top of page
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 11, 2024
  • 3 min read


ree

 “በሮም ሳላችሁ እንደሮማውያን ፥ when in Rome do as Romans do” የሚባል አባባል አለ። ለባለፉት ዓመታት የምጥረው ነገር ቢኖር የምኖርበትን ሀገር በጥንቃቄ መረዳት ነው። ብዙ ቅዠት ውስጥ ገብቼ አላውቅም። ምን ማለቴ ነው? እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደ ዘመነኞቹ ምዕራባውያንን እየሰደብኩኝ እና ስለክፋታቸው እየተናገርኩኝ ፥ ሕይወቴን ለማትረፍ ግን በመጨረሻ ወደ እነሱ የመጣው አይደለውም። ይልቁንስ ጥቂት ጥሩ ነገር ባይኖራቸውም በብዙ ከኛ እንደሚሻሉ በማመን እና ባለማፈር ምርጫዬ የማደርገው ስልጣኔ እንደሆነ በመናገር ነው። የስልሳዎቹ ትውልዶች ኢምፔሪያሊዝም ይውደም እያሉ ምዕራባውያንን እስኪበቃቸው ካወገዙ በኋላ ግን ሁሉም በመጨረሻ የተጓዙት የሰው ልጆች መብት በአንጻራዊነት ወደ ተከበረባቸው የምዕራብ ሀገራት እንጂ አንዳቸውም ወደ ራሺያ እና ኩባ ወይም ወደ ማኦ ሀገር ቻይና የሄዱ አልነበሩም። ከዚህ በላይ hypocrisy ወዴት ይኖር ይሆን። ሰለሞን ደሬሳ የሚለው አለው “ለሀገሬ የምመኘው ለራሴ የምመኘውን ነው።” ብዙዎቻችን የምንታዌ (dual) ሕይወት መኖር ነው ምርጫችን። ማለትም የምናምነው፣ የምንተገብረው እና የምንናገረው ተዋህዶልን አያውቅም። የምዕራባውያንን ስልጣኔ ሲያወግዝ እና ሲደሰኩር የምታዩት የሃይማኖት መምህር ፥ ተሰዶ በመጨረሻ የምታገኙት የምዕራባውያን ሀገር ነው። የትኛውን ፈጣሪ ሊያስደስት ያን ሁሉ እንደደሰኮረ እርሱ ይወቀው። የእርሱ ምርጫ ግን አልነበረም። የምንታዌ ሕይወት ማለት ይሄ ነው። አንደበት እና ተግባር ያልተዋሀዱበት ሕይወት። ይሄን ረጋ ብለው የሚያስቡ ሰዎች እንዲህ ብለው ይገልጹታል unintegrated life።



ወደ ርዕሴ ልምጣ እና ምንድነው ግን የአሜሪካ ጥበብ? ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፎክስ ሚዲያ አንከር ከነበረው ተከር ካርለሰን ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ስለአሜሪካኖች ፍልስፍና ሲናገር “እነርሱ (እናንተ) የተግባር ሰዎች ናቸው፤ እኛ ደግሞ ፍልስፍና (ሀሳባዊነት) እና መንፈሳዊነት የሚማርከን ነን” አለ። አሜሪካውያን ፕራግማቲስት ይባላሉ። ሁሉ ነገራቸው ምንድነው የሚሰራው፣ ምንድነው የተሻለ ውጤት የሚያመጣው ከሚለው ሀሳብ የሚመነጭ ነው። ለዚህም በሁለት ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት እና አስገራሚ የስልጣን (power) ባላንስ በሚታይባቸው የአራቱ መዋቅሮቻቸው (ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው፣ ሕግ ተርጓሚው እና ሚዲያው) በመመራት ይሄ የፕራግማቲስት ሳይክል ሀገሪቷን የሚጠሏት ሰዎች ሳይቀር በመጨረሻ ለመጠለል የሚመጡባት እና የምርጦች ምርጥ መናኸሪያ እና የእንቁ አዕምሮዎች መጠራቀሚያ አድርጓታል። ይሄን ፍልስፍና የሚገልጽ አንድ ጸሎት አላቸው። “እግዚአብሔር ሆይ መለወጥ የማልችለውን ነገር እንድቀበል መረጋጋትን ፥ መለወጥ የምችለውን ነገር እንድቀይር ጀግንነትን ስጠኝ፤ ጥበብን ግን ስጠን የሁለቱን ልዩነት ለማወቅ።” “God, grant me the serenity to accept the things I cannot change, the courage to change the things I can, and the wisdom to know the difference.”


በመጨረሻ ግን ሕይወት ማለት ይሄስ አይደል። ይሄ ጥበብ። በእውነትስ የጥበብ ትርጉምስ ከዚህ ውጪስ ነውን? መለወጥ የማንችለው እና መለወጥ የምንችለው የቱ እንደሆነ ማወቅስ አይደል ትልቁ ጥበብ። ጀርሚ ጎልድበርግ እንዳለው “ጀግንነት ማለት እንደምንጎዳ እያወቅን ማድረግ ማለት ነው። ደደብነትም ግን ተመሳሳይ ትርጉም ነው ያለው። ለዛም ነው ሕይወት ከባድ የሆነው።” የደደብነት እና የጀግንነት ትርጉሙ ተመሳሳይ ስለሆነ ነው ሕይወት ከባድ የሆነው። ምክንያቱም ተመሳሳይ ተግባር ደደብነትም ሊሆን ይችላል ፥ ጀግንነትም ሊሆን ይችላል። ምን ጊዜ ደደብነት ፥ ምን ጊዜ ጀግንነት እንደሆነ ለማወቅ ግን ጥበብ ይፈልጋል።


 ተቀጥረን የምንሰራውን ሥራ ትተን የራሳችንን መሞከር ደደብነትም ሊሆን ይችላል ፥ ጀግንነትም ሆኖ አንድ ቀን ያን ውሳኔ ልንኮራበት እንችላለን። ጥበብ ብቻ ነው “መቼ” የሚለው የሚያውቀው። የአሜሪካ ብቃት የሚመስለኝ ይሄ ነው። አንድ ሰው ብቻውን፤ አንድ ግለሰብ ብቻውን የዚህ ጥበብ ሁልጊዜ ባለቤት እንደማይሆን ማወቅ እና አጠቃላይ ሥርዓተ መንግስቱን እና አስተዳደሩን እንደ ቤተሙከራ በሚያይ ፕራግማቲስት አስተሳሰብ ማዋቀራቸው። ለአንድ ፍልስፍና እና ለአንድ ወጥ ለሆነ ዶግማ ያልተገዛ ሀገረ መንግስት ማዋቀራቸው። በነጻ ገበያ ሥርዓት የሰዎች ፍጹም የሆነ መልካምነትንም ሆነ ክፋት እንዲገለጥ የሚያስችል ውቅር መስራታቸው። ከዛም ዘወትር ነገሮችን ለማሻሻል እና የተሻለ ምርጥ አድርጎ ለመስራት የሚጥር አስተሳሰብን መትከላቸው። ለዚህ ደግሞ መጠበቂያው የጥሎ ማለፍ ሥርዓትን ማስቀመጣቸው ነው። እስካልተለወጥክ ድረስ ፥ የተሻለ ነገር ማምጣት እስካልቻልክ ድረስ በአሜሪካ ውስጥ ርህራሄ አታገኝም። ስለዚህም ሕይወት በፍጥነት የሚሄድ ሳይክል ነው። በዚህ ፈጣን ሳይክል ላይ ለመቀጠል ዘወትር ፔዳሉን መምታት ያስፈልጋል።



አሜሪካኖች የሚሉን እንቁላል ጥብስ መብላት ከፈለክ እንቁላሉን መስበር ግድ ነው። ጥሩ ነገሮችን መስራት ትፈልጋለህ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ለመስራት መድፈር አለብህ። ያን ደግሞ ማድረግ የምትችለው ሕይወት እንደ ሆነችው መመልከት ስትችል ብቻ ነው። በፍልስፍና እና በማንኛውም ዶግማ መነጽር የምታይ ከሆነ ያልተዋሀደ ሕይወት ይገጥምሃል። የምትናገረው እና የምትሰራው ተቃራኒ ይሆናል።



የአሜሪካኖች ጥበብ ይሄ ነው። “በዚህ ዓለም ለውጥ ማምጣት ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ግልጽ የሆነ ፥ ጭጋግ የሌለበት ዕይታ ሊኖርህ ይገባል። ይሄ ዕይታ በፍልስፍና ያልታወረ፣ በዶግማ ግራ ያልተጋባ እና ነገሮች እንዴት እንደሚሰሩ የሚገነዘብ፣ ሰዎችን የሚመሩ ድብልቅ ፍላጎቶች (mixed motives) የሚረዳ እና አንዳንድ ሰዎችን የሚያስተዳድሩ ዝቅተኛ ስሜቶችን (base interests) የሚገነዘብ ነው።” ይሄን ዓለም እንዳለው እና እንደሆነው ለመረዳት የሚደረግ ጥበብ ነው ይሄ ጥበብ። ነገሮችን በግልጽ፤ ራቆታቸውን ለመረዳት የሚጥር ፥ ጥበብ ነው ይሄ ጥበብ።

 
 
 

ree



በድንገትም ሆነ ታስቦበት የወጣ ቃል ፥ አሸናፊ የማድረግ አቅም አለው። ለምሳሌ ብዙዎቻችን የምናውቀው እና የአሜሪካን የፍርድ ቤት ሥርዓት ወደ ድራማ ትይንት የቀየረው የO J. Simpson ጠበቃ Johnnie Cochran የተናገረው፣ በመጨረሻም O J. Simpson በጁሪው ነጻ እንዲሆን ያደረገው ቃል ይሄ ነበር፦ “If it doesn’t fit, you must acquite” - ፖሊስ በማስረጃነት ስላቀረበው ጓንት ነበር ይሄን የተናገረው። “ልኩ ካልሆነ ልክ አታስገቡት” የሚል አውዳዊ ትርጉም አለው።



የታዋቂው የተከላካይ ጠበቃ የማርክ ገራጎስ ቃልም የብዙ ጠበቆች መስመር ሆኖ ቀርቷል፦ “just because someone says it’s true doesn’t make it true” “የሆነ ሰው እውነት ነው ስላለ ብቻ እውነት አይሆንም።”


የሕግ ሊቀ ሊቃውንት የሰር ዊሊያም ብላክስቶን ቃልስ ፦ “Better that ten guilty persons escape than that one innocent suffer.”። (“አንድ ንጹሁ ሰው ከሚታሰር አስር ወንጀለኛ ነጻ ቢወጣ ይሻላል!”) የሚለው እና የወንጀል ሕግ ሥርዓት መሠረት ሆኖ የቀረው ከዚህ ሊቅ አንደበት የወጣ ነው። ወደ ሀገራችን ስንመጣም ከፈረንሳዩ የሶርባን ዩኒቨርስቲ በሕግ የተመረቀው ልዩ ፍጥረት አክሊሉ ሀብተወልድ እንዲህ የሚለው ቃሉን አንረሳውም።



“አንድ ግብ ብቻ ነው ያለን


ኢትዮጵያ!


አንድ መተባበሪያ አላማ ብቻ ነው ያለን


ኢትዮጵያ!!


አንድ ፕሮግራም ብቻ ነው ያለን


ኢትዮጵያ!!!”



ይሄን የመሰለ ውበት ያለው እና ሁሉን አቃፊ የሆነ መስመርን እንዴት ባለ ጥንቃቄ የሚያፈልቅ፤ ልክ እዚህ ሀገር ባሉ ሊቃውንት ደረጃ ያለ ሰው ነበር አክሊሉ።



ይሄን ያነሳውት ዛሬ ዎልስትሪት ጆርናል የክልሌን ገዢ እጩ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጠ እና ለዛ ያበቃውን ዋነኛ ምክንያት ሲጠቅስ፤ ካሚላ ሀሪስ ባይደንን እንደተካችው፤ ገዢያችን ቲም ዋልዝ ትረምፕን እና ቫንስን “ዊርዶች” ብሎ መግለጹ ነው ይላል። ከዛ በኋላ ሁለቱ ዊርዶች የሚለው ቃል የሊብራል ሚዲያ ቃል ሆነ። ዋልዝንም ለአሸናፊነት አበቃው። ቃላት በዘፈቃድ የሚወጡ አይመስለኝም፤ ጊዜ እና ሁኔታን፤ አውድን እና ሰሚን አስተውሎ እና አጥንቶ የሚለቀቅ ቃል ፥ የቃል ፍጥረትን የሰው ልጅን ይማርኩታል። ቃላት ያድኑናል፤ ቃላት ይገሉናል።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 5, 2024
  • 2 min read

ree


ማርከስ አርሊየስ እንደ ዘራያዕቆብ ፋላስፋው ንጉስ ተብሎ ይጠራል። በየቀኑ የጻፈው ሪፍሌክሽን “Meditation” በሚል ርዕስ ከሞተ በኋላ ሰዎች አግኝተው መጽሐፍ አድርገው አትመውታል። ይሄ መጽሐፍ ንጉስ ማርከስ አርሊየስ ከራሱ ጋር ያደረገው ንግግርን በየቀኑ የጻፈበት ነበር። ይታተማል ብሎ አንድ ቀንም አላሰበም። ይሄው ግን ለ3 ሺ ዓመታት ምርጥ መጽሐፍ ሆኗል።



ማርከስ ሰውን ከጋሪ ጀርባ እንደታሰረ ውሻ ይመስለዋል። ሕይወታ ጋሪ ናት። ውሻው ከዚህ ከሚሮጥ የሕይወት ጋሪ ጀርባ ታስሯል። የውሻው ምርጫ ሁለት ነው። ከጋሪው ጋር መሮጥ ወይም በጋሪው እየተጎተተ እና አፈር ላይ እየተንከባለለ ቆሳስሎ መንፋቀቅ። ምክንያቱም ከጋሪው ጋር በጠንካራ ገመድ ታስሯል። በመጨረሻ ውሻው ቢሮጥም ቢንፋቀቅም ደክሞት ይሞታል። ነገር ግን ከጋሪው ጋር ቢሮጥ ቢያንስ ሳይቆስል እና ሳይሰቃይ ይሞታል። በጋሪው እየተጎተተ እና አሮጥም ብሎ እየተንፋቀቀ ከሆነ ግን ሞቱን ማፋጠን ብቻ አይደለም ፥ አጭሯም ሕይወቱ የስቃይ ናት የምትሆነው።



 በተመሳሳይ አንዳንድ ሰዎች በሕይወት መቀየር በማይችሉት ነገር ሲጨነቁ ጊዜያቸውን ያባክናሉ። የዛሬውን እና የወደፊቱን ከማሰብ ይልቅ ፥ ትላንት እንዲህ ባደርግ ወይም እንዲህ ባላደርግ በማለት ምንም መለወጥ በማይችሉት ነገር በመጨነቅ ራሳቸውን ለብስጭት፣ ለጭንቀት እና ለሕመም ይዳርጋሉ። “መተው” የሚለው ጥበብ የሌላቸው ፥ ከሕይወት ጋር ወደፊት የመጓዝ ብልሃት ያልገባቸው ምስኪኖች ናቸው።



በምንም መስፈርት ብትመዝኑት ይሄ ሕይወት ያልቃል። በምንም መስፈርት ብትመዝኑት ሞት ይገታዋል። ሕይወት ደግሞ ይቀጥላል። የዓየር ንብረቱም ተለውጦ ቢሆን፣ በሙቀት እየሞትን፣ በጎርፍ እየተጥለቀለቅንም ሕይወት ይቀጥላል። ምርጫው ማርከስ እንዳለው በግድ የሚጎተት ውሻ ወይም እስከቻለው ድረስ ከሕይወት ጋሪ ጋር የሚሮጥ መሆን ነው። ሕይወት ለእኛ ስሜት እምብዛም ግድ የላትም። በተዋቀረው የተፈጥሮ ዑደት ነገሮች እርስ በእርሳቸው ባላንስ እየተደራረጉ ይቀጥላሉ። በዚህ ኃይል እና ፍጹም ጉዙፍ በሆነው የተፈጥሮ ዑደት ፊት ከትንኝ ያነሰ ቦታ ያለን ነን። ግን የገዘፈ ሥራ ሠርተን፤ ቢያንስ ግን መረዳት በምንችለው መጠን ሕይወትን ተገንዝበን ልናልፍ እንችላለን። ያ የሚሆነው ግን ክፍት አዕምሮ ሲኖረን እና ወደ ፊት ለመጓዝ፣ ለዚህ ተፈጥሮአዊ የማይደገም የየቀን አዲስ ልምድ ራሳችንን ስናሰምር ነው። አለዛም ሕይወት ግን ይቀጥላል። እኛም ተንፏቃቂ ውሻ ሆነን እንቀጥላለን።



ማርከስ በዚው መጽሐፉ ላይ ሕይወት ወንዝ ነው ይላል። “አንድን ወንዝ ሁለቴ አትረግጠውም” ይላል። ምክንያቱም ወንዝ ሁልጊዜ ወደፊት መፍሰስ ነው። ልክ እንደ ወንዝ የትላንት ሕይወታችንን መመለስ ፈጽሞ አንችልም። ብቸኛው የምንችለው ዛሬን ከትላንት በተለየ መኖር ነው። ልክ ከጋሪው ጋር እንደታሰረው ውሻ ያለን ምርጫ ሁለት ነው። ያለፈውን እየረሳን ቅዱስ ጳውሎስ ለፉልጵስዩስ ሰዎች እንዳለው (ምዕ 3 ፥ 13) “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” ዛሬ ላይ እና ነገ የሚገጥመንን ለመዋጀት መሮጥ ወይም ለሕይወት ሩጫ እንቢ ብሎ እየቆሰሉ እና እየተንፋቀቁ ሞታችንን ማፋጠን። እኔ እና ቤቴ የሚሻለውን መርጠናል እንዳለው ኢያሱ ፥ የኔ ምርጫ እየተንፋቀቁ ይሄን ሕይወት የበለጠ አክብዶ በማማረር እና በቁጭት ኖሮ ከመሞት ከሕይወት ማዕበል ጋር በመተባበር ወደፊት መፍሰስ ነው። የሆንኩትን እየተቀበልኩኝ ፥ አዲሱን የማይታወቀውን በጥበብ እና በማስተዋል በመጋፈጥ መኖር ነው።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page