top of page



1.  ለራሳችሁ ሥራ አስኪያጅ ተደርጋችሁ ብትሾሙ ምንድነው የምታደርጉት?



ራስሽን እንደ አንድ ለትርፍ እንደተቋቋመ ድርጅት ተመልከቺ። ስምሽ ምህረት ነው እንበል። ምህረት ለምትባት ትርፍ ማምጣት ግዴታዋ ለሆነ ድርጅት፤ የድርጅቱ ቦርድ ሥራ አስኪያጅ አድርጎ ሾመሽ። አሁን ሥራሽ የሚሆነው በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የማይሰራን ነገር ማሶገድ ፥ ትርፍ ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን ማብዛት ነው። መስሪያ ቤት ስለሚሆን ስሜት የለውም። ትርፍ እና ኪሳራን መለካት በጣም ቀላል ነው። ስለዚህ ውሳኔዎችሽ በሜትሪክስ የተለኩ ናቸው። በእኔ አስተዳደር ይሄን መስሪያ ቤት ትርፍ በትርፍ አደርገዋለሁ ብለሽ ተነሳሽ። ግን ደግሞ የረጅም ጊዜ ትርፍ እንጂ የምትፈልጊው ለጊዜው ብቻ ትርፍ አግኝተሽ የአንድ ዓመት ድርጅት ማድረግ አትፈልጊም። ስለዚህ ጠንካራ ሠራተኞችሽን ትንከባከቢያለሽ። ደካማ ሠራተኞሽን በቶሎ ትቀንሺያለሽ። እስቲ ራስሽን እንደዛ ብታስቢ ምንድነው ፈጥነሽ የምታሶግጂው? ምንድነው በብዛት የምታደርጊው? የቱ ነገሮች ናቸው ለረዥም ጊዜ ስኬትሽ ዋጋ ያላቸው?




2. ትኩረትን መጨመር



ልህቀት ማሶገድን ይፈልጋል።



ብዙ ሰዎች በሕይወት ውስጥ የማይገቡበት የቢዝነስ እና የፕሮፌሽን መዓት የለም። ራሳቸውን በሁሉም ዘርፍ መለጠጥ ይወዳሉ። ሁሉም ነገር ትኩረት የሚፈልግ ሲሆን ምንም ነገር ትኩረት አያገኝም። ስኬታችን እሺ ከምንለው ነገሮች በላይ እንቢ በምንላቸው ጉዳዮች የተወሰነ ነው። አስር ነገሮችን ዘርዝሩ። በጣም ለእናንተ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች። ከዛ ውስጥ ሦስቱ ላይ ብቻ አተኩሩ። ሦስቱ ነገሮችን ብቻ ከዛ ውስጥ ለማተኮር ሞክሩ።



3. መዘውሩን አታቁሙት



ማስተላለፍ ሕልምን በጸጥታ የሚገድል ነው።



የምናስተላልፈው ሁሉንም ደረጃዎች አሁኑኑ መውጣት አለብን ብለን ስለምናስብ ነው። ሥራችንን ሁሉ በደረጃ እንክፈለው። አንድ ደረጃ ከዛ ደግሞ ሌላኛውን ደረጃ ለመውጣት እናስብ። ማራቶኑን ሥራ በአንድ እና በሁለት ኪሎ ሜትሮች ከፋፍሉት። ስኬት የሚጀምሩ ሰዎችን ነው የሚሸልመው የሚጠብቁ ሰዎች ሳይሆን።



4. የማንነት ሰርክል



አንተ በዙሪያ የከበቡህ ሰዎች አቭሬጅ ነህ። እኔ ሰዎችን የምለካው ከሚውሉበት አካባቢ በመነሳት ነው። እኛ ማለት ጊዜያችንን የምናሳልፍበት ነን። አካባቢህ ወደፊት መሆን የማትፈልገው ሰዎች ጥርቅም ካልሆነ በፍጥነት ያን ቦታ ለመልቀቅ ሞክር።



ጊዜዬን የምሰጣቸው ሰዎች እጅግ የማክብራቸው ወይም ሊታገዙ የሚችሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። ጊዜዬን እንደማቃጠል የሚቆጨኝ ነገር የለም። አዕምሮዬን እና መንፈሴን የማያንጹ ቦታዎች እና ሰዎች ከእኔ ሕይወት ውስጥ በፍጥነት እንዲወጡ ነው የምፈልገው። በዚህ የሚመጣብኝን የወቀሳ ድንጋይ እንደ ሰማዕቱ እስጢፋኖስ በደስታ ነው የምቀበለው።



አስተውሉ፦ ምንም ጥቅም የሌላቸውን ወዳጅነቶች ማሶገድ የዕድገት ሀ ሁ ነው።


5.  አታካብድ



ስኬታማ ሰዎች ነገሮችን ማቅለል የሚወዱ ናቸው። በርግጥ አንዳንድ ነገሮች መቅለል ከሚገባው በላይ አይቀሉም። ራሳችሁን ይሄን ጠይቁ፦ ሕይወትን በማክበድ ነው ወይስ በማቅለል ነው እየኖርኩት ያለውት? ለምሳሌ ሰው ምክር ሳይጠይቀን መምከር ሕይወትን በማክበድ መኖር ማለት ነው። ለዚህ ሰውዬ እኛ ጥቅም ነው ያልነውን ነገር እየጋትነው ነው! በተመሳሳይ በጣም ደክሞን ከባድ ውሳኔዎችን መወሰን ወይም ጠንካራ ውይይቶችን ከፍቅር አጋራችን ወይም ከወዳጆቻችን ጋር ማድረግ ሕይወትን በከባድ ሁኔታ መኖር ማለት ነው። በየቀኑ ቢያንስ ለሰላሳ ደቂቃ ስፖርት መስራት ቀላል ሕይወትን ለረዥም ዘመን ለመኖር መወሰን ነው። አምሽቶ መተኛት የነገውን ቀን መጥፎ በማድረግ ሕይወትን በነጋታው አክብዶ ለመኖር እንደመወሰን ነው።



እስቲ አንድ ነገር ዛሬ ብትቀይሩ ነገን የተሻለ ሊያደርግ የሚችለው ምንድነው?



6. የተግባር ዕቅድ



የጊዜ ገደብ የሌለው ዕቅድ ተራ ሕልም ነው።



ማስፈጸም የማይችል ሰው ሕልመኛ ነው። መፈጸም የሚችሉ ሁሉ የቻሉት ለተግባራቸው የጊዜ ገደብ ስላበጁለት ነው።



7. ማወቅ የምፈልገው የምሞትበትን ቦታ ነው ፥ ወደዚያ ላለመሄድ።



ሁላችንም የሆነ መጥፎ ዝንባሌ አለን። አንዳንድ ሰው ለገንዘብ በጣም ስሱ ልብ አለው። አንዳንድ ሰው ለሴሰኝነት። አንዳንድ ሰው ለክብሩ። አንዳንድ ሰው ለመጠጥ እና ለሱስ። እነዚህ ሰዎች ይሄን ደካማ ጎናቸውን በቶሎ ተረድተው፤ ገደብ ካላበጁለት የሚሞቱበት ቦታ ያ ነው። እንደ ቶሎስቶይ የመሬት ነጋዴ ፥ በቃኝ ማለት አቅቶት መሬት ለመሰብሰብ ሲዳክር ሞተ። አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ ያለበት ቦታ ሁሉ ይገባሉ። ለጥቂት ትርፍ ብለው የሞት ቀጠና ውስጥ ይደንሳሉ። አንዳንድ ሰዎች ለክብራቸው ሲሉ የውርደት ሞት ይሞታሉ። አንዳንድ ሰዎች ሴሰኝነት ድካማቸው ስለሆነ፤ ሴቶች ይጫወቱባቸዋል። የት ነው የምሞተው ብሎ መጠየቅ ወሳኝ ነው። የቱ ነው ደካማ ጎኔ? ስሱ ብልቴ። ወደ ዛ እንዳልሄድ።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Dec 22, 2024
  • 3 min read


ከውድ ጓደኛዬ ጋር በቅርብ በስልክ ስናወራ አንዱ ርዕሳችን ሰዎች ማጣትን እና መተውን የሚወስዱበት መንገድ ነበር። ሰው በተፈጥሮ ማጣት ከማግኘት በላይ ይሰማዋል። አስር ሺ ብር ያጣ ሰው እና 12 ሺ ብር ያገኘ ሰው የሀዘን እና የደስታ መጠናቸው በጣም የተለያየ ነው። ያጣው ሰው የሚያዝነው ካገኘው ሰው ደስታ ይልቅ በብዙ እጥፍ ነው። ለምሳሌ ጠዋት ላይ 10 ሺ ብር አግኝተን ከሰዓት 5 ሺ ብር ብናጣ ፥ እጦታችን ሁሉመናችንን ይቆጣጠረዋል። በዚህም የተነሳ ሰዎች ብዙ ጊዜ በከሰረ ነገር ላይ ተጨማሪ ጊዜያቸውን ማጥፋት ይቀላቸዋል፤ ያ ነገር ላይ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ።

 

የዚህ አንዱ ማሳያ በመጥፎ ግንኙነቶች ውስጥ የምናጠፋው ጊዜ ነው። ቀላል የማይባሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከጎዷቸውሰዎች ጋር ወዳጅነታቸውን ይቀጥላሉ። እየጠቀማቸው ካለ ወዳጅነት ይልቅ፣ የተጣመመን ለማቅናት የሚወስዱት ጊዜ ይበልጣል። ስኬት ማለት ግን የሚሰራን ነገር በብዛት ማድረግ ፥ የማይሰራን ነገር በቶሎ መተው ነው። ለዚህ ደግሞ መጨከን ያስፈልጋል። ግራ የሚያጋቡንን ሰዎች፣ ፍላጎታቸውን በግልጽ ማኖር የከበዳቸውን እና ለወዳጅነታችን ያላቸው አክብሮት እምብዛም የሆኑ ግለሰቦችን መቁረጥ ፥ ስሜታችንን ከመጥቀሙ ባሻግር ለጥሩ ግንኙነቶች የበለጠ ጊዜ እና ዕድል እንድንሰጥ ያደርገናል። ይሄን ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ተፈጥሮአችን ማጣትን ከማግኘት በላይ ይፈራል። ስለዚህ ከተፈጥሮ ተቃራኒ መቆምን ይጠይቃል።

 

በኢኮኖሚክስ opportunity cost የሚባል ጽንሰ ሀሳብ አለ። ይሄ ማለት እያንዳንዱ ድርጊታችን እና ምርጫችን opportunity cost አለው። ከመጥፎ ወይም አሉታዊ ወዳጅነት ጋር የማሳለፍ opportunity cost ከጥሩ ወዳጅነት ጋር የማሳለፍ ነው። ከዛ ሰው ጋር የምናሳልፈው ሰዓት opportunity costቱ ጥሩ መጽሐፍ የማንበብ፣ ስሜታችንን የሚጠግኑ ነገሮችን የመስራት ሊሆን ይችላል። ግን ይሄን በማግኘት አናስበውም። በማክበር፣ በፍቅር፣ በታማኝነት እና በመልካም ቃላት ከጎናችን ሊሆኑ የማይችሉ ሰዎችን መተው (መቁረጥ) አለመቻል የሚያሳጣንን ነገር ማሰብ ለተፈጥሮአችን የተመቸ አስተሳሰብ ይሆናል። በመጥፎ ወዳጅነት ላይ የሚጠፉ እያንዳንዱ ደቂቃዎች ከጥሩ ወዳጅነት ጋር ልናሳልፋቸው የምንችላቸው ሰዓቶች እንደሆኑ ካሰባችሁ ፥ ለውሳኔ አሰጣጥ ይቀለናል።

 

ማቋረጥ፣ መተው፣ መልቀቅ፣ ተስፋ መቁረጥ የሚሉ ቃላት አሉታዊ (negative) ስሜት ብቻ ነው ያላቸው ብዙ ጊዜ። ለዚህ ነው አብረውን የሚሰሩ ሰዎችን፣ ወዳጆቻችንን ወይም የቅርብ ሰዎቻችን መተው እና ከእነሱ ጋር ማቆም የሚያስፈራን። ግን ለጥሩ ነገር ጅማሮ መጥፎ ነገር መቋረጥ ይኖርበታል። የበጎ ነገር መንደርደሪያ የመጥፎ ነገር ማብቂያ ነው። መጥፎ ነገር ወይም ለእነሱ የማይሰራን ነገር መተው ያልቻሉ ሰዎች ለእነሱ የሚሰራ እና በጎ የሚሆንላቸውን ለመጀመር አይችሉም። ቅድም እንዳልኩት በምንም መስክ ያለ ስኬት ማለት የሚሰራን ነገር አብዝቶ መስራት እና የማይሰራን ነገር መተው ነው።

 

በማይሰራ ነገር ላይ የምናጠፋው ጊዜ ከሚሰራ ነገር ላይ እየተቀነሰ እንደሆነ ካልገባን፤ ስለ አለን ውስን ሰዓቶች እና ሪሶርሶች ብዙ ግንዛቤ የለንም ማለት ነው። ሌላው ሰብአዊ ባህሪያችን የታዳጊነት እና ሰዎችን የመቀየር ስነልቦና እንዲኖር አድርጓል። እውነታው ግን ይሄን አስተሳሰብ የምንጠቀመው ሰዎች ከኛ የዓለም እይታ ጋር የሰመረ ባህሪ እንዲኖራቸው ነው። ወዳጆቻችን በራሳቸው ለራሳቸው የሚሆን ባህሪ ይዘው ይሆናል። ጥሩ ጓደኛ፣ ጥሩ ሚስት ወይም ጥሩ ቤተሰብ ላይሆኑ ይችላሉ። ግን እንደዛ የመሆን መብት እንዳላቸው መዘንጋት የለብንም። ብቸኛው ምርጫችን ያ ሰው ለኛ የሚሆን nurturing (ጠጋኝ) ባህሪ እንደሌላቸው መወሰን እና ያን ወዳጅነት ማብቃት ነው። ያ ሰው መጥፎ ስለሆነ ላይሆን ይችላል። ከኛ ጋር የሚስማማ ማንነት ግን እንዲኖረው ስላልመረጠ፤ የታዳጊነት እና ነገ ይሻሻላል የሚለው ባህሪያችን ያን ሰው ከኛ ጋር እንዲስማማ በማድረግ ጊዜያችንን በከንቱ እናጠፋለን።

 

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ከቁጥር 11 ጀምሮ ያለው አፍቃሪው አባት ታሪክ ብዙ አስተማሪ የሕይወት ምክሮች አሉት። አንዱ ትምህርት ልጁ ወደ ሞት ቀጠና እንደሚሄድ እያወቀ ገንዘቡን ከፍሎ ሰጥቶ መሸኘቱ ነው። እኛ ብንሆን የምናደርገውን ተመልከቱ። ፈጽሞ ልጃችንን አደጋ ውስጥ አንከተውም። በሽማግሌ ማስመከር፣ ማሳፈር፣ በጭቅጭቅ እና በኃይል ፍላጎቱን እንዲተው ማድረግ ነው። ያ ምን ያህል ልቡ የከጀለን ሰው ያስቆመዋል? መቼም የሚሰራ ስትራቴጂ ግን አይደለም።


ሲ ኤስ ሉዊስ እንዲህ ይላል “እየሰመጠ ያለን ሰው ለመርዳት እስከሚሰምጥ መታገስ ያስፈልጋል። ያለመስመጥ ትግሉን ሳይጨርስ የእርዳታ እጅ መዘርጋት ፥ ራስን ለአደጋ ማጋለጥ ነው።” በተመሳሳይ ሰዎች የውሳኔያቸውን ክፉ ውጤት በአግባቡ ተመልክተው፣ ሪፍሌክት አድርገው፣ የኛን እርዳታ ለመቀበል እጃቸውን እስከሚዘረጉ ድረስ ለመርዳት እና ለመታደግ መጣር የመማርን እና ፍጹም የመቀየርን ዕድል ነው የሚዘጋው። ለዚህ ነው የታዳጊነት ፓራሹታችንን ያለ ሰዓቱ ላለመክፈት መጠንቀቅ ያለብን።

 

ሰዎች ለምርጫቸው ኃላፊነት የሚወስዱ እና ከዛ የሚማሩ ካልሆኑ፤ ከእነዚህ ሰዎች ጋር የምናሳልፈው ጊዜ ጉዳቱ ለኛ ብቻ አይደለም፤ ለእነዛም ሰዎች የመማርን እና የመለወጥን ዕድል ነው የሚነሳው።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Dec 15, 2024
  • 3 min read




ጥንታዊ መጽሐፎች የሚነግሩን ይሄ ሕይወት ጦርነት እንደሆነ ነው። እስቲ በደንብ ይሄን ለመረዳት አሁን እየተካሄደ ያለ ጦርነት እንመልከት። ለምሳሌ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ናቸው። ጦርነቱ ገና አልተጠናቀቀም። እምብዛም የተገመተው ውጤት አልተገኘም። በጦርነቱ እስካሁን በሁለቱም ወገን ያሉት የጠበቁት አልሆነም። ብዙ ውጊያዎች እስካሁን ተካሂደዋል። ለምሳሌ በአንቶኖቭ ውጊያ፣ በካርኪቪ ውጊያ፣ በኬርሰን ውጊያ፣ በሉናስክ ውጊያ እና ሌሎች ሩሲያ ስታሸንፍ ፥ በቮዝነሰስኪ ውጊያ፣ በሚካሪ ውጊያ፣ በኢርፒን ውጊያ፣ በሰሚ ውጊያ እና ሌሎች ዩክሬን አሸንፋለች። ውጤታቸው ገና ያልታወቁ ውጊያዎች አሉ። እንደቀጠሉ ያሉ። ጦርነቱ በመጨረሻ እንደሁሉም ጦርነቶች አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ ሆኖ ይጠናቀቃል። ግን አሸናፊው የሚፈልገውን በመጨረሻ ላያገኝ ይችላል።



ሕይወትም ልክ እንደዚ ጦርነት ናት። ዩክሬን ከሩሲያ ጎረቤት መሆኗ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ነው። ጎረቤት ሀገርህን መምረጥ አትችልም። በሕይወትም ብዙ ማንመርጣቸው ነገሮች አሉ። ዕድል ብቻ የሆኑ፣ ከኛ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ክስተቶች አሉ። በሚገርም ሁኔታ ግን የሕይወትን ደስታ እና ስኬት የሚወስነው ከማንመርጣቸው ነገሮች በላይ የምንመርጣቸው ጉዳዮች ናቸው።


የመጀመሪያው የሆነውን ነገር እንደሆነ የመቀበል ምርጫ ነው። ሪያሊቲን (ነባራዊ እውነታን) እንዳለ የማየት ምርጫ።



ምንም ሩሲያ ኃያል ብትሆን ሁሉንም ውጊያዎች ማሸነፍ አትችልም። ከሩሲያ አንጻር ዩኩሬን ምንም ትንሽ ብትሆን ሁሉንም ውጊያዎች አትሸነፍም። በኛም ሕይወት ሁሉንም አውደ ውጊያዎች አናሸንፍም። ይሄ ሕይወት የልጅ አውደ ውጊያ አለው፣ የገንዘብ አውደ ውጊያ አለው፣ የጓደኝነት አውደ ውጊያ አለው፣ የጤና አውደ ውጊያ አለው፣ የመንፈሳዊነት አውደ ውጊያ አለው፣ የታዋቂነት እና የማህበረሰባዊ ክብር አውደ ውጊያ አለው፣ የውበት አውደ ውጊያ አለው፣ የጥበብ እና የእውቀት አውደ ውጊያ አሉት፣ የትዳር እና የፍቅር አውደ ውጊያ አሉት፣ የጥሩ ቤተሰብ አውደ ውጊያ አለው፣ የሥራ እና የሙያ አውደ ውጊያ አሉት፣ የመኖሪያ አከባቢ አውደ ውጊያ አለው። እነዚህ እና ሌሎች የውጊያ አውዶች ናቸው በሕይወት ጦርነት ውስጥ ያሉት። ስኬታማ ሕይወት ማለት ሁሉንም አውደ ውጊያዎች ማሸነፍ ማለት አይደለም። እንደዛ የሚያስብ ሁሉ በዚህ የሕይወት ፍልሚያ በፍጥነት ከጫወታ ውጪ የሚሆን ነው። የመጀመሪያው እውነት ሁሉንም ውጊያዎች እንደማናሸንፍ ማወቅ ነው። ሁለተኛው ትልቁ ጥበብ ግን የትኛው ውጊያ ወገብ ሰባሪ እንደሆነ መረዳት ነው። ማለትም በፍጹም መሸነፍ የሌለብን ውጊያ የትኛው ነው የሚለውን ማወቅ። ያን ውጊያ የተሸነፈ ሁሉንም አውደ ውጊያዎች ቢያሸንፍ እንኳ ጦርነቱን ይሸነፋል።



ታላቁ የጦር አዋቂ ሰን ዙ እንዳለው የምርጥ ጄኔራል መለያው ይሄን አውደ ውጊያ ማወቅ ነው። ምርጥ ጄኔራል ብዙ ውጊያዎችን ተሸንፎ እንኳ ጦርነቱን ግን ያሸንፋል። ሁሉም ውጊያዎች ላይ ያለንን አቅም በእኩል መጠን ማፍሰስ አንችልም። ስለዚህ አንዳንዶቹን ለመሸነፍ መተው አለብን። ለአንዳንዶቹ ውጊያዎች ተፈጥሮ ሳይቀር ለሽንፈት የሚሆን ማንነት ሰጥታናለች። ስለዚህ ያንን መቀበል ያስፈልጋል። ዩኩሬን ምርጫዋ ቢሆን ከሩሲያ አጠገብ ጎረቤት ባትሆን ይሻላት ነበር። ግን አንዳንድ ምርጫዎች በዚህ ዓለም ዝግ ናቸው። የመቀበል እና የለውጥ ሚዛን ነው በጦርነቱ አሸናፊ የሚያደርገን።



የሆነን ግለሰብ ሕይወት አይታችሁ የእናንተ ሕይወት እንደዛ ሰው እንዲሆን መመኘት የመጀመሪያው የሽንፈት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆኛ መንገድ ነው። ሰን ዙ እንደሚለው ጦርነትን ሳትዋጋ ማሸነፍ ከቻልክ የምንጊዜም ምርጥ ጄኔራል ነህ። እንዴት ነው ሳትዋጋ የምትሸነፈው? (ለጊዜው ሳንዋጋ ማሸነፉን እንተወው እና!)። እንደ ሌሎች እኛም እንድንሆን በመመኘት። የሕይወት ምርጫችን እኛን ብቻ ነው ሊመስል የሚገባው። ተመሳሳይ መጽሐፍ እያነበቡ፣ ተመሳሳይ ምግብ እየበሉ፣ በተመሳሳይ ቤተሰብ እና በተመሳሳይ አካባቢ ያደጉ ሁለት መንትያ ልጆች ሳይቀር በዚህ ምድር ላይ ለሚገጥማቸው ነገር የሚሰጡት ግብረ መልስ ለየቅል ነው። ልጆች እንደእነ እከሌ ልጆች እንዲሆኑ መመኘት ልጆችን ለሽንፈት ማሰልጠን ነው። ያ ልክ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ተላልፎ እንደመሰጠት ነው። እውነት ነው ሰው በመሆናችን ከሌሎች ጋር የምንጋራቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ግን በዚህ ሕይወት ያለን ጥልቅ ደስታ እና ሀዘንን አስመልክቶ ከማንም ጋር አንጋራም። በጦርነት መኃል አሰቃቂን መከራ ተቀብሎ የሚስቅ እንዳለ ሁሉ ፥ ፌሽታ በበዛበት መኃል የሚቆዝም አለ። “ለምን?” ካልን መልሱ ያን ሰው ብቻ ነው የሚመስለው። ሕይወትን በሌሎች መነጽር ብቻ ለማየት የሚደክም ማንም ምንም ነገርን አጥርቶ የማየት እርከን ላይ አይደርስም።



በመጨረሻም የሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ የማሰብ እና የማሰላሰል አቅሙ ነው። ያም አውደ ውጊያ ነው። በነጻነት የማሰብ እና ነገሮችን በጥልቀት የማየት አቅምን ማዳበር የሕይወትን ጦርነት ለኛ በሚስማማ መልኩ ለማጠናቀቅ ጥቅም አለው። ይሄ ሕይወት የኛ ሕይወት ነው። ባንተ ሕይወት መዝገብ ውስጥ ያለፈው እና ያለው ያንተ ነው። ስለዚህ ኃላፊነት እንውሰድ። ሁሉን ልታሸንፍ አትችልም። ዓላማህ በጦርነቱ ማብቂያ ጫፍ ላይ ስትደርስ ፥ የአንድ ደቂቃ ዕድል ብታገኝ ፥ ይሄ ሕይወት ውብ ነበር ለማለት ነው። በስንፍና ያለፍከው ነገር እንደሌለ በማየት፣ የራስህን ጀርባ እየመታህ "በራሴ ሕይወት ላይ ምርጥ ጄኔራል ነበርኩኝ" ለማለት መብቃት ነው። ምክንያቱም ይሄ ሕይወት ያንተ ሕይወት ነው። ሽንፈቱም ድሉም ያንተ ነው።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page