በሊዮ ቶሎስቶይ
ትርጉም በሙሉዓለም ጌታቸው
ክፍል አንድ
1
ታላቅ እህት ታናሽ እህቷን ልትጎበኝ ወደ ገጠር መጣች። ታላቋ በከተማ የሚኖርነጋዴ ያገባች ሲሆን ፥ ታናሿ ደግሞ አንድ በገጠር ያለ ገባር አግብታለች። እህትማማቾቹ ለሻይ ተቀምጠው ሲያወጉ ፥ ከተሜዋ ወይዘሮ ስለከተማ ኑሮ በረከቶች በማጋነን ማውራት ጀመረች ፥ እንዴት በምቾት እንደሚኖሩ፣ እንዴት ምርጥ ምርጥ ልብስ ልጆቿ እንደሚለብሱ፣ ስለሚበሉት ምግብ፣ ስለሚጠጡት መጠጥ፣ ስለሚሄዱበት ቲያትር እና መዝናኛዎች በኩራት አወጋች።
ታናሿ በተራዋ በንዴት ውስጥ ሆና ፥ የከተሜን ሕይወት እያጣጣለች ፥ የገባሮችን ሕይወት በማድነቅ ተናገረች። “ያንቺን ሕይወት በእኔ አለውጥም ፥ ኑሮአችን ከባድ ሊሆን ይችላል ፥ ቢያንስ ግን ጭንቀት የለበትም።” አለቻት። “ከኛ የኑሮ ደረጃ የሚሻል ትኖሪያለሽ ፥ ከሚያስፈልግሽም በላይ ታከማችያለሽ። ነገር ግን ያለሽን ሁሉ ማጣትሽ አይቀርም።” “አባባሉንም ታቂያለሽ አይደል ‘ማግኘት እና ማጣት መንታ ወንድማማቾች ናቸው’ የሚለውን።” “ባብዛኛው ዛሬሃብታም የሆኑ ሰዎች ፥ ነጋ ዳቦ ይለምናሉ ፥ ስለዚህ የኛ ሕይወት ነው ዋስትና ያለው። የገባር ሕይወት ወፍራም ባይሆንም ረዥም ነው ፥ መቼም ሃብታም ባንሆንም ፥ በቂ የምንበላው ግን አናጣም” አለች በድፍረትና ራስን በመከላከል መንፈስ።
ታላቋም ንቀት በተሞላበት ሁኔታ “በቂ?” “እውነትሽን ነው ነገሩ ከአሳማ እና ከከብቶች ጋር እየተጋሩ ለመኖር በቂ ነው። ክብር ስላለው ሕይወት ምንድ ነው የምታውቂው? ያንቺ ገባር እንዴትም ያለ ጥሩ ባሪያ ቢሆን የተለየ ነገር መፍጠር አይችልም ፥ እንደዚሁ እንደሆንሽ ፥ ልጆሽም በከብቶች ኩበት ላይ እንደተኙ ነው የምትሞቺው” አለቻት።
“ምንድነው ይሄ ሁሉ?” አለች ታናሿ። “ልክነው ስራችን ከባድ እና አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን የማረጋግጥልሽ ነገር ለማንም ማሸርገድ እንደማያስፈልገን ነው። አንቺ እና ያንቺ ከተሜዎች በፈተና የተከበባችሁ ናችሁ። ዛሬ ሰላም ሊመስልሽ ይችላል ነገ ግን ሰይጣን ባልሽን በቁማር፣ በወይን ወይም በሴቶች ጾር ያጠቃዋል ፥ከዛም ዛሬ የተመጻደቅሽበት ሁሉ አመድ ይሆናል።” “ይሄ በዓይንሽ ፊት ስንቴ እንደከሰተ ትክጃለሽ?”
ፋሆም ፥ የቤቱ ጌታ ፥ የታናሺቱ ባል በመደብ ላይ ተኝቶ ፥ የሴቶቹን ጫወታ ያደምጥ ነበር።
“ይሄ እኮ ፍጹም እውነት ነው!” አለ በልቡ። እኛ ገባሮች ከልጅነታችን ጀምሮ ምድርን “በማረስ እረፍት የለንም ፥ እነዚህ ሃሳቦች በአዕምሮአችን ሊያርፉ በቂ ጊዜ እንኳን የለንም። ብቸኛው መከራችን በቂ መሬት የሌለን መሆኑ ነው። በቂ መሬት ቢኖረኝ ሰይጣንን እንኳን አልፈራም ነበር።” አለ።
ሴቶቹም ሻያቸውን መጠጣታቸውን ጨርሰው ፥ ጥቂት ስለአልባሳት ካወጉ በኋላ፥ ሻዩን አነሳስተው ወደ መኝታ ሄዱ። ሰይጣን ግን ከመደቡ በስተጀርባ ተቀምጦ የሚወራውን ሁሉ ያደምጥ ነበር። ታናሿ ባሏ እንዲታበይ ስለገፋችው እና ብዙ መሬት ቢኖረኝ ሰይጣንን እንኳን አልፈራም ወደማለት ስላደረሰችው ሰይጣን በእጅጉ ተደሰተ። “ያዝ እንግዲ” አለ ሰይጣን ፥ “ምርጥ የሚጠመድ አገኘን ፥ አሁን መሬቶችን ሰጠዋለው ፥ በዚህም የእጄ መዳፍ ውስጥ አስገባዋለው” አለ።
2
በመንደሩም አንዲት የመሬት ከበርቴ ትኖር ነበር ፥ ወደ 3 መቶ የሚጠጋ ሄክታር መሬት ነበራት። ከገባሮቿ ጋር ለብዙ ዘመናት በሰላም ነበር የኖረችው አንድ ክፉ ወታደር ለመሬቷ ጠባቂነት አስጠግታ በገባሮቹ ላይ ቀንበራቸውን እስከሚያጠብቅባቸው ድረስ።
ፋሆም እጅግ ጠንቃቃ ገባር ቢሆንም አንዴ ፈረሱ የሴትየዋን የአጃ እህል በላ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከብቱ ከጓሮዋ ገባ፣ የሆነ ቀን ደግሞ ጠቦቱ የሚወቃ እህል ጋር ገብቶ ተገኘ እየተባለ ለነዚህ ሁሉ ቅጣት መክፈል ነበረበት።
ፋሆም ቅጣቶቹን ቢከፍልም ፥ ቤት ተናዶ መሄድ ጀመረ ፥ ቤተሰቡንም ያጎሳቁል ጀመር። በበጋው በሙሉ ፋሆም በዚህ ወታደር ምክንያት ሲሰቃይ ቆየ ፥ ከዚህ የተነሳ የበረዶው ወቅት በመግባቱ ተደሰተ ምክንያቱም ከብቶቹ ከበረታቸው አይወጡም ነበርና። ከብቶቹ ወደ ግጦሽ ባለመሄዳቸው ውስጡ ባይደሰትም ፥ ቢያንስ ከጭንቀት ተገላግሏል።
በክረምት ሴትየዋ መሬቷን ልትሸጥ መሆኑ ተሰማ ፥ መንገድ ተሻግሮ የሚገኘው የእንግዶች ማረፊያ ጠባቂ መሬቷን ሊገዛ እየተነጋገረም እንደሆነ ገባሮቹ ወሬ ሲደርሰቻው በንቃት መከታተል ጀመሩ። የዚያ የእንግዶች ማረፊያ ጠባቂ መሬቱን ከገዛማ ፥ ከዚህ ወታደር በላይ በቅጣት ያሰቃየናል ሲሉ ገባሮች መከሩ።ሁላችንም ኑሮአችን በዚህ መሬት ላይ ነው የተመሰረተው ስለዚህ ይህ መሬት ከእጃችን እንዳይወጣ ማድረግ አለብን ብለው መከሩ።
ገባሮቹ ወደ ሴትዬዋ ሄደው መሬቱን ለጠባቂው እንዳይሸጡት ለመኗት ፥ በገባሮች ህብረት ስምምነት መሰረት ለእነሱ እንድትሸጥላቸው የተሻለ ገንዘብ ሰጧት። ሴትየዋም መሬቱን እንዲገዟት ፈቀደችላቸው። የገባሮቹ ኮሚቴዎችም መሬቱን በጋራ በመግዛት ፥ በጋርዮሽ እንዲተዳደር ሃሳብ አቀረቡ።ሁለቴ ቢሰበሰቡም መስማማት አልቻሉም ፥ ሰይጣን በመካከላቸው የመለያየትን ዘር ዘርቷልናል። ስለዚህ በግል መሬቱን ለመግዛት ተስማሙ ፥ ሁሉም እንደየአቅሙ እንዲገዛ ወሰኑ ፥ ሴትዬዋም ልክ እንደመጀመሪያ ለዚህም ሃሳብ ተስማማች።
ፋሆም ጎረቤቱ 50 ሄክታር መሬት መግዛቱን እና ሴትዬዎም የክፋያውን ግማሹን አሁን ፥ ግማሹን ከዓመት በኋላ ለመቀበል እንደተስማማችለት ሲሰማ በቅናት ተቃጠለ።
“ተመልከቱ ፥ መሬቱ ሁሉ ተሸጠ ፥ ለኔም ምንም አልደረሰኝም ሲል” አሰበ። ይሄንንም ለሚስቱ አማከራት።
“ሌሎች ሰዎች እየገዙ ነው ፥ እኛም 20 ሄክታር መሬት መግዛት ያሻናል ካለዛማ ኑሮ የሚገፋ እየሆነ አይደለም” አለ። ይሄ ወታደር በሚጥልብን ቅጣት ወገባችንን እየሰበረን ነው።
ባልና ሚስት በጋራ ተመካክረው መሬቱን እንዴት መግዛት እንዳለባቸው አቀዱ። ያላቸውን መቶ ሩብል፣ መሳሪያቸውን እና ንቦቻቸውን በመሸጥ እንዲሁም አንደኛው ልጃቸውን በጉልበት ሰራተኝነት በማስቀጠር እና ቅድመ ክፍያ በመቀበል፣ እንዲሁም ከወንድሟ በመበደር መሬቱን ለመግዛት የሚያስችል ግማሽ ገንዘብ ማሰባሰብ ቻሉ።
ይሄን ካደረገ በኋላ ፋሆም ፥ 40 ሄክታር መሬት ለመግዛት በማቀድ (ግማሹ በዛፍ የተሸፈነ ነበር) ወደ ሴትዬዋ አመራ ፥ ከሴትዬዋም ጋር በመስማማት ተጨባበጡ ፥ ግማሹን በቅድሚያ ለመክፈል ፥ ግማሹን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊከፍል ተስማምተው ፥ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስለዚህ ፋሆም አሁን የራሱ መሬት አገኘ። በገዛው መሬት ላይ ዘር ተበድሮ ዘራ። አዝመራው በደንብ አማረለት ፥ በዚህም የሴትዮዎንም የሚስቱ ወንድምንም ብድር በአንድ ዓመት ውስጥ መክፈል ቻለ። አሁን በራሱ መሬት ላይ ማረስ፣ ከብቶቹን በራሱ መሬት ላይ ማሰማራት፣ ለግጦሽ መልቀቅ እና እንደፈለገ ዛፍ መቁረጥ ቻለ። ወደ እርሻ ሲሄድ፣ የሚያድገውን ሰብል ሲመለከት፣ ያደገውን ሣር እና የተከመረውን እህል ሲያይ ልቡ በሃሴት ሞላ። በሱ መሬት ላይየበቀለው ሣር ፥ ያበበው አበባ በማንም መሬት ላይ ካለው ልዩ ሆኖ ታየው። ድሮ በዚህ መሬት ላይ ሲያልፍ ልክ እንደሌሎች መሬቶች ነበር ሆኖ የሚታየው ፥ ዛሬግን ልዩ ሆኖ ተመለከተው።
3
ፋሆም በደስታ ተሞልቶ እና ረክቶ ይኖር ነበር ጎረቤቶቹ የእህል መስኩ ላይ መመላለስ ባያበዙ ኖሮ። በትህትና ጎረቤቶቹን በማሳው እንዳይመላለሱ ቢጠይቃቸውም ጭራሽ ከብቶቻቸውን መልቀቅ እና የጢሰኞቹ ፈረሶች ደግሞ ከብቶቹ በቀደዱበት በመግባት ማሳውን ማበላሸት ተያያዙት። ፋሆም ሳይሰለች ከብቶቹን ማባረር እና ባለቤቶቹንም ይቅር ማለት ተያያዘው። ለረዥም ጊዜም ቀበሌ ሄዶ ሳይከስ ቆየ። በመጨረሻም ትግስቱ ሲያልቅ በቀበሌው ፍርድ ቤት ከሰሳቸው። መሬቱን ፈልገው እንደሆነ ግብቶታል ፥ ከዛ የዘለለ ክፋት እንደሌላቸው ቢገባውም አሁን አንዳች ነገር በቶሎ ካላደረግ ዝምታው እና ትግስቱ ሊያጠፋው እንደሚችል አመነ። ስለዚህ ተገቢውን ትምህርት ሊያስተምራቸው ወሰነ።
በዚህም መጀመሪያ አንዱን ጢሰኛ አስቀጣው፣ በመቀጠል ሌላውን፣ ከዛም ሌላኛውን ... በዚህም ጎረቤቶቹ ቂም ቋጥረውበት ሆን ብለው ከብቶቻቸውን ወደ ማሳው መልቀቅ ጀመሩ። አንድ ጢሰኛ ጭራሽ በማታ ተደብቆ ወደ ፋሆም እርሻ በመግባት አምስት የሎሚ ዛፎችን ለልጣጫቸው ሲል ቆርጦ ጥሎ ሄደ። አንድ ቀን በእርሻ ውስጥ ሲያልፍ ነጭ ቅርፊቶችን ዓይቶ ምንድነው ብሎ ሲጠጋ የተቆረጡ የዛፍ ግንዶችን ተመለከት። በዚህም ፋሆም ንዴቱ ሰማይ ነካ።
“አንድ ብቻ እዚህ ቆርጦ ቢሆን ጥሩ ፥ ይሄ የተረገመ ግን ያሉትን ሁሉ ነው የቆረጠው ፥ ይሄን ያደረገውን ባገኝ ልኩን አስገበዋለው” አለ በብስጭት።”
ያደረገውን ለማወቅ ማሰላሰል ጀመረ። በመጨረሻም አለ “ይሄን ሊያደርግ የሚችለው ስምዖን ነው ፥ ማንም እንደዚህ አያደርግም።” ተነስቶ ወደ ስምዖን መኖሪያ ሄደ ፥ ከራሱ ንዴት ውጪ በስምዖን ቤት ዙሪያ ስምዖን ዛፎቹን መቁረጡን የሚያሳይ ምንም ነገር አላገኘም። ፋሆም ግን ልቡ አንዴ ስምዖን ነው ስላለ ምንም አለማግኘቱ ጭራስ ስምዖን እንደሆነ እንዲያምን የበለጠ አደረገው። በዚህም ለፍርድ ቤት ክስ አቀረበ። ክሱም በፍርድ ቤቱ ቢታይም ስምዖንን ጥፋተኛ ሊያስብል የሚችል ምንም ነገር አልነበረም። ፋሆም ግን ንዴቱን ስምዖንን ነጻ ነህ ባሉት ዳጆች ላይ ገለጠ።
“ሌባን ዛፎቹን እንዲጨርሳቸው በነጻ ለቀቃችሁ። እናንተ ራሳቹ ቅን እና ንጹሁ ብትሆኑ ይሄን ሌባ በነጻ ባለቀቃችሁ ነበር” አላቸው።
በዚህም ፋሆም ከጎረቤቶቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከዳኞቹም ጋር ተጣላ። ቤቱን ሊያቃጥል ነው የሚል ወሬም ተሰራጨ። ፋሆም ከድሮ የበዛ መሬቶች አሁን ቢኖሩትም ፥ ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት እና ከጎረቤቶቹ ጋር ያለው ሰላም ግን ተበጠበጠ።
በዚህ ሰዓት ነው ሰዎች ወደ አዲስ ቀዬ ለቀው እየሄዱ መሆናቸውን የሰማው።
ፋሆም ግን በውስጡ “ሰው ሁሉ እየሄደ ከሆነ እኔ መሄድ አይጠበቅብኝም።ይልቁስ እነሱ የለቀቁትን መሬት እኔ መያዝ እና መጠቅለል እችላለሁ። ገና ምን አለኝ እና ነው ተዘልሌ የምቀመጠው። ርስቴን ማስፋት መቻል አለብኝ” አለ።
በአንዱ ቀን ፋሆም በቤት ሳለ አንድ ጢሰኛ በፋሆም መንደር ሲያልፍ ወደ ቤት ተጋብዞ ገባ። በዛም ፋሆም ከየት እንደመጣ ሲጠይቀው “ከቮልጋ እንደመጣ እና ብዙ ሰዎች በዛ እየሰፈሩ መሆናቸውን” ነገረው። አንድ አንድ ሲባባሉ ፥ ጢሰኛው በቮልጋ ስላየው እንደተዓምር ለፋሆም ይነግረው ጀመር። ሰዎች በነጻ እስከ ሃያ አምስት ሄክታር እንደሚያገኙ እና ከመሬቱ ለምነት የተነሳ የሚዘራው አጃ የፈረስ ቁመት እንደሚደርስ፣ ከዛም የሚወጣው እህል አስገራሚ እንደሆነ ነገረው። በተለይ አንድ ባዶ እጁን የመጣ ገበሬ ፥ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ስድስት ፈርስ እና ሁለት ከብቶች መግዛት እንደቻለ ነገረው።
የፋሆም ልብ በፍላጎት እሳት ነደደ። በልቡም “ለምንድነው በዚህ ጠባብ ሸለቆ የምሰቃየው ፥ ሌላ ቦታ በሰላም መኖር ከቻልኩኝ፧ ቤቴን እና ንብረቴን ሸጬ እዛ ሄጄ እንደ አዲስ እጀምራለሁ አለ። በዚህ ጠባብ ቦታ ሁሌ መከራ ነው ያለው ፥ ነገር ግን መጀመሪያ ራሴው ሄጄ ስለስፍራው ማጥናት ይኖርብኛል” አለ። በበጋም ወደ ተባለው ቦታ አቀና ፥ በጀልባ መጀመሪያ ከዛም በእግሩ ከሦስት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ተጓዘ። ሁሉም ነገር ያ ጢሰኛ እንዳለው ሆኖ አገኘው፣ ሰው ሁሉ መሬት አለው፣ ገንዘብ ያለው ሁሉ መሬት መግዛት ይችላል፣ በተለይ በሁለት ሺሊንግ እስከ 20 ሄክታር መሬት መግዛት እንደሚቻል አየ።
ምኞቱን ሁሉ ካየ በኋላ ወደ ቀየው ተመልሶ ፥ በጋው እስከሚወጣ ጠብቆ መሬቱን እና ከብቶቹን በትርፍ ሸጠ። ከማህበሩም ራሱን አገለለ። ጸደይ እስከሚገባ ጠብቆ ፥ ቤተሰቡን ጠቅልሎ ፋሆም ለአዲስ ሰፈራ ወደ ቮልጋ አቀና።
4
አዲሱ መኖሪያው እንደደረሰ ፥ ፋሆም መሬት ለማግኘት የገበሬዎች ሕብረት አመለከተ። እስፈላጊውን ሰነዶች እንዳሟላ ሲያዩ ፥ ለእሱ እና ለወንድ ልጆቹ አምስት ባለ ሃያ አምስት ሄክታር መሬት ማለትም መቶ ሃይ አምስት ሄክታር የተለያዩ ቦታዎች አገኘ።
ወዲያውም መሬቱ ላይ ቤት ሰራ፣ ከብቶችንም ገዛ። አሁን ያገኘው መሬት ከበፊት በሦስት ዕጥፍ ይበልጣል ፥ መሬቱ ደግሞ የወጣለት ለም ነበር። ከዚህ በፊቱ ጋር ሲነጻጸር አሁን በአስር እጥፍ ይበልጣል። ከበቂ በላይ መሬት፣ ለግጦሽ የሚሆን መስክ እና የፈለገውን ያህል ከብት ማኖር የሚችል ስፍራ አገኘ።
መጀመሪያ ፥ ቤት በመስራት እና በመስፈር ጥድፊያ ውስጥ ሆኖ ፥ ፋሆም በሁሉም ነገር ደስ አለው ነገር ግን ትንሽ እንደቆየ ሁሉን ነገር ለመደው፣ ከዛም አሁንም በቂ መሬት እንደሌለው ይታሰበው ጀመር። በመጀመሪያ ዓመት በመሬቱ ላይ ስንዴ ዘርቶ በብዛት ሰበሰብ። ስንዴ በብዛት መዝራት ፈልጎ ነበር ግን ያለው መሬት ላሰበው የሚበቃ አልሆነለትም ፥ ያለው ደግሞ አላረካውም። ባለው ለም እና የራሰ መሬት ላይ በመኃል ለመሬቱ እረፍት ሳይሰጥ ከሁለት ዙር በላይ ማብቃል አልቻለም ። ሌላ በዛ ያለው መሬት ደግሞ ለግጦሽ ሣር የተተወ እና ብዙ ሰዎች የሚመኙት ነው ስለዚህ ለሚፈልጉት ሁሉ ለማከፋፈል ስለማይበቃ ሁሉም ተጣሉበት። ሀብታም የነበሩት መሬቱን ወስደው ስንዴ መትከል ፈለጉ ፥ ድሆቹ ደግሞ በማከራየት ታክስ መሰብሰብ ፈለጉ በዚህም የገበሬ ማሀበሩ በቀሪው መሬት ላይ ሳይስማሙ ቀሩ። ፋሆም ግን መሬት ከሌላ ሰው ተከራይቶ ብዙ ስንዴዎችን ዘራ። ብዙ ስንዴ ዘርቶ እጅግ ብዙ ቢያመርትም መሬት እሱ ካለበት ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ስለሚርቅ እህሉን ማመላለስ ጉልበት እና ወጪ አበዛበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፋሆም የጢሰኛ ነጋዴዎች በሌላ የእርሻ መሬትላይ እየኖሩ እና እህል እያመረቱ ሀብታም መሆናቸውን አስተዋለ ፥ ከዛም እኔምእኮ እንደነሱ እነዚህን ያልተያዙ መሬቶች ገዝቼ፣ ቤት እዛ ላይ ብሰራ የተለየ ሕይወት መኖር እችላለው ብሎ አሰበ። ከዛም በጣም ጥሩ እና የተደላደለ ሕይወት ይኖረኛል።
ነጻ መሬቶችን የመግዛት ፍላጎት በአዕምሮ ውስጥ ያለዕረፍት ተደጋግሞ ያቃጭለበት ጀመር።
ለሦስት ዓመታት መሬት በመከራየት እና ስንዴ በመዝራት ቀጠለ። የዝናብ ወቅቶቹ ሳይቆራረጡ እና እህሉም ጥሩ እየያዙለት ፥ በጥሩ ሁኔታ እያመረተ ቀጠለ። እንደዛ መቀጠል ይችል ነበር ግን የሰዎችን መሬት እየተከራየ እና እነሱን እየተለማመጠ መኖር ደከመው። ጥሩ መሬት ሲገኝ በዛ ያሉ ጢሰኞች ተሽቀዳድመው ነበር የሚገዙት በዚህም በጣም ምስጥ እና ፈጣን ካልሆንክ ምንም አታገኝም። በሦስተኛው ዓመት እንዲህ ሆነ ፥ አንድ ገባር ነጋዴ እና ፋሆም ከጢሰኞቹ የታረሰ እና ዘር የተዘራበት መሬት ተከራዩ ፥ በኋላ ግን በተዘራው ላይ የይገባኛል ክርክር ተነስቶ ወደፍርድ ቤት በመሄዳቻው እህሉ ሳይታጨድ ጊዜው በማለፉ በዛ ላይ የዋለው ጉልበት ሁሉ በከንቱ ፈሰሰ።
በዚህ ጊዜ ነው ፋሆም ምርር ብሎት የራሴ መሬት ቢሆን ይሄ ሁሉ ጭቅጭቅባኖረ ፥ ያለምንም ጣልቃ ገብነት እህሌን በአግባቡ በሰበሰብኩኝ አለ።
በዚህ ጊዜ ነው ፋሆም መሬት ለመግዛት ቆርጦ የተነሳው። ከዛም 13 ሺ ሄክታር ገዝቶ በመሬቱ ምክንያት ችግር ውስጥ ስለገባ በርካሽ መሸጥ የፈለገ ጢሰኛ አገኘ። ፋሆም በድርድር እና በልመናም ጭምር ከጢሰኛው በአንድ ሺ አምስት መቶ ሩብል ፥ ግማሹን አሁን ግማሹን ወደፊት ለመክፈል ተስማምቶ መሬቱን ገዛው። በዚህም የመሬት ሽያጩን በውል አስሮ ሁሉን በእጁ አስገባ። በዚህ ጊዜነው አንድ ነጋዴ ለፈርሱ እህል ለማግኘት በፋሆም ቤት ያለፈው። ፋሆምም ሻይ አቅርቦለት ማውራት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነው ይሄ ነጋዴ ከባሽክሪ መምጣቱን እና በዛ አስራ ሥስት ሺ ሄክታር መሬት በአንድ ሺ ሩብልስ ብቻ መግዛቱን ለፋሆም የነገረው። ፋሆም ወሬው ማርኮት መጠየቅ ጀመረ። ነጋዴውም የሚያስፈልግህ ብቸኛው ነገር በጎሳው መሪ መወደድ ነው። መቶ ሩብልስ ሰጠውት። ልብሶች እና ካባዎች ገዥቼ ሄድኩኝ፣ የሻይ ካርቱን፣ ምንጣፍ እና ወይን ለሚጠጡትም ገዥቼ በፊታቸው ሞገስ ሳገኝ መሬቱን በርካሽ ሸጡልኝ። ለፋሆም የገዛበትን ውል፣ መሬቱ ወንዝ ዳር እንዳለ የሚያሳይ ካርታ እና ለምነቱን የሚገልጽ ሰነድ አውጥቶ አሳየው።
5
ፋሆም ነጋዴውን በጥያቄዎች አጣደፈው። ነጋዴውም ከምትገምተው በላይ ብዙ መሬት አለ፣ ዓመት ሙሉ ብትራመድ አትጨርሰውም ፥ ሁሉም መሬት ደግሞ የባክሺሮች ነው። እነሱ ነው የሚቆጣጠሩት።
ፋሆም ወዲያው በልቡ “ይሄን አይደል የምፈልገው አለ። በዚህ ባለኝ ገንዘብ ለምንድነው አስራ ሦስት ሺ ብቻ የምገዛው ፥ ለምን መግዛት የምችለውን ያህል ሁሉ አልገዛም? ይሄን ገንዘብ እዛ ይዜ ቢሄድ እዚህ መግዛት ከምችለው አስር እጥፍ ገዛለው” አለ።
ፋሆም ወደ ስፍራው የሚኬድበትን መንገድ ጠየቀው ፥ ነጋዴውም እንደሄደ ወደ ተባለው ቦታ ለማቅናት ወዲያው መዘጋጀት ጀመረ። ቤቱን ለሚስቱ ኃላፊነት ሰጥቶ ከአሽከሩ ጋር ወደ ስፍራው አቀና። በመንገዳቸውም በከተማ ቆመው ካርቱን ሙሉ ሻይ፣ ወይን እና ነጋዴው እንደመከረው ስጦታዎችን ገዛ። ከሦስት መቶ ኪሎሜትር በላይ ከተጓዙ በኋላ በሰባተኛው ቀን ባሽኪሮች ዱንካናቸውን ጥለውበት ያሉበት ቦታ ደረሱ። ሁሉም ነገር ነጋዴው እንዳለው ነበር። ሰዎቹ የሚኖሩት በከፍታ ላይ ከታች ወንዝ ባለበት ነበር፣ ድንኳናቸውም ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነ ነበር። መሬት አርሰው አያውቁም ፥ ዳቦም አይመገቡም። ከብቶቻቸው እና ፈረሶቻቸው በመንጋ በከፍታው ቦታ ላይ ተሰማርተዋል። የከብት ግልገሎች ከድንኳኑ ጀርባ ታስረዋል ፥ በቅሎቻቸው በቀን ሁለቴ ይመላለሳሉ። ሴቶቹ ባዝራዎችን አልበው አይብ ያዘጋጃሉ። ወንዶቹ ወተት እና ሻይ ከመጠጣት፣ የበግ ሥጋ ከመብላት እና ትንባሆ ከመሳብ ውጪ ሌላ ምንም የሚጨንቃቸውም አይመስሉም። ሁሉም ደንዳና እና ደስተኛ ናቸው ሲታዩ። በበጋው ሁሉ ስለመሥራት አስበውም አያውቁም። ቸልተኞች ነበሩ፣ ከራሳቸው ቋንቋ ውጪ የሀገሪቱን (ራሽያኛ) ቋንቋ አያውቁም ነገር ግን ገራገሮች ናቸው።
ፋሆምን እንዳዩት ፥ ከድንኳኖቻቸው ግር ብለው ወጥተው ከበቡት። አስተርጓሚም ተፈልጎ መጣ ፥ ፋሆም መሬት ፈልጎ እንደመጣ ነገራቸው። ባሽኪሮች ፋሆም በመምጣቱ በጣም ተደሰቱ፣ ምርጥ ወደ ተባለው ድንኳናቸው አስገቡት። በምንጣፍ ላይ ባለ ትራስ ላይም አስቀመጡት እነሱ ግን በሱ ዙሪያ ምንጣፍ ላይ ተቀመጡ። ወተት እና ሻይ አቀረቡለት፣ በግም ለሱ ሲባል ታረደ፣ የበግ ሥጋም አብስለው አቀረቡለት። ፋሆምም ከጋሪው ስጦታዎችን አውርዶ ለሁሉም አከፋፈለ፣ ሻይ ቅጠሉንም ሰጣቸው። ባሽኪሮችም እጅግ ተደሰቱ። እርስ በእርሳቸውም አወጉ እና አስተርጓሚው እንዲተረጉምለት ነገሩት። ሊነግሩህ የፈለጉት በጣም እንደወደዱክ እና በባህላችን መሰረት እንግዳን ማስደሰት እና ለገጸ በረከቱ መክፈል ግድ ነው። ስጦታ ሰጥተኸናል፣ በል አንተ ደግሞ እኛ ካለን የትኛው ነገር በእጅጉ እንዳስደሰተኸ ንገረን እና እንስጥህ አሉት።
ፋሆምም እዚህ በእጅጉ ያስደሰተኝ መሬታችሁ ነው። የኛ መሬት በሰው ታጭቋል፣ ለምነቱም ወድሟል እናንተ ግን ብዙ መሬት አላችሁ ፥ ለምነቱም አስደናቂ ነው። እንደዚህ ዓይነት መሬት ገጥሞኝ አያውቅም አለ።
አስተርጓሚውም ያለውን ነገራቸው። ባሽኪሮችም እርስ በእርሳቸው ለጥቂት ጊዜ ተወያዩ። ፋሆም የሚሉት ነገር ባይገባውም እየሳቁ እንደሚያወሩ እና ፊታቸው ላይ ደስታ አነበበ፣ ሲያወሩም በጩኸት ነበር። ከዛ ሁሉም ዝም ብለው ፋሆምን ማየት ጀመሩ። ተርጓሚውም ሊነግሩህ የፈለጉት ለሰጠሃቸው ስጦታ የምትፈልገውን ያህል መሬት ሊሰጡ እንደፈለጉ ነው። የምትፈልገውን መሬት በእጅህ መጠቆም ብቻ ነው ከአንተ የሚጠበቀው ከዛም ያንተ ይሆናል አለው።
ባሽኪሮች ድጋሚ ማውራት ጀመሩ ፥ አሁን ግን እርስ በእርስ ያልተስማሙ መሰሉ። ፋሆምም አስተርጓሚውን ምንድነው የሚያጨቃጭቃቸው ብሎ ጠየቀው። እሱም አንዳንዶቹ የጎሳውን መሪ መጀመሪያ መጠየቅ እንዳለባቸው እና ያለ እሱ ምንም ማድረግ እንደሌለባቸው እየተናገሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ያለእሱ መወሰን እንደሚችሉ እይገለጹ ነው አለው።
ክፍል ሁለት እና የመጨረሻው ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት ይጠብቁ።

እግዚአብሔር ይስጥልን ቀጣዩን ለማንበብ waiting u በጉጉት። የሳምንት ሰው ይበለን። ጸጋዉን ያብዛልህ