top of page
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Aug 5, 2024
  • 2 min read



ማርከስ አርሊየስ እንደ ዘራያዕቆብ ፋላስፋው ንጉስ ተብሎ ይጠራል። በየቀኑ የጻፈው ሪፍሌክሽን “Meditation” በሚል ርዕስ ከሞተ በኋላ ሰዎች አግኝተው መጽሐፍ አድርገው አትመውታል። ይሄ መጽሐፍ ንጉስ ማርከስ አርሊየስ ከራሱ ጋር ያደረገው ንግግርን በየቀኑ የጻፈበት ነበር። ይታተማል ብሎ አንድ ቀንም አላሰበም። ይሄው ግን ለ3 ሺ ዓመታት ምርጥ መጽሐፍ ሆኗል።



ማርከስ ሰውን ከጋሪ ጀርባ እንደታሰረ ውሻ ይመስለዋል። ሕይወታ ጋሪ ናት። ውሻው ከዚህ ከሚሮጥ የሕይወት ጋሪ ጀርባ ታስሯል። የውሻው ምርጫ ሁለት ነው። ከጋሪው ጋር መሮጥ ወይም በጋሪው እየተጎተተ እና አፈር ላይ እየተንከባለለ ቆሳስሎ መንፋቀቅ። ምክንያቱም ከጋሪው ጋር በጠንካራ ገመድ ታስሯል። በመጨረሻ ውሻው ቢሮጥም ቢንፋቀቅም ደክሞት ይሞታል። ነገር ግን ከጋሪው ጋር ቢሮጥ ቢያንስ ሳይቆስል እና ሳይሰቃይ ይሞታል። በጋሪው እየተጎተተ እና አሮጥም ብሎ እየተንፋቀቀ ከሆነ ግን ሞቱን ማፋጠን ብቻ አይደለም ፥ አጭሯም ሕይወቱ የስቃይ ናት የምትሆነው።



 በተመሳሳይ አንዳንድ ሰዎች በሕይወት መቀየር በማይችሉት ነገር ሲጨነቁ ጊዜያቸውን ያባክናሉ። የዛሬውን እና የወደፊቱን ከማሰብ ይልቅ ፥ ትላንት እንዲህ ባደርግ ወይም እንዲህ ባላደርግ በማለት ምንም መለወጥ በማይችሉት ነገር በመጨነቅ ራሳቸውን ለብስጭት፣ ለጭንቀት እና ለሕመም ይዳርጋሉ። “መተው” የሚለው ጥበብ የሌላቸው ፥ ከሕይወት ጋር ወደፊት የመጓዝ ብልሃት ያልገባቸው ምስኪኖች ናቸው።



በምንም መስፈርት ብትመዝኑት ይሄ ሕይወት ያልቃል። በምንም መስፈርት ብትመዝኑት ሞት ይገታዋል። ሕይወት ደግሞ ይቀጥላል። የዓየር ንብረቱም ተለውጦ ቢሆን፣ በሙቀት እየሞትን፣ በጎርፍ እየተጥለቀለቅንም ሕይወት ይቀጥላል። ምርጫው ማርከስ እንዳለው በግድ የሚጎተት ውሻ ወይም እስከቻለው ድረስ ከሕይወት ጋሪ ጋር የሚሮጥ መሆን ነው። ሕይወት ለእኛ ስሜት እምብዛም ግድ የላትም። በተዋቀረው የተፈጥሮ ዑደት ነገሮች እርስ በእርሳቸው ባላንስ እየተደራረጉ ይቀጥላሉ። በዚህ ኃይል እና ፍጹም ጉዙፍ በሆነው የተፈጥሮ ዑደት ፊት ከትንኝ ያነሰ ቦታ ያለን ነን። ግን የገዘፈ ሥራ ሠርተን፤ ቢያንስ ግን መረዳት በምንችለው መጠን ሕይወትን ተገንዝበን ልናልፍ እንችላለን። ያ የሚሆነው ግን ክፍት አዕምሮ ሲኖረን እና ወደ ፊት ለመጓዝ፣ ለዚህ ተፈጥሮአዊ የማይደገም የየቀን አዲስ ልምድ ራሳችንን ስናሰምር ነው። አለዛም ሕይወት ግን ይቀጥላል። እኛም ተንፏቃቂ ውሻ ሆነን እንቀጥላለን።



ማርከስ በዚው መጽሐፉ ላይ ሕይወት ወንዝ ነው ይላል። “አንድን ወንዝ ሁለቴ አትረግጠውም” ይላል። ምክንያቱም ወንዝ ሁልጊዜ ወደፊት መፍሰስ ነው። ልክ እንደ ወንዝ የትላንት ሕይወታችንን መመለስ ፈጽሞ አንችልም። ብቸኛው የምንችለው ዛሬን ከትላንት በተለየ መኖር ነው። ልክ ከጋሪው ጋር እንደታሰረው ውሻ ያለን ምርጫ ሁለት ነው። ያለፈውን እየረሳን ቅዱስ ጳውሎስ ለፉልጵስዩስ ሰዎች እንዳለው (ምዕ 3 ፥ 13) “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” ዛሬ ላይ እና ነገ የሚገጥመንን ለመዋጀት መሮጥ ወይም ለሕይወት ሩጫ እንቢ ብሎ እየቆሰሉ እና እየተንፋቀቁ ሞታችንን ማፋጠን። እኔ እና ቤቴ የሚሻለውን መርጠናል እንዳለው ኢያሱ ፥ የኔ ምርጫ እየተንፋቀቁ ይሄን ሕይወት የበለጠ አክብዶ በማማረር እና በቁጭት ኖሮ ከመሞት ከሕይወት ማዕበል ጋር በመተባበር ወደፊት መፍሰስ ነው። የሆንኩትን እየተቀበልኩኝ ፥ አዲሱን የማይታወቀውን በጥበብ እና በማስተዋል በመጋፈጥ መኖር ነው።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Jul 31, 2024
  • 2 min read


"ሁሉም ስላጠፉ የእኔም ጥፋት ችላ ሊባል ይገባል ወይም እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ነው የሳቱት" የሚለው እና ለራስ የመማር ዕድልን መንፈግ ፍጹም የሆነ ስንፍና ነው። ይሄ ነገ ተመሳሳይ ጥፋት ለማጥፋት የሚሰጥ ማረጋገጫ ነው። እንዲህ የሚል ሰው ነገ በተመሳሳይ ወይም በባሰ ጥፋት ላይ ታገኙታላችሁ።


ለምሳሌ ሁሉም ሰው "ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያሻግረናል" ብሎ ስላመነ፤ "የኔም በሰዓቱ እንዲህ ብሎ መቀበል እና ማመን ችግር የለውም" የሚል ሰው፤ ነገም ተመሳሳይ ጥፋት የሚያጠፋ ሰው ነው።

ይሄ ልጆች ያላቹ ወላጆች ዘወትር የሚገጥማችሁ የስንፍና መልስ እኮ ነው። "ስልክ አይቻልም፣ አይሰጣችሁም!" ስትሏቸው ለልጆቻችሁ ፥ ስልክ ጎበዝ ተማሪ ለመሆን እንዴት አስፈላጊ እና ጠቃሚ እንደሆነ አይደለም የሚያብራሩላችሁ። ይልቁንስ የሚሏቹ አንድ ነገር ነው። "ሁሉም ተማሪዎች ትምህርት ቤት ውስጥ ስልክ አላቸው፤ ሁሉም ናቸው እንደዛ የሚያደርጉት ስለዚህ እኔም እንደ ሁሉም ልሁን።" ይሄን የልጆች መልስ ነው ዛሬ አዋቂ ስንሆን የምንመልሰው።


በሕይወት መንጋነትን ከሰዎች ልታስቀሩ አትችሉም። ማስቀረት የምትችሉት እናንተ መንጋ አለመሆንን ብቻ ነው። ሕዝብ አለመሆንን ግን ማስቀረት እንችላለን። ልጆቻችንም ገና ልጅ እያሉ መማር ያለባቸው ብቻቸውን የመቆም ብቃትን ነው። ሁሉም ስለተሳሳቱ የኛን ጥፋት፤ ለጥፋቱም የምንቀበለውን ቅጣት ዝቅ አያደርገውም። ተፈጥሮ ለዚህ ዓይነት የጅልነት ምክንያት ቦታ የላትም። ሁሉም ርቃኑን ነው ብሎ ዝናብ ከመዝነብ አያቆምም። ማንም መጠለያ የለውም ብሎ የተፈጥሮ ዑደት አይታጎልም። ስለዚህ ይሄ ሰበብ እራሳችንን ለማጽናናት የስነልቦና ጥገጋ ብቻ ነው የሚያደርገው። መማር የሚፈልግ ሰው ደግሞ ከእንደዚህ ዓይነት የስነልቦና ሕክምና ራሱን ያርቃል። መማርን የሚወድ ሰው ርቃኑን የመቆም ድፍረት አለው። "ጠቢብን ተቸው ይወድሃል" እንዳለው ጠቢበኛው ሰሎሞን "ሰነፍን ደግሞ ተቸው ይጠላሃል" ነው መልሱ።


ለመማር እና ለመለወጥ የሚፈልግ ሰው ከብዙ ሰዎች ጋርም ይሁን ብቻውን ጥፋት ካጠፋ ኋላፊነት ከመውሰድ ፈጽሞ አይቆጠብም። ከጥፋቱ ለመማር እንጂ የሚቸኩለው ፥ ስለሚሰማው ስሜት አይደለም። በጓደኝነትም ሆነ በማንኛውም አጋርነት ውስጥ ፈጽሞ ማራቅ ያለብን (ዕድሉ ካለን እና ከቻልን) ስለምንሰጣቸው ትችት ከጥፋታቸው በላይ እንድንጨነቅ የሚያደርጉን ሰዎችን ነው። እነዚህ ለለውጥ እና ለዕድገት ጸር ናቸው። ቁስላቸው ከመዳኑ በላይ የሚጨነቁት ፥ ቁስሉን እንድናሻሽላቸው ነው።


 ስንናገር በነጻነት እንድንናገር የማይፈቅዱልን እና ያን safety (ደኅንነት) የማይሰጡን ሰዎች ሕይወታችንን በመጨረሻ ሲዖል ያደርጓታል። በሕይወት (በተለይ ግብ ላለው ተልዕኮ) ከፍትፍቱ በላይ ስለፊቱ መጨነቅ የለብንም። እርሱ የቢዝነስ ደንበኛ ለማያዝ እንጂ ለሕይወት አጋር አይሆንም።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Jul 28, 2024
  • 3 min read




ይሄ ሕይወት እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የምንኖርበት አይደለም፤ ከኛ በኋላም ብዙዎች እኛ ዛሬ የሚያሳስበን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳስባችዋል። ሞኞች የሕይወትን ውጣ ውረድ ልክ እነሱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ ያህል ይጋፈጡታል። ብልሆች ግን ከሆነው አንዳች ያልሆነ፤ አዲስም የሚሆን ነገር እንደሌለ ይገነዘባሉ። ከንቱ ነው ፥ አይደለም ማለት የሞራል ፍርድ ነው። የዚህ ጹሁፍ ዓላማ የሞራል ፍርድ መስጠት አይደለም። እንደብዙዎቹ የሰንበት ዕይታዎች ሕይወትን እንደሆነው ለማየት መጣር እንጂ። ግን ማበብም መጠውለግም የሕይወት አካል ነው። ሁለቱም ውበት ናቸው። አንዱ ካለአንዱ ትርጉም አይሰጥም።


በተቻለ መጠን ሕይወትን በምልአት ለመረዳት መጣር ከብዙ ድካም ያድናል። ማለትም ሕይወት ፊዚክስ፣ ቦይሎጂ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ሕግ ወይም ሳይኮሎጂ እያለ ተከፋፍሎ አይንቀሳቀስም። በሕይወት ውስጥ እነዚህ ነገሮች ተከፋፍለው የሉም። ሁሉም በአንድነት በሁሉም ቦታ በጥምረት፣ ያለመለያየት በውህደት ነው የሚሰሩት። እኛ ለመረዳት ከፋፈልነው እንጂ።



ስለዚህ ትልልቅ ነገሮችን ልክ ለመሆን ትልልቅ ሀሳቦችን በአግባቡ መረዳት ወሳኝ ነው። ፒተር ካፉማን ሁለት ትልልቅ ሀሳቦችን ያነሳል፦ (1) መልካምነትን ማንጸባረቅ (መልካም ሁን ደግሞ መጀመሪያ አድርገው) (2) ዘላቂ በመሆን ፥ ትንንሽ ድሎችን ሰብስብ። የዘመናት የአሸናፊነት ጥበብ ከእነዚህ የሚመነጭ ነው። ሁልጊዜ መጀመሪያ መልካም አድርግ ከዛ ደግሞ ይሄን ሁልጊዜ አድርገው።



ይሄ ቀላል ይመስላል። ነገር ግን በሕይወት በጣም ከባባድ ነገሮች መፍትሔያቸው ቀላል ነው። ቀሊል መሆንም ነው በጣም ከባዱ ነገር። እስቲ ይሔን ለመረዳት ራሱ ካፉማን ከሚለው እንነሳ። በሕይወት በጣም ወሳኙ ነገር ዘርፈ ብዙ አዋቂ መሆን ነው። ያ ደግሞ መታወርን ይቀንሳል። ማለትም እውነተኛ አሳቢ ማለት ነገሮችን የሚረዳ ነው። ምክንያቱም በተረዳንበት ነገር ስህተት ሰርተን አናውቅም። መረዳት ማለት ደግሞ ማድረግ ያለብንን ነገር ማወቅ ነው። በአንድ ዘርፍ ብቻ አዋቂ መሆን ማለት በኩሬ ውስጥ እንዳለች እንቁራሪት መሆን ነው። ለዚህች እንቁራሪት ውቅያኖሱ ኩሬው ነው። ኩሬው ነው ሁሉ ነገርዋ። እቺ እንቁራሪት የምትወስነው ውሳኔ ሁሉ ከኩሬው የሚሰፋ አይደለም።



በሕይወት ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ማድረግ ያስፈልጋል። የመጀመሪያው ሁልጊዜ መልካም መሆን። ግን እሱ ብቻ ሳይሆን መጀመሪያ መልካም መሆን። ሳንቀደም መልካም ሆኖ መቅደም። ድመትን በጭራዋ ያዟት። የሚከተለውን መገመት ከባድ አይደለም። ለመማር ግን ጥሩ ነው። ሁለተኛ ድመትን በጭራዋ በኩል አትይዟትም። ድመትን በጭራዋ በመያዝ ለድመት የምትነግሯት ነገር ወዳጅዋ እንዳልሆናችሁ ነው። አያያዛችሁ ለጥሩ እንዳልሆነ ነው። ደግሞ አሻሾት። መጀመሪያ በጥሩ ሁኔታ ዳብሷት። ከዛ በምላሷ ልትልሳችሁ ፥ ልትተሻሻችሁ ትጠጋለች። ለምን? አሁን መልካም ሆናችዋል። መጀመሪያ መልካም ሆናችሁ ቀርባችዋል። በመልካምነት ቀደማችሁ። ይሄ በሕይወት እጅግ ሩቅ መንገድ ያስጉዘናል። በመልካምነት ቅደሙ። ለዛ ሰው ምን መልካም ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ። ምን መልካም ላድርግለት ብላችሁ አስቡ። ይሄ ሰው ገንዘብ ይሰጠኛል ወይም ምን አገኝበታለሁ ሳይሆን ምን ልጥቀመው ብላችሁ አስቡ። የምታገኙት ውጤት አስገራሚ ነው የሚሆነው። ብዙ ሰው ግን በተቀራኒው በየቀኑ የሚሰራው በብዙ ሰው ለመወደድ እንጂ ብዙ ሰው በቀን ውስጥ ለመውደድ አይደለም። እስቲ ሌላው ሰው የሚሰማው ስሜት እና ሌላው ሰው የሚፈልገው ነገር ይሁን የመጀመሪያው ግባችን። ያ ሁሉን ነገር ሲለውጠው ታያላችሁ።



ሁለተኛ ዘላቂነትን በሕይወት ውስጥ መለማመድ ነው። የማናቋርጠው ነገር ምን አለ። ታላቅ ሰው አሳዩኝ። በሕይወት ያላቋረጠው ነገር ብቻ እዛ ደረጃ እንዳደረሰው አሳያችዋለው። ውሻችሁን በተከታታይ በሆነ ሰዓት መግቡት ከዛ ደግሞ በሌላኛው ቀን ዝለሉት። የሆኑ ቀናት ተንከባከቡት ከዛ ደግሞ ዝለፉት። ምን እንደሚሰማው ታውቃላችሁ? ምንም ወጥ ባህሪ አታዩበትም። ስለ እናንተ ምንም መገመት ስለማይችል ውሻውም የማይገመት ይሆናል። ኒሮቲክ እና ፍጹም አስቸጋሪ እንዲሁም ፈሪ ስለሚሆን ፈጥኖ መተናኮል ይጀምራል። ይሄ ለሰውም ተመሳሳይ ነው። በመልካም ባህሪው ያልቀጠለ ሰው ከክፉ ሰው በላይ ሰዎች ይጠሙበታል። ምክንያቱም የማይገመት ነገር ለሰው ልጅ አዕምሮ አስፈሪ ነው።



በሞኝነቱ የቀጠለ ሞኝ ጠቢብ ይሆናል ይባላል። ጀምረን ያልቀጠለው ነገር ነው ባብዛኛው የጸጸት ውጤት። የዛሬ ውድቀት ወይም የፈለግንበት ያለመድረስ ምክንያት ጀምረን ያልቀጠልነው ነገር ነው።


 


እነዚህን የሰንበት ዕይታዎች መጻፍ ለእኔ ወጪ አለው። ዌብሳይት ያስከፍለኛል። ረፈት አልባ የሆነውን የደንበኞቼን ስልክ (ገንዘብ የሚያስገባልኝን) ለጊዜው መግታት ያስፈልገኛል። ከዛ ደግሞ ትርጉም የሚሰጥ እና የታሰበበት ነገር ለመጻፍ መጨነቅ ይሻል። ይሄ ሁሉ ስለሌላው ማሰብን፣ ሌሎች እንዴት ከዚህ ጹሁፍ እንደሚጠቀሙ መጨነቅን እና ያ ከምንም ነገር በላይ ታላቅ ዋጋ እንዳለው ከልብ መገንዘብን ይጠይቃል። ከዛ በላይ ለጊዜው መጎዳትን ይሻል። በመጨረሻም ሰዎች ሲሪየስሊ እንዲወስዱን ፥ አለማቋረጥ እና ዘላቂ መሆንን ማሳየት ይፈልጋል። ይሄ ሁሉ መልካምነትን መጀመሪያ ለማድረግ፣ ቀላል የማይባሉ ሰዎች መጀመሪያ ከንቱ ልፋት አድርገው ሲወስዱ ያን ለመቀበል መዘጋጀት እና መጽናት ይጠይቃል።



ሕይወት ውቅያኖስ ናት። ከኩሬው ካልወጣን በቀር ካለንበት ጣሪያ በላይ እምብዛም ተሻግረን ማሰብ አንችልም። ይሄ ሕይወት ረጅም ነው። ብቻችንን ከሄድን ቶሎ ልንሄድ እንችላለን ብዙ ርቀት ግን አንጓዝም። ሌሎች አብረውን እንዲጓዝ ከፈለግን ደግሞ የሌሎችን ፍላጎት ማስቀደም ይኖርብናል። መልካም መሆን ብቻ ግን አይደለም ከሌሎች በፊት መልካም መሆን እንጂ። ግን ደግሞ ሰዎች በቀላሉ አያምኑንም ስለዚህ በበጎ ባህሪያችን መጽናት ይጠይቃል።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page