- Mulualem Getachew
- Aug 10
- 3 min read

፩) የኢዮብ ወዳጆች ለመከራ እና ለክፋት መልስ አለን ብለው መቅረባቸው፤
እውነት ለመናገር ብዙዎቻችን ብዙ ነገር አናውቅም። ግን አላውቅም ማለት በጣም ከባድ ነው። መክበዱ ብቻ አይደለም መልስ ሳይኖረን ተረጋግተን መኖር እና መቀጠል ይሳነናል። በተለይ ዓይናችን ሥር ትልቅ ክስተት ስናይ የዛን መንስኤ መተንተን ያስጎመጀናል። በተማሩ ሰዎች መካከል ደግሞ አላውቅም ማለት ነውር ይሆናል። አለማወቅ ተማርን ማለታቸውን ያሳንስባቸዋል። ማህበረሰባዊ ጫናውም ከፍተኛ ነው። አንድ አክስቴ ብዙ ጊዜ ስትጠይቀኝ አላውቅም፣ አላውቅም ስላት “እንዴ የተማርክ አይደለህም እንዴ?” አለችኝ። የዚህ ዓይነት ጫና ስለማናውቀው ነገር ሳይቀር ትንታኔ እንድንሰጥ ይጋብዘናል። ዝም ማለት በትልልቅ ክስተቶች ፊት እጅግ ከባድ ነው። የኢዮብ አዋቂ ወዳጆቹ የተሳናቸው ያ ነበር። በእግዚአብሔር ጉባኤ ተወስኖ በጻዲቁ ኢዮብ ላይ የተከናወነው ነገር ለማናቸውም የሰው ልጆች የተገለጠ አልነበረም። ግን የኢዮብ ወዳጆች ዝም ከማለት ይልቅ ለኢዮብ መከራ ምክንያት ፈለጉለት። ኃጢአተኛ ስለሆንክ ነውና ንስሃ ግባ አሉት። ቢያንስ በሀሳብህ በድለሃል አሉት። ውጤትን ዓይተው መንስኤውን ተነተኑ።
የደራሲ ዓለማየው ገላጋይን አንድ የተቆረጠ ቪዲዮ ተመለከትኩኝ። ያለንበት ድህነት እና መከራ እረፍት የነሳው ይመስላል። ይሄ አዋቂ ደራሲ ከዛ እንዲህ አለ “እግዚአብሔር ጣልቃ አይገባም በሕይወታችን።” የየቀን ሠሪውን እግዚአብሔርን “ሁሉን ነገር ሠርቶ ጨርሶ ቀድመው ለነቁ ሰዎች አስረክቦናል” አለን። “ለዚህም ነው ከዚህ በፊት የጠፉ ሰዎች ሲያይ ጣልቃ ያልገባው፣ በእኛም ሕይወት ጣልቃ አይገባም፣ ራስህ ሠርተ ለፍተህ ልበስ፣ ብላ፣ ተጋደል። እርሱ ጣልቃ አይገባም፣ ለዚህም ነው የሰለጠኑት፣ ቀድመው የነቁት ሁልጊዜ የሚገዙን” አለ። ይሄ መከራ ላይ፣ ድህነት ላይ፣ ችግር ላይ ቆሞ ስለመንስኤው የማውራት ዝንባሌ እና አባዜ ነው። ጥራት ባለው አስተሳሰብ ዙሪያ ብዙ የተማሩ ሰዎች የሚሰሩት ትልቁ የማሰብ ስህተት ነው፣ መንስኤን ከውጤት ለማግኘት መጣር። ይሄ ጥራት ላለው አስተሳሰብ ጋንግሪን ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ስናያይዘው ደግሞ ቁጣው እንደእሳት የሚነድበት የአስተሳሰብ ዝንባሌ ነው። ስለኢዮብ ባይሆን ኖሮ ቁጣዬ እንደ እሣት በልቷቹ ነበር ነው ያለው።
በየቀኑ ይሄን የአስተሳሰብ ስህተት እንሰራለን። የታመመ ሰው እናያለን ፥ እግዚአብሔር ቀጣው እንላለን። ሀብታም እናያለን ፥ እግዚአብሔር ባረከው እንላለን። ድሀ እናያለን ፥ ሰነፍ ነው፣ እግዚአብሔር አልባረከውም እንላለን። ውጤት ላይ ቆሞ መንስኤን የማግኘት አባዜ። እስቲ በሕይወታችሁ አንድን ነገር ስንት ሁኔታዎች ሊያመጡት እንደሚችሉ ጠይቁ እና ያን ለእናንተ የተገለጠውን ብቻ ፈትሹ። በእናንተ ሕይወት እንደዛ ከሆነ፣ እጅግ ውስብስብ በሆነው በዚህ ዓለም አነዋወር ውስጥ የአንድ ነገር መንስኤ ከኛ የማሰብ አቅም ቢያንስ ያለጥልቅ ጥናት የረቀቀ ሊሆን ይችላል ብላችሁ አትገምቱም?
ደራሲ ዓለማየው መንስኤውን ለማወቅ በመቸኮሉ፣ ውጤቱንም በአግባቡ የተረዳው አይመስልም። ለምሳሌ በእውነት ይሄ ዓለም ኃያል የሆነው የሰው ልጅ (በዘመናዊ ቴክኖሎጂ) ደካማ የሆነውን ፍጹም የሚገዛበት ነው ወይስ ብዙ ዓይነት ኃይሎች በሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እና የነገ ሕይወታችን ላይ ያልተጠበቁ እና ተገማች ያልሆኑ አሻራቸውን እና ተጽዕኖዎችን የሚያሳርፉበት ዓለም ነው? በዚህ ዓለም ሰዎች የፈጠሯቸው ግዙፍ ቴክኖሎጂዎች ፥ በጣም ደካማ በሆኑ ፍጥረታት ወይም ክስተቶች አቅጣጫቸውን ሲቀይሩ እና ሲዘወሩ አላየንምን? ለምሳሌ የኮቪድ ቫይረስ እንዴት የሰው ልጆችን ሁሉ ባህሪ እና አነዋወር በቅጽበት እንደለወጠ ተመልከቱ። ይሄ ክስተት የሚነግረን ይሄ ዓለም በኃያላን ፍላጎት እንደፈለጉት የሚዘወር ዓለም እንዳልሆነ አይደለምን? የታላቋን አሜሪካ የውጪ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ የደኅንነት ፖሊሲ ፍጹም የቀየረው ከደካማዋ ሀገር አፍጋኒስታን የመጣ ጥቃት አልነበረምን? በርግጥስ ይሄ ዓለም ኃያላን እንዳሰቡት የሚኖሩበት ዓለም ነውን?
መሥራትን፣ ለፍቶ ማደርን፣ መፍጠርን ለማበረታታት የግድ ጽንፍ መሄድ አያስፈልገንም። እነዚህ ነገሮች ጥሩ ናቸው። ግን ሌላም እውነት አለ። እነዚህ ብቻ በቂ አይደሉም። እነዚህ ብቻ መልስ አይደሉም። “ሥራ ነጻ ያወጣኻል፣ Arbeit macht frei” የሚለውን መፈክር እናውቀዋለን። ይሄ በፍሬድሪክ ኒቼ ተጠንስሶ ናዚዎች የወረሱት እና በናዚ ካምፖች ሁሉ የተሰቀለ መፈክር ነበር። ሥራ ብቻውን የጥላቻ እና የትዕቢት ባርነት ውስጥ ጀርመኖችን ጨምሮ፣ ውድቀታቸውን አስከተለ እንጂ ነጻ አላወጣቸውም።
ጠቢበኛው ሰሎሞን ስለመንስኤ ሲናገር ከኛ ውጪ ባሉ ኩነቶች ማለትም በጊዜ እና በዕድል የሚወሰኑ እንደሆነ ተናግሯል። እዚህ ላይ የደረሰው ከብዙ ማሰብ በኋላ እንደሆነ ሲያሳይ “እኔም ተመለስሁ” ብሎ ይጀምራል። “እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።” መክ 9፥11።
፪) ሁለተኛው ነቀፋ ቲዎሎጂ እና አይዶሎጂ ነው። የኢዮብ ወዳጆች ጠንካራ ቲዎሎጂ ነበራቸው። ያም ክፋት ስለሚሸነፍበት መንገድ ነው። የእነሱ መንገድ ብቻ ኢዮብን ከቁስሉ እንደሚፈውሰው ደሰኮሩ። እየተፈራረቁ የቁስሉ መድኅን እነሱን መስማት መሆኑን ነገሩት። ይሄ በሃይማኖት ሰዎች መካከል በጣም ጠንካራ ዝንባሌ ነው። ለሁሉም ነገር መፍትሔ አለን። ለሁሉም ነገር ስንዱ ነን። የሚገርመው ግን ክፋትን እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያሸንፍ ከኛ የተሰወረ ጥበብ መሆኑ ነው። ክፋትን በመስቀሉ እንደሚረታ ለማንም የተሰወረ ነበር በብሉይ ኪዳን። መስቀል ነበር \ የእግዚአብሔር ጥበብ ፥ ክፋትን የረታበት። የሰው ልጆችን ቁስል የፈወሰበት። ያ ግን በድንግዝግዝ ተመለከቱት እንጂ ለአንዳቸውም አበው አልተገለጠላቸውም ነበር። ቲዎሎጂ በፍጥነት አይዶሎጂ ይሆናል፤ ለሁሉም ነገር መልስ አለኝ ብሎ ሲያስብ። ክፋት እና መጥፎ ነገሮች ለምንላቸው ሁሉ መልስ አለኝ ብሎ ሲገምት። ዝምታ እና ለእግዚአብሔር ዕድል እና ጊዜ መስጠት ብዙዎቻችን በየቀኑ መማር ያለቡን ጸጋዎች ናቸው። “ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ፦ ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር።” ኢዮ 13፥5።