” ይላሉ ሐዋርያው ያዕቆብም (4፥6) ሐዋርያው ጴጥሮስም (5፥5) በመልዕክታቸው። እኛ ግን አንድ ሰው ትዕቢተኛ ነኝ ብሎ ሲነግረን የምንደነግጠው ከብዙ ዓይነት ኃጢአቶች ባነሰ ነው። ለምሳሌ ይሄን ጹሁፍ “በዝሙት ቁጥር አንድ ነኝ፣ በቃ ስሜቴን መቆጣጠር አልችልም ፥ ከሁሉም ሴቶች ጋር መዳራት እፈልጋለሁ” ብዬ ብጀምር ብዙዎቻችሁ ከመደንገጥ አልፋችሁ ሴቶች ከሆናችሁ እኔ ጋር ድጋሚ ላለመቅረብ ትጠነቀቃላችሁ። ዳይብሎስን ብትጠይቁት ግን ሁሉን ዓይነት ፈተና እና ፍትወት ከእናንተ ወስዶ ትዕቢትን ብቻ ቢሰጣችሁ ረክቶ ይቀመጣል። በመጽሐፉ ቅዱስ እና በቅዱሳን አንደበት ከእግዝአብሔር ፍጹም ተቃራኒ ሆኖ የተሳለ እንደ ትዕቢት ምንም ነገር የለም። በትዕቢት ፊት እግዚአብሔር ሁልጊዜ የቁጣ እጁን ያነሳል።

 

የትዕቢት ክፋት ራሱን ስታንዳርድ (the only test and supreme standard) ማድረጉ ነው። ለአንድ ነገር ጥሩ ወይም መጥፎ መሆን ለትዕቢተኛ ሰው ስታንዳርዱ እርሱ እንጂ እውነት አይደለም። ጥሩ መስሎ፣ ተውቦ መታየት መፈለግ ወይም ምርጥ ነገር መስራትን መናፈቅ ትዕቢት አይደለም ስታንዳርዱ እኛ እስካልሆንን ድረስ። ይልቁስ ለትዕቢት የእርሱ ስብዕና ነው የሁሉ ነገር መስፈርት እና ደረጃ። ቼስተርተን እንዳለን ለትዕቢተኛ ማንነቱ በጣም ግዙፍ ስለሆነበት ሕይወትን በትልቁ መስፈርት አይመዝንም፤ በመጨረሻ ግን በጣም በትንሹ ነገር መዝኖ እናገኛዋለን (The pride feels himself too larage to measure life by the laragest things; and ends by measuring it by the smallest thing of all)።

 

ጄ ኬ ቼስተርተን የትዕቢት ትልቁ መገለጫ በራስ መደሰት መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በራሳችሁ ፈጽሞ እንዳትደሰቱ። በዳንስ ተደሰቱ፣  ከፈለጋችሁ በቲያትር ደስ ይበላችሁ ወይም በጃዝ እና ኮክቴል ተደሰቱ። የምትደሰቱበት ነገር ካጣችሁ እና የግድ ካላችሁ በናይት ክለብ ተደሰቱ፣ በመዳራት ተደሰቱ፣ በስርቆት ተደሰቱ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ባሉት ወንጀሎች ሁሉ ተደሰቱ፤ ግን አደራ ፥ አደራ በራሳችሁ መደሰትን እንዳትማሩ።”

 

በራሱ መደሰት የጀመረ ሰው መቼም፣ መቼም ከቅዱስ ጳውሎስ ጌታ ጋር አይገናኛም። እስጢፋኖስን የሚያህል ጻድቅ ገድለን እንኳ በዙፋኑ ያለውን ጌታችንን ማግኘት እንችል ይሆናል። ዓለም ላይ ያለውን ወንጀል ሁሉ ፈጽመን በመጨረሻ ፈያታዊ ዘየማን የመሆን ዕድል አናጣም ይሆናል። ከሰባ በላይ የሰው ልጆችን ቀርጥፈን በልተን የድንግል ማርያምን ርሕራሔ እንደ በላየ ሰብ ላንነፈግ እንችላለን። ግን በራሳችሁ ተደሰቱ ፥ ከመስቀሉ ጌታ ጋር መቼም ሕብረት አይኖረንም።

 

በቅርብ ካነበብኩት ታሪክ ነው። ከመካከላቸው አንዱ ምንም ዓይነት ማህበራዊ ሚዲያ እንደማይጠቀም፣ በኢንስታግራም ላይም ምንም ፎቶ እንደማይለጥፍ በመናገር “ማህበራዊ ሚዲያ ሁሉ እኔ እኔ የማለት እና ስለራስ የመጎረር መድረክ ነው ፥ እኔን በዚህ ደረጃ ወርጄ አታገኙኝም” አላቸው ጓደኞቹን። አንዱ ጓደኛው ረጋ ብሎ “ኢንስታግራም አለመጠቀምህ ከሌሎች የተሻልክ እንደሆንክ እንዲሰማህ አድርጓል ወይስ እንደእነሱ አለመሆንህ የኩራት ስሜት እንዲሰማህ አድርጓል?” ብሎ ጠየቀው።

ልጁ ግን ትዕቢት ያልጸናበት ነበርና እየገባበት ካለው የዝቅታ ጉድጓድ የበለጠ ሳይወርድ ወዲያው ቆመ። “ዋው!!! ዋው! ሳላውቀው ለካ እንደ ፈሪሳዊው ሆኛለው። በውስጤ ‘እንደእነሱ አይደለውም’ እያልኩኝ ነበር።” አለ። ማርከስ አርሊየስ"ከሁሉ የከፋው ትዕቢት ስለትህትናችን መጎረር ነው" ይላል። ከሁሉ የከፋው ትዕቢት በውስጣችን “እንደእነዛ ያላደረገን፣ እንደእነሱ ስላልሆንኩኝ ወይም በስመአብ እኔማ እንዲህ አይደለውም” እያሉ በመልካም ባህሪያችን መጎረር ነው።  ለዛ ነው ዳይብሎስ የሰጠንን ትዕቢት እስከተቀበልን ድረስ ፥ ጽድቅን እና ትሩፋትን እንድንሰራ ሳይቀር የሚያግዘን። ሰይጣን ክርስቶስን ወደ ቤተመቅደስ እንደወሰደው አንርሳ። (ማቴ 4፥5)።

 

 ጆናታን ኤድዋርድ ትዕቢትን “በልብ ውስጥ ያለ አደገኛ ነቀዝ፣ የነፍስ አዋኪ፣ ከክርስቶስ ያለንን ግንኙነት የሚመርዝ፣የሚያመር” ይለዋል። ኤድዋርድ እንዲህ ይላል “ልዩነት ያለበትን ቤተክርስቲያን አሳዩኝ፣ መከፋፈል ያለበትንቤተክርስቲያን አሳዩኝ፣ ጠብ ያለበትን ቤተክርስቲያን አሳዩኝ ፥ እኔ ደግሞ ትዕቢትን አሳያችዋለው።” ትዕቢት ባለችበትልዩነት እንጂ አንድነት፣ ጠብ እንጂ ፍቅር ኖሮ አያውቅም። ድንግል ማርያም ያለችን ይሄን ነው “ትዕቢተኞችንአዋረዳቸው” (ሉቃስ 1፥15)። ሰባት ገዳይ ኃጢአት አሉ፣ ትዕቢትን ግን የሚደርሳት የለም። የሁሉም ወላጅ ናት። ዳይብሎስአንዳች እቅድ ማስፈጸም የማይችልበት ልብ ፥ ትሁት ልብ ብቻ ነው። ጥንብ አንሳን የሞተ ጠረን ከየትምእንደሚጠራው፣ የትዕቢት ሽታ ዳይብሎስን ከየትም ስቦ ይጠራዋል። በዛ ነፍስ ላይም ይሰፍራል። ዳይብሎስ የትኛውንምታላቅ ጽድቅ ብንሰራ ግድ አይሰጠውም ትዕቢተኛ እስከሆን ድረስ።

 

አንድ ጥንታዊ አባት እንዲህ ይላል “የእግዚአብሔርን ሥራ ብትጠይቁኝ፣ የእርሱ ሥራ ይሄ ነው እላችዋለው፦ ትሁታንን ከፍ ማድረግ ፥ ትዕቢተኞችን ደግሞ መበታተን።”  የሰው ልጅ ያለ ትህትና ትዕቢትን ራሱ ማጣጣም አይችልም።


476 views0 comments

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page