top of page
Search

“ከሚቃጠለው እሣት ባያድነን እንኳ ፥ ለአቆምከው ምስል አንሰግድም!”

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • 15 minutes ago
  • 3 min read
ree


እ.ኤ.አ. በጁላይ 2021 የተጻፈ እና በድጋሚ የተለጠፈ



በመንፈሳዊ ሕይወት ያደኩት በሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ነው። በዕድሜም በብዙ ንባብም መጎልመስ ስጀምር፣ በጉዙዎቼ ከብዙ አገራት ሰዎች ጋር ጥልቅ ውይይቶችን ሳደረግ መንፈሳዊ ብዬ ከተቀበልኩት ነገር ብዙ ለውጬያለው። አንዳንድ ከራሴ ጋር ያደረኩዋቸው ውይይቶች ለራሴ እስከሚያስፈሩኝ ድረስ በሀሳብ ተወስጄባቸዋለው። ካርል ዩንግ እና የሱን ፍልስፍና በስፋት ያስፋፋቱ እንደ አላን ዋትዝ እና ያን ፒያት እንደነገሩን በልጅነታችን ያለንን ስሪት በጣም እጅግ በትንሹ ብቻ ነው መለወጥ የምንችለው። አድካሚ “የኢንቴሌክቿል” ጉዞ ከሄድን መድረስ የምንችለው ራሳችንን ማወቅ ላይ ብቻ ይሆናል። ይሄ በልጅነት እንዴት እንደተሰራን ጥቃቅን ነገሮችን ሳይቀር በማስታወስ የሚደረግ አሰጨናቂ ጉዞ ነው።



ካርል ዩንግ ራሱን ለማወቅ በወንዝ ዳር እንደ ሕጻናት ጭቃ እያቦካ በመጫወት ሕጻን እያለ የተሰሙትን ስሜቶች ከ“unconscious” አዕምሮ ፈልቅቆ ለመረዳት በመጣር የሚሰማውን ስሜት ይመዘግብ ነበር።



አንድ ነገር ዘወትር አሰላስላለው። ቅዱስ ገብርኤል በእኔ ባህሪ ላይ ያለው ተጽዕኖ። በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ገብርኤል የጽናት ምሳሌ ነው። “ንቁም በበህላዌነ ፥ ባለንበት ጸንተን እንቁም” ብሎ ዓለም በአምላክ ቃል ከጸናች በኋላ ከፈጣሪ ቀጥሎ ጽናትን ያወጀ መላክ ነው። ከእሱ እና ከሌሎች ቅዱሳን በኃይሉ የገዘፈው የሳጥናኤል ግርማ ሳይረታው አምላኩን እስከሚያይ የጸና ፥ ያጸና መላዕክ ነው። ያዳናቸው ቅዱሳን ሁሉ የሱ ባህሪ አለባቸው። ፊት ለፊታቸው የገጠማቸው ጠላት ታይቶ የማይታወቅ ግዙፍ፣ ብዙዎች የተርበደበዱበት እነሱ ግን የመዳን ተስፋ እንኳ ርቋቸው ለእምነታቸው መከራውን ለመቀበል የተዘጋጁ ሰዎችን ነው በቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በዓላት የሚዘከሩት።



በሌላ አነጋገር ከልጅነቴ ጀምሮ እምነት እና አሸናፊነት ተለያይቶ ነው ስሰበክ የነበረው። ለሆነ ነገር ዋጋ የምትከፍለው እንደምታሸነፍ ስለምታምን ሳይሆን ያ ነገር “አንተነትህን” ስለሚወስን ነው። ሠልስቱ ደቂቅም ሆኑ ሕጻን ቂርቆስ እንድናለን ብለው ወደ እሳት እና የሚንተከተክ ውሃ ውስጥ አልገቡም። ለእምነታችን መሞት ነው አሸናፊነት ፥ ብንድንም ፥ ባንድንም ለእኛ ግዳችን አይደለም። ለእኛ ዋናው ነገር “እምነታችን” ነው ያሉ ቅዱሳን ናቸው። ከዓመት ዓመት ያለመስልቸት የምንሰበከው እነዚህ ታሪኮችን ነው። በጽናት ስለቆመው መላዕክ እና ባንድንም ለማናምንበት ነገር አንበረከክም ስላሉ ቅዱሳን። እኔ ያደኩበት ቤተክርስቲያን መምህሩ (ፓስተሩ) አፈር ለአፈር እያንከባለለን አላደግንም። ስለመቆም እና ጥብአት እያስተማረን እንጂ። ውጤቱን አስልቼ (መዝኜ) አይደለም ለመሠረታዊ እሴቶቼ የምቆመው። እምነቴ ውጤቱን ያመጣው ይሆናል እንጂ ውጤቱ እምነቴን አይሸርፈውም። በኦሮቶዶክስ በተለይ በኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ምሰሶ የሚባለው አትናቲዎስ የሚታወቀው “ዓለሙ ሁሉ ጠልቶሃል” ብሎ ሰይጣን ሲነግርው ፥ “እኔ ቀድሜ ዓለሙን ሁሉ ጠልቼዋለው” ብሎ በተናገረው ንግግሩ ነው። ይሄ እምነትን በውጤት አለመመዘን ቤተክርስቲያኒቷን በተረዱ ሰዎች ላይ የሚታይ ባህሪ ነው።



ወደ ንባብ ዓለም ስገባ የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ “I stand alone” መጽሐፍ እጅግ ይማርከኝ ነበር። አንድም የኃይለሥላሴ ባለስልጣን ደፍሮ ንጉሱ እና ሥርዓታቸው የገቡበትን ንቅዘት ለመናገር ባልፈቀዱ ሰዓት በእንጦጦ ቤተ-ክርስቲያን ያደገው ብርሃኑ ድንቄ ግን አላስቻለውም። ኋላም ጥገኝነት መራራ በሆነበት የነጭ አሜሪካ ተሰዶ ስለእምነቱ ፍጹሙ ስቃይን የተቀበለ ሰው ነው። ደርግም ሲመጣ አሁንም የእምነት ጉዳይ ነውና ደርግን አወገዘ። ኋላ ይሄ እምነቱ በጤናው ጨምሮ በሁሉም ነገር ዋጋ አስከፈለው። እሱ ግን ለእምነቱ የከፈለው ዋጋ ሳይጸጽተው አለፈ። ለእኛም “ብቻዬን ቆምኩኝ” የሚለውን መጽሐፉን አበረከተልን።



የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሲዖል እንደሚገቡ የተነገረላቸው ቅዱሳን ያላት እና "ሲዖል እንኳ ብንገባ የምናመልከው ገነት ወይም ሲዖል ያስገባናል ብለን አይደለም” ያሉ ቅዱሳን የነበራት ናት። ይሄ ነው ትምህርቷ። በዚህ ትምህርት የሚፈጠር የሰው ስነ-ልቦናን አስቡ።



ምንድነው ግቡ ሲዖል እና ገነት ካልሆነ ታዲያ ብሎ ለሚጠይቅ ፥ “ፍቅር” ትላለች ቤተክርስቲያን። መውደድ! በምታገኘው ነገር ሳይሆን በእምነትህ ፥ ለእምነትህ ባለህ ፍቅር ተደሰት። አንተነትህ ሸቀጥ አይደለም። ጸጋዬ ገብረመድህን “ይህችን ነው ኢትዮጵያ የሚላት።”



የቅዱስ ገብርኤል በዓል ተራ ንግስ እና ቅዱስ መላዕክ ማክበር ብቻ የሚመስለው ወይም ለቁስ ስኬት ስዕለት ለማስገባት ሰዎች የሚሯሯጡበት የሚመስለው ይኖራል። ይሄን የሚያደርጉም በዓሉን እና መላዕኩን እየሰደቡ ያሉ ይመስለኛል። በዚህ የቤተክርስቲያን ጥልቅ ፍልስፍና ላይ ቆሞ የሚንጎራደደው መድረክ መሪ የውጤት ተኮር ስዕለቶችን ዝርዝር ሲተርክ ይውላል።



እውነት ለመናገር በዚህ ዘመን ያለችው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እና የብልጽግና የፕሮቴስታንት ቸርቾች ጋር ያለው የፍልስፍና ልዩነት ግራ ይገባኛል። የብልጽግና ፕሮቴስታንት የኢንዱስትሪያል አውሮፓ ፍጥረት ነው። ፍልፍስናው ሁሉ ኢንዱስትሪ ነው። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ግን የቁሱ ዓለም ተቃራኒ ናት። ቄሳርን የለየች ነበረች። ዛሬ ያ የለም። እየተፈጠረ ያለው ትውልድም በሽንፈት የሚርድ ፥ በአሸናፊነት ያለ ልክ የሚወጠር ነው። ጦር ሜዳ የሚወስደው እምነቱ እና ክብሩ ሳይሆን ማሸነፍ መቻሉን እርግጠኛ ሲሆን ነው። ምንአልባት የብልጽግና ሃይማኖት ስኬት እየታየ ይሆናል።


አድዋ ላይ የጊዮርጊስን ታቦት ይዞ የዘመተው ሕዝብ እዛ ድረስ የወሰደው ሰውነት ስለሚባል ክብር ነው። ሰማዕት ጴጥሮስ በመድፍ ፊት ሃሳቡን ያለወጠው እና ጣልያንን እያወገዘ የጥይት አረር የተቀበለው ውጤት ተኮር ሃይማኖት ስላነበረው ነው። እንዴት የሰው ልጅ ማንነት በምንአልባት በሚወሰን የወደፊት ውጤት ይሰፈራል። ቅዱስ ገብርኤል የገባቸው አባቶቻችን ኢትዮጵያን የወደዷት ከዚህ እምነት በመነሳት ነበር። ኢትዮጵያ “ባያድነን እንኳ (ባይደላኝ፣ ብራብብሽ፣ ብሰቃይብሽ፣ ወዝ እና አቅም ባይኖርሽ) ፥ ለጠላቶቻችችን ውርደት አንገዛም” የሚለው እምነት ሃውልት ነበረች። ይሄን እምነት ነው አባቶቻችን ኢትዮጵያ የሚሉት።


 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page