top of page
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Apr 6
  • 3 min read

ree

ብሩስ ሊ “በሕይወቴ ረዥም ጊዜ ለመማር የወሰደብኝ ግን ደግሞ ለማሸነፌ መሰረታዊ የሆነው ነገር ርጋታን መጎናጸፍነበር” ብሏል። በዚህ ዘመን ከምንም ነገር በላይ እያጣን ያለነው ነገር ርጋታ ይመስለኛል። ሁሉንም ነገር እኛ ባልነው ሰዓት እና ጊዜ ብቻ ማከናወን መፈለግ። ዛሬ ወይም በጣም አጭር በተባለ ጊዜ ውስጥ ሀብታም መሆን። ወይም አዋቂ መሆን።ወይም ታዋቂ። ይሄን ለመከወን ደግሞ ሁሉንም አቋራጭ መንገዶች ለመጠቀም መፈለግ። በዚህ ፍላጎታችን መስመር ውስጥ እንከን ከገጠመን ሰማይ ምድሩ ነው የሚገለባበጥብን።

 

መስከን የሚባል ነገር ርቆናል። ችግር የመቋቋም እና የመቻል አቅማችን ተሟጧል። ኃይሌ ገብረሥላሴ አንዴ እንዲህ ብሎ ነበር። “ታዋቂ መሆን አልነበረም በጣም ከባዱ ነገር ፥ ታዋቂነትን ያጎናጸፈኽን መልካም ስም ይዞ መቆየት እንጂ።” ጅል ውሳኔዎች የፍጥነት ውጤቶች ናቸው። ቶማስ ጀፈርሰን እንዲህ ይላል “ከተናደድክ እስከ አስር ቁጠር። በጣም ከተናደድክ ግን እስከ መቶ ቁጠር።” ይሄ ታላላቅ ተግባራትን የሰሩ ሰዎች ንግግር የሚነግረን የሰው ልጅ አዕምሮ ሁልጊዜ የምንመካበት እንዳልሆነ ነው። በፍጥነት ወቅት ባላንሱን ይስታል።

 

የሆነ ሰው ሲያናደኝ ራሴን የምጠይቀው “በዚህ ምድር ላይ ይሄ ሰው የተናገረውን ንግግር ሰምተው ምንም የማይመስላቸው ሰዎች የሉም? ልክ እኔን የተናገረኝን ቢናገራቸው ፥ ምንም እንዳልተፈጠረ የሚያልፉ የሉም? መልሴ ሁልጊዜ ማለት በሚቻል መጠን “አለ!” ነው። ስለዚህ ይሄ ነገር ግለሰባዊ (subjective) ነው ማለት ነው። የእኔ የዕይታ አድማስ መጥበብ እና የቆዳዬ ስሱነት እንጂ የሰውዬው ንግግር አይደለም ማለት ነው። ያ subjective የሆነ ግብረ መልሴ ዓለምን ከሌላ ሰው አንግል እንዳየው ያግዘኛል። ይሄ ማለት ቀላል ነው ማለት አይደለም። ፈጽሞ። ያልተገራ ውሻ ዘወትር ውስጣችን አለ።ውሻ እየበላ ያለውን ብታነሳበት ይነክስሃል። ምግቡን የሰጠኸው እና ነገም የምትሰጠው አንተ ብትሆን እንኳ።በተመሳሳይ ክብራችን፣ እንጀራችን፣ ኢጎአችን፣ ድንበራችን ፥ ተነካ ስንል ፥ እንናከሳለን። ለውሻው ራስን መግዛት እና ስለነገ ማሰብ ከባድ እንደሆነው ሁሉ ፥ እኛም ያን ማሰብ በጣም ይከብደናል።

 

ይሄ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያልቆመ ነገር አለ። ሰውን በንዴት እና በቅናት ተነሳስቶ ማጥቃት። ምንም እንኳ ይሄን የሚያደርጉ ሰዎች መጨረሻቸው ጸጸት እንደሆነ እያወቅን እንኳን ዛሬም ያን የሚያደርጉ ሰዎች እልፍ ናቸው።

 

የሒሳብ ሊቁ ብሌዝ ፓስካል “የሰው ልጅ ችግር ሁሉ የሚመነጨው ፥ ሰው ብቻውን በርጋታ አንድ ክፍል ውስጥ ለመቀመጥ ባለመፍቀዱ ነው” ይላል። ሊቁ ጸጋዬ ገብረመድኅን ይሄን ግብዣ ነው ለሁላችንም ያቀረበልን። “አብረን ዝምእንበል” በሚለው ግጥሙ። “አጉል ነው ብለን ሳንፈርድ ድንቅም ነው ብለን ሳናደንቅ አስቲ ለአንድ አፍታ ዝም እንበል” ፥ መገዳደል እና መፍክር ማብዛት ለተጣባው ፖለቲካችን ምክር ሰጠን።

 

ዳንኤል ኮነመን “ብዙ ሰው የሚወደው ስፖርት ፥ ውሳኔ ላይ በፍጥነት መዝለል ነው (jumping to conclusion)” ይላል። ምንአልባት ያን አለማድረግ አንችል ይሆናል። ለሆነ ሰው ስልክ ደውለን ሳያነሳልን ሲቀር ፥ ንቆኝ ነው ማለት ይሆናል መጀመሪያ የሚቀለን። ምን አልባት የሆነ ነገር ፈልገን ስናጣ ፥ እከሌ ሰርቆን ነው ማለት ይሆናል የመጀመሪያው ውሳኔያችን። መጥፎ መጥፎውን ይሆናል መጀመሪያ አዕምሮአችን የሚያሳስበን። እንዲህ አስቤ ከዛ ውጤቱ ሌላ ሲሆን ፥ ራሴን “አየ አይደል!ትቸኩላለህ። ይሄ የመጀመሪያህ አይደለም። ብዙ ጊዜ እንዲህ ብለህ ከጠበከው ውጪ ሆኗል። ስለዚህ ተጠንቀቅ እለዋለሁ።” ከራሳችን ጋር መወቃቀስ እና ራሳችንን ሰው ሳይታዘበን በፊት እንታዘበው። ትላንት ተሳስተሃል። አሁንስ ልትሳሳት ብትችልስ? ስለዚህ ታገሰ። ተረጋጋ እንበለው።

 

ብሩስ ሊ እንዳለው ርጋታን መላበስ ፥ የትኛውንም ውጊያ የማሸነፊያ ጥበብ ነው። በሀገራችን መሪዎች ውስጥ እጅግብዙ ያሳኩ መሪዎቻችን አብዛኛው ጊዜ የሚታወቁት በታጋሽነታቸው ነው። በአጭር ሕይወታቸው የተቀጩ እንደ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ኢያሱ እና መንግስቱ ኃይለማርያም ያሉት ደግሞ ቁጡዎች እና ፈጥነው ውሳኔ መስጠት የሚወዱ ነበሩ። እነዚህ ረጅም አልመው በአጭር የተቀጩ  መሪዎች ናቸው። በዘመናቸው ለሕዝባቸው ጦርነትን አብዝተው የሰጡ ነበሩ።

 

ታሪክ የሚነግረን መረጋጋት እና መታገስ የስኬት ጨው መሆኑን ነው። መረጋጋት ማለት ግን ውሳኔ ለመወሰን የሚቸገርን ሰው አይወክልም። የተረጋጋ ሰው መወሰን ተቸግሮ አይደለም። ይልቁንስ ውሳኔው ነው ያረጋጋው። በአዕምሮ ውስጥ ቀጣይ የሚወስዳቸው ርምጃዎች ሁሉ ግልጽ ስለሆኑለት ወይም በርጋታ ውስጥ ያልተገለጡ እና በቅርብ ሊያውቃቸው የሚገቡ መረጃዎችን እየጠበቀ ስለሆነ ነው የተረጋጋው። ንድፈ ሀሳቡን በርጋታ ውስጥ በተግባር እየፈተሸው ነው። ርጋታ ማለት ጉዞ አልባነት አይደለም። ይልቁንስ ርጋታ ማለት የድብቅ እና የስውር ሩጫ ማለት ነው። ርጋታ ማለት ንፋሱን ቁጡ እና ቀበጥባጣው ሰው እንዲሰብረው ግን አንተ ከኋላ ሆነ የደውሉን ፍጻሜ የምትጠባበቅበት ስፍራ ማለት ነው። ርጋታ ማለት ነብር በሆዱ እየቧጠጠ ወደ ሚያድነው ታርጌት ከእይታ ተሰውሮ የሚቀርበብት ሁኔታ ማለት ነው።


ርጋታ ማለት እዩኝ የሌለበት ፈጣን እድገት ማለት ነው።

 
 
 

ree


ዋረን በፌት “ዓለምን የሚያስተዳድረው ስስት ሳይሆን ቅናት ነው” ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ ውድቀት በሰው ላይ የተሰነዘረው በሰው ክብር በቀናው ሰይጣን እንደሆነ ይነግረናል። ከዛም የመጀመሪ ወንድማማቾች የተገዳደሉት በቅናት እንደሆነ ተጽፏል። ሕይወት በሜጋ ፎን ለዘላለም የምትናገረው አንድ ሀቅ አላት። “ሁላችንም መቼም እኩል እንደማኖን።” አንዷ እጅግ ውብ ናት ሌላኛ መልክ የሌላት። አንዱ ሞገሱ እና ውበቱ የሚያስደነግጥ ሌላኛው ደግሞ የቀነጨረ የሆነባት ዓለም ናት። አንዱ ሀብትን፣ ዝናን፣ የሕይወትን ስኬት እና ስልጣንን ሁሉ በእጁ ይል ፥ ሌላኛው ደግሞ በእጁ ምንም የለም።



ጥቂት ልዩነቶች ፍትሕ በማጣት የመጡ ቢሆንም ብዙዎቹ ግን ፍጹም ዕድል እና የዕድል ጉዳይ ብቻ ናቸው። አንዳንዶቻችን በጣም ጤናማ ሆነን ስንወለድ ሌሎቻችን ደግሞ የዘር ሕመም አለብን። አንዳንዱ ዜግነቱ በአምስት ሚሊዮን ዶላር የሚሸጥ ሀገር ላይ ይወለዳል። ሌላኛው ደግሞ ሀገር አልባ ሆኖ ይፈጠራል።



ቅናት የእነዚህ ልዩነቶች የተሳሳተ መድኃኒት ነው። የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ዘወትር የማታጡት አንድ ነገር ቢኖር ቅናት ነው። የቅናትን ጥንታዊነት ማየት አስደናቂ ነው። የትኛውም ጥናትዊ ሃይማኖት ውስጥ ቅናት የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ነው ያለው። በጥንታዊ የግብጽ ታሪክ ውስጥ ኦስሪስ እህቱን አግብቶ ስልጣኔን ወደ ግብጽ ያመጣል። ያገባት እህቱ በጣም ቆንጆ እና ብልህ ነበረች። በተቃራኒው ኦስሪስ አስቀያሚ እና የሚጠላው ሴዝ የተባለ ወንድም ነበረው። ሴዝ በኦስሪስ ውበት፣ ስኬት እና ብቃት እጅጉን ይቀና ነበር። የሴዝ ሚስት ኦስሪስን በድብቅ ስለወደደችው ፥ አታላው አብራው እንዲተኛ ታደርገዋለች። በዚህ ወቅት ከኦስሪስ አረገዘች። በቅናት የበገነው ሴዝ ኦስሪስን በመጨረሻ ይገለዋል።



ቅናት ከሰው ልጅ እኩል ጥንታዊ ነው።



እርግጥ ነው ሰዎች በቅናት ተነሳስተው ራሳቸውን ሊያስተምሩ፣ ሊያሳድጉ እና ሊያሻሽሉ ይችላሉ። ግን ቅናት ከቁጥጥር ከወጣ ፥ የሌሎች ስኬት የኛ ሞት ይሆናል። ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እንደሚለው ጥንብ አንሳን የሚገለው ሽቱ ነው። ቅናተኛ ሰውም የሚመተው በወንድሙ መልካምነት ነው። የሌሎች ከፍ ማለት እኛን ለተሻለ ለውጥ ካነሳሳን መልካም ነው። የሌሎች መሻሻል ግን እኛን እንቅልፍ ነስቶን የእነሱን መውደቅ ካስመኘን ፥ ሽቱ የሚገለን ጥንብ አንሳ ሆነናል ማለት ነው። ቅናተኛ ሰው በወንድሙ ለቅሶ ላይ ለመገኘት ደስተኛ ነው። ሠረጉ ግን ያጠቁረዋል። ክስረቱ ልቡን ቅቤ ያስጠጣዋል። ስኬቱ ግን ያደማዋል። እርሱ ከሚያገኝ ይልቅ ወንድሙ ቢያጣ የበለጠ ደስ ይለዋል።



ቅናት ፍጹም አስቂ ባህሪ ነው። በሚበልጠን አይደለም የምንቀናው። በምናውቀው እና በሚበልጠን ነው የምንቀናው። የአንድ ሚሊዮን ዶላር ያለው ሰው የሚቀናው በኢለን መስክ ሳይሆን ከሱ ተሻግሮ ባለው ባለ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ግለሰብ ነው። የሰፈር ሁለተኛ ቆንጆዋ የምትቀናው ከሀገሩ ውብ በሆነችው ሳይሆን ከሰፈራቸው አንደኛ በሆነች ነው። ቅናት የፉክክር አድማሱ ጠባብ ነው። ማጥቃት በሚችለው ብቻ ነው ቀናተኛ ሰው የሚታመመው።



ሳይኮሎጂስት ቅናት ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያዩ ጉድለት ስለሚሰማቸው ፥ ስሜታቸው የሚያፈልቀው አሉታዊ (negative) ጥበቃ ነው ይላሉ። ለምሳሌ በጓደኛው የሚቀና ግለሰብ የሚቀናው የራሱን ሕይወት ተመልክቶ ለማሻሻል የሚጠይቀውን ልፋት ወይም አስተሳሰቡን ለመቀየር የሚያስፈልገውን የመረዳት ደረጃ ከመድረስ ይልቅ ፥ ብዙ ድካም የሌለበትን የቅናት አጭር መንገድ ይመርጣል። ቃየንን ተመልከቱቱ። እግዚአብሔር ስጦታህን አልቀበልህም ሲለው ፥ ሌላ አምላኩን የሚያስደስት ስጦታ ለማቅረብ ከመልፋት ይልቅ ፥ በአቤል ቀና። አጭሩን መንገድ መረጠ። ምክንያቱም ስህተት ሰርቻለው ብሎ ማመን ለሰው ከባድ ነገር ነው። ወይም በውበት ሌላኛው ወንድሜ ይበልጠኛል ብሎ ማመን። ያ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው። ያን መቀበል አለብኝ ከማለት ይልቅ ፥ የዛን መልከ መልካም ሰው ማንነት ማጉደፍ ቀላሉ መንገድ ነው። ቅናት ስሜታችን ስንፍናችንን የሚጠብቅበት ቀላሉ መንገድ ነው።



የሕይወትን ሀቅ ከመቀበል ይልቅ ፥ ቅናት ከዛ የእውነት ማዕበል በተቃራኒው እንድንቀዝፍ ያደርገናል። በሌሎች ደስታ ደስ የማይለን ከሆነ ፥ በፍጥነት ራሳችንን እንፈትሽ። የቅርብ ሰዎቻችን ውድቀት የሚያረካን ከሆነ ፥ ጊዜያችንን እየገደልን ነው።



ብዙ ክፋቶች የራሳቸው የሆነ ጥቅም አላቸው። ለምሳሌ የሚሰክር ሰው በመጠኑም ቢሆን በስካር ውስጥ ደስታ ያገኛል። ስርቆት ለጊዜውም ቢሆን ከሰረቅነው ነገር ተጠቃሚ ያደርገናል። ቅናት ነው ሌላውን ለመጉዳት ለመጎዳት የሚፈቅድ። ቅናት ነው ራሱ እየተጎዳ ሌላው እስከተጎዳ ድረስ ደስታ የሚሰማው። ፍጹም ደደብ የሆነ ክፋት ቅናት ብቻ ነው። የሚቀናውን ሰው ምንም አይጠቅመውም። ሌላውን ለማከርፋት እርሱ ቢከረፋ ግን ግድ የለውም።



ቅናትን የማሸነፊያው ዋነኛው መድኃኒት የምንቀናበትን ሰው ሄደን እንደምንቀናበት መንገር ነው። ከቅናት ስትፈወሱ ታዩታላችሁ። ባብዛኛው ያ ሰው በእናንተ እንደሚቀና ሁሉ ሊነግራችሁ ይችላል። ከዛ ግን ስለራሱ ጉድለት እና እንደምናስበው የሚያስቀና ነገር ያለው ብቻ ሳይሆን ጉድለት እንዳለው ይነግራችዋል። ቀጥሎ እንደ ዛ ግልጽ በመሆናችሁ የዛን ሰው ክብር እና ፍቅርም ታተርፋላችሁ። በመጨረሻ ያ ቅናት ከእናንተ ቀስ እያለ ሲተን ታዩታላችሁ።



ችግሩ ብዙዎቻችን በዚህ ባህሪያችን በእጅጉ ስለምናፍር ያን አናደርግም። ትዕቢታችን ደግሞ መዋረድ አድርጎ ስለሚቆጥረው ያን እንድናደርግ አይፈቅድልንም።


ከዛ መልስም ግን መፍትሔ አለ። በሕይወታችን መለወጥ የማንችላቸውን ነገሮች ለመቀበል መስራት። መለወጥ የምንችላቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ በትዕግስት ለመለወጥ መትጋት። ትዕግስት እና ትጋት በመጨረሻ መለወጥ የምንችላቸውን ነገሮች ቀይሮ ያሳየናል።



በሽቱ ለማጌጥ እንጂ ለመሞት አንዳረግ። በሌሎች ስኬት እና ደስታ ለመደሰት እንጣር።

 
 
 
  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Mar 3
  • 3 min read

ree

ስለአድዋ አከባበር ሳስብ፣ በዚህ አከባበር የሚበሽቅ ሰው ወይም የሚናደዱ ስብስቦች ባይኖሩ እንዴት ነበር የሚከበረው ብዬ አስባለሁ? ወይም በዓሉ የይገባኛል ክርክር ባይኖርበት እንዴት ነበር ስለበዓሉ የሚኖረኝ እይታ የሚቀየረው?


ሰዎች ስንባል ስነልቦናችን ድል የሚያሰባስበን፣ ከዛ ደግሞ አሸናፊነትን ለኛ ለማድረግ የምንሮጥ ነን። ማንም ሽንፈትን ወይም ተሸናፊነትን ከራሱ ጋር ማያያዝ አይፈልግም። የሆነ ሰው ሀብታም ወይም ታዋቂ ሲሆን ዘመዴ ነው፣ ጓደኛዬ ነው፣ አውቀዋለሁ ብሎ ለመናገር እና ራሳችንን ከዛ ሰው ጋር ለማያያዝ የምንጥር ነን። አሸናፊው ደግሞ ድልን በራሱ ጥረት ብቻ እንዳገኘ፣ ጉብዝናው እና ብልሃቱ ለዛ እንዳደረሰው በመናገር ከሌሎች እሱ ልዩ የሆነበትን ነገር ለማሳየት ይጥራል። እነዚህ ወደ ማህበረሰብ ሲወርዱ ትርክት ይፈጥራሉ። ሰው ደግሞ በትርክት (story) የሚያስብ ፍጥረት ነው። ይሄ ትርክት ማንነትን ይፈጥራል። ከዚያ በዚህ ማንነት ዙሪያ እነሰባሰባለን። እንጋጫለን። ለዚህ ማንነት ብዙ ዘፈኖች፣ ወረቦች፣ ዲስኩሮች በማውረድ ፥ ከዚህ ማንነት ጋር ሁለመናችንን እናሳስራለን። አድዋ አንዱ የማንነት መገንቢያ፣ የመሰባሰቢያ እና እርስ በእርስ የመጋጫ ትርክት ነው። የድል አድራጊነት ታሪክ ስለሆነ ማንነትን በዚህ ላይ መገንባት የሰው ልጅ ዝንባሌ ነው።


ሽንፈትን ቤትውስጥ እንዳለ ቆሻሻ ከእይታ እንሰውረዋለን፣ የህሊና ሰላምም ስለሌለው ወደማይታይበት መዛግብት እንከተዋለን። ምንም እንኳን ሽንፈት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከድል በላይ በዝቶ የሚገኝ ክስተት ቢሆንም ለማንነት ግንባታ ትርክት ግን አይመችም። ከድል በላይ እውነት (reality) ሽንፈት ነው። ሽንፈት ሰዎች መሸሽ የሚፈልጉትን እና የሚሸሹትን ሕመም እንዲጋፈጡ የሚያደርግ ነው። ድል ብዙ ውሸትን በውስጡ አዝሏል። ድል ከእውነት በላይ ፍላጎት ነው፤ ሽንፈት ግን የፍላጎት መነጽር የጎደለው ለእውነት የቀረበ ነው።



በየዕለት ሕይወታችን ብዙ ማንነት አለን። ከአርሴናል ደጋፊዎች ጋር መድፈኞች ነን፣ ከኦሮቶዶክስ ክርስቲያኖች ጋር ኦርቶዶክሳዊ ነን፣ እንደ ኢኮኖሚ መደባችን የመንግስት ሠራተኞች ወይም ባለሀብቶች ወይም ዲያስፖሮች ነን፣ ከገዢዎች ጋር የገዢው ደጋፊ ነን፣ ከአማጺ ኃይሎች ጋር አማጺያን ነን፣ ቀነኒሳ ወይም የዲባባ ልጆች ሲሮጡ ኢትዮጵያዊ ነን፣ ከሌላው ዓለም ጋር በሚደረግ ትግል አፍሪካዊ ነን፣ በጥቁሮች ላይ በሚደርሰው በደል ጥቁር ከሆነው ሁሉም ሕዝብ ጋር እንቆማለን፣ በምዕራባውያን ሀገር ስንኖር ደግሞ ከኮኬዥያን ውጪ ካለው ጋር የቀለም (color) ሰዎች ብለን ራሳችንን እንመድባለን፣ ስለሰው ልጆች ውድቀት ስናወራ ደግሞ ራሳችንን ከሰው ዘር ጋር ሁሉ መድበን መላዕክት እንዳልሆንን እና መሳሳት የኛ ባህሪ መሆኑን እንናገራለን። ይሄ ሁሉ ማንነት ግን በሆኑ አጋጣሚዎች ወደ ደቃቅ ማንነቶች ወርደው የትግል እና እርስ በእርስ የመገዳደል ምክንያት ይሆናል። አንድ ሰው በአንድ ጊዜ የብዙ ማንነቶች ባለቤት ቢሆንም፣ ግጭት ውስጥ የሚያወርደው ግን የብዙ ማንነቶች ባለቤት መሆኑ እና በጠላትነት ከፈረጀው ጋር ካለው ልዩነት ይልቅ አንድ የሚያደርገው እንደሚበዛ መርሳቱ እና ያን ማሰብ አለመፍቀዱ ነው።



ፋኖ እና ሸኔ ሆኖ እየተዋጉት ላሉት “ሁለቱም ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ወይም ሁለቱም እልም ያለ ድህነት ያደቀቀው ሀገር አባል መሆናቸው እና ሁለቱም ያለምንም የተረጋጋ ሕይወት ይሄን ዓለም በቅርብ የሚሰናበቱ ሰዎች ስብስብ አባል ናችሁ” ብትሏቸው ከመጣላት ቆም ብለው ማሰብ አይችሉም። ምክንያቱም ማንነትን ማሰብ እና ማሰላሰል ረቶት አያውቅም። (ፋኖን ያስነሳው በደል እና ግፍ ሸኔ ጋር አለ ብዬ አላምንም። ሁለቱ በብዙ ነገር የተለያዩ ናቸው)።



አንድም ብዙዎቻችን በጥቁር እና ነጭ (binary) ነው የምናስበው። ጥሩ እና መጥፎ ሰዎች አሉ፣ ደግ እና የዋህ የሆኑ እንዲሁም አረመኔ እና ርህራሄ አልባ የሆኑ ሰዎች አሉ ብለን እንጂ ማሰብ የምንፈልገው፤ በጎ ነገር ለመስራት የሚጥሩ ግን ደግሞ ፍላጎታቸው እያስቸገራቸው መጥፎ ሥራም የሚሰሩ ግራጫ ሰዎች ብቻ ናቸው ያሉት ብሎ ለመቀበል ይቸግረናል። ሁልጊዜ ወጥነት ያለን (consistent) ሰዎች እንድንሆን ስለምንፈልግ ሌሎችንም የምንረዳው እንደዛው ነው። ፍላጎት ደግሞ እውነት ሆኖ አያውቅም።



በቅርብ አንድ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተሰደደ እና የሕግ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ቢሮአችን የመጣ ኢትዮጵያዊ ሶማሌ፣ ዘሬን ጠየቀኝ። “ቅይጥ ነኝ” አልኩት። “አታጭበርብር፣ ዋናው አባትህ ነው። አባትህ የምን ዘር ነው? አለኝ። ይሄን ሲሰማ የነበረ እዚህ የተወለደ እና ያደገ ሌላ ባለሙያ ደንቆት፣ “ቆይ የእናቱ አይቆጠረም ማለት ነው?” አለው። “አዎ! ዋናው አባት ነው” አለው። ይሄን ሰው እንደምሳሌ አቀረብኩት እንጂ በየቀን ውሎአችን ሰውን በሳጥን ውስጥ ከተን ለመረዳት የምናደርገው ጥረት ሁሉ አንዱን ጥሎ ሌላውን ማንሳት ነው። የሰው ልጅ እንዴት ያለ ውስብስብ የሆነ ፍጥረት እንደሆነ ለመገንዘብ አንፈቅድም። አሌክሳንደር ሶልዦቪስኪ እንዳለው “በጽድቅ በተሞላው የጻዲቁ ልብ ውስጥ የክፋት ጥግ አለ። በክፋት በተሞላው የአረመኔው ሰው ልብ ውስጥ የጽድቅ ድልድይ አለ።” ያን መቀበል ግን ለኛ ፈራጆቹ ከባድ ነው።



ከሶማሌ ክልል የመጣሁ ይሄው የሀገሬ ልጅ፣ ቀጥሎ እንዲህ ብዬ ጠየኩት። “ዘመድ አለህ እዚህ፣ ማነው እየረዳህ ያለው?” መለሰ። “እኛ ሶማሌዎች የኛ ጎሳ ካለ ይበቃናል፣ በጎሳ እንረዳዳለን። እናንተ ሀበሾች ግን የተቸገረ ሰው ስታዩ ከንፈራችሁን በመምጠት፣ እጃችሁን ጭንቅላታችሁ ላይ በማድረግ ምስኪን፣ ሲያሳዝን ብላችሁ አልፋችሁ ትሄዳላችሁ” አለኝ። ነገሩ እንደቀልድም እንደ ጥሩ እይታም ቢያስቀኝም፣ ይሄ በእርስ በእርስ ጦርነት ለ30 ዓመታት እርስ በእርስ ሲገዳደሉ ከኖሩ ማንነቶች ጋር ራሱን በጎሳ የሚያዛምድ ሰው ነው የመሀል ሀገሩን ሰው፣ በሱ አጠራር ሀበሾች የሚላቸውን በአስመሳይነት የከሰሰው። እውነት ነው የሶማሌ ማህበረሰብ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል አለው። እርስ በእርስ የመገዳደልም ሰዋዊ ባህል ግን አለው። ያን የክፋት ጥግ ግን ሁልጊዜ እንደቆሻሻ ጠርገን ከሰው እይታ እንሰውረዋለን፣ ከህሊና ግንዛቤ እናርቀዋለን። ምክንያቱም ለማንነት ግንባታ አይመችም።



ከመቶ ዓመት በፊት አድዋ ላይ ድል ያደረጉ የአርበኞች ልጆች ነን። ነገር ግን መቶ ዓመት ሙሉ በረሀብ የምናልቅ፣ በስደት የምንረግፍ፣ በሕግ የሚመራ ሀገር መመስረት ያልቻልል፣ ሀገራችን ድረስ መጥተው ሊገዙን ወደ መጡት ነጮች ሀገር መሄድ እና መኖር ከልጅነት ጀምሮ ህልማችን የሆንን ዜጎች እና በክላሺንኮቭ መሳሪያ ወንድም ወንድሙን እየጣለ የሚኖርባት ሀገርም ፈጣሪዎች ነን። የመጀመሪያው ለዘፈን ይመቻል፣ ሁለተኛው ግን የየቀን ሕይወታችን እውነት ነው።

 
 
 

Contact the author

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • Instagram

Thanks for submitting!

  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page