top of page
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Jul 14, 2024
  • 2 min read



ከማኬቬሌ እስከ ሀገራችን ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ድረስ የሚነግሩን ሕዝብ እና ሰው የተለያዩ መሆናቸውን ነው። ሁለቱም ስለሰው ባህሪ ብዙ የጻፉ ናቸው። ግን ሕዝብ ሰው አይደለም ብለውናል። ከበደ ሚካኤል ጎርፍ ሲለው ማኬቬሌ የሚወደውን የሚያጠቃ ፍጥረት ነው ይለዋል። በርግጥ ከሩቅ ሲታይ ሕዝብ የነጠላ ሰዎች ጥርቅም ይመስላል።የሰዎችን ባህሪ ካወቅን ደግሞ ሕዝብ እንዴት መልስ እንደሚሰጥ ማወቅ አይከብደንም ልንል እንችላለን። ግን ሕዝብ የሰዎች ስብስብ ቢሆንም እንደሰዎች አያስብም። ለግለሰቦች የረፈደው ሰዓት ለሕዝብ ገና ልጅ ነው። ለግለሰቦች ጥሬ የሆነው ለሕዝብ በስሎ ጎርምቷል። ሕዝብ የማይታወቅ የማሰቢያ ቅል አለው። የሚመቆው እና የሚበርደው፣የሚገነፍለው እና የሚረጋው በምክንያት አይደለም። ምክንያት ከሕዝብ ጋር አይስማማም። ሕዝብ ከፍ ለማለት መሰላል ሊሆን ይችላል ፥ ከፍ ብሎ ጸንቶ ለመቆም ግን መሠረት አይሆንም። ሕዝብ ከላይ አውርዶ የሚጥል ንፋስ ሊሆን ይችላል ፥ቀብሮ የሚያስቀር የመቃብር ድንጋይ ግን አይደለም።

 

ሕዝብ ማለት ራቆቱን ያየውን ንጉስ እንደ ለበሰ እና ከመልበስም በላይ በውብ አቻ በማይገኝለት መከናነቢያ እንደተጎናጸፈ ለማመን ምንም ሰቀቀን የለበትም። ፈቅዶ ለመታወር ሕዝብ አያመነታም። እጅግ ምክንያታዊ እና አስተዋይ ሰው ፥ ሕዝብ ሲሆን ጠባዩ ይቀየራል። ምክንያትም፣ ማስተዋልም መለያዎቹ መሆናቸው ይቀራሉ። ሕዝብ የራሱ መልክ እና ጠባይ አለው። የአመለከውን ለመስቀል፣ የሰቀለውን ለማምለክ ለሕዝብ ምንም አይቸግረውም።

 

ከሃምሳ ዓመት በላይ ሕዝብ ሲወርድ ሲውጣ እርሱ ግን ከቢዝነስ ስኬት ወርዶ የማያውቀው ዋረን በፌት እንዲህ ይላል፤ “ሌሎች  ስስታም ሲሆኑ አንተ እጅህ ይፈታ ፥ ሌሎች እጃቸው ሲፈታ ደግሞ አንተ ስስታም ሁን።” በዚህ ዓለም ላይ ከባዱየቤት ሥራ እውነትን ማወቅ ነው፤ አንድ ግን እውነት የማይገኝበትን ቦታ ልንገራችሁ ፥ ከሕዝብ ዘንድ። እውነት ወዴት እንደሆነች ማወቅ ቢሳናችሁ፤ ፈጽሞ መሆን የማትችልበትን ቦታ ግን እናውቃለን። ከሕዝብ ዘንድ። እውነትን የሚፈልግ ሁሉ ከሕዝብ ውጪ መፈለግ ይኖርበታል። ሕዝብ ሰፊ መንገድ ይፈልጋል፤ ምክንያቱም ጠባብ አይበቃውም።

 

የአይሁድ ሸንጎ ያደረገው እኛ በየቀኑ የምንለውን ነው። “ይሄ ሁሉ ሰው እንዲህ እያመነ አንተ እንዴት ትለያለህ” ብለን ብዙ ጊዜ እናውቃለን። “አረ ሰው ምን ይልሃል!” የሁልጊዜ ቋንቋችን ነው። ይሄ የአይሁድ ሸንጎ ፍርድ ነው። ግን የኛም ፍርድ ነው። የቀያፋ ፍርድ ነው ይሄ። ብዙ ነገራችን በየዕለት ሕይወታችን በሕዝብ ውሳኔ የተመራ ነው። ምክንያቱም ሕዝብ ማሰብን አይወድም መመሳሰልን (conformity) እንጂ። እውነት ግን በተቃርኖ ወይም ኢደመነፍሳዊ ውስጥ ነው ያለችው።

 

የተቃርኖ ጌታ ራሱ የእውነት ጌታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “ማንም ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።” “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ መጨረሻ ይሁን።” “ጌታም መሆን የሚሻ ባሪያ ይሁን” አለን። “ሸክም የከበዳችሁ ኑ ወደ እኔ የእኔን ቀንበር በትከሻችሁ ተሸከሙ የዛኔ ታርፋላችሁ”አለን ማረፍ ቀንበር በመሸከም መሆኑን ሲነግረን። “የሚሰጥ ከሚቀበል በላይ ይበለጽጋልም” አለን። እነዚህ ሁሉከሕዝብ የተለዩ እውቀቶች ናቸው። እውነቶች ናቸው ከሕዝብ ጋር ግን የማይሄዱ። የሞቀ ውሃ ከቀዝቃዛ ውሃ ቀድሞ በረዶ እንደሚሰራ በሳይንስ እናውቃለን። የሚጨው ውሻ እምብዛም እንደማይናከስ ከልምዳችን ደርሰንበታል።በተመሳሳይ ፥ ሪያሊቲ ያለው ለስሜታችን በቀረበው እና በሚመስለው ውስጥ አይደለም። ከደመነፍሳችን ተቃራኒ ስንሄድ ነው፤ ከሕዝብ ውጪ ለመቆም ስንደፍር ነው ሪያሊቲን ማየት የምንችለው።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Jul 7, 2024
  • 3 min read



ምንአልባት በብሉይ ኩዳን ወደ እርሷ ተመልከቱ ከተባልነው ፍጥረት መካከል ጉንዳን ብቸኛዋ ሳትሆን አትቀርም። ከልጅነቴ ጀምሮ በጉንዳኖች እደነቃለሁ። በጣቶቼ ጨፍልቄ እስከምገላቸው ድረስ ተስፋ ሳይቆርጡ መንገድ እየቀየሩ የሚጓዙ ነበሩ። ፍጥነታቸውን ለመግታት በእነሱ ዓይን የሰማይ ስባሪ የሚያህል ጣቴን በመንገዳቸው ላይ ስደቅን ወዲያው በጣቴ ወደ አልተዘጋው ቦታ አቅጣጫ ቀይረው ለመጓዝ ይጥራሉ። መድከም፣ መቆም አላይም። ከእነሱ በመጠን ፍጹም ከሚበልጠው ጣቴ ጋር እምብዛም ሲላተሙ እና ጉልበት ሲጨርሱ አላይም። ወደ አልተዘጋው፣ ወደ ሌላው ክፍተታ ያለብዙ ጊዜ መግደል ይነጉዳሉ እንጂ።

 

“አንተ ታካች ፥ እስከ መቼ ትተኛለህ?” “ወደ ጉንዳን ሂድ ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን።” ይለናል ጠቢበኛው ሰሎሞን። (ምሳ 6፥6)። ዝንብን ደግሞ በተቃራኒው ተመልከቱ። የእናንተን ትዝታ አላውቅም፤ የእኔ የዝንብ ትልቁ ትዝታ ግን ልጅ ሆኜ በክፍሌ ተኝቼ ሳለው ከመስታወት መስኮት ጋር እየተጋጩ የሚፈጥሩት ድምጽ እና አላስተኛ የሚሉኝ ነገር ነው። ወደ ውጪ ለመውጣት ከመስታወት መስኮት ጋር እየሄዱ ሲላተሙ እና ከዛ ደግሞ መውጣት ሲሳናቸው የሚፈጥሩት ድምጽ፣ በመጨረሻም ከመስታወቱ ጋር አብዝተው በመላተም ከታች ወድቀው ሲሞቱ ነው የማስታውሰው።


ትንሽ ዞር ቢሉ ሰፊ በር ነበር ወደ ውጪ የሚያወጣቸው ግን በቀለማት የሸበረቀችው ዝንብ ይሄ መች ታይቷት። ከመስታወት ጋር መላትም እና የማታሸንፈውን መግጠም ነው ተግባሯ። ምንአልባትም ያ የሚመር እንቅልፍ የሚነሳ ድምጽ የዝንብ ማማረር ይሆናል።


ወደ ጉንዳን ተመልከቱ ይለናል ታላቁ ንጉስ ሰሎሞን። በዙሪያው ካሉ ግዙፍ ነገስታት በላይ፣ ከሚቀድሙት ታላላቅ አበው በላይ፣ በጫካው ንጉስ ተብሎ ከሚያጎራው አንበሳ በላይ ፥ ትንሻ ነፍስ፣ እጅግ ትንሻ ፍጥረት የጥበብ ጅረት ሆና እየታየችው።

 

አስቂኝ ፍጥረት ነን። ዓለምን እንደሆነው ለማየት እና ለማወቅ የምንጥር ሳንሆን በአይዶሎጂ እና በቲዎሎጂ መነጽር አጥበን ለማየት የምንፈልግ፣ እውነትን ላለመጋፈጥ ሩቅ መንገድ የምንሄድ ነን። ዓለም ያልሆነችውን በፍልስፍና ዓይን እናያታለን። ቻርልስ ኬተሪንግ ከ300 በላይ የፈጠራ ውጤቶችን በማግኘት ለሁሉም የፓተንት መብት ያገኘ አስገራሚ ሰውነበር። ኬተሪንግ እንዲህ ይላል “ሰዎች በተማሩ ቁጥር ይደድባሉ።” (ይሄ የዩኒቨርስቲ ትምህርትን ሲያመለክት ነው)።

“ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩን አንድ ትልቅ ትምህርት ውድቀትን መፍራት ነው” ይላል ኬተሪንግ። ውድቀትን መፍራት ደግሞ የፈጠራ ጠላት ነው። ስለዚህ ማነብነብ ይሆናል እውቀት፣ መሸምደድ እና ሌሎች የሄዱበትን መንገድ ማጥናት ይሆናል እውቀት።

 

ጉንዳንን የጥናቱ ተልዕኮ ያደረገው ጠቢበኛው ሰሎሞን ከታካች ሰው በተሻለ ወቅቶችን በማጥናት ለነገ ሳይቀር እንዴት እንደሚሰበስቡ ይነግረናል። በተለይ ድህነት እንደ ወንበዴ ፥ ችግርም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ጠላት የሚመጣበትን ሰው እየተመለከተ ፥ “አምላክ ሆይ ምን አደረኩ” በማለት "ዕድሌ ነው፣ ምኔ ነው” እያለ ከጉንዳን አንሶ ሲያየው ፥ “ተነስ አንተ ታካች ወደ ጉንዳን ሂድ፣ ጉንዳንን ተመልከት” ይለዋል።

 

ጉንዳኖች ከሁሉም በላይ የሚያውቁት የሚመስለኝ ነገር ይሄ ዓለም ከእነሱ በኋላም እንደሚቀጥል ነው። ከሁሉም በላይ የሚረዱትም እነሱ ጉንዳን እንደሆኑ ነው። ይሄን ዓለም እኛ አልፈጠርነውም። ይሄ ዓለም ፍትሐዊ ላይሆን ይችላል። ይሄ ዓለም ብዙ የማንፈልጋቸው እንቅፋቶች ሊኖሩበት ይችላል። የምታመልኩትም ፈጣሪ ይሄን በማድረጉ ልትወቅሱት ትችላላችሁ። ግን ማወቅ ያለብን ነገር ይሄ ዓለም የእኛ ብቻ አይደለም። ስለዚህ እኛ እንደምንፈልገው የመሆን ግዴታ የለበትም። ይሄ ዓለም የእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር በራሱ መንገድ ነገሮችን ይሰራል። እኛ የተሻለ መንገድ ሊኖረን ይችላል። እኛ ግን የራሳችን ዓለም የለንም።


የኛ ድርሻ ይሄን ዓለም መረዳት ነው። ማወቅ በምንችለው መጠን ይሄ ዓለም እንዴት እንደሚሰራ መገንዘብ ነው። የዛኔ ብቻ ነው ዝንብ ከመሆን ጉንዳን ወደ መሆን የምንለወጠው። ከዚህ ዓለም ጋር ከመላተም ይልቅ አጋራችን የምናደርገው። አሁን ላለንበት ኃላፊነት በመውሰድ ፥ ከተዘጋው ጋር ከመደባደብ የተከፈተውን ለማማተር እልፍ የምንለው።

 

ጠቢበኛው በጉንዳኖች የተደነቀባቸው ሌላኛው  “አለቃና አዛዥ ፥ ገዢም” ሳይኖራቸው ሥርዓትን አለማጣታቸው ነበር። “መሪ ስለሌነን ነው ወይም መሪ ነው የጎደለን” የሚለው መነዛነዝ የታካች ሕዝቦች መገለጫ ነው። የሌለው ነገር እንዲገልጸው የሚፈልግ ሁሉ ፥ ውድቀት እና ሽንፈት መጎናጸፊያው እና ዘውዱ ናቸው። ስለሌለን ነው ለማግኘት የታገልነው። ተፈጥሮ ካደረገችልን ትልቁ ውለታ ውስጥ ብዙ ጉድለትን መስጠቷ ነው። ጉድለት ነው፣ ማጣት ነው የሕይወት ጉዞ ውበት። ሕይወትን መተኛት ብቻ ያላደረግናት፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥምረት ያስፈለገን፣ መደራጀት እና መማር፣ መሰልጠን ያሻን ፥ ጉድለት የሚባል ትልቅ ስጦታ ስለተሰጠን ነው። ሕይወት ከዋለችልን ትልቁ ውለታ ውስጥ ማጣትን፣ መጉደለን፣ እንከንን የሚያህል ነገር ያለ አይመስለኝም። ሕመም ነው የጤና ውበት። ረብሻ ነው የሰላም ጌጥ። ረሀብ ነው የማግኘት ፈንጠዝያ። ጉንዳኖች ታካች ለሆንን የሚያስተምሩን ይሄን ነው። “ተነስ አንተ ታካች ፥ ወደ ጉንዳኖችም ሂድ። ተመልከታቸውም።”

 

 

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Jun 30, 2024
  • 2 min read

Updated: Jul 27, 2024



የሃርፐር ሊን To Kill a Mockingbird እያነበብኩኝ፤ እንዲህ ይላል “ከዛ ሰው የእይታ አድማስ ነገሮችን ለመረዳት እስካልሞከርክ ድረስ ፈጽሞ ሰውን ልትረዳው አትችልም።” ... “በቆዳው ላይ እስካልወጣህ ድረስ ፥ በዛ ቆዳ ውስጥ እስካልተራመድክ ድረስ መረዳት አትችልም።”

 

በዚህ ምድር ላይ የአንዱ ሰው የሕይወት ታሪክ በተወሰነ ደረጃ እና መልኩ ብቻ ነው ለኛ ትምህርት እና ጥቅም የሚኖረው። ሕይወት ለያንዳንዳችን ልዩ ናት። እኛን የሚመስል ሰው ፈጽሞ አልተወለደም። አይወለድምም። በመልክ እና በቅርጽ ወይም በማንነት እና ባስተዳደግ ብዙ ብንመሳሰል እንኳ ፥ አሁንም ልዩ ነን። የኛን ልምድ እና ያን ልምድ የመገንዘቢያ ውቅራችንን የሚመስለው የለም። በሚገርም ሁኔታ ልዩ ነን።


ሁለት መንታ ልጆችን ብትወስዱ፣ በተመሳሳይ ወላጆች ያደጉ፣ ተመሳሳይ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት እየበሉ፣ ተመሳሳይ የልጅነት እና የዕድገት ሂደትን ያለፉ፣ ከተመሳሳይ የመጽሐፍ መደርደሪያ መጻሕፍትን ያነበቡ ሁለት ልጆችን ብትወስዱ እንኳ የተለያየ ስብዕና ታገኛላችሁ። አንዱ የሕይወት ውጣ ውረድ አውጠልጥሎት ሲወድቅ አንዱ ደግሞ እነዛን መከራዎች እንደመሰላል ከፍ ላለ የሕይወት ልዕልናዎች መወጣጫ ሲጠቀመው ታገኙታላችሁ። አንዱ በትንሽ ነገር ሲደሰት እና ሲዝናና ስታገኙት አንዱ ደግሞ ሲጨነቅ ታዩታላችሁ። በመልክ መመሳሰላቸው ሕይወት ለእነሱ በምትሰጠው ግብረ መልስ እንዲመሳሰሉ አያደርጋቸውም።

 

በመንታዎች መኃል ይሄን ያህል ልዩነት ካየን ደግሞ በዚህ ሕይወት ውስጥ ብዙ የሚለያይ የሕይወት ልምዶች ያሉን ሰዎች እንዴት ዘርፈ ብዙ ማንነቶች እንደሚኖሩን ገምቱ። ለዚህ ነው ካርል ዩንግ ሰዎችን መርገም እና መተቸት እምብዛም ረብ የለውም የሚለው። ሰዎችን ከመረዳት እና ከመቀበል ውጪ ብዙም ዕድል የለንም።

 

ብዙ ጥረታችን እና ልፋታችን የሚባክነው ግን ለመረዳት እና ለመቀበል ሳይሆን ሌሎችን ለመለወጥ ነው። የብዙ ማህበረሰብ ትልቁ ኢንቨስትመንቱ ሰዎችን የማረሚያ እና የመለወጪያ ተቋሞችን መገንባት ነው። የራሱ ሕይወት ተገልጦ ቢታይ ፈጽሞ በሰው ፊት ሊቆም የማይችለው ሰባኪ ፥ የተሰባኪውን ሕይወት ለመለወጥ የጥቅስ እና የተግሳጽ ናዳ ያወርዳል።

 

ትልልቅ ወንጀል እየሰሩ ሕዝብን የሚያስተዳድሩ ዘራፊ ፖለቲከኞች ቀላል የማይባል የሀገሪቷን ገንዘብ የሚመድቡት ለማረሚያ ተቋሞች ነው። በብዙ ማህበረሰብ ውስጥ የወላጆች ተቀዳሚ ሥራ ልጆችን ማረም ይመስላል። ትምህርት ሳይገባን ሲቀር ወይም የማስተማር ዘይቤው ሳይጥመን ሲቀር በምናሳየው ባህሪ የሚቀጡን መምህራን ነበሩን። ቅጣት እና ዱላ የአዕምሮን በሮች ይከፍት ይመስል።

 

በፍርድ እና በብየና የተዋቀረ ስነልቦና ነው ብዙዎቻችን ያለን። ግን ሁላችንም፣ ቀጪዎቹ እና ፈራጆቹ ሳንቀር የምንፈልገው አንድ ነገር ቢኖር እንዲሁ እንዳለን የሚቀበለን ሰው ነው። ምንም ምንም ፍርድ ሳይሰጥ፣ምንም ምንም በውስጡ ስለእኛ አሉታዊ ነገር ሳይቋጥር እንዳለን የሚቀበለን ሰው ነበር የሁላችን መሻት። ከተራራ ላይ ስናይ ከታች ያሉ ቤቶች ያረጀው ክፍላቸው ሳይቀር ሊታየን ይችላል። ግን የቆምንበት ተራራ ነው ያን ሁሉ የሰው ጉድ ያሳየን እንጂ የኛ ከፍታ አይደለም። እኛ ከቆምንበት ተራራ በላይ ቆሞ የሚያየን ደግሞ የኛን ዝገትን ያያል። በዛ ተራራ ላይ ቆሞ የሚያየን ሁሉ ያ ዝገት የሕይወት ጉዞአችን የውጣ ውረድ ውይብና እንደሆነ እንዲቀበለን ነው የምንፈልገው።

 

ለዛ ዝገት ላለው ሕይወት ክብር ነው የሚገባው።ለውጣ ውረዳችን እና ለሕይወት ልምዳችን ፍርድ ሳይሆን መረዳት፣ ነቀፋ ሳይሆን መቀበል፣ ውግዘት እና ምክር ሳይሆን ግንዛቤን ነው ይምንሻው።


ትችት አይለውጥም ይጨቁናል እንጂ። ነቀፋ ከክፉ ባህሪ ነጻ አያወጣም ለሀፍረት ያስገብራል እንጂ። የሚተቹ እና የሚነቅፉ ሰዎች ለጎሰቆለው ሕይወት ወዳጅ እና አጋር ሳይሆኑ ጨቋኞች እና አስገባሪዎች ናቸው። የራሱን ጨለማ ክፍል ማየት ያልቻለ ሰው ግን ረጋሚ እና ጨቋኝ ነው የሚሆነው። በርሱ ውስጥ ያለውን የክፋት ጥግ እና የእንክርዳድ ማሳ ማስተዋል ያልቻለ ሰው ፥ ሌላውን ሰው መቀበል ይቸግረዋል።

 

ለዚህ ነው የመምሰል ሕይወት አሰልቺ እና አድካሚ የሚሆነው። ፍጹም ልዩ የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በሌላው ሰው ቁመት እና ወርድ ሲለካ እና ያን ለመሙላት ሲጥር ይባክናል። ይሄ ሕይወት ስጦታ ነው። በተለያዩ ሰዓቶች የተጠሩ ሰዎች ሕይወት በተባለ ማሳ ላይ ተሰማርተዋል። ማንም በርሱ ያለው መልካም ማንነቱ እና ውብ ስብዕናው እንዲያድግ እና እንዲለመልም እንደሚፈልገው፤ በወቀሳ በሚወቅረው ዓለም ፊት ግን ሕይወት ራሱ የፍትሕ እጦት ፍሬ ሆና ነው የምትታየው።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page