የቶልስቶይ ወንጀለኞች
- Mulualem Getachew

- Aug 10
- 4 min read

የሰንበት ዕይታ - 17
የዛሬው ጹሁፍ በውሳኔ አሰጣጥ ጉዳይ እና በሕይወት ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን ስንወስን የሚገጥሙን የስነልቦና ዝንፈቶችን (cognitive dissonance) ይዳስሳል።
ስለውሳኔ ስናስብ ስለራሳችን ማሰብ ግድ ይለናል። ምክንያቱም ለራሳችን ያለን ግምት ነው በውሳኔ አሰጣጥ ሂደታችን ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድረው። ስለራሳችን ያለን በጎ አመለካከት ለአዕምሮም ሆነ አካላዊ ጤናችን እና በሕይወት ላለን ደስታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ለዚህም ነው ስለራሳችን በጎ እና የማይለዋወጥ ምስል (consistent self-image) እንዲኖረን ብዙ ነገሮችን ስንሰራ የምንታየው።
ይሄን የማንነት ምስል ለመጠበቅ ስኬትን ለራሳችን የመውሰድ ጠንካራ ዝንባሌ ሲኖረን ውድቀትን ደግሞ ለሌሎች እንሰጣለን። ገና ልጅ እያለን በቋንቋችን ሳይቀር የሚዋሃደን ይሄ አስተሳሰብ ነው። ጥሩ ውጤት በትምህርት ስናገኝ “አገኘው!” እንላለን። መጥፎ ውጤት “ሲ” ወይም “ዲ” ስናገኝ “አስተማሪው ሰጠኝ” ነው የምንለው። ይሄ ውድቀትን ለራስ ባለመስጠት ስነልቦናዊ ማንነታችንን እየጠብቅን ነው። በዚህም ራሳችንን ከተራ ሰዎች የተሻልን እንደሆን እናምናለን፣ በእውቀት፣ በውበት፣ በባህሪ፣ በጥረት እና በችሎታ ከብዙ ሰዎች እኛ የተሻልን እንደሆን እናምናለን ወይም ማመን እንፈልጋለን።
ይሄ ስለራስ ያለ የተጋነነ በጎ አመለካከት በጥቂት ሰዎች ላይ የሚስተዋል ሳይሆን ብዙ ሰዎች ያላቸው ማንነት ነው። አንዳንዴ ግን ሕይወት ይሄን ስለራስ ያለንን ግምት ይቀደዋል (smash it)። ከሥራ እንባረራለን፣ ሰዎች ይተውናል፣ ማግኘት ተስፋ ያደረግነውን ነገር እናጣለን ወይም በሰዎች ፊት ከፍተኛ ነቀፋ ይደርስብናል ፥ እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ደግሞ ለራሳችን ከሰጠነው ግምት ተቃራኒ የሆኑ ውሳኔዎችን እንወስናለን።
ይሄ ስለራስ ባለ ልዩ እና ከእውነታው የተለየ ምስል ምክንያት ፊት ለፊት ያለን ሀቅ ለመቀበል እንቸገራለን። በዚህም ቀላል እና ጊዜያዊ የነበሩ ችግሮቻችን ሥር ይሰዳሉ። ይሄን ስሱ (fragile) የሆነ ስለራስ ያለን ግምት ለመጠበቅ ጊዜያችንን ባልሆኑ ነገሮች እናባክናለን፣ አላስፈላጊ እና ጊዜ አባካኝ ክርክሮች ውስጥ እንጠመዳለን፣ አንዳንድ ሰዎች ወደ ሱስ ወይም ለእነሱ የማይመጥን ግንኙነቶች ውስጥ ይነከራሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የቶልስቶይ ወንጀለኞች ለዚህ አመለካከት ገላጭ ምሳሌዎች ናቸው። ቶልስቶይ በልቦለዶቹ ወንጀለኞቹ ሁለት ዓይነት ስነልቦና እንዳላቸው ያሳየናል።
የመጀመሪያው እውነትን ይሸሹታል ፥ በመካድ፤ መካድ የሚከሰተው ስለሕይወት ኃያል እውነት ፊትለፊት ሲገጥመን እና ያን ከመቀበል ይልቅ መካድን ስንመርጥ ነው። ለምሳሌ ልጆቿቸው ከመስመር እየወጡ እና ያልሆነ ሕይወት ውስጥ እየገቡ የሚመለከቱ ወላጆች ይሄን ወዳጆቻቸው ሲነግሯቸው የመጀመሪያው ግብረ መልሳቸው መካድ ነው። እነዛ ያሳደጓቸው ልጆች፣ ከምንም ነገር በላይ የሚወዷቸው ልጆቻቸው በመጥፎ ሕይወት ውስጥ ተገኝተዋለ ብለው ማሰብ አይፈልጉም። ስለዚህ ወሬውን ያመጡላቸውን ሰዎች መንቀፍ ወይም መቀየም ይቀላቸዋል እውነታን ከመጋፈጥ ይልቅ።
በተመሳሳይ ቆዳችን ላይ የሆነ ጥቁር ነጥብ ቢወጣ፣ መጀመሪያ ሊያስደነግጠን ይችላል። ከዛ ግን እንረሳዋለን። ከሳምንታት በኋላ ስናየው የበለጠ ጠቆረ እንጂ የተለወጠ ነገር የለም። ምንአልባት ከዚህ ከሳምንታት መካድ በኋላ የበለጠ መጥቆሩ ከመካድ ሊያወጣን ይችላል። የመጀመሪያው ግብረ መልሳችን ግን መካድ ነው። እንዲሁ እንደወጣ እንዲሁ እንዲጠፋ መመኘት ነው።
ልጃቸው ወደጦርነት የሄደ እና ከዛ ያልተመለሰ ቤተሰብ አውቃለሁ። ጦርነቱ ካለቀ ረጅም ጊዜ ቢሆንም የልጃቸው አለመመለስን ሞቶ ነው ብሎ መቀበል አይፈልጉም፤ ሰው ሁሉ ያን ቢያምንም። ይሄ እውነታ የሚነግረኝ በጣም የምንወደው ነገር ሲሆን በዛ ነገር ላይ የደረሰ ክፍ ነገርን መቀበል ይከብደናል። በጣም የምንጠላው ነገርም ሲሆን ያ ነገር በጎ ነገር እንዳለው መቀበል እንቸገራለን። ስለዚህ ጠንካራ ስሜቶች ሁልጊዜ መካድ ይከተላቸዋል። ለምሳሌ ሂትለር ሕጻናትን የሚወድ እና ለሕጻናት ስሱ ልብ እንዳለው መቀበለ ይከብደናል። ምክንያቱም ሂትለር በብዙ ነገር ክፉ እና አረመኔ ስለሆነ። አንድ የሚሊተሪ ስትራቴጂስት “ጠላቴን አልጠላውም፣ ምክንያቱም ጥላቻ ጠላቴን እንዳላይ ይከልለኛል” ይላል። ጥላቻ የወረረው አዕምሮ ፈጽሞ ስትራቴጂክ ውሳኔዎችን መወሰን አይችልም። ፍቅርም የወረሰው አዕምሮ እውነታን የመጋፈጥ አቅም የለውም።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሱስ (addiction) ነው። የሰው ልዩ ባህሪው ራሱን ፍጹም መውደዱ ነው። በዚህም ማናችንም ደደብ እንደሆንን እና የሆኑ ነገሮችን ማድረግ እንደማንችል መቀበል ይቸግረናል። ለዚህ ነው በሌሎች ላይ ውበት ስናይ የሚቀናን መተቸት ወይም የሚነቀፍ ነገር መፈለግ የሚሆነው። ምክንያቱም ያ ሰው ከኛ የሚያንስበትን ነገር ነው የምንፈልገው። ሱስ ከዚህ የሚመነጭ ነው። ሱሰኛ ሰዎችን ተመልከቱ። (በርግጥ በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ማን ሱሰኛ ያልሆነ አለ?) ሁሉም በማንኛውም ሰዓት ያን ሱስ ማቆም እንደሚችሉ ነው የሚያምኑት። ምክንያቱም አልችልም የሚለው ስሜት በከፍተኛ ደረጃ ለራሳቸው የሰጡትን በጎ ስሜት (self-iamge) ይጎዳዋል። ስለዚህ ሰው ሁሉ የሚያውቀውን እውነት ይክዱታል። ከሱ መውጣት እንደከበዳቸው።
ሾፐናወር ለሰው ልጅ መቀበል ከሚከብደው አሉታዊ ስሜት ከሆኑት ትልቁ “ደደብ ነኝ የሚለው ስሜት ነው” ይላል። ይሄ ያለመቻል ስሜት ለራሳችን የሰጠነውን የተጋነነ ስሜት፣ ራስን ከመውደድ እና ስሱ (frgile) የሆነውን ማንነታችን እንዳይጎዳ ከመጠበቅ የመጣ ፍላጎት ስለሆነ ፊት ለፊት ያለውን ሀቅ እንሸሻለን፣ እንክደዋለን። ይሄ የጥሩ ውሳኔዎች ሁሉ የመጀመሪያው እንቅፋት ነው።
ሁለተኛው የቶልስቶይ ወንጀለኞች ባህሪ ምክንያት መስጠት (self-justification) ነው፤
የቶልስቶይ ወንጀለኞች ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ ያን ወንጀል በዛ ሁኔታ (context) ውስጥ ወይም በእነርሱ ላይ ከደረሰባቸው አንጻር ተገቢ እንደሆነ ምክንያት ይሰጣሉ። ጉቦ የሚሰጥ ሰው ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት ጉቦ ከሚቀበለው ልዩነት የለውም። ሁለቱም ካለጉቦ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ነው የሚናገሩት። ጉቦ ተቀባዩ ያለጉቦ የኑሮ ውጣ ውረድን ማሸነፍ እንደማይችል ሲናገር ፥ ጉቦ ሰጪውም የቢሮክራሲውን ውጣ ውረድ ያለጉቦ ማለፍ እንደማይችል ነው የሚገልጸው።
ሁለቱም ወንጀል እየሰሩ እና በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቃቸውን አስነዋሪ ተግባር እየሰሩ መሆናቸውን ማመን አይፈልጉም። ይልቁስ ከመሠረታዊ እምነታቸው ጋር እንዳይጋጭ ለዛ ምክንያት ይሰጣሉ።
ምክንያት የመስጠት (justification) ትልቁ መገለጫ ማቆም ነው። ለምሳሌ ሲጋራ ለማቆም ጥሮ ያልቻለ ግለሰብ የሚያደርገው ሲጋራ መጥፎ ነው ብሎ ማመን ያቆማል። ይልቁስ ሲጋራ እያጨሱ እስከ 90 እና 80 ዓመት የኖሩ ጥቂት ሰዎችን መጥቀስ ይጀምራል ወይም “ሕይወት ማለት ካላጨስክ እና ካልጠጣክ ምኑን ሕይወት ሆነ?” ማለት ይጀምራል። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአገቱኒ መጽሐፉ የነገረን የዚህ ባህሪ ተጠቂ መሆኑን ነበር። አቆመ። ቤተክርስቲያን መሄድ እና ማስቀደስ አቆመ። ንጉሱ “ለምን አቆምክ?” ብለው ሲጠይቁት የመለሰው “መጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላኛውን አዙርለት ይላል፤ እኔ ግን መልሼ ነው የምመታው። ለነገ አትጨነቁ ይላል፣ እኔ ደግሞ ልጆች አሉኝ አለመጨነቅ አልችልም። ስለዚህ አቆምኩኝ” አለ። አለመጨነቅ ጥሩ መሆኑን ሳይሆን ፥ ለመጨነቁ ምክንያት መስጠት ተያያዘ። መታገሰን ገንዘብ ከማድረግ ይልቅ ፥ ታገሱ የሚለውን ስብከት መስማት ማቆም የቶልስቶይ ወንጀለኞች ባህሪ ነው።
በሕይወታችሁ ጥሩ ውሳኔ ለመወሰን ትፈልጋላችሁ? በተቻለ መጠን እውነታን ተጋፈጡ። ሲ ኤስ ሉዊስ ለኦክስፎርድ ተማሪዎቹ የሚላቸው ይሄን ነበር “እውነታን በጥቂቱ ካሳየናችሁ ፥ እውነትን የማየት ድፍረት በጥቂት ከሰጠናችሁ፤ ያን ጊዜ ስኬታማ ፕሮፌሰሮች እንባላለን። የኛ ዓላማ እውነትን የሚያዩ እና ያዩትን እውነት የመናገር ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ማፍራት ነው።”
እውነታው ከምናስበው በላይ ደደቦች ነን። እውነታው ብዙ ነገሮችን ማቆም አንችልም። እውነታው ስሜታዊ ነን። እውነታው ፈሪዎች ነን። እውነታው ከመጠን በላይ በሰዎች መወደድ እንፈልጋለን። እውነታው እንደምናስበው ጥሩዎች አይደለንም። እውነታው ሰንፎች ነን። እውነታው አድሎአዊ እና ዘረኞች ነን። ይሄን ስለራስ መቀበል ያማል፣ ግን ይሄን በጊዜ እንደመቀበል ምንም ፈጣን የመፍትሔ እና የለውጥ መንገድ የለም። አዎ ለዚህ ብዙ ምክንያቶችን መስጠት እንችላለን፤ ግን እውነታውን አይቀይሩትም።
ቻርሊ መንገር ስለወዳጁ ልጅ እና አባቱ ስላለው ነገር እዚህ ጋር ማንሳቱ በጣም ጠቃሚ ነው። ልጁ ከአባቱ የሳንቲም ማጠራቀሚያ “በኋላ እተካለሁ” እያለ ሁልጊዜ ይወስዳል። ይሄን ባህሪ ያስተዋለ አባት “ልጄ! ግድ የለህም ስትወስድ በኋላ እተከዋለሁ እያልክ ተደብቀህ ከምትወስድ ፥ በወሰድክ ቁጥር ሁሉ ራስህን ሌባ እያልክ ጥራ” አለው። ያ ልጅ ዛሬ አድጎ እና ተለውጦ የካሊፎርኒያ ቢዝነስ ስኩል ዲን ሆነ። መጥፎ ነገር ስናደርግ ራሳችንን በዛ ስም እንጥራው። አዎ፣ “ዝሙት እየሰራው ነው። እየሰርኩኝ ነው። ወንጀል እየሰራው ነው።” እንበል። በውሸት ምክንያት የተገነባን የራስ ምስል (self-iamge) ከመጠበቅ ይልቅ፤ ራሳችንን ለዛ ባህሪ ተገቢ በሆነ ስም እንጥራው። ከዛ ባህሪ ለመላቀቀ ትልቅ እርዳታ ይኖረዋል። ከአስርቱ ትዕዛዛት ሁለተኛው “የተቀረጸ ምስል ለራስህ አታኑር” የሚል ነው። ይሄ የተቀረጸ ምስል አንዱ የራስ ምስል (self-iamge) ነው። በምክንያት የምንጠብቀው፣ እውነትን በመካድ ያቆምነው፣ ይሄ ስሱ ምስል (fragile self-image)፣ የሰዎችን መጥፎ ንግግር እና ነቀፋ መቋቋም የማይችለው ፣ በተግሳጽ እና በአሉታዊ ኮሜንት የሚፈርሰው ፣ ላይክ እና አስመሳይ የማሽሞንሞን ቃሎች የሚያለመልሙት የተቀረጸው የራስ-ምስል (carved self-image) ለጥሩ የሕይወት ውሳኔ ሁለተኛው እንቅፋት ነው።






Comments