top of page
Search

ጽናተ ቅስም

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • 4 days ago
  • 3 min read
ree

አንዳንድ ጊዜ እውነተኛ ትምህርት በምቾት ውስጥ ካለፉ ወይም ከስቃይ ውስጥ ከወጡ ሰዎች ነው መማር የምንችለው የሚለውን እርግጠኛ መሆን እቸገራለሁ። ምክንያቱም ብዙ በችግር ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች አያለሁ፤ ምቾት ግን የሚገላቸው። ቢሆንም "ሁላችንም ይሄን እንዴት አልፈዋለሁ?" ብለን የምንጨነቀው ችግር ሲመጣ ነው። የዛሬ የሰንበት ጹሁፌ በፍጹም መከራ ውስጥ ያለፈውን ቪክተር ፍራንክል ምክሮች ላይ ያተኮረ ነው። ይሄ ድንቅ ሰው ከመጀመሪያው ግልጽ የሚያደርገው ችግር አንጻራዊ እንደሆነ ነው። በአሜሪካ በሶፋው ላይ ቁጭ ብሎ ያለ ሰው እና በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት መካከል ያለ ሰው እኩል ሊቸገሩ ይችላሉ። ምክንያቱም የመከራ ከባዱ ክፍል ብዙ ጊዜ አካላዊ ሳይሆን ስነ ልቦናዊ ስቃዩ ነው። “መከራ እንደ ጋዝ ነው” ይላል። “አንድ ጠብታ ጋዝ በበርሜል ውስጥ ቢከተትም ሆነ በአንድ ትልቅ ክፍል ውስጥ የሚቆጣጠረው ክፍት ቦታ ተመሳሳይ ነው።” ያ ጠብታ ጋዝ ክፍሉን ሁሉ መቆጣጠር ይችላል። በተመሳሳይ በበርሜል ውስጥም ቢገባ በርሜሉን ሁሉ ይቆጣጠራል። መከራም ትልቅነቱ እና ትንሽነቱ አይደለም። የዛን ሰው አዕምሮ ትንሽም ይሁን ትልቅ በምልአት ነው የሚቆጣጠረው።



ለዚህ ነው ፍራንክል በናዚ ካምፖች ውስጥ ስላለው እና እርሱ ራሱ ስላለፈበት ሕይወት ሲናገር “ማንም አካሉ ጠንካራ ስለነበረ ያን መከራ አላለፈውም። ይልቁንስ ያን መከራ ያለፉት ሰዎች የመኖር ምክንያት (meaning) የነበራቸው ናቸው” ይላል። “ለምን የሚለውን የመለሰ ሰው የትኛውንም እንዴት ያልፈዋል” ይላል። የተረፉ ሰዎች ከዛ ካምፕ የሚወጡበት ምክንያት ነበራቸው። ሕይወታቸው አሁንም ያላለቀ እና የሚያሳኩት ትርጉም እንዳላት ያምናሉ። ከዛም የተነሳ መከራን እንደ ቅጣት ሳይሆን እንደ ፈተና ብቻ ነው የሚያዩት። ፍራንክል ሳይቀር ከኦሽዊትዝ ካምፕ ወጥቶ ይሄን ስቃዩን ሌክቸር ሲያደርግ እና የሕይወትን ትርጉም ሲያስተምር ራሱን ይስለው ነበር።



ይሄን ያለፉ ሰዎች ባብዛኛው “ይሄ ግን በእኔ ላይ ለምን ሆነ?” ሲሉ አይጠይቁም። “ለዚህ መከራ የሚስማማ ስብዕና ምንድነው? ብለው ነው የሚጠይቁት።



ፋራንክል “ብዙ ጊዜ በሕይወት ምርጫ ላይኖረን ይችላል። መቼም የማንነጠቀው ነጻነት ግን አለን? ይላል። ያም አመለካከታችን ላይ ያለን ነጻነት ነው። በሆነ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን በዛ ሰዓት ሊኖረን የሚችለውን አመለካከት የመምረጥ ነጻነት ግን አለን።



ተስፋ ከመቁረጥ አዕምሮአችንን መመለስ፣ የውስጥ ሰላምን ለመጠበቅ ራሳችንን ከክፋት ማራቅ፣ እጅ ላለመስጠት መወሰን፣ በሌሎች ላይ ላለመፍረድ መጠንቀቅ እና ክብርን በትንንሽ ነገሮች ሳይቀር መጠበቅ።



“በሚገርም ሁኔታ በናዚ ካምፖች ውስጥ የሰዎችን መልካምነት ብቻ ተመልክቶ ማን ሊተርፍ እንደሚችል መገመት ይቻል ነበር” ላል ፍራንክል። ቁራሽ ዳቦዎቻቸውን ለሌሎች ያጋሩ፣ በራብ ወቅት ሳይቀር ክብራቸውን የጠበቁ፣ ሌሎች እስረኞችን ያልዱ ሰዎች የመትረፍ ዕድላቸው ሰፍቶ እና ከእነዛ ካምፖች በሕይወት ቆይተው ሲወጡ አይቻለሁ። ይላል።



እዚህ ጋር ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በጻፈው መጽሐፍ ላይ ያለ የወሎ ረሀብ ታሪክ ትዝ ይለኛል። የአሜሪካው ሴናተር ኬኔዲ ረሀብተኞቹን ጎብኝቶ ተመልሶ ሆቴሉ መተኛት ያቅተዋል። በተመለከተው የተራቡ ሰዎች ብቻ ግን አይደለም። እነዛ የተራቡ ሰዎች ሰልፍ ጠብቀው፣ ዳቦ አየን ብለው ሳይጋፉ እና ሳይደባደቡ የተሰጣቸውን አመስግነው ተቀብለው መሄዳቸው እና በዛ ሁኔታ ውስጥ እንኳ ክብራቸውን መጠበቃቸው ነበር ያስደነቀው።



ብዙዎቻችን እንደዚህ ሥርዓት መያዝ እና አለመስገብገብ ሕይወትን ለማስቀጠል ትርጉም ያለው ላይመስለን ይችላል። ይሄ ማንነት ግን በመከራ ውስጥ ቅስምን ከመሰበር ይጠብቀዋል። ቅስም ከአጥንት ውስጥ ያለ አጥንት ነው። የተሰበረ ቅስም ያለው ሰው ጠንካራ አጥንት ቢኖረው እንኳ ቆሞ አይሄድም። የቅስም ጽናቱ ደግሞ ሞራል ነው።




ፋራንክል “አዕምሮ እውነትን መቀበል ሲክድ ይሰበራል” ይላል። የአዕምሮ ጥንካሬ አሁን ያለውን እውነት በመቀበል የሚመጣ ነው። ጽናት መሸሽ ለማንችለው መከራ ትርጉም በመስጠት የሚገኝ ነው። መቀበል ማለት እጅ መስጠት አይደለም። አለመካድ እንጂ። የሚታየውን ነገር ኮስሞቲክስ እና ሊፒስቲክ አለመቀባት እንጂ።



ጽናተ ቅስም ያላቸው ሰዎች ፍርሃትን ካልገሩት ፥ ፍርሃትን እንዲሁ ከፈቀዱለት አሳስሮ እንደሚያስቀምጥ ያውቁታል። ተስፋቸው ህልም አይደለም። ማለትም የዛሬ ሦስት ወር ወይም ከዓመት በኋላ ይለወጣል ብለው አይደለም የሚያምኑት። ይሄ እብደት፣ ይሄ ክፋት፣ ይሄ መከራ ግን እንደሚያልፍ ያምናሉ።



የመከራው ፍጻሜ በግልጽ አልታየው ያለው ጻዲቁ ኢዮብ በወዳጆቹ ወቀሳ ፊት እና በተሸከመው የስቃይ ሰውነት መካከል ቆሞ እንዲህ ነበር ያለው “እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ።” ኢዮ 19፥25። ቻርሊ መንገር እንዲህ ይላል “የሚደርስበት የፕሬዠር ደረጃ እንጂ የማይሰበር ሰው የለም።” ምን ያህል ግፊት ይፈልጋል ነው እንጂ ሰው ሁሉ ይሰበራል። ለዚህ ነው ብርቱ ኢዮብ ሳይቀር “ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን? ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን?” ያለው። ኢዮ 6፥12። በመከራቸው ወቅት “ከዚህ መከራ አንድ ቀን ይታለፋል። በዚህ መከራ ውስጥ የሕይወት ትርጉም አገኛለሁ።” ያሉ ሰዎች የገጠማቸውን የመሻገር አቅም ያገኛሉ።



መከራን ማለፍ የሚችሉ ሰዎች በመከራቸው ሰዓት ሳይቀር ትንንሽ ደስታዎችን ይፈልጋሉ። በሚያዩት የተፈጥሮ ውበት ይደሰታሉ። በዛ መከራ መካከል ከከዷቸው እና ከተዎቸው ሰዎች ላይ ዓይናቸውን አንስተው ባልጠበቁት ሰዓት የደረሱላቸውን ሰዎች ደግነት እያዩ ያመሰግናሉ። በዛ መከራ ውስጥ ሳይቀር በቀልዶች እና በራሳቸው ባህሪ ይስቃሉ። ይሄ ሕይወት ከዚ ውጪ መሆን አይችልም። በዚህ መካከል ማለፍ ነው ስብዕና።




ሕይወት ትርጉም የሚኖራት በመከራ ውስጥ ማለፍ ለፈቀዱ ነው። በዚህ ውስጥ እንኳ እያለፉ ራስ ወዳድነት ሳያሸንፋቸው በመስጠት ሲያምኑ፣ ለእነሱ በቂ ያልነበረውን ለመጋራት ሲፈቅዱ፣ ነውር ሳይነካቸው ወደ መታረጃው ቦታ ሲገቡ ግን ደግሞ ትንሣኤ እንዳለ ፥ ክፋት በመጨረሻ እንደሚሸነፍ ሲያምኑ ፥ የዛኔ የእነርሱ ታሪክ ለማስተማሪያነት እንደሚውል ሲያውቁ ፥ ቅስማቸው እንደ ጸና ፥ አንገታቸው እንደ ቀና ይሻገራሉ።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page