top of page
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Sep 1, 2024
  • 3 min read

ree



“የሰው ሕይወቱ ብርቱ ሰልፍ ነው” ይላል የዚህ ሰልፍን ትርጉሙን አጥብቆ የጠየቀው ጻዲቁ ኢዮብ። ጥበበኛ ወዳጆቹ የሰጡት መልስ ዛሬ ከሃይማኖት ሰዎች የምትሰሙትን ነው። ኢዮብ ከወዳጆቹ እንደ አንዱ ነበር። የሚለየው እውነትን ለመጋፈጥ ደፋር በመሆኑ ነበር። ግን መከራ ብቻ ነበር ያን ድፍረት የገለጠው። የሚያጣው ምንም ነገር ሳይኖር ሲቀር ፥ እንደ ሰነፍ መሳደብን ገንዘብ ማድረግ ባይፈቅድ እንኳ ፥ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ያለውን ጥበብ ግን ጠየቀ። ማለትም የጽድቅ ፍጻሜው በረከት ነው የሚለውን ሁልጊዜ እውነት ያልሆነውን ፍልስፍና ጣለ። የዚህን ፍልስፍና ውሸት ከኢዮብ በቀር ማንም ሊያሳየን አይቻለውም ነበር። ምክንያቱም በእግዚአብሔርም በሰይጣንም እኩል ሊመሰከርለት የቻለ ሰው ኢዮብ ብቻ ነበር። ስለ ጽድቁ። ስለ ፍጹምነቱ። የኢዮብን ፍጹምነት የጥርጥር አባት ራሱ ሰይጣን አልተጠራጠረም። ምን አልባት ሰይጣን ከወደቀ በኋላ ያመነው ነገር ቢኖር ይሄ ብቻ ይሆናል።



ይሄ ፍጹም ሰው ብቻ ነበር “ስለ ኃጢአቴ አይደለም ይሄ ሁሉ መከራ የደረሰው” ብሎ ሊናገር የሚችል። ስለዚህ የመከራን እውነተኛ መልክ ኢዮብ ነበር ያሳየን። የሕግ ሰዎች ሳይቀር በአጭር መሞትን በወላጆች መረገም ጋር ያያይዙት ነበር። ረዥም ዕድሜን ደግሞ ወላጅን ከማክበር ጋር። ኢዮብ ግን መከራ ከጽድቅም ከኃጢአትም ነጻ ሆኖ መኖር የሚችል መሆኑን በማሳየት መልኩን ገለጸልን። የኢዮብ መጽሐፍን አይሁዶች ቢረዱት ኖሮ ያን ከሚያክል ስህተት እና ግፍ በጠበቃቸው ነበር። ግን ችግሩ የኢዮብን መጽሐፍ ከክርስቶስ የመስቀል ሞት በኋላ ራሱ እኛም እንደ አይሁድ አልተረዳነውም።



“ስለ ሕይወት መልስ አለኝ” ከሚል ሰው በላይ መጥፎ ሰው ወዴት ይኖር ይሆን። መጥፎ በክፋት ሳይሆን መጥፎ ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር ማለቴ ነው። እስቲ የትኛውንም የሚዲያ ዓይነት ከፍታችሁ ስሙ። መልስ የሚፈልግ እኮ ጥቂት ነው። መልስ የሚሰጥ እንጂ። ሕይወትን በምልዓት ያለፈባት ሰው ደግሞ በእነዚህ ሰዎች ይቆስላል። ምክንያቱም ከርሱ የሕይወት ልምድ በተቃራኒ ቆመው ስለርሱ ሕይወት ይነግሩታል። የኢዮብ ወዳጆች በዚህ ጨለማ ውስጥ ያሉ ናቸው። “እውቀትን መጨመር ሕመምን መጨመር ነው” ይላል ጠቢበኛው፤ ግን እውቀትን የጨመረ ሰው ሌላ ሰውን የማሳመም አቅሙ እና ዕድሉ እየቀነሰ ነው የሚመጣው። እውቀት የሌላቸው ሰዎች እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ነው የሚሆኑት። ሁሉም ስለድርጊታቸው እየታመመ እነሱ ግን ጤነኛ ነው የሚሆኑት።



 መጽሐፈ ኢዮብ ጽድቅ በራሱ ግብ እንደሆነ የተገለጸበት መጽሐፍ ነው። ምንአልባት ሌሎች መጽሐፎችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አካሎችን ሳይቀር ውድቅ ያደረገ ነው። ሰይጣን ይሄ የቆየ ፍልስፍናን ስለሚያምን እንዲህ አለ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን?” “ሰው በጎ ነገር በመስራቱ አንዳች ክፍያ ማግኘት አለበት” አለ ሰይጣን። ጽድቅ በራሱ በቂ አይደለም በማለት። ኢዮብ የዚህ ውርርድ ተያዥ ነበር። የጽድቅ ክፍያ ራሱ ጽድቅን መስራት እንደሆነ ኢዮብ ነገረን።



ሸክላ ሠሪው ሸክላውን የመስበር መብት እና ሲፈልግ ተንደገና የመጠገን መብት አለው ፥ የለውም አይደለም የኢዮብ ጥያቄ። ሲሰብርም ሆነ ሲጠግን አንዳች ምክንያት ሊኖረው ይገባል እንጂ። “የዚህ ዓለም ውበት አንድ ኃያል አምላክ አለ በመጨረሻ ለኃጢያተኛው በረከትን የሚነፍግ ለጻድቁ በረከቱን የሚያለብስ” አሉት ወዳጆቹ። በሌላ አነጋገር “የእግዚአብሔር አምላክነት ኃይለኝነቱ ነው” አሉ የኢዮብ ወዳጆች። ስለዚህ እውነትን ሳይቀር ለኃይል አስገዟት። በምንም በማይረታ ኃይል ፊት ፥ እውነት መናገር ከባድ ስለነበር ብዙ የሚያጡት ነገር ያላቸው የኢዮብ ወዳጆች ፊት ለፊታቸው ካለው ግራ መጋባት ይልቅ ለኃይል ተንበረከኩ። ፍጻሜያቸው ታናሽ እንደሆነ የሞቱ ከአቤል ጀምሮ ያሉ ንጹኃንን ረሱ። ስለዚህ ብቻ ንስሃ ግብ “ጅማሬ ታናሽ ቢሆን እንኳ ፍጻሜ ታላቅ ይሆናል” አሉት። ዓለምን ከዚ በላይ ያቀለለ ፍልስፍና ከየት ይኖራል። ይሄ ዓለም ግራ የገባው ሰው ማሰብ ጀምሯል። ለዚህ እንቆቅልሽ ወጥ የሆነ መልስ የሰጠ ሰው የማሰብ እንጥፍጣፌ ያልቀረለት ነው።



በሬናይሰንስ ፍልስፍና ውስጥ ለማይታጣው the Songs of Ronland ለተባለ ጥንታዊ መጽሐፍ በ1916 ድጋሚ መታተም መግቢያ የጻፈው ጄ ኬ ቼስተርተን፤ በዚህ መጽሐፍ ላይ ያን ቅዱስ እና ታላቅ ጦርነት አሸንፎ፣ ሰላማዊ አገዛዝን አስፍሮ እፎይ ብሎ ስለተኛው ንጉሱ Charlemagne ይነግረናል። ንጉሱ ያን ቅዱስ ጦርነት አጠናቀኩኝ፣ አገዛዜ ሰላም ሆነ ብሎ መልካም እንቅልፍ ተኝቶ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ቀሰቀሰው። እርሱ እና ሠራዊቱ ሌላ ሩቅ ቦታ ለአዲስ ጦርነት እንደሚፈለግ ነገረው። ንጉሱ ከእንቅልፉ ነቅቶ አለቀሰ። ኢዮብን እያስታወሰ መራራ ለቅሶን አለቀሰ። ረፍት የማይሰጥ ሕይወት ፥ የማያልቅ ጦርነት ፥ የማያባራ ጠላት ሲሆንበት አለቀሰ። ገና አረፍኩኝ ሲል መልአኩ ቀሰቀሰው። ሩቅ እና አዲስ ለሆነው ሠልፍ።



የማያልቅ ምዕራፍ ነው ይሄ ሕይወት። ጥቂት እንደተኛን የምንቀሰቀስበት። ለአዲስ ትግል። ለአዲስ ምዕራፍ። ምንአልባትም ለዚህ ይሆናል ኢዮብ ከቁስሉ እንደተፈወሰ መጽሐፍ ቅዱስ ያነገረን። ኢዮብ ያገኘው ጥበብ ከቁስሉ ጋር መኖር ስለሆነ ሊሆን ይችላል። ቁስሉን መቀበል ስለሆነ። በዛ ጉድለት፣ በዛ አለማወቅ ውስጥ መጽናናትን አገኘ። ከሰው መልስ ይልቅ የእግዚአብሔር ጥያቄዎች እረፍት ሰጡት። ምንአልባትም የሰው ልጅ ሞተር ይሄ ያልተፈታ እና የማይፈታ እንቆቅልሽ ነው። ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ እንዳለው በጽድቅ ጉዞ ውስጥ ፍጽምና የለም። በዚህ ጉዞ መርካት ላይ የደረሰ ሁሉ የክፋትን እና የጥፋትን ጉዞ ጀምሯል። ፍጻሜ የሌለውን ነገር ፍጻሜ መስጠት ተቃራኒውን ነገር መጀመር ማለት ነው። ያረፋችሁ የመሰላችሁ እስክትቀሰቀሱ ነው። የምትዋጉም ለመጨረስ ሳይሆን የማያልቀው ይሄ እንደሆነ እወቁ ሕይወት ማለት። በዚህ በማያልቅ ጦርነት ውስጥ መቀጠል ነው ሕይወት።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 26, 2024
  • 2 min read

ree


ይሄ ከሳምንት የቀጠለ ነው። ባለፈው ሳምንት ችግራችንን እንዴት እንፍታ በሚል ርዕስ መወያየት ከጀመርን በኋላ፤ በግልበጣ አስተሳሰብ (reverse thinking) መሠረት ይሄን አጥርቶ ለመረዳት በተቀራኒው ማሰብ ጥቅም እንዳለው አውርቼያችሁ ነበር። ማለትም ችግራችንን እንዴት አለመፍታት እንዳለብን። የመጀመሪያው ፈጥነን ክርስቶስን ወይም ሃይማኖትን በችግራችን ውስጥ ማስረግ (smuggling Jesus) እንደሌለብን አወራን። ከዛ ደግሞ ጊዜን የችግር ፈቺ አድርጎ አለማቅረብ እና ኋላፊነትን ለገለልተኛ ጊዜ አለመስጠት እንደሚገባ ተነጋገርን። ለዛሬ ችግራችንን እንዴት መፍታት እንደሌለብን የምንነሳው ከዚህ ነው።


3) ፍላጎትን እና እውነትን (reality) መነጠል፤

 

በሕይወት በጣም ወሳኝ ነገር ቢኖር እውነትን እንዳለ መረዳት መቻል ነው። ለዚህ ትልቁ እንቅፋት ፍላጎት ነው። ፍላጎት ብዙ ጊዜ የስሜት ልጅ ነው። በአስተዳደግ፣ በዶግማ፣ በማህበረሰብ እና በፖሮፓጋንዳ እጆች ተኮትኩቶ የሚያድግ እና የፋፋ ነው። ፍላጎት እና እውነትን ማስታረቅ እጅግ ከባድ ነገር ነው። በርግጥ ሰዎች ፍላጎት ባይኖራቸው ለብዙ አስገራሚ ለውጦችም ባልተጋበዙ ነበር። ፍላጎት ነው የብዙ አስደናቂ ግኝቶች ሞተር። በተመሳሳይ ፍላጎት ነው የብዙ መጥፎ ውሳኔዎች ክብሪት። ሰዎችን ለመረዳት ከፈለግን በጥልቀት የገለጡትን እና ያልገለጡትን ፍላጎታቸውን መረዳት ያስፈልጋል። ራሳችንን ማወቅ ከፈለግንም የሚጋልበንን ፍላጎት የተባለ ፈረሰኛ ማንነቱን ማወቅ እና በጥልቀት መገንዘብ ግድ ይላል። ፍላጎት ነው የደስተኛ ሕይወትም ሆነ የሐዘን ደም ሥር።

 

አለመፈለግ አይቻልም። ምክንያቱም አለመፈለግ ራሱ ፍላጎት ነው። አለመፈለግን የሚፈልግ ራሱ አለመፈለግን በመፈለግ ፍላጎት ውስጥ ነው። ከፍላጎት ነጻ መሆን አይቻልም። ማወቅ ያለብን  እውነታን ለመገንዘብ ፍላጎት እንቅፋት እንደሆነ እና ፍላጎትን የሚያህል የእውነት ዕውርነት እንደሌለ መገንዘብ ብቻ ነው። ዓለምን እና በዙሪያችን ያሉትን ነገሮች ሁሉ የምናየው በፍላጎት መነጽር ነው። ይሄን መነጽር እንዳረገ የሚክድን ሰው ያህል አደገኛ ሰው የለም። እኔን ከጠየቃችሁኝ፤ ከዚህ ሰው ጋር በምንም ነገር ባልዋሃድ እና ባልጎዳኝ እመርጣለሁ። ላንተ ስል ነው፣ አንዳች ፍላጎት የለኝም፣ ፍላጎቴ ምንም ሳይሆን ያንተ ፍላጎት ነው ከሚለኝ ሰው ጋር ከመራቅ ውጪ ምርጫ የለኝም። በክህደት ውስጥ መጓዝ ማለት ይሄ ነው።

 

በዚህ የአስተሳሰብ ስሌት ውስጥ ያለ ሰው ራሱን ለመፈተሽ ዝግጁ ስላልሆነ፤ በሌሎች ላይ የሚያየውን ማናቸውምስሜቶች በፍርድ ዓይን ነው የሚመለከተው። ስለዚህ በፍጥነት “ይሄ ሰው መጥፎ ነው፣ ጥሩ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ሉሲፈርነው፣ ገገማ ነው፣ ተንኮለኛ ነው” እና መሰል ቃላቶችን ከፍርድ አዕምሮ አውጥቶ ይናገራል። በዚህም ሌሎችን መረዳት ይሳነዋል። መረዳት ከተሳነን ደግሞ ጥሩ መፍትሔ የመስጠት አቅም አይኖረንም።

 

መቼ መጥፎ ውሳኔ እንደምንሰጥ ታውቃላችሁ? መቼ ነው ከመኪና ጋር የምንጋጨው? ከኋላችን የሚመጣውን ወይም ከጎናችን የሚያልፈውን መኪና ካላየነው የመጋጨት ዕድላችን ከፍተኛ ነው። በተመሳሳይ ሌሎችን ካልተረዳን፣በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን በጥልቀት ለመረዳት ካልጣርን፣ ይሄ ማለት ደግሞ ፍላጎታቸውን ካላወቅን ስህተት የመስራት ዕድላችን የትየለሌ ነው። ልክ እንደዛው በራሳችን ውስጥ የሚርመሰመሱ እና ለፈጣን ውሳኔ የሚዳርጉን የፍላጎት ወጠምሻዎችን ካላወቅናቸው፣ መሠረታቸውን ካልተረዳን ከራሳችን ጋር ግጭት ውስጥ የሚከቱን እልፍ ስህተቶችን በሕይወት መንገዳችን መፈጸማችን የማይቀር ነው። ይሄ ማለት ቀናችን እና ጊዜያችን ሁሉ “ለምን እንዲህ አደረኩኝ፣ ምናለ ያኔ እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ፣ ምናለ ዝም ብል፣ ምናለ ያን ነገር ፈጽሜ ቢሆን፣ እጄን በቆረጠው ያኔ፣ ብረጋጋ ምናለ” በሚሉ እና በመሰል ቃላቶች የተሞላ ይሆናል።

 

 ይቀጥላል።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 18, 2024
  • 3 min read


ree

የሁሉም ሰው የሕይወት ተልዕኮ ውስጥ የሰዎችን መከራ ማቅለል አንዱ ነው። ብዙዎቻችን ግን ለችግራችን የምንሰጠው መፍትሔ የበለጠ ችግር ይዞብን ይመጣል። እንግሊዝ ሕንድን ቅኝ በገዛችበት ወቅት ተናዳፊ እባብ ቀኝ ገዚዎችን አስጨነቀ። ለዚህ ቀላሉ መፍትሔ እባቦቹን አድኖ መግደል ነበር። ይሄን ለማበረታት ደግሞ ለሕንዶቹ ተናዳፊ ኮብራ እባቦቹን አጥምደው ባመጡ ሰዓት ማበረታቻ ገንዘብ ቃል ተገባላቸው። ሕንዶቹ ግን ማበረታቸውን ለማግኘት ሲሉ ጭራሽ ኮብራ እባቦቹን ማርባት ተያያዙት። እባቦቹን ለመቀነስ የወጣው ሕግ እባቦቹን በብዙ እጥፍ አበዛቸው።



በየቀኑ የሰዎችን ችግር ስሰማ እና ያን መፍትሔ ለመስጠት መጣር ነው ሥራዬ እና ኑሮዬ። ሰዎች ለብዙ ችግራቸው መፍትሔው ቀላል እና ርካሽ እንደሆነ ሲነገራቸው ደስ ይላቸዋል። መፍትሔው ረዥም መንገድ ሊወስድ እንደሚችል ማንም መስማት አይፈልግም፤ በጥልቀት ከሚያስተውሉ ሰዎች በቀር።



ዛሬ በአማራ ክልል የተነሳው ጦርነት ልክ እንግሊዝ እባቦቹን ለማጥፋት እንደሄደችበት ያለ መፍትሔ የሞከሩ ሰዎች የፈጠሩት መከራ ነው። ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት አጭሩ የማስገበሪያ መንገድ መስሎ ታያቸው። ይሄው ሀገሪቷን ረዥም የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ነከራት። አንድ ቦታ ቶሎ የመድረሻው መንገድ ረዥሙ መንገድ እንደሆነ ብዙዎቻችን የሚገባን አጭሩን መንገድ ከሞከርን በኋላ ነው። እንዴት ነው ግን ችግሮቻችንን የምንፈታው? እንዴት ነው በሕይወታችን ውስጥ ያሉትን ችግሮች የፈታነው ፥ ፈተን የምናውቅ ከሆነ!



መቼስ አንድ ችግር በሕይወታችን ፈተን እናውቃለን። እንዴት ነው ያን ችግር የፈታነው? እንዴት ነው ዘላቂ መፍትሔ የሰጠነው? ያን የመገምገም እድል አግኝታችዋል? በርግጥ ለብዙ ችግራችን ሌሎች ችግሮችን ስንፈጥር ነው የኖርነው። ለዚህም ይመስላል፤ ሀብት ያለው ሰው ልጆቹ እና ቤተሰቦቹ ያልተሳኩለት የሚሆነው። የድኅነትን ችግር ፈቷል፤ ግን ልጆቹን አጥቷል። ወይም ትዳሩን አጥቷል። ወይም ወዳጆቹን። በዚህም ደስታን አጉድሏል። ሌሎች ደግሞ የቤተሰብ ፍቅር አላቸው ግን ጠኔ ፍቅራቸውን ይፈታተነዋል። አንዳንዶች ልጆቻቸውን ጨዋ ማድረግ ችለዋል ግን ፈጣን አዕምሮ እና በራሳቸው የሚቆሙ ልጆች አይደሉም።



ስዊዘርላንድ እያለው የሰማውት ነው። የስዊዝ መንግስት በስልሳዎቹ ከሁለተኛው ጦርነት በኋላ የገጠመውን የቤት እጥረት ለመቅረፍ ባለአንድ ክፍል ጠባብ አፓርትመንቶችን አብዝቶ ገነባ። ከሠላሳ እና አርባ ዓመት በኋላ ግን ሲዊዘርላንድ ውስጥ ከፍተኛ ብቸኝነት ተስፋፋ። አንዱ ምክንያት በእነዚህ ጠባብ አፓርትመንቶች ውስጥ ከአንድ ግለሰብ በላይ መኖር ከባድ ስለሆነ ነበር። ቤተሰባዊ እና የጋሪዮሽ ሕይወት የሚያበረታታ አልነበረም። የቤት እጥረት መፍትሔ ብቸኝነትን በማሕበረሰብ ውስጥ አዋለደ። ቤተሰብን አፈረሰ።



ለችግሮቻችን እንዴት ነው መፍትሔ የምንሰጠው? ግን መጀመሪያ ለችግሮቻችን መፍትሔ እንዴት መስጠት እንደሌለብን ልግለጽ።



1) መለኮታዊ ሰበብ አለመፈለግ፤



ይሄ ከማመን እና አለማመን ጋር አይገናኝም። ግን ራስን ከማወቅ ጋር እንጂ። የብዙዎቻችን ሕይወት ከዚህ የመመረጥ እና የፈተና መንገድ በብቃት የተነሳ የተወገደ ነው። ግን ብዙዎቻችን ራሳችንን አንድ ፐርሰንቱ ውስጥ እንጂ 99 ፐርሰንቱ ውስጥ ከተን ማየት አንሻም። የኛ ሕይወት ውስብስብ በሆኑ የመንስኤ እና ውጤት ጥምረቶች የሚመተር እና የሚጓዝ ነው። ምርጫችን ነው አሁን ላለንበት ውጤት የዳረገን። ችግር ሲፈጠርም ሮጠን የመለኮት እጅ የኛን የኃላፊነት ድርሻ እንዲተካ አንሩጥ። በርግጥ ማስተዋል እና ርጋታን መለመን አንድ ነገር ነው። ግን ማስተዋል እና ርጋታ እየለመኑ መተኛት ካልቻልን ማስተዋል እና ርጋት ወደ እኛ አይመጣም። ለምሳሌ አንድ ነገር አቅደን መፈጸም ሲሳነን ፥ ሰይጣን ሊያሰናክለን ወጥኖ ያደረገው ነው ከሚል እምነትም ሆነ ቃሎች እንራቅ። ከዛ ይልቅ የኛ ሕይወት ለዚህ ዓይነት ፈተና ገና ብቁ እንዳልሆነ በመገንዘብ የራሳችንን ድርሻ ላይ በማተኮር ያን ለመቅረፍ እንጣር።



2) ጊዜ ይፈታዋል በሚል ራሳችንን አናታል፤



ብዙ ነገሮች ስሜት የላቸውም። ማለትም ፍርድ የላቸውም። ኒውትራል ናቸው። ለምሳሌ ስለሞት ስናወራ ፥ ሞትን ልክ እንደ አንድ ግለሰብ አድርገን ነው የምናወራው። ከሞት ጋር ተፋጥጬ፣ ሞት መጥቶብኝ ወይም ከሞት ጋር ተናንቄ የሚል እና ሞትን ግዝፈተ አካል ሰጥተነው ነው የምንናገረው። ከቋንቋ ውበት እና ንግግር አንጻር ከሆነ መልካም። ይሄ ግን አስተሳሰብ ከሆነ የመረዳት አቅማችንን ያሽመደምደዋል። ሞት ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ የምንሻገርበት ነው። ሽግግር (state) ነው። ልክ ጊዜም ኒውትራል ነው። ምንም ዓይነት የፍርድ ዝንባሌ የሌለው ኒውትራል ሂደት ነው። ጊዜ የመፍትሔ ዘለላዎች የሉትም። በራሱ የሚፈታልን ወይም የሚያባብሰው አንዳች ነገር የለም። ጀግናም አይደለም ፈሪም አይደለም። ታጋሽም አይደለም አይናደድምም። ስለዚህ ለጊዜ ችግራችንን አሳልፈን አንሰጠውም። መታገስም የጊዜ ሳይሆን የኛ ነው። መናደድም የኛ ውሉድ እንጂ የጊዜ አይደለም። ስለዚህ ለጊዜ ችግራችንን በመስጠት የሚገኝ ምንም ነገር የለም። በዕድል እና በክስተት ለመመራት ከመፍቀድ ውጪ።



ይቀጥላል።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page