እንቢ ማለትን በምግብ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አከራካሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ እና የተለያዩ ሊቃውንትም ግራ ከሚጋቡበት ነገሮች ውስጥ ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው እንስሳት ለምግበ እስራኤል መለየታቸው ነው። በተለይ በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ላይ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ መልካም መሆናቸው በይፋ ተገልጾልን፣ ፍጥረቱን እንደሚወድ እና እንደሚመግባቸው በብዙ የመጽሐፍ ክፍል ተነግሮን ሳለ፣ እንደገና ንጹሁ የሆኑ እና ንጹሁ ያልሆኑ ተብለው መለየታቸው እስራኤሎችን ሳይቀር ግራ የሚያጋባ ነው።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በግብጽ አሌክሳንደሪያ ብዙ ግብጾች ይኖሩ ነበር፤ በአይሁድ የአመጋገብ ምርጫ የሚደነቁ ሄለናዊያን እና ግሪኮች እነዚህን አይሁዶች ለምን ንጹሁ እና ንጹሁ ያልሆነ ምግቦች በማለት አንዳንድ እንስሳትን እንደማይበሉ ጠይቀዋቸው ነበር። ፋይሎ የሚባል ሊቅ በሰዓቱ ለዚህ ምክንያት ነው ያላቸውን ዘርዝሮ ጽፎ ነበር። የአርስጣጢለስ ደብዳቤ ለአሌክሳንደርም ይሄን ጉዳይ ያብራራል። እውነታው ግን በርግጠኝነት ማናቸውም ምክንያቱን እንደማያውቁት ነው የሚያሳየው።
ይሄ በዘሌዋውያን ምዕራፍ 11 እስራኤል እንዲበሉት ተብለው የተጠቀሱት እንስሶች አንዳንዶቹ በእንደዚህ ባህሪያት ተለይተዋል፤
፩) የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ።
፪) በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው።
፫) በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ ሁሉ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤
፬) በሆዱ የሚሳብ፥ በአራትም እግሮች የሚሳብ፥ ብዙ እግሮችም ያሉት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ የተጸየፉ ናቸውና አትብሉአቸው።
ስለሚበሩ ወፎች የተነገረ መለያ ሕግ ባይኖርም፤ የማይበሉት እንደ ቁራ፣ ዳክዬ፣ ጥንብ አንሳ ተዘርዝረዋል።
በብሉይ ሕግ ስለንጽህና በምግብ ብቻ ሳይሆን በአልባሳትም ተጠቅሷል። ለምሳሌ ሁለት ዓይነት ቀለማት ያሉት ልብስ መልበስ ንጹሁ አይደለም። የሞተ እንስሳ መንካትም እንዲሁ ከንጽህና ያሶጣል። እነዚህን ነገሮች ማድረግ ኃጢአት ነው ሳይሆን፣ ወደ ተቀደሰው ቤት እና ወደ መቅደሱ ለመግባት ግን የመንጻት ሥርዓትን መፈጸም ያስፈልጋል።
አንዱ የሊቃውንት መከራከሪያ እነዚህ ንጹሁ አይደሉም የተባሉ እንስሶች በጣዖት በሚያመልኩ ሕዝቦች ዘንድ የአማልክቶቻቸው ወካይ ናቸው ተብሎ መጠቀሱ ነው ይላሉ። ለምሳሌ በዮሐንስ ራዕይ ሰይጣን በእንቁራሪት ተመስሏል፣ እንቁራሪት ደግሞ ንጹሁ አይደሉም ስለዚህ አትብሏቸው ከተባሉት ነው ወገኑ። ሌላኛው መከራከሪያ ደግሞ ንጹሁ የተባሉ እንስሳት የወገኖቻቸው ወካይ ናቸው፤ ለምሳሌ በውሃ ውስጥ የሚኖር እንስሳ ክንፍና ቅርፊት ከሌለው የአሣን መስፈረት አያሟላም ፥ ስለዚህ ያን ዘር (የአሣን) አጉዳይ ስለሆነ ንጹሁ እንዳልሆነ ይቆጠራል የሚል ነው።
በስፋት በሀገራችን ሊቃውንት ሳይቀር የምንሰማው መከራከሪያ ደግሞ ዝምድና ነው። ለምሳሌ አሳማ ሁሉን የሚበላ፣ የሚከረፋ፣ ሆዳም ስለሆነ ያንን እንደ ኃጢአተኛ እና ከክብሩ እንደተዋረደ ማንነት አድርጎ በምሳሌ በማቅረብ፤ ለመብላት ንጹሁ ያልተባለው ለዛ ነው የሚል ነው። ጥንብ አንሳም ከዚህ ምሳሌ የሚካተት ነው።
ሌሎች ደግሞ ንጹሁ የተባሉት እንስሳት ለፈጣሪ በመሥዋዕት መልክ የሚቀርቡ በመሆናቸው፤ የፈጣሪ ምግብ ናቸው፣ በዚህም ንጹሁ ተባሉ። በተቃራኒው አሳማ፣ ግመል ደግሞ ለመሥዋዕት ስለማይቀርቡ፣ የሰው ልጆችም መብላት የለባቸውም የሚል ነው።
ሌሎች ደግሞ እንደ ጠንካራ መከራከሪያ አድርገው የሚያነሱት ከጤና አንጻር ነው። እንደ እንቁራሪት፣ አሳማ ያሉ እንስሶች ከውሏቸው እና አመጋገባቸው አንጻር ለጤና አደገኛ ስለሆኑ (ሁሉን የሚያግበሰብሱ በመሆናቸው) ለዛ ነው አትብሉ የተባልነው ይላሉ።
እውነት ለመናገር ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች እምብዛም አሳማኝ አይደሉም። ለምሳሌ ቀላል የማይባሉ ንጹሁ የተባሉ እንስሶች የክፋት ምሳሌዎች፣ የባዕድ አምልኮ ምልክቶች ነበሩ። በንጽህናም ከወሰድን ፍየል እምብዛም ከአሳማ የሚለይ የአመጋገብ ሥርዓት የለውም። ዶሮም ሁሉን የሚመገብ ነው። ከጤናም አንጻር የሚነሳው ክርክር ውሃ የሚቋጥር አይደለም። አሳማ ከምግባር አንጻር በመጥፎ እና በሁሉ አግበስባሽነት ቢመሰልም፣ በምንም ክፋት የማይመሰሉ እንስሶችም ንጹሁ አይደሉም እና አትብሏቸው ተብሏል። ለምሳሌ ዳክዬ፣ ሎብሰተር፣ ፈረስ እና ሌሎችም። ስለዚህ የክፋት ምሳሌ ናቸው መባሉም አሳማኝ መከራከሪያ አይደለም። ለፈጣሪ ምግብነትም (ከመሥዋዕት አንጻር) ተብሎ የሚቀርበው ምክንያት መሻገር የማይችሏቸው ነጥቦች አሉት። ለምሳሌ ለመብላት ንጹሁ ሆነው ለእግዚአብሔር ግን በመሥዋዕትነት ማቅረብ የማይፈቀዱ እንስሶች ነበሩ። አጋዘን አንዱ ነው። ይበላል ግን አይሠዋም።
ከበሽታ እና ከንጽህና አንጻርም እስራኤሎች የተለየ ጤናማ ሕዝቦች አልነበሩም። ንጹሁ የተባሉ እንስሳትን ብቻ በመብላታቸው ያተረፉት የተለየ የጤና ጉዳይ የለም። ሌሎች በሚጠቁበት በሽታ ሁሉ ተጠቅተዋል። ረዥም ዕድሜ በመኖር በአርኬዎሎጂ ጥናት መሠረት ሩቅ ምስራቆች የተሻሉ ናቸው። እነዚህ ደግሞ በአመጋገብ ባህላቸው ከእስራኤሎች የተለዩ ነበሩ።
አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ንጹሁ እንስሳት እና ንጹሁ ያልሆኑ ብሎ ለመብል ሲከፍላቸው ፈጽሞ ከሰውነት ጤና እና ከረዥም ዕድሜ ጋር እንዳላያያዛቸው ነው።
በዚህ ክርክር ውስጥ እግዚአብሔር ለእስራኤላውን ንጹሁ እና ንጹሁ ያልሆኑ እንስሳት፣ አዕዋፋት እና የባህር እንስሶች ብሎ ሲለይ በምን ምክንያት ነው የሚለውን ከዳሰሱ እና አሳማኝ ሆነው ያገኘውትን ነጥቦች ልዘርዝር፤
1) መገደብን፣ እንቢ ማለትን ማስተማር፤
ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፥ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም።” እግዚአብሔር ሁሉን መልካም አድርጎ ከፈጠረ በኋላ፣ በገነት ውስጥ መታዘዝን፣ የሰውን በፍጥረቱ ውስጥ ያለውን ቦታ እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት የምታሳይ ያለመብላት ሕግ አውጥቶ ነበር። ያ ፍሬ በገነት ውስጥ ከነበሩት ፍሬዎች የተለየ ውበት ወይም ማስቀየም እንዳለው የተነገረን ነገር የለም። ሔዋን ለመብላት ስታስብ ፍሬው ያማረ እንደሆነ ከማየቷ በቀር። ይሄ ግን ሌሎቹ የሚበሉ ፍሬዎች ከዛ ዛፍ ያነሰ ውበት ወይም አስጎምጅነት እንዳላቸው ምንም አልተገለጸም። አንድ ነገር ግን ተነግሮናል፣ ያ ዝፍ የሞት ፍሬ መሆኑ። ምክንያቱም እርሱን መብላት ያለመታዘዝ ምልክት ነው። የአመጽ ምሳሌ ነው። በተመሳሳይ ለእስራኤል ንጹሁ እንስሳት ተብለው የተዘረዘሩትን በመስመር ማስቀመጥ እና ሁሉንም በሆነ መስፈረት ማኖር አይቻልም (arbitrariness አለባቸው)። ይሄ የሚነግረን ጉዳዩ ከመብልነት እጅጉን የተሻገረ እንደሆነ ነው።
እስራኤል እንቢ ማለትን፣ ለእግዚአብሔር ሲል መተውን፣ በዚህም ራስን መግዛትን እንዲማር የወጡ ሕጎች ናቸው። የሥጋ ትልቁ ፍላጎት እና ፈተና የሆነውን መብላት በመገደብ ፥ እንቢ ማለትን እና የፍቃድ ጡንቻን ማጠንከርን ለእስራኤል አስተማረው። እስራኤል እነዚህ የኛ ምግቦች አይደሉም፣ ለኛ አይሆኑም በማለት በሕይወት ራስን መገደብን እና ኃጢአት እንኳ ባይሆን ለእኛ የተፈቀደ አይደለም በማለት እንቢ ማለትን በሕይወት እንዲማሩ የተተከለ የፍቃድ (will power) ጡንቻ ማጎልበቻ ናቸው። ለእግዚአብሔር ስንል ምክንያት እንኳ ባይኖረው እንቢ ማለትን እንዲማሩ አደረጋቸው። በዚህም በሕይወት ነገሮች ስላጓጓቸው እና ስሜታቸው ስላሻው ብቻ እንዳያደርጉ ፥ ለምኞታቸው እንቢ የማለትን ጡንቻ ገና በጊዜ እንዲያዳብሩ አደረጋቸው።
የአይሁድ ቤተሰቦች በዚህ ዘመን ሳይቀር ይሄን የምግብ ባህል በጥንቃቄ ይከተላሉ። ተመልከቱ ይሄ ራስን የመግዛት፣ በዚህም የሕይወት ስኬትን የመቆናጠጥ ማንነት ከአይሁድ ዘር በላይ በዚህ ዓለም ማን ምሳሌ ሊሆን ይችላል። የኖቤል ሽልማትን ብቻ ውሰዱ። እስከዛሬ ከ965 የኖቤል ተሸላሚዎች ውስጥ፣ 214 አይሁዶች ናቸው። በአሜሪካ ውስጥ የአይሁድ ቁጥር 2.4% ነው፤ በአሜሪካ ቢዝነስም ሆነ ፖለቲካ ግን 71% ከሚሆነው የነጩ ማህበረሰብ ምንም ያልተናነሰ ተጽዕኖ የአይሁድ ማህበረሰብ ነው ያለው። በዚህ ዓለም ላይ ከቁጥሩ አንጻር የአይሁዶችን ያህል ስኬት የተጎናጸፈ አንድ ዘር መጥራት የሚችል ይኖራል? የትኛውንም የስኬት ሜትሪክሶችን አምጡ እና የአይሁድን ማህበረሰብ አስቀምጡ፤ ይሄ ማህበረሰብ ካለው ቁጥር አንጻር እጅግ አስገራሚ ስኬት የተጎናጸፈ ሆኖ ታገኙታላችሁ።
ማንንም ጠይቁ ፥ ለጊዜያዊ ፍላጎቱ እንቢ ማለት የቻለ ሰው፣ ራሱን መቆጣጠር እና መግዛት የሚችል ሰው በምንም ዘርፍ በመጨረሻ ያሸንፋል። ይሄን ነበር በምግብ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያስተማራቸው። በዚህ ሕግ ሕይወታቸውን ሁሉ አበራላቸው። እንቢ የማለትን ማንነት አጸናላቸው።
2) ሥርዓትን ያስተምራል ፦ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ላይ “ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?” እንዳለው ጠቢቡ፤ በሕይወት ሥርዓት ያለው ትንሽ ሠራዊት ሥርዓት የሌለውን እልፎች ይረታል። ዛሬም ስለእስራኤላውን ይሄ እውነት ነው። ጎረቤቶቻቸው በቁጥር በስንት እጥፍ እየበለጧቸው፣ ራሳቸውን የለዩ፣ በሥርዓት ማንነታቸውን ያሰለጠኑ በመሆናቸው በእልፍ የሚበልጧቸው በፊታቸው ይርዳሉ። (You develop an ordered soul that says no to certain things).
3) ማንነት ነው ፦ እነዚህን ምግብ እኛ እስራኤላውያን በመሆናችን አንበላም በማለታቸው ፥ ራሳቸውን ሁሉን ከሚበላው ዓለም ለዩ። በዚህም በቁጥር በብዙ እጥፍ ከሚበልጡአቸሁ ጎረቤቶቻቸሁ ማንነታቸውን ጠብቀው ማቆየት ቻሉ።
4) የእግዚአብሔርን ንጽሕ እና ቅድስና የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ሴቶች በወራዊ ልማዳቸው ወቅት ወደ ቅዱሱ ስፍራ ወንዶችም ዘራቸው የፈሰሰ እንደሆነ ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እንዳይገቡ በብሉይ ሕግ ተደንግጎ ነበር። ሴቶች ወራዊ ልማዳቸውን ማስቀረት የሚችሉት ነገር አይደለም፤ ስለዚህም ኃጢአት አይደለም። ነገር ግን ወደ ቅድስናው ስፍራ በዚህ ወቅት መቅረብ አይችሉም፤ ለምን? ይሄ የእግዚአብሔርን ቅድስና እና ንጽህና የሚናገር ነው። “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና፤ በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ።” ዘሌዋውያን 11፥44። ኃጢአትን አለመስራት አንድን ሰው ቅዱስ አያደርገውም። ቅድስና የዓላማ ተግባር ነው (affirmative action)። ቅድስና መተግበርን ይሻል፣ መራቅን ብቻ አይደለም። አንድ ሰው ኃጢአት መሥራት እየቻለ፣ ስለእግዚአብሔር ብቻ ሲል ከተወ ያ ቅድስና ነው። ምክንያቱም የዓላማ ተግባር ነውና። ቤቱ ውስጥ ምግብ የሞላለት እና ምንም ያልጎደለበት ሰው ላይሰርቅ ይችላል። አለመስረቁ ቅዱስ አያደርገውም። ከመጸወተ ግን ያ ቅድስና ነው። ሰይጣን ስለኢዮብ ያለው ይሄን ነበር። “እርሱ ስለሞላለት፣ ምንም ስላልጎደለበት፣ ዙሪያውንም ከክፍ ስላጠርክለት እንጂ ምንም ጽድቅ የለውም” ነበር ያለው። ሰይጣን ሳይቀር ከኃጢአት መራቅ በራሱ የጽድቅ ምልክት እንዳልሆነ ያውቃል ማለት ነው። እነዚህ ምግቦች ለእግዚአብሔር ሲባል ብቻ መተውን፣ በዚህም መቀደስን የሚያስተምሩ ምልክቶች ናቸው።
በአዲስ ኪዳን እነዚህ ምግቦች ያላቸው ቦታ ግልጽ ነው። በቤተክርስቲያናችንም እንዴት እንደሚታዩ ብጹዑ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የቤተክርስቲያን ታሪክን በጻፉበት መጽሐፋቸው ዳሰውታል።