top of page
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Dec 1, 2024
  • 4 min read




ድሮ የምሰራበት የስፖርት ቦታ በትልቁ “NO PAIN NO GAIN ወይም ካለሕመም ምንም የምታገኘው ነገር የለም!” የሚል የተጻፈ መፈክር ነበረው። አንዳንዴ ወደ ኋላ በመሄድ በሕይወቴ ያሳለፉኳቸውን ከባባድ ጊዜዎችን ለማስታወስ እጥርና “ምናለ እንደ ዛ ባልሆን” ልል ይቃጣኛል ፥ ሕመሙን በማስታወስ። ግን ያ ሀሳብ ከአንዱ የአዕምሮ ክፍሌ ሳያልፍ ነው ያን የመስቀል ጉዞ “እሰይ ሆነ ፥ እሰይ ደረሰብኝ” ብዬ በድጋሚ የማፈቅረው። ብዙዎቻችን ያለ መስቀል ትንሣኤ ፈጽሞ እንደማይኖር አይገለጽልንም። እሁድን የሚናፍቅ ቢኖር አርብን መታገስ ይጠበቅበታል።


ሕመምን የምንታገሰው ጀግና  ፥ ስለሆንን ወይም የተለየ ፍጡር ስለሆንን አይደለም።


እንደሚሞት፣ ለዛውም የመስቀል ሞትን እንደሚሞት ራሱ ጭምር እየተናገረ የመጣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይቀር መስቀሉን በቅርብ ርቀት ሲያየው ፥ “ይሄ ጽዋ ፈቃድህ ቢሆን ከእኔ ይራቅ” ብሎ ጸልዪል። የጌታችን ያልተሰማ ጸሎት ይሄ ብቻ ነበር። “ዋጠው፣ ይሄን ጽዋ ጠጣው” ብሎ አባቱ ጨከነበት። አጽናኞችን ግን ላከለት። እውነተኛ አባት የሚያደርገው ይሄን ነው። የሕመምን ጽዋ ለልጆቹ ያስጎነጫል። እውነተኛም እናት ከዚህ የአባት ጭካኔ ጋር ትስማማለች። ምክንያቱም የልጇን ትንሣኤ ትፈልጋለች እና። ልጇ ሁልጊዜ ልጅ ሆኖ እንዲቀር አትፈልግም። ለዚህ ነው እመቤታችን ድንግል ማርያም አንድም ጊዜ ጌታን ከመስቀል ሞት እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ልጄ ሆይ ፥ አትሙትብኝ” ብላ ስትከላከል ያልታየችው። ያልተሰማችው። ያ ሞት ያለጊዜው ሲመጣ ብቻ ልጇን ካለጊዜው ከሆነ ሕመም ጠበቀችው እንጂ ፥ በዕድሜው ለሆነው አርብ ግን ድንጋል ማርያም ተባባሪ ነበረች። ይሄ ትንሣኤን ለራሱ ለሚሻ ፥ ለልጆቹ ለሚመኝ ሰው ሁሉ የተጻፈ ታሪክ ነው።



አሁን አሁን ሕይወትን ካለብዙ ነገሮች ማሰብ እያቃተን ነው። በተለይ በምዕራቡ ሀገራት። መብራት፣ ኮምፒውተር፣ ጉግል፣ ፍርጅ፣ መኝታ ቤት የተቀመጠ መጸዳጃ ቤት ፥ ሕይወትን ካለእነዚህ የማያውቅ ትውልድ ነው ያለው። አንዱ ለልጄ “በኛ ጊዜ ጉግል (Google) አልነበረም ስለው አላመነኝም” ብሏል። ምክንያቱም ካለ ጉግል የሰው ልጅ ምን ያህል መረጃን ለማግኘት እንደሚደክም ይሄ ልጅ ፈጽሞ የማይረዳበት ዘመን ነው።



አሁን አሁን ወደ ሕክምና ስፍራ ብትሄዱ የመጀመሪያው የሚሰጣችሁ ነገር ሕመም ማስታገሻ ነው። በየቤቱ የተለያዩ ዓይነት የሕመም ማስታገሻዎች አሉ። መውሰድ ባንፈልግ እንኳ ቢያንስ ከራስ ምታት ማስታገሻ እስከ ተለያዩ ኦፒዎዶች ቤታችን አሉ። እንቅልፍ እንቢ ካለንም ብዙ መጨናነቅ አሁን አያስፈልገንም። በተለያዩ መልኮች የእንቅልፍ ማስተኛ ሽሮፖች እና ክኒን ሞልተውልናል። የሰው ልጅ ብዙ ታሪኩ ግን እንዲህ አልነበረም። እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለዘመን መጨረሻ ድረስ የሕመም ብቸኛ ምርጫ ጥርስን ነክሶ መቻል ነበር። ምን አልባት ትንሽ ማደንዘዣ አልኮል ይሰጥሃል ወይም የምትነክሰው ነገር ያቀብሉህና ፥ የሰውነትህ አካል ሳይቀር ያለማደንዘዣ ይቆረጥ ነበር። ልክ እንደ ክርስቶስ አጠገብህ የሚያጽናኑህ ይኖሩ ይሆናል እንጂ ያን ሕመም ስለ ሕመሙ ብቻ ተብሎ የሚያስቀረው አልነበረም። ምክንያቱም ለረዥሙ የሰው ልጅ ታሪክ ሕመም የሰው ታሪክ አካል ነበር። የሕክምና ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ሳይቀር ፥ ሕመምን ለማስቀረት ያደረጉት ጥረት የረዥም ጊዜ ታሪክ አልነበረም። ትልቁም የሳይንስ ትኩረት አልነበረም።



ጆናን በርክ በStory of Pain በሚለው መጽሐፉ እንደጻፈው ኬሚስት ሀምፍሬ ዴቪይ የLaughing Gasን (ላፊንግ ጋዝን) የሕመም የማስታገሻ ባህሪውን ካገኘ በኋላ እንኳ በሕክምናው እና በሳይንሱ ዓለም እንደ ትልቅ ግኝት ተቆጥሮ በቶሎ ወደ ተግባር አልተገባም። ለሕመም ማስታገሻነት በስፋት ጥቅም ላይ እስኪውል መቶ ዓመታት ፈጅቷል ። ሌሎችም የሕመም ማስታገሻዎች፣ ለምሳሌ እንደ ኒትረስ ኦክሳይድ ሲገኝም የሕክምናው ዘረፍ እንደ ዛሬው ተሯርጦ ወደ መጠቀም አልገባም። ጆናን በርክ እንደሚለው የሕመም ትርክት ለብዙ ሰዎች ለመቀበል የሚቸገሩት አልነበረም። ሕመም ለዶክተሮችም ሆነ ለታካሚዎች የሕክምናው እና የመዳን ሂደት አካል ነበር። እንደውም አንዳንድ ሰርጅኖች ያለ ታካሚው የስሜት እንቅስቃሴዎች እና ጩኸት ሕክምናውን ማድረግ አይፈልጉም ነበር።



ከሁሉም በላይ ግን ለብዙ ሰዎች ለብዙ የታሪክ ዘመን ሕመምን ራስን በመቆጣጠር፣ በመግዛት እና በክብር ጨክኖ ማለፍ የማንነት መገለጫቸው እና የጀግንነት ጌጣቸው ነበር። ሕመም የጀግንነት፣ የወንድነት እና የታላቅ ስብዕና መገለጫ ነበር። ሕመምን ሳይመጣ ይለማመዱት ነበር። በሚበሉት ነገር ሳይቀር የሚያቃጥል፣ የሚለበልብ እና ጎምዛዛ ነገር በማብዛት የሕመም የመታገስ ሐሞታቸውን ያጠነክሩ ነበር። በእኔ ዕድሜ ሳይቀር የሚያቃጥል ቃሪያ በምግብ ጠቅልሎ አባቴ ያጎርሰኝ ነበር። ፈጽሞ ያን እንድተፋው አይፈቀድልኝም ነበር። ጨክኜ አኝኬ እድውጠው እንጂ። ከዛ የሚብስ ነገር ሊመጣ ስለሚችል ያን ቃጠሎ ቃሪያ አኝኬ እውጠዋለሁ። የአባትነት ሥራ ልጅን ከሕመም መጠበቅ አልነበረም። ይልቁንስ በየደረጃው ለሕመም ማጋለጥ እንጂ።



ዛሬ ግን የሕክምናው ዘርፍም ተለውጧል። በአሜሪካ ዶክተሮች የሚገመገሙት ታካሚዎች የሕክምናው ፕሮሲጀር ሲካሄድ በተሰማቸው የሕመም መጠን ሆኗል። ምንም ሕመም ካልተሰማቸው ያ ዶክተር ትልቅ እና በጎ ሬቲንግ ያገኛል። ያም ለደሞዝ እና ለእርከን ዕድገት አስተዋጽኦ አለው። ስለዚህ ዶክተሮች ምን ያደርጋሉ? ሱስ እንደሚያሲዝ እያወቁ የተለያዩ የሕመም ማስታገሻዎችን ለታካሚዎቻቸው ያስቅማሉ። ዛሬ አሜሪካ ውስጥ መጨነቅ መድኃኒት አለው። መወፈር መድኃኒት አለው። ትኩረት ማጣት የሚቃም መድኃኒት አለው። ያለመድኃኒት የማይንቀሳቀሱ ጥቂት መጤዎች ብቻ ቢሆኑ ነው። ከ1980ዎች ጀምሮ የዓለም የጤና ድርጅት ሳይቀር እነዚህ የሕመም ማስታገሻ ኦፒዶዎች በስፋት እንዲመረቱ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ መግፋት እና ማበረታታት ጀምረዋል።



የሚገርመው ግን የሕመም ማስታገሻዎች የረዥም ጊዜ ጥቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ምንም ሳይንቲፊክ የሪሰርች ውጤቶች አለመኖሩ ነው። ያ ብቻ ሳይሆን አሁን በስፋት እየወጡ ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሕመም ማስታገሻዎች የቁስሎች የመዳንን ሂደት በጣም እንደሚያዘገዩት ነው። ልክ ነው አንዳንድ የቀዶ ጥገና ሕክምናዎች የግድ የሕመም ማስታገሻዎች (anesthesia) ያስፈልጋቸው ይሆናል። ግን ከየት ወዴት እንደመጣን ብቻ እዩት?



የሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ ለራሱ የሚነግረው ትርክት ነው። ብዙ ጊዜ እንደጻፉኩት የደስተኛ ሕይወት ምንጭ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት እንጅ ምቾት አይደለም። ደሃ ራሱን አጠፋ ሲባል መስማት በጣም ዝቅተኛ ነው። ራስን ማጥፋት እንደ ፊንላንድ፣ ደቡብ ኮሪያ እና መሰል የምቾት መጠናቸው ከፍ ባሉ ሀገራት ላይ ነው የሚብሰው። የሰው ልጅ ሕመምን እና መከራን ለማለፍ የሚታገለው ትግል እና በዚህ ወቅት ለራሱ የሚነግረው ትርክት ነው የደስታው መሠረት። ትርጉም ያለው ሕይወት ማለት ይሄን ሕመም ጥርስ ነክሶ ሲታለፍ ነው። ይሄ ሕመም የትውስታ ማህደራችን (memory) ውስጥ ካልተቀበረ ፥ የምናገኘው ጥሩ ነገሮች እና ምቾቶች ሁሉ አያስደስቱንም። መስቀሉ ነው የትንሣኤው ውበት። ያ ትንሣኤ ውበት የሚኖረው ፥ ልብሳችንን ተከፋፍለው፣ በጦራቸው አይነሳም ብለው ወጋግተው፣ በተሳለቁብን እና ባሾፉብን መኃል ከዛ ሕመም በላይ ሆነን ፥ ከቀናት መሰወር በኋላ ላያስቆሙን ብድግ ስንል ነው። እነዛ ሕመሞች የትንሣኤው ዘላለማዊ ጌጦች ናቸው። ኢዮብ ያለ ሕመሙ እና ጥርሱን ነክሶ ራሱን ሳያዋርድ ሕመሙን መታገሱ ነበር ዖፅ ከምትባል መንደር በላይ ለዘላለም ገዝፎ እንዲታይ፣ እንዲተረክለት ያደረገው። ሰው እንዴት ነው ጌጦቹን የሚርቀው? እንዴት ይሄን የደስታ ምንጭ ከልጆቻችን እናርቃለን?

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Nov 28, 2024
  • 4 min read


September 2023


የሁለት ሺ ዓመት ታሪክን በሚደንቅ ውበት የሳለ፣ በታላቁ የስዕል ጠቢብ በቪንሰንት ቫን ጎ “ይሄን ስዕል መሳል የቻለ ሰው ብዙ ሞትን ራሱ የሞተ ነው” ተብሎ የተመሰከረለት ፥ በዚህ ምድር ሁሉን ነገር አግኝቶ ያጣ ፥ የ17ኛው ክፍለ ዘመን የደች የምን ጊዜም ምርጥ ሰዓሊ ራምበረንት እና የጠፋው ልጅ ታሪክ።



ራምበረንት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ታዋቂ ሰዓሊ ነበር። በጊዜው ሀብታም ሰው ሁሉ ለሱ ማንኛውንም ክፍያ ከፍሎ በሱ መሳልን ፥ የሱን የቡርሽ አሻራ በቤቱ ማኖር የሚፈልጉ ሁሉም ከበርቴዎች እና ባላባቶች ነበሩ። በዚህ ዝናው በሚመጣ ሀብት እና ክብር ራምበረንት የጉብዝናውን ወራት ፍጹም በተጋነነ የዝሙት እና የስካር ሕይወት ማሳለፍ ጀመረ። ደንበኞቹን መስደብ እና ማመናጨቅ፣ የጠመዳቸውን ሰዎች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍሎ የሚያሳስር፣ የአዕምሮ ሕክምና ጣቢያ ውስጥ የሚያስጨምር ሆነ። ያን ረምበረንት ነበር ዓለም እስከመጨረሻው የሚያውቀው ፥ ለራሱ ክፋት ሁለተኛ ዕድል የሚሰጠው የሰው ልጅ ሌላ ሰው ሲሳሳት እና ሲበድል ቢያየው ግን የወደፊቱን ብቻ ሳይሆን የቀደመውንም ጽድቅ ነው የሚነሳው። ድሮም ሲያስመስል ነበር ይላል። ወደፊትም በጎ ይሰራል ብሎ አይቀበልም።



ራምበረንት ያን ፍርድ ነው ከዓለም ያገኘው። በሉቃስ ወንጌል (15፥12) የምናገኘው ታናሹ ልጅ ልክ እንደ ራምበረንት ከአባቱ ሀብት ተካፍሎ (ጸጋ ወስዶ) ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ ይላል መጽሐፍ ቅዱስ። በዚህ የሉቃስ ወንጌል ላይ ጥናት የሰራው የሀርቫርዱ ሄነሪ ኖዌን በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ባሉ ማህበረሰቦች ባህል አባት ሳይሞት ፥ ልጅ የአባቱን ንብረት አይጠይቅም ይላል። በሌላ አነጋገር ታናሹ ልጅ ያለው “አባቴ ሆይ አትሞትም እንዴ? የማትሞት ከሆነ ቆሜ አልጠብቅህም” ነው። ሞቱን ተመኝቶ ንብረቱን ተካፍሎት ርቆ ሄደ።



ራምበረንት ይሄን ልቅ ሕይወት ሲመራ የመጀመሪያ ወንድ ልጁን በ1635 በሞት ተነጠቀ። ከመቼውም ጊዜ በላይ ለቀሪ ልጆቹ መራራት እና ከሚስቱ ሳሲካ ጋር በሀዘኑ ምክንያት ቅርበትን ፈጠረ። ራምበረንት ግን የመጀመሪያ ሴት ልጁን በ1638 በሞት ተነጠቀ። ብዙም አልቆየም በ1640 ኮሪኒላ የተባለች ሴት ልጁ በሞት ተለየችው። በዚህ ጊዜ የራምበረንት ዝና እና ክብር ወርዶ ፥ ሕይወቱ መመሰቃቀል ጀመረ። የገንዘብ ዕዳ ውስጥ እየተነከረ መጣ። በዚህ ወቅት ነበር ሚስቱ ሳሲካ የዘጠኝ ወር ልጅ አሳቅፋው በ1642 በሞት የተለየችው። ከልጁ ሞግዚት ጋር ግንኙነት ቢመሰርትም ፥ በክስ እና በመጨረሻም እሷ በአዕምሮ ሕክምና ጣቢያ ውስጥ በሚያሳስር ፍርድ ተጠናቀቀ። ስቶፈል ከተባለች ሴት ጋር ተጋባ ፥ ሁለት ልጆች ወለደችለት። ነገር ግን አሁንም የወለደችለት ወንድ ልጁ በ1652 ሞተበት። በዚህ ወቅት ቤቱ እና ስዕሎቹ ሁሉ በሀራጅ ተሸጡበት። በዚህ ሰዓት የሳላቸው ስዕሎች በጣም ልዩ እንደሆኑ እና “ሰውን እና ተፈጥሮን በሚደንቅ መነጽር ማየት የጀመረበት፣ ከዚህ በፊት በስዕሉ የሚታዩ ውጪያዊ ጫጫታዎች የራቁት ነበሩ” ይላል ስለሱ የጻፈው ጃኮብ ሮዘንበርግ። ሁለተኛ ሚስቱ በ1663 ሞተችበት። ከዓምስት አመት ቆይታ በኋላ ራምበረንት ከመጀመሪያ ሚስቱ የወለደው ብቸኛ ወንድ ልጁ እና በጣም የሚወደው ቲተስ ሞተ። ራምበረንት በዚህ ወቅት ነበር ፥ ቡሩሹን አንስቶ ማንም ስሎት በማያውቀው ጥልቀት የጠፋውን ልጅ ታሪክ የሳለው።



የእርያዎችን አሰር መብላት ሲከለከል የአባቱ ቤት ሕይወት እንደታወሰው የጠፋው ልጅ ብቻ አይደለም ራምበረንት አሁን እግዚአብሔርን ያወቀው። ይልቁስ በጠፋው ልጅ ታሪክ የተሰወረውን የአባት ፍቅር ነበር ራምበረንት በስዕሉ አውጥቶ ያሳየው። የጠፋው ልጅ ልሂድ ሲል ፥ እንደ ወላጅ “አትሂድ አላለውም” ያ አባት። ታናሹ ልጅ ለመሄድ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሰጠው እንጂ። ከዚህ ቤት ውጪ ደስታ እንደሌለ ቢያውቅም ፥ ደስታን ከአባቱ እቅፍ ውጪ ለፈለገች ነፍስ በዓለም የሚያስፈልጋትን ሁሉ ሰጥቶ ሸኛት። ያ ሀብት እንደሚያልቅ፣ መቁሰል እና መጎዳት እንዳለ ቢገነዘብም ፥ ያ አባት ግን አደጋን ለመጋፈጥ ለፈቀደች ነፍስ ነጻነትን ሰጣት። ራምበረንት “ታናሹ ልጅ ከአባቱ ቤት ሲሄድ ብቻ ሳይሆን ወደ አባቱ ቤት ሲመጣም አባቱን እንዳላወቀው ስለገባው” ነበር ፥ የጠፋውን ልጅ ጭንቅላት የሕጻን ልጅ ሰውነቱን የአዋቂ አድርጎ የሳለው። አባቱ ቤት ሲመለስ ንግግር እየተለማመደ፣ ምን መናገር እንዳለበት እያሰበ ነበር የመጣው። የሱ ንግግር የአባቱን ልብ የሚያራራ መስሎት። ከእግዚአብሔር ፍቅር በላይ የኛ ቃላት ፍቅር የተሸከሙ ይመስለናል። አባቱ ግን ገና ሩቅ ሳለ አዘነለት። ልጁ ንስሐውን ሳይጨርስ አባቱ ልጁን አለበሰው፣ እጁን በቀለበት እግሩን በጫማ አሳመረው።



ራምበረንት ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንደ ልጅ ካሎናችሁ አትገቡም የሚለውንም አሳየን።የጠፋውን ልጅ ጭንቅላት ከማህፀን የወጣ ጭንቅላት አስመስሎ ስሎ። አባቱን ሁለት ዓይነት እጆች ያሉት፥ የሴት እና የወንድ አድርጎ ሳለው። እንደምንጎዳ እያወቀ ለነጻ ፍቃዳችን እሺታውን የሚሰጥ አባት (ልቤ ጨከነ እንዳለ ዳዊት)፥ ስንመለስ ደግሞ በፍቅር ሮጦ የሚቀበለን እናት ነው እግዚአብሔር። ራምበረንት ግን ታላቁንም ሳለው። በውስጥ ሳለ የጠፋውን ፥ ከጠፋው ይልቅ በውስጡ መራራነትን ያዘለውን። ከወንድሙ መዳን ይልቅ የሰባው ፍሪዳ መታረድ ያስጨነቀው ፥ መመለሱ ሳይታወቅ ታሪኩ የተጠናቀቀው ታላቁ ልጅ። ባለፈው ዓመት በሀገራችን ያየነው ይሄን የታላቁን ልጅ ማንነት ነበር።



ታላቁ ልጅ በልቡ በታናሹ ልብ ውሳኔ የሚደሰት ሰው ነበር። የሚጠብቀው አባቱ ሞቶ ታናሹን ማስቀናት፣ ከሱ የበላይ ሆኖ መኖር ነበር። ሁልጊዜ ከአባቱ ጋር መሆኑ አላስደሰተውም ፥ የሚጠባበቀው አንድ ቀን የአባቱን ሁሉን መውሰድ እንጂ። ስለዚህ ከአባቱ ምንም እንዳይጎድል በስስት ይጠብቅ ነበር። የክህነት ቀሚስ ገድቧቸው እንጂ እንደታናናሿቹ መጋደል ያማራቸው፣ ታናናሾቹ ሲታረቁ ሞተን እንገኛለን ብለው የአባታችንን ቤት ቆልፈው የሄዱ ታላላቆችንም ያየነው ባለፈው ዓመት ነበር።



ለምን እንደሆነ አላውቅም ፥ ስለራምበረንት እስከማውቅ ድረስ የጠፋው ልጅ ያባከነው ‘ገንዘብ እና ጸጋ’ ብቻ ነበር የሚመስለኝ። ለካ ሁሉም ነገር ስጦታ ነው። ማለትም ራምበረንት ልጆቹን እና ሚስቱን አጣ ፥ እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ ነበሩ። ኢዮብ ልጆቹን እንዳጣ፣ ኑኃሚን ከባሏ እና ከሁለት ልጆቿ ጋር ከእስራኤል ወጥታ ፥ ባሏን እና ሁለት ልጇቿን አጥታ ባዶ እጇን እንደተመለሰች ፥ የሚወሰደብን ነገር ምን እንደሆነ አናውቀውም። ሁሉም ግን የሱ ስጦታ ነው። ከሱ በተለየን መጠን የሚጠፉ ፥ የሚባክኑ፣ የሚያልቁ ናቸው።



ራምበረንት የመጨረሻ ልጁን ባጣ በሁለት ዓመት ውስጥ እሱም ሞተ። በሉቃስ ወንጌል 2፥28 እንደምናገኘው ስምዖን “እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ። ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ”፤ ራምበረንት በክርስቶስ እቅፍ ውስጥ በመጨረሻ አረፈ። ከሩቅ ያየው አምላኩ ከሱ ብዙ አልጠበቀምና ወደራሱ ሰበሰበው። የራምበረንት የመጨረሻ ስዕልም የነበረው ይሄ የአዛውንቱ ስምዖን ነበር። "አሰናብተኝ ፥ ነፍሴ የተጠማችሁን በመጨረሻ አየውት" የሚለው የአዛውንቱ የስምዖን ስዕል ነበር የራምበረት ፍጻሜ።



አዲሱ ዓመት ወደ ልቦናችን የምንመጣበት ዓመት ይሁነን። የእግዚአብሔር ፍቅር ይግባን። እሱም ወንድምን ከፍሪዳዎች በላይ መውደድ እና አባታችን እኛን በፍጹም ፍቅሩ እንደሚወደን ማወቅ ነው። “ይሄ የምወደው ልጄ ነው” የሚለው ድምጽ ከእርሱ ጋር ሕብረት ቢኖረን ለኛም ነው። የፈረድንባቸው እና ከመጠን በላይ የምንጠላቸው ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። የሰባውን ፍሪዳ የሚያርድላቸው፣ አንባር የሚያጠልቅላቸው ፥ ጫማ የሚያደርግላቸው አንገታቸውን አቅፎ የሚስማቸው ናቸው። ይሄን ስናውቅ በወንድሞቻችን ላይ ጥላቻ ሊኖረን እንደምን ይችላል? ይሄ ፍቅር ካለበትስ ቤት ወዴት እንሄዳለን?

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Nov 24, 2024
  • 3 min read




“ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤ ቀርባም። ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው።


 ኢየሱስም መልሶ። ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥


 የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት።” ሉቃ 10፥41፡42።



ይሄን ታሪክ ሳነብ ትዝ የሚለኝ ሴኒካ ለሉሲለስ ወዳጁ የጻፈለት ደብዳቤ ነው። እንዲህ ይለዋል “ሉሲለስ ሆይ ካንተ የሚወሰድብህ ነገር ሁሉ ያንተ አይደለም። ያንተ ባልሆነ ነገር መደገፍን አሶግድ።” ጌታችን ለማርታ “ማርያም የማይወሰድባትን መረጠች” ይላታል። መንገድ ላይ ቆመው የሚለምኑ ሰዎችን ሳይ በእኔ አዕምሮ ስለተወሰደባቸው ሀብት እና ክብር ሳይሆን የሚያስበው፤ ስላልተወሰደባቸው ድፍረት ነው። ኑሮን የመቀጠል ድፍረት። በሕይወት የመኖር እና የመቀጠል ጀግንነት።



በያንዳንዱ ቀን ያለኝ ብርታት ሰዎች ከኔ ሊወስዱብኝ የማይችሉት ነገርን ገንዘብ ባደረኩኝ መጠን ነው። ከአምላኳ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ማረፍን ማንም ከማርያም የሚወስድባት አይኖርም። ለዛች ነፍስ የክብር ቦታ፣ VIP ወይም ፊትለፊት ላይሰጣት ይችላል። ታላቅ አስተዳዳሪ፣ ታላቅ ሰባኪ ወይም ታላቅ ምናምን ብለው ላይጠሯት ይችላሉ። ግን ከክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ፍጹም መደሰትን ማንም አይነጥቃትም።



ከሁለት ዓመት በፊት ውድ ፍራሽ ለጥሩ እንቅልፍ እንዲሆን ገዛው። ግን በሚገርም ሁኔታ ፍራሹን የገዛው ቀን ምንም እንቅልፍ ሊወስደኝ አልቻለም ነበር። በጠዋት ዳውን ታወን ወዳለው ቢሮዬ ልገባ ስል ከሕንጻው ሥር፤ ሰዎች በፍጥነት በሚራመዱበት ሥፍራ አንዱ አስገራሚ እንቅልፍ ተኝቷል። ውድ ፍራሽ አልነበረውም እንቅልፍ ግን ነበረው። ለአምስት ደቂቃ የሚሆን ጊዜ ቆሜ አየውት። የአስር ሺር ዶላር አልጋ ሊኖርህ ይችላል፤ እንቅልፍ ከሌለህ ግን ትርጉም የለውም። ያን እንቅልፍ ፍራሽ እምብዛም አይሰጥህም። ቅዱስ ጳውሎስ እና ሲላስ በእስር ቤት ሆነው በፍጹም ደስታ ይዘምሩ ነበር። በዓለም ላይ ተፈተው ያሉ ሰዎች ግን ያ ደስታ አልነበራቸውም። ጳውሎስ እና ሲላስን በእግረ ብረት ሆኖ መታሰር ያን ደስታ ሊቀማቸው አልቻለም። የማይቀሙን ነገር አለን?



ሰዎች የማይወስዱብን ነገሮች አሉን?


 ትረምፕም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የማይቀሙን ነገሮች ይኖሩን ይሆን? እኔ ስለሃይማኖት ወይም በዛ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለሚገባቸው ነገሮች ብቻ እየተናገርኩኝ አይደለም። በጣም ብዙ ድንቅ ሰዎችን በሕይወት ተገናኝቻለው። ማንም የማይወስድባቸው ደግነት፣ መረጋጋት፣ ትህትና፣ እውቀት፣ ማስተዋል፣ ጥበብ፣ ስክነት ያላቸው ሰዎች። መክሰርም ሆነ ማግኘት ምንም ያልነቀነቃቸውን ሰዎች አይቻለው። አንዳንዶቹ ምንም ሃይማኖት የሌላቸው ነበሩ። እነዚህ ማንም የማይቀማቸው ውበት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ።



ማርታ ጌታን ለማስደስት በጓዷ ትተጋ ነበር። የጌታ መደሰት በማርታ እጅ ላይ የነበረ አልነበረም። በርሷ ቁጥጥር ውስጥ አልነበረም። እርሷ ግን ብዙ ለፋች። ብዙ ተጨነቀች። ማርያም ደግሞ ነፍሷን አደመጠች። ያ ውብ ጌታ እግር ሥር መቀመጠ እርሷን እንደሚያስደስታት ገባት። ስለዚህ አደረገችው። የእርሷ ደስታ ግን በእጇ ነበር። ጌታ ስለመደሰቱ ሳይሆን የእርሷ ነፍስ ስለማረፏ አሰበች። ያን ራስን ማወቅ ከእርሷ ማን ይወስድባታል?



 ሊዮ ቶልስቶይ ስለመደሰት ሲናገር በጣም ቀላል መርህ ነው ያለው። “መደሰት ትፈልጋለህ?” “እንግዲያው ደስተኛ ሁን!” ብቻ ነው የሚለው። ብዙዎቻችን መደሰት ብንፈልግም ደስተኛ የሚያደርገንን ነገሮች ግን አይደለም የምንሰራው። ይልቁንስ ክብር፣ ቦታ፣ ዝና፣ ኢጎ፣ አዋቂ መስሎ መታየት፣ ከቡድን የመነጠል ፍርሃት፣ እንደ ማርታ ሰው ምን ይለኛል የሚል ጭንቀት እና ሌሎች ስሜቶች ነው የሚያስተዳድሩን። የሚቀሙን ነገሮችን ብቻ ነው የምንሰበስበው። ክብር እንደ ጥላችን ነው። አንዳንዴ ከኛ በላይ ትልቅ ነው። አንዳንዴ ከኛ በጣም የሚያንስ ነው። ምክንያቱም የኛ አይደለም።



 የማርታ ሃብቶች ሊወሰዱብን የሚችሉ ናቸው። አያስፈልጉም ሳይሆን ብዙ መትጋት ያለብን ግን የማርያም ሃብቶች እንዲበዙልን ነው። የማርያም ሃብት ያለው ሰው የማርታ ሃብትን በሂደት ገንዘቡ ማድረግ ይችላል። የማርታ ሃብት ያለው ሁሉ ግን የማርያም ሃብት አለው ማለት አይደለም። በማንኛውም እና በየትኛውም ቦታ ብንሆን ቀና ብለን የምንሄድበት ጥበብ አለን? በሁሉም ስፍራ አሸናፊ የሚያደርገን ማንም የማይነጥቀን ሰውነት አለን? ያ በማዕበል እና በወጀብ መኃል ቀና እንዳልን የሚያስኬደን ውሳጣዊ ሃብቶች አሉን? የማርያም ሃብቶች።



መስቀል የበዛባቸውን ሰዎች አላያችሁም? ግን ከፊታቸው ይሄ ሕይወት ውብ ነው የሚል ደስታ የማታጡባቸው! ሲመሽ ደስ የሚላቸው ሲነጋም ፀሐይዋን በድጋሚ አወጣት ብለው የሚደሰቱ ሰዎች። ሉሲለስ ሆይ ካንተ የሚወሰድብህ ሁሉ ያንተ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች አልገጠሟችሁም? “ወፈርኩኝ አይደል?” ብለው ጠይቀዋችኹ፤ “አዎ” ስትሏቸው የሚያኮርፏችሁ? በሕግ ትምህርት ቤት እያለሁ፤ አንድ ከእንግሊዝ የመጣች ተማሪ ነበረች። ፊቷ በርበሬ መስሎ አንድ ቀን እኔ የማጠናበት ክፍል ከጓደኞቿ ጋር መጣች። “ፊትሽ ምን ሆኖ ነው?” ስላት (እንግዳ ስለሆነብኝ ነበር)፤ አበደችብኝ። ጓደኞቿም “ያን መጠየቅ አልነበረብህም” አሉኝ። ምን አልባት ልክ ናቸው። ግን ተመልከቱ ምን ያህል insecure እንደሆነች! በሽበት፣ በቁመት፣ በእርጅና እና በሌሎች ጉዳዮች እንዲህ የሚሰማን ሰዎች ሞልተናል። የማርታ ሃብቶች ብቻ ያሉን። ማርያም ግን የማይቀሟትን መረጠች።



ሊወዱን ሊጠሉን፣ ለጊዜው ሊያከብሩን ወይም ሊሰድቡን ይችላሉ። ይሄን ሁሉ እንደ ኢምንት ቆጥረን ፥ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን እንዳለው በዚህ የሙገሳ እና የስድብ ውርጅብኝ ውስጥ ዝም የምንል ምን ያህሎቻችን ነን? የማይቀሙን የውስጥ ጽናት ያለን? የመንፈስ ቅስማችን የማይወሰድብን ምን ያህሎቻችን ነን? የማይቀሙንን እንያዝ። የማይወስዱብንን ገንዘብ እናድርግ። “ሉሲለስ ሆይ ካንተ የሚወሰድብህ ነገር ሁሉ ያንተ አይደለም።”

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page