top of page
Search

ፕሮፓጋንዳ እና እውነት

  • Writer: Mulualem Getachew
    Mulualem Getachew
  • Sep 28
  • 3 min read
ree

እምነት የእውቀት ጉድለት ክፍተት መሙያ ነው። ከስሜት የአዕምሮአችን ክፍል ጋር የተያያዘ ነው። ማሰላሰል የሚካሄድባቸው የአዕምሮአችን ክፍል ሂፒካምፐስ እና ፕሪ ፍሮንታላ ኮርቴክስ እኛን የመቆጣጠር አቅማቸው በጣም አነስተኛ ነው። በተቀራኒው የስሜት ክፍላችን የሆነው አሚግደላ ልክ እንደ ዝሆን ጠንካራው እና መሪው ነው። እምነት ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ የተሟላ እውቀት ሳይኖራቸው ሲቀር የሚደገፉበት ምርኩዝ ነው። ማናችንም ስለፈጣሪ ሙሉ እውቀት የለንም። ወይም ስለዚህ ዓለም አመጣጥ። ሁለት አማራጮች ብቻ ነው ያሉን። ማመን፦ ይሄ ዓለም እንዲህ ነው የተፈጠረው ብለን። ወይም መላምቶችን መዘርዘር። መላምቶችንም የምንቀበልበት መንገድ ሁለት ነው። ማመን ወይም ይሄ መላምት ነው። ፍጹም ውሸት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አላውቅም። ባለማወቄም ሳልሸማቀቅ እኖራለሁ ብሎ መቁረጥ።

 

ልክ ከእውቀት በላይ እምነት በዚህ ዓለም ላይ ጠንካራ የሰዎችን ባህሪ ለዋጭ ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ፤ ከእውነት በላይ ፕሮፖጋንዳ ሰዎችን ይቆጣጠራል። አንድ ነገር እውነት ተብሎ በሰዎች ቅቡልነት እንዲኖረው ኦብጀክቲቭሊ (objectively)  መታወቅ አለበት። ለምሳሌ ግራቪቲ እውነት ነው። ምክንያቱም ኦብጀክቲቭሊ ይታወቃል። ይሄ ማለት ሁላችን እናውቀዋለን ማለት አይደለም። ግን በአግባቡ ምርምር እና ጥናት ካደረግን እናውቀዋለን። ፀሐይ በምስራቅ ነው የምትወጣው። ሁሉም ሰው ይሄን ላያውቅ ይችላል። ግን የፀሐይን በምስራቅ መውጣት አይቀይረውም። እነዚህ አይነት እውቀቶች ናቸው ሌሎች እውቀቶችን እየጨመሩልን እንድንሄድ የሚያደርጉን። ብዙ ጊዜ ሰዎች ከእነዚህ ዓይነት እውነቶች ይልቅ በእምነት የሚገኝ እና በድግግሞሽ የሚደመጥን ትርክት የበለጠ የመቀበል እና ለዛ ዋጋ የመክፈል ዝንባሌ አላቸው።

 

ሁላችንም የሆነ የምናምነው ነገር ውሸት ነው። አሁን ላይ ከምናምናቸው ነገሮች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ውሸት ነው።የብዙዎቻችን ደግሞ ብዙ የምናምናቸው ነገሮች ውሸቶች ናቸው። ለምሳሌ የቁልቋል ተክል ፈሳሹ ከሰገራ ጋርተቀላቅሎ የሚፈጥረውን ኬሚካል ብንቀባው መላጣነትን ያስቀራል ብዬ ብጽፍ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያነበው ሰው ስቆ ሊያልፍ ይችላል። ከዛ ሌላ የሕክምና ሰው ይሄንኑ የሆነ ቦታ አስፍቶ ጽፎ ብታዩት። ከዛ ሌሎች ሰዎችም እየተቀባበሉ ጽፈው ብትመለከቱት። የዛኔ ለመሞከር ልትነሳሱ ትችላላችሁ። ከዛ የሆነ ሰው “ይሄው የእኔ ጸጉር ሞልቶ ተመልከቱ” ብሎ ቢያሳያችሁስ። አሁን ጭራሽ ከማመን አልፋችሁ እናንተም ወሬውን ማሰራጨት ትጀምራላችሁ። ሰዎች ለአንድ ሀሳብ በተደጋጋሚ ከተጋለጡ ያንን የማመን ዝንባሌ አላቸው። አንድን ነገር በተደጋጋሚ ከሰማነው እውነት እየመሰለን ይሄዳል።ለዚህ ነው ፕሮፖጋንዳ በጣም አዋጭ የሆነው።

 

ለፕሮፓጋንዳ ምርጡ ምሳሌ ፕሬዝዳንት ትረምፕ ነው። ፕሬዝዳንት ትረምፕ የተዋጣለት ኮሚኒኬተር ነው። ማንም የሚረዳውን ቋንቋ ይናገራል። ስለሚናገረው ነገር እውነትነት ተጨንቆ አያውቅም። ግን በተደጋጋሚ ያንን ለመናገር አያመነታም። በዚህም ብዙ ሰዎች በመጨረሻ እርሱ የሚናገረውን ያምናሉ። ኢኮኖሚው እየወደቀ ፕሬዝዳንት ትረምፕ በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚው እያደገ ነው ለማለት ምንም ችግር የለበትም። በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ተመልከቱ። መደመር መደመር እያለ ይሰብካል። በተቃራኒው እርሱን የሚቃወም ሰው ለደቂቃ አጠገቡ አይታገስም።ትላንት አብረውት ወደ ስልጣን የመጡት ሁሉ ዛሬ ሀገር ጥለው ወጥተዋል ወይም ተገድለዋል። ሌሎች ደግሞ ፍጹም ገብረዋል። ግን አሁንም መደመር የሚል መጽሐፍ አጽፎ ያስመርቃል። አብይ ምስኪን እና ስሱ ሆኖ ለመታየት ነው በሚዲያ የሚጥረው። በድርጊቱ ግን ጨካኝ እና ለሰው ልጆች ሕይወት ምንም ደንታ የሌለው ሰው ነው። ግን የእርሱን ምስኪንነት፣ እጅ ሳሚነት፣ ትከሻ ዳባሽነት፣ ጺም ነካኪነት፣ የእናቶችን እጅ ሳሚነት ሚዲያው በማሳየት ፥ምስኪን የመሰለ ስዕል ስለእርሱ አሁን ሳይቀር (ይሄን ሁሉ ካየን በኋላ) ይመጣብናል። ምክንያቱም ሰው አብዝቶ የሚያየውን ነገር የማመን ዝንባሌ አለውና።

 

ሌላኛው ጉዳይ እውነት ደባሪ ነው። እስቲ ተመልከቱ ብዙ የሃይማኖት መጽሐፎችን። ከፍታችሁ አንብቧቸው። ከዛ ደግሞ የተረት መጽሐፎችን አንብቧቸው። በሚደንቅ ሁኔታ በሃይማኖት መጽሐፎች ላይ የምታገኟቸውን ታሪኮች ከሃይማኖት ጋር በማይገናኙ መጽሐፎች ብታገኟቸው ኖሮ ፈጽሞ አምናችሁ አትቀበሏቸውም። ስለዚህ ታሪኮቹን ለማንበብ ራሱ በስሜት መዘጋጀት እና በሆነ መጠን የውስጥ መሻታችሁ አንዳች ከፍ ያለ በስሜት ከፍታ አንድን ነገ ርለማግኘት መዘጋጀት አለባችሁ።


እውነት ግን በተቃራኒው በጣም ደባሪ ነው። ማነው ሒሳብን እንደ ስብከት የሚማረው? ማነው ውስብስብ ማክሮ ኢኮኖሚን ወይም አልጀብራን ወይም ሴሉላር እና ሞሎኪውላር ባይሎጂን ተመስጦ የሚሰማ? በተቃራኒው ታሪክን ስንሰማ ያለንን መመሰጥ እዩ ምክንያቱም ታሪክ ብዙ ነገሩ ግነት እና የሰው ድራማቲክ ትረካ ነው።

 

ለዚህ ነው ፕሮፖጋንዳ መሳጭ የሚሆነው። አንደኛው የፕሮፓጋንዳ መለያው ቀልድ፣ ሳቅ እና ፈገግ ማስባል ነው። ፕሬዝዳንት ትረምፕን ተመልከቱ አሁንም። እርሱ ሲናገር የሚጠሉት ሰዎች ሳይቀር ይስቃሉ። ሰውዬው ብዙዎች አፍረው የማይናገሩትን ነገር ያለምንም ጥንቃቄ ያወጣዋል፣ ከዛ ያንን የሚሰማ ሁሉ ይስቃል። በመሳቅ ሳናውቀው ወደ እርሱ ቀስ እያልን እንሳባለን። ምናአልባትም ለዚህ ይሆናል ታላቁ ሰባኪ ዮሐንስ አፈወርቅ ሳቅን ይጸየፍ የነበረውበእርሱ እምነት ጤነኛ የሆነ ሰው ይሄ ሁሉ ግፍ በሚፈጸምበት ዓለም ላይ ሊስቅ አይችልም ብሎ ያስባል።ለዚህም ይመስላል የእርሱን ስብከት ብዙዎች በዘመናቸው የሚታገሱት ያልነበረው። ማስታወቂያዎች ለዚህ ነው የሚያስቁ ሰዎችን እና ታሪኮችን ለእቃቸው ማስታወቂያነት የሚጠቀሙት። ቀስ እያልን ለፕሮዳክታቸው ፍቅር ያድርብናል።

 

ከፕሮፓጋንዳ ይልቅ ለእውነት እንዴት እንገዛ?

 

መጀመሪያ የምንሰማው ነገር በኛ ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም ብለን አናስብ። ስለሁሉም ጉዳይ ደግሞ እውቀትላይኖራችሁ እንደሚችል ብቻ ሳይሆን ለማጣራትም ጊዜም እንደሌላችሁ እወቁ። በሆነ ነገር ፍላጎት ካደረባችሁ፤ ከዜና ተቋማት ያንን እውቀት ከማግኘት ይልቅ፤ ጊዜ ስጡት እና ጥናት አድርጉበት። ሁሉንም ነገር ማጥናት ስለማትችሉ፤ በብዙ ጉዳይ ላይ አቋም አይኑራችሁ። አቋም ባለመያዝ ምቾት ይሰማችሁ።


ባስ ላይ፣ መኪና ውስጥ ወይም ስልካችሁ ላይ ዝም ብሎ የሚመጣላችሁን ዜና አትቃርሙ። አዕምሮአችን ያስገባውን መረጃ ልክ እንደ ምግብ ነው የሚመለከተው። ያስገባውን ያላምጠዋል። ከዛ ውሳኔ ለመወሰን ይጠቀምበታል።መጨነቅ፣ መፍራት፣ መረበሽ ውሳኔዎች ናቸው። መደሰት፣ ጽንፈኛ መሆን፣ መጥላት፣ መውደድም ውሳኔዎች ናቸው። መደገፍ እና መቃወምም ውሳኔዎች ናቸው። እነዚህ ሁሉ አዕምሮአችን ውስጥ በገቡ ብዙ ውሸቶች (ፕሮፖጋንዳዎች) የሚሰጡ ውሳኔዎች ናቸው። ለዚህ ነው ወደ አዕምሮአችን ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ስለምናስገባቸው መረጃዎች መጨነቅ ያለብን። ነጻ የሚመስሉን መረጃዎች ሁሉ በመጨረሻ ከፍተኛ ወጪ ያሶጡናል።

 
 
 

Comments


  • Facebook
  • X
  • Instagram

© 2024   by Mulualem's Sixth Sense

Designed and built by Abel

bottom of page