
በእኔ ዓይነት ሥራ ወይም የሰዎችን መከራ እና ስቃይ መስማት የየዕለት ሥራችሁ ሲሆን ፥ ሰውን የሚያሳዝን እና የሚያስለቅስ ታሪክ ልክ የፀሐይ በምስራቅ የመውጣት ያህል ኖርማል ይሆንባችዋል። በሂደት፣ ብዙ ሰዎች እንደሆኑት፣ ትደነድናላችሁ። በተለይ ይሄ ሥራዬ ነው ብላችሁ ከወሰዳችሁት ፥ ራሳችሁን እንዲረበሽ አትፈቅዱለትም። በዚህም ሰዎች ለእናንተ ቴክኒካል ችግር ይሆኑባችዋል። ልክ እንደ ማሽን መጠገን ከቻላችሁ የምትጠግኗቸው፣ አለበለዚያ ግን የምትተዎቸው።
በቅርብ ከአንድ የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰሬ ጋር ምሳ ነበረን። በመኃል በቅርብ የመኪና አደጋ ደርሶባት ሆስፒታል ገብታ ስለነበረችው ሚስቱ በትካዜ ያወራኝ ጀመር። ስለሕክምናው ሲነግረኝ፤ ለዶክተሮቹ ሚስቴ ቴክኒካል ችግር (techinical problem) ነበረች። ለነርሶቹ ግን ሚስት፣ እናት፣ ሴት እና የእነሱን ርዳታ ፈልጋ በእጃቸው ላይ የወደቀች ተረጂ ነፍስ ነበረች። ዶክተሮቹ እንደ ማሽን ለመጠገን ዓይተዋት ሲወጡ ፥ ነርሶቹ ግን አጽናንተዋትም ጭምር ነበር የሚለዩን አለኝ።
ከሰዎች ጋር የሚያገናኝ ሥራ እንሰራ ይሆናል። እንጀራ የሚያመጣ። የሰዎች ችግር የገንዘብ ምንጫችን ሊሆን ይችላል። ግን እነዛ ሰዎች ሰውነታቸው ከተረሳን ፥ በመጨረሻ የራሳችንን ልብ ጭምር እናጣዋለን። ዋረን በፌት ለሼሬ ሆልደሮቹ ዛሬ በጻፈው ዓመታዊ ሪፖርት ፥ “ይሄን ሪፖርት ትላልቅ ኩባንያዎች በየዓመቱ እንደሚያዘጋጁት ዓይነት ሪፖርት ዓይደለም የምንጽፈው እና የምናዘጋጀው። ይልቁንስ እኛ ሼር ሆልደር ብንሆን ምን ዓይነት ሪፖርት ነው ማንበብ የምንፈልገው ብለን በማሰብ ነው የምናዘጋጀው። ገንዘባችሁን እኛን አምናችሁ ፥ በኛ ኩባንያ ላይ ኢንቨስት ካደረጋችሁ ፥ ልክ እኛ በእናንተ ቦታ ብንሆን ማንበብ የምትፈልጉትን በማሰብ ነው የምንጽፈው” ይላል። ለዚህም ነው የበፌት ዓመታዊ ሪፖርት እንደ ልብ አንጠልጣይ ፊልም በጉጉት የሚጠበቀው። የሚነበበው። ለምን? ምክንያቱም ራሱን በሌሎች ጫማ ውስጥ መክተት ችሏል። የሌሎችን ሰውነት የየቀን ዕለታዊ የሆነው ሥራው እንዲያስረሳው አልፈቀደም። ያን ነው ትልቅ ልብ የምለው። ያ ልብ በፈጣሪ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ ለፈጣሪያቸው የሚሰጡት ልብ ነው። ሁላችንም አምላካችንን ትልቅ ነው ብለን እናምናለን። ሺ ዘመናት ተደጋግሞ ቢሰማው ፥ ምንም የሱ ጉልበት ፍጹም ኃያል ቢሆን ፥ ፊት ለፊቱ ተንበርክኮ የሚለምነውን ፍጥረቱን ግን ለመስማት ያዘነብላል ብለን እናምናለን። የኛ ስቃይ ለሱ ትልቅ ወይም አዲስ ስለሆነበት ሳይሆን ፥ ትልቅ ልብ ስላለው እንጂ።
ትልቅ ልብ ያለው መሪ ሲኖረን ፥ ሕጻናት ተጨፍጭፈው የችግኝ ተከላ ድግስ ደግሶ የሰዎችን ለቅሶ ለርሱ የሁልጊዜ ሥራው እንደሆነ አያስመስልም። ብዙዎቻችን ይሄ የሚጠቅመው የኛን ተገልጋይ ብቻ ይመስለናል። በፍጹም። ራሳችንን እንጂ። ሥራችን ሌሎችን እንደ ማሽን አሳይቶ ፥ የሰውነት ልብን ሊነፍገን ካልቻለ ፥ በመጨረሻ ሰዎችን የመረዳት እና የመገንዘብ ታላቅ ልብ ገንዘብ እናደርጋለን። ሰውነትን በምላት የመጎናጸፍ ዕድል እናገኛለን። ከዚህ የሚገኝ ርካታ ደግሞ ወደር የለውም።
ትልቅ ልብ ማለት የኛን ርዳታ ፈልጎ ፊትለፊታችን የቆመው ሰውን እኔ ብሆን እንዴት ነው የሚሰማኝ ብሎ የሱ ቁስል እንዲሰማን የመፍቀድ ልምምድ ነው። ዛሬ አሜሪካ ውስጥ የምታዮቸው መሪዎች ፥ አቅም እና ጉልበት የሌላቸውን ምስኪን ስደተኞች በሰንሰለት አስረው ወደ ማጎሪያ ማዕከል በመጣል መደሰት የቻሉት ፥ “ሕገወጦች” የሚል ስም ስለሰጧቸው ነው። ያ ስደተኞችን ለማሰቃየት እና የእነሱን ታሪክ ለመስማት እንዳይችሉ አቅሙን ሰጣቸው። እኛም የተለየን አንሆንም። ቆም ብለን ፥ የሌላውን ሰው መከራ ወደ ራሳችን ለማስጠጋት ካልወሰንን። እኔ ብሆንስ ካላልን።
ቶሎስቶይ በ1500 ገጽ በከተበው "ዎር ኤንድ ፒስ" መጽሐፍ ውስጥ አስገራሚ ብቃቱን የገለጸበት ሦስት መስመር ጹሁፉ ይመስለኛል። ዶሎኮቭ የተበላ ቁማርተኛ፣ የሽጉጥ ፍልሚያን የሚያዘወትር፣ ቢጠጣ ቢጠጣ የማይጠረቃ እና ቤተሰብ እንዳላሳደገው የሚኖር ሰው ነበር። የተለያዩ የአውሮፓ አገራትን ትምህርት ቀምሶ ወደ ሩስያ የመጣ እና የአባቱን ግዙፍ ሃብት በመውረስ ሃብታም ከሆነው "ፒየር" ከሚባል ሰው ጋር ዶሎኮቭ ይጣላል። የሽጉጥ ፍልሚያ የጥሉ መቋጫ እንዲሆን ይስማማሉ። ሁሉም ዶሎኮቭ ካለው ፍጹም የልምድ ብልጫ በመነሳት ፒየርን እንደሚገለው ገመቱ። ከፍልሚያው በፊት ዶሎኮቭ ለወዳጁ ሮስቶቭ "ይኸውልህ ወደ እንደዚህ ዓይነት ግጥሚያ ስትሄድ እንደምትሞት አስበክ ኑዛዜ ጽፈክ፣ የመጨረሻ ቃልህን በሚያምር ቃላት ከትበኸ መጓዝ የለብህም። ግን እንደምትገድል ቅንጣቢ ጥርጣሬ ሳይኖርኽ ከገባህበት ሁሉም ነገር ይሰምራል። ልክ እንደ ድብ አዳኝ ፥ ፍርሃቱን ከገለጠ ድቡ ያንን በማሽተት እንደሚያከሽፍበት ሁሉ ፣ ፍርሃት ከተሰማክ ሁሉ ነገር እዛው ያከትማክ።" ሲያቀብጠው እዚህ ጉድ ውስጥ እንደገባ የገባው ፒየር ግን አንዴ ለግጥሚያው እሺ ብያለው እንግዲህ የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ በሚል ፍልሚያው ሜዳ ላይ ቆመ። ፒየር ዶሎኮቭን ክፉኛ አቆሰለው። ዶሎኮቭ ፒየርን ሳተው። ሮስቶቭ ጓደኛውን አቃቅፎ ወደ እርዳታ ከነፈ። በመኃል ዶሎኮቭ እያቃሰተ እነዚህን ቃላት ይተፋል "ይሄን ከሰማች ትሞታለች፣ አትተርፍም፣ ለእኔስ ግድ የለኝም እሷ ግን ... እሷ ግን ቆማ መሄዷን እንጃ። ወይኔ ... ይሄን ጉድ ...ማየት የለባትም ... በሕይወት አትኖርም ..." ሮስቶቭ ግራ ገባው! "ስለ ማን ነው የምታወራው?" አለው። "ስለ ... እናቴ! .... ስለ እህቴ!" ከዚህ በኋላ ሮስቶቭ አዕምሮ ውስጥ የተመላለሰው ቃላቶች ናቸው ዘወትር የሚገርመኝ። "ዶሎኮቭ ወንበዴው፣ ዶሎኮቭ ቁማርተኛው፣ ዶሎኮቭ አጭበርባሪው ... አፍቃሪ ልጅ እና ወንድምም ነበር!"
በኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚ የሆነው እና የሆሎኮስት ተራፊ Daniel Kahneman በደች ግዛት ውስጥ ከጀርመን ወታደሮች ቤተሰቦቹ ደብቀውት እያለ ከተደበቀበት ቦታ አፈትልኮ ይወጣል። "መንገዱ ኦና ነበር። ሰው አይታይም" ይላል ጊዜውን ሲያስታውስ። "ዞር ስል አንድ ወታደር ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጠምን። ለመሸሽ ሞከርኩ። ጠራኝ። ሮጬ ማምለጥ እንደማልችል ስለገባኝ ወደ ወታደሩ ሄድኩ። የናዚ ጀርመን ወታደር ነበር። በሁለት እጆቹ ወደ ላይ ላጥ አርጎ አነሳኝ። ዓይኖቹ እንባ አቀረሩ። ስንት ዓመትህ ነው አለኝ። ነገርኩት። 'አንተን የሚያህል ልጅ አለኝ። በጣም ናፍቆኛል' ብሎ ሳመኝ እና ወደ መሬት መለሰኝ።" ዳኒ ስለ ሰው ያለው አመለካከት ከዛ ጊዜ ጀምሮ እንደተለወጠ ይናገራል።
ዳንኤል የእውቀት ልህቀቱ እና የሰውን ተፈጥሮ በማወቅ አቻ የማይገኝለት ሰው የነበረ ቢሆንም እስኪሞት ድረስ ግን ሰዎችን ነጭ ወይም ጥቁር ብቻ በሚል ፍረጃ (ማለትም ጥሩ ወይም መጥፎ) ወጥመድ ሳይወድቅ ቀረ። በክፉው እና በደካማው ሰው ውስጥ ሳይቀር የጽድቅን ልምላሜ ፥ የሰውነትን ዘር ማሽተት እንዲችል ሆነ። ትልቅ ልብ ማለት ያ ነው። ትልቅ ሆኖ ለመሞት ፈቀደ። ትልቅ ሰው ሆኖ ይሄን ትንሽ ሕይወት ፈጸመ።
Comments