በመመሳሰሉ ሳበን፣ ልዩ በመሆኑ ማረከን።
- Mulualem Getachew
- Aug 10
- 2 min read
የሰንበት ዕይታ - 13

መሪ እኛን ካልመሰለ መሪዬ ብሎ መቀበል ከባድ ነው፣ መሪ እኛን ከመሰለ ደግሞ ለምን መሪያችን ይሆናል? ከኛ ከልወጣ እኛን እንዴት ያውቀናል፣ ከኛ ከወጣ ደግሞ እኛን ከዚህ እንዴት ያወጣናል? አብሮን ካልበላ፣ አብሮን ካልጠጣ፣ አብሮን ካልተቸገረ፣ አብሮን ካልዘመረ፣ አብሮን ካልጸለየ የኛ ነገር እንዴት ይገባዋል ብለን እንመን? በሁሉ ነገር ከኛ ካልተለየ ከምንም ነገር እኛን ሊለየን አይችልም! የምናውቀው ነገር ብቻ ነው የሚስበን ፥ ልዩ የሆነ ነገር ብቻ ነው የሚማርከን። የምናውቀው ልዩ ካልሆነ፣ ልዩ የሆነው የምናውቀው ካልሆነ ዓይናችንን አይስበውም፣ አዕምሮአችንን አይማርከውም። ራሱን ድኋ ካደረገ ሀብታም ነው ማለት ነው፣ እረኞች ከሰገዱለት የበጎቹ ጌታ እርሱ ነው ማለት ነው፣ ጥበበኞች ከተንበረከኩለት ጥበብ እርሱ ነው ማለት ነው፣ ካህናት ካልሄዱ ራሱ ካህን ነው ማለት ነው፣ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ከሌለው እርሱ እንግዳ አይደለም ማለት ነው። ስላላወቅነው እርሱ እንደሆነ አወቅነው፣ ስላሳደድነው እውነት እንደሆነ ገባን፣ ወደ ግብጽ በመውረዱ የአባቶቻችን ዘመድ እንደሆነ ተገለጠልን። ወደ ግብጽ ስላልጠራን፣ በግብጽ ስላላገኘነው ከአባቶቻችን የተለየ እንደሆነ አወቅን። በመመሳሰሉ ሳበን፣ ልዩ በመሆኑ ማረከን።
ሕጻን ተወልዶልና ግን የዘላለም አባት ነው፣ የሰላም አለቃ ነው ግን የኛን ሰላም ያናጋዋል፣ ንጉስ ነው ግን እግራችንን ነው የሚያጥበው፣ አምላክ ነው ግን አምላኬ ለምን ተውከኝ ይላል። ወንድ ልጆች ሲገደሉ አባታችን ሙሴ ወደ ገዳዩ ቤት ገባ፣ ወንድ ልጆች ሲገደሉ ወንዱን ልጅ በመጠቅለያ ይዛ ወደ ግብጽ ወረደች።
አካላዊ ቃል ፥ ቃል አልባ ሕጻን ሆነ፤ ቤት ያልተገኘለት ልደት በሁሉ ቤት የሚከበር ልደት ሆነ። ያለእናት የተወለደው ልጅ፣ ያለ አባት ደግሞ ተወለደ። የሰውን ልጅ በኃጢአቱ ምክንያት ከገነት ያሳደደው አምላክ፣ በሰው ልጅ በንጽህናው ምክንያት ከቤተልሄም ተሳደደ። ለካህናት እና ለጠቢባን ረቂቅ የሆነው ልደት ለእረኞች እና ለበጎቹ ግልጽ ሆነላቸው። ቅርብ ለነበሩት የራቀው ልደቱ ለሩቅ ምስራቆቹ ቅርብ ሆነላቸው። ምድራውያን ከልደቱ ሲሸሹ ሰማያዊያን በቤተልሄም ቆሙ። የሚሰግዱት በሄሮድስ ሲያልፉ የሰገዱት ከሄሮድስ ራቁ። አዋቂዎች ሊሰይፉት ሲነሱ ሕጻናት ስለእሱ ተሰየፉ። ምኞታችንን ሕይወት እንድንነሳው ፥ ሕይወት ያለምኞት ተወለደ።
መንግስቱ የማይታየው ንጉስ፣ አሳዳጃችንን ያሳደደልንን ተሳዳጅ፣ ልብስ አልባው አልባሽ፣ በቤት ያኖረን ቤት ያልተገኘለት። ያን ነው ታናሿ ቤተልሄም የሰጠችኝ ታላቁ ጌታ። ከሁሉ አንሶ የተገለጠውን ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም የተባለችው ከተማ ሰጠችን። ከሁሉ ለመብለጥ ከሁሉ ታናሽ ሁኑ፣ ለመቅለል ቀንበሬን ተሸከሙ ፣ ዓለምን ለመውረስ ዓለምን ካዱ ፣ ራሳችሁን ለማዳን ራሳችሁን እጡ፣ ፊተኞች ለመሆን ኋለኞች ሁኑ፣ አለቃ ለመሆን ሠራተኞች ሁኑ የሚለን ሕጻኑ አባት፣ ማረፊያ አልባው አሳራፊ፣ ሰላም የነሳነው የሰላም አለቃ፣ ሄሮድስን የሚሸሽ የዘላለም ንጉስ፣ የራሱ የሆኑት ያላወቁት ከርሱ ያልሆኑት ያወቁት በዳዊት ከተማ ተወለደ።
መልካም ገና!!!
Comments