ጓደኝነት
- Mulualem Getachew
- 13 hours ago
- 3 min read

በሕይወቴ ታደልኩት ከምለው ነገር በምርጥ ጓደኞች መከበቤን ነው። እኔን ለማድመጥ ከማይሰንፉ፣ ለነቀፋ ሳይሆን ለማገዝ በፈቀዱ እና ሙላት እንዲሰማኝ በሚያደርጉ ጓደኞች ነው ተከብቤ የኖርኩት። እንዲህ የሚባል አባባል አለ። አንተ የአምስት በዙሪያ ያሉ ሰዎች አቭሬጅ ነህ። የሰው ልጅ መቀየር ከፈለገ ማድረግ ያለበት ጓደኞቹን መለወጥ ነው። ሁልጊዜ የጓደኞቹ አቭሬጅ ስለሚሆን። በዓለም ላይ የድንቅ ለውጦች እና ተቋማት ውጤት የምርጥ ጓደኞች ጥምረት ነው። ዋረን በፌት እና ቻርሊ መንገር፣ ዳንኤል ኮነመን እና አሞጽ ትሮቪስኪ፣ ተፈሪ መኮንን እና ራስ ካሳ፣ መኮንን ሀብተወልድ እና ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ መዝሙረኛው ዳዊት እና ዮናታን እና መሰል ጥምረቶችን ማንሳት ይቻላል። ከስኬታማ ሰው ጀርባ ጠንካራ ሚስት አለች የሚባለው እውነት ቢሆንም ሁልጊዜ ግን አይደለም። ሁልጊዜ እውነት የሆነው ከማንኛውም ስኬት በስተጀርባ ጠንካራ ጥምረቶች እና ወዳጅነቶች ያሉ መሆኑ ነው። ብዙ ስኬታማ ወንዶች ክፉ ሚስት ኖሯቸው ያውቃል። የትኛውም ስኬታማ ሰው ግን ምርጥ ጓደኛ የሌለው የለም።
ብዙዎቻችን ይሄን ምርጥ ጓደኛ ለመፈለግ እንኳትር ይሆናል። በሚገርም ሁኔታ ግን እኛ መልካም ሰው ሳንሆን ፈጽሞ እነዚህን ጥምረቶች ከመጀመሪያውም መፍጠር አንችልም። የምርጥ ጓደኛ አንዱ ብቃት ራሱን ከመጥፎ ሰዎች ማራቅ ነው። ስለዚህ እኛ ልበ ጠማማ እና መሰሪ ከሆንን እነዚህን አስገራሚ ጥምረቶች አናገኛቸውም። ለመልካም ጓደኝነት የሚያስፈልግ ዘር በውስጣችን አስቀድሞ ከሌለ ምርጥ ጓደኞችን ማፍራት አንችልም።
ምንድናቸው እነዚህ ዘሮች?
1) ጓደኛ እንዲሆኑ የምትመርጣቸው ሰዎች ከአንተ ጋር ሁልጊዜ በሀሳብ የሚስማሙ መሆን የለባቸውም። ያንተን blindspot (ግርዶሽ) የሚያሳዩ ሰዎች ነው የሚያስፈልጉ። በራሳቸው ቆመው ማሰብ የሚችሉ ሰዎች ካልሆኑ ጥሩ ጓደኞች አይሆኑህም። ለዚህ ደግሞ አንተ ውስጥ አንድ ዘር ያስፈልጋል። ትችትን በደስታ እና በሳቅ የምትቀበል፣ ፉገራን የምትችል እና ጓደኞችህ ካንተ ጋር ነጻ ሆነው ማውራት እንደሚችሉ የሚሰማቸው ሰው መሆን አለብህ። ካለዛ መስማት የምትወደውን የሚነግሩህ የገደል ማሚቱዎች እንጂ ጓደኛ አይኖርህም።
2) ጓደኛ እንዲሆኑ ለምትፈልጋቸው ሰዎች ስኬት ከልብ መጨነቅ መቻል። ይሄ በጣም ከባድ ነው። ቅናት የሰው ልጅ ጥንታዊ ማንነቱ ነው። ከልጅነት ጀምሮ በቅናትም ነው ተኮትኩተን ያደግነው። “ጌታ ሆይ እኔ ራሴን ከጠላቴ እጠብቃለሁ። አንተ ግን ከወዳጄ ጠብቀኝ” የሚባለው የቅናትን ኃያልነት ለመግለጽ ነው። የሚቀናብህ እና በቅናት የሚያጠቃ ደግሞ አጠገብህ ያለው ወዳጅህ ነው። ለዚህ ነው ጥሩ ጓደኛን ለማግኘት የቅናትን ሥሮች ከውስጣችን ነቃቅለን ማቃጠል ያለብን። እንዴት? ለጓደኛ ምክር ከመስጠታችሁ በፊት ራሳችሁን ጠይቁ። “ይሄን ምክር ለራሴ ቢሆን እሰጠዋለሁ? ይሄ ምክር የጓደኛዬን ስኬት በማሰብ የተሰጠ ወይስ የርሱ ስኬት ለእኔ በሆነ መጠን የስሜት ጉድለት ስለሚያመጣ የቀረበ ምክረ ሃሳብ ነው?
አንዱ የምንቀናው ያ ሰው ቢሳካለት እናጣዋለን፣ ከጎናችን አይሆንም ብለን ነው። ለዚህ ነው ከልብ የዛን ሰው ጥቅም ለማሰብ መለማመድ ያለብን።
በዚህ ምድር ምርጥ ጓደኛ የማግኛው ትልቁ ቁልፍ ለዛ ሰው ፍጹም የሆነ ስኬት እና ደስታን መመኘት ነው። ስኬታማ እንዲሆን ደግሞ መደገፍ። ነገር ግን በጎ የምንመኝለት ሰው ቅናተኛ ከሆነ ይሄ ባህሪያችን ብዙም ላይለውጠው ይችላል።
3) ክፉ ካደረገብን በላይ ክፉ እንዲሰማን ያደረገብን ሰውን እናስታውሳለን። በተቃራኒው መልካም ስሜት እንዲሰማን ያደረገንን ሰው እንወደዋለን። ጓደኛ እንዲሆኑን የምንፈልጋቸው ሰዎች በጎ ስሜት ስለራሳቸው እንዲያድርባቸው ማድረግ አለብን። እነርሱን ዝቅ የሚያደርግ እና ጎዶሎ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ ምርጥ ጓደኛን የማጫ ዋነኛው መንገድ ነው። በጎ ስሜት እንዲሰማቸው ወዳጅ እንዲሆኑን ለምንፈልጋቸው ሰዎች እናድርግ። ስለ ስሜታቸው እንጨነቅ። ሰው የሚያስብ እንስሳ አይደለም። የሚሰማው እንስሳ ግን ለማሰብ የሚጥር ነው። ስለ ሌሎች ስሜት መጨነቅ ሌሎችን የማትረፊያ መጀመሪያ ነው።
4) ዓላማችሁ የሚያስቡ ወዳጆች ማግኘት ነው። ስለዚህ ኮንቨርሴሽን (conversation) የምትወዱ ካልሆናችሁ ጥሩ ጓደኞችን ማግኘት ከባድ ነው። በርግጥ በቡድን ውስጥ ማውራት ምቾት የሚሰጠው (extrovert) እንዳለ ሁሉ የራሱ ምቹ ሁኔታ (comfort zone) እስኪፈጠር የሚጠብቅ (introvert) ተፈጥሮ ያለው ሰውም አለ። የማውራት ተፈጥሮአችን ይለያይ እንጂ ሰው የሚያወራ እና ሀሳብ የሚለዋወጥ ፍጥረት ነው። የምትፈልጉት ወዳጅ ሀሳብ ያለው መሆን አለበት። ሀሳብ ማፈልቅ የሚችል እና የሚያስብ። ከእናንተ ስሜት ጋር የሚነጉድ ሳይሆን ያላያችሁትን የሚያሳያችሁ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ቁልፉ እናንተ ናችሁ።
እነዚህን አራት ነጥቦች በጥልቀት ብታዮቸው ካለ ባላንስ እርስ በርስ ይጋጫሉ። ጥበብ ማለት ሊጋጩ የሚችሉ ነገር መቀመሚያ ነው። ብዙ ወለፈንዲዎችን (paradox) አቻችሉ እና አስማምቶ የሚሄድ ሰው ነው ጥበበኛ የምንለው።
ጥሩ ነገሮችን ሁሉ ለማግኘት ከባድ ናቸው። ሕይወት ደግሞ የሚነግረን መልካም ነገሮችን ለመሳብ ማግኔቱ እኛ ጋር እንደሆነ ነው። መልካም ዘር መልካም መሬትን ይፈልጋል። መልካም መሬት ያለ ጥሩ ዘር ዋጋ የለውም። ሁለቱ ሲጣመሩ ነው አስገራሚ ውጤት የምናየው። መልካም መሬት ካልሆንን የዘሩ ጥሩነት ምንም ጥቅም የለውም። መልካም መሬት ካላገኘን ምርጥ ዘር ቢኖረን ጥቅሙ ምንም ነው። ነጮች “it takes two to tango” ይላሉ። ጓደኝነት የጋራ ጉዞ ነው።
Comments