አዶናይ
- Mulualem Getachew

- Nov 23
- 5 min read

በቅርብ እህቴን ስለ አዶናይ ጠየቀኳት። ተደንቃ “አንተ ደግሞ ምን ስትሰራ አወቅከው?” አለችኝ፤ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳየውት ነግሬያት፤ አሁንም ምን ታስቤያልሽ ስላት ፥ “እኔ ምን አገባኝ፤ አንተስ ደግሞ ስለዚህ ሰው ምን ይጨንቀሃል” ብላኝ በዚህ ዘጋነው።
አዶናይ ግን የዚህ አሁን ያለንበት ዘመን መገለጫ ይመስለኛል። አዶናይ ዝም ብሎ የሚተው ሰው አይመስለኝም። ስለዚህ የሰንበት ዕይታዬን በእርሱ ዙሪያ ላደርግ ነው።
ትላንት አስተሳሰቡን የምወድለት ፈላስፋውን አላን ዶ ቦቶን ስሰማ እንዲህ አለ በመኃል፤ “የጨዋ እና ጥሩ ቤተሰብ አንዱ መገለጫ ልጆቻቸው ምንም የታዋቂነት ፍላጎት ሳይኖራቸው ሲቀር ነው።” አለ። ሲያብራራ “በልጅነቱ ለቤተሰቡ ዓለማቸው እና ሁሉመናቸው እንደሆነ ተሰምቶት ያደገ ልጅ፤ ሲያድግ በማያውቃቸው ሰዎች መወደድን አይናፍቅም። የማያውቃቸው ሰዎች አወቁት፣ አላወቁት፣ ወደዱት ጠሉት ለእርሱ ምኑም አይደለም። በልጅነቱ መታየት፣ መወደድ ያልቻለ ሰው ነው ካደገ በኋላ ይሄን ከሌሎች ለማግኘት የሚጥረው። ልክ የዘጠና ፐርሰንት ኮሜዲያንን የልጅነት አስተዳደግ ታሪክ ስታጠኑ፤ በልጅነታቸው ሁሉም የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት የሚቸገሩ ነበሩ። ለዚህ ነው ሌሎችን ለማሳቅ ተምረው እና አጥንተው ወደ ዛ ፕሮፌሽን የተሳቡት።”
ይሄን በማህበራዊ ሚዲያ አጋርቼው፤ አንድ ወዳጄ ኮሜንት እስከሚሰጥበት ድረስ እውነት ለመናገር ከአዶናይ ጋር የሚገናኝ አልመሰለኝም ነበር። በኋላ ግን ሰግጥ፤ ፈምስ ትዝ አለኝ።
አዶናይ የዚህ ዘመን ብቻ መገለጫ ሳይሆን፤ የብዙዎቻችንም መገለጫ መሆኑ የገባኝ ለዛ ነው። አብዛኞቻችን በሌሎች መደነቅ፣ መታወቅ እና ምርጥነታችን በሰዎች ሁሉ እንዲመሰከርልን እንፈልጋለን። የኛነታችን Value (ቦታ) ራሱ በተከተሉን እና ባደነቁን ሰዎች ብዛት የሚወሰን ነው። ምክንያቱም ጎስቋላ ልጅነት ነበረን። ልጆችን ደግሞ የሚያሳድገው ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰብም ጭምር ነው።
እኔ እውነት ለመናገር አዶናይን በተለየ መውቀስ አልፈልግም። መጀመሪያ አዶናይ ታናሽ ወንድሜ ቢሆን ኖሮ የምመኝለት እንዲሳካለት ብቻ ነው። ቶልስቶይ ጠላት አድርጋችሁ የምታዩት ሰው የምትወደው እናት፣ የምታዝንለት እህት እንዳለችው ስትመለከቱ፤ ያን ሰው እንደ ሰው ማየት ትችላላችሁ የሚል ዓይነት ፍልስፍና አለው። ለዚህ ነው ወንበዴውን ዶሎኮቭ ስለ እህቱ እና ስለ እናቱ በሞቱ ጫፍ ሰዓት ላይ ሲጨነቅ ያሳየን።ወንበዴውን በወንበዴነት ብቻ ሳይሆን እናቱን እና እህቱን በሞቱ ሰዓት ሳይቀር በሚያስብ አፍቃሪ ወንድምም እንደሆነ እንድናይ ነው የጋበዘን።
የመጀመሪያው አዶናይ ከሌሎቹ በላይ በፍጥነት መታወቅ ቻለ እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሁሉም ዓለም የሚታየው ይሄ አይደለምን? በኛ እንኳ ዮኒ ማኛ፣ ሞጣ፣ ጂጂ፣ ዘመድኩን አልነበሩ መድረኩን የያዙት። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ፥ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነገር የሚናገሩ፣ ታላላቆችን የሚያዋርዱ፣ ለባህል እና ለሞራል ያልተገዙ አልነበሩምን? እነዚህ ሰዎችን ስንቶቻችን በይፋም ሆነ በድብቅ ሰማናቸው?!
በአሜሪካ ውስጥስ ብሔራዊ ጀግና የተባለውን ቻርሊ ከርክን ተመልከቱ። ለኮሚኒቲ ኮሌጅ እንኳ ብቁ ያልሆነ፣ ከየትኛውም ኮሌጅ ያልተመረቀ፣ አንዳች ለማህበረሰብ የሚጠቅም ነገር ያልፈጠረ ግን የሀርቫርድ የሕግ ትምህርት ቤትን ወርቅ የወሰደች የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ዳኛ “ጥቁር በመሆኗ ነው እንጂ ለዛ የሚበቃ እውቀት የላትም” ብሎ በድፍረት የተናገረ፣ “ጥቁሮች አይሮፕላን አብራሪ ሆነው ካየው ያ ሰው እውነትም ብቃት አለው ብዬ አስባለው” ያለ፣ ስለ ባርነት በጎ ነገርን የተናገረ ሰው አልነበረም አሜሪካ እንደ ጀግና የቀበረው? ጀግና ያደረገው! ይሄን ልጅ ማህበራዊ ሚዲያ አገነነው እንጂ የትኛው እውቀቱ እና የፈጣራ ችሎታው ነበር እዚህ ያደረሰው? ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ታዋቂ የሆኑትን ባብዛኛው ተመልከቱ? የትምህርት ደረጃቸውን ተመልከቱ። ከዛ ደግሞ ለምን ታዋቂ እንደሆኑ እዩ። የምታገኙት ሁሉ እኮ ተመሳሳይ ነው። በትምህርት ደረጃቸው የወረዱ፣ የኮንስፓይረሲ ንደፈ ሀሳብ የሚያራምዱ፣ ትልልቅ የተባሉትን የሚዘረጥጡ እና የሚያዋርዱ ሰዎች ናቸው የተከታይ መዓት ያላቸው።
የእነሱን የተከታይ እና የታዋቂነት መጠን እያዩ ደግሞ ብዙዎች ያን መንገድ እየተከተሉ ነው። ምክንያቱም እብድ የሆነ ነገር ማድረግ፣ ማህበረሰብ ያከበረውን ነገር ለጆሮ ጭው በሚል መልኩ አዋርዶ እና ፈንቅሎ መውጣት ነው የሚያስፈልገው። ከዛ በብዙዎች መታየት፣ የላይክ ብዛት እና የሺዎች እና የሚሊዮኖች ተከታዮች ብዛትን ማሳየት ወይም መሰብሰብ። ፎቶ ትለጥፋላችሁ፣ ጹሁፍ ትለጥፋላችሁ የሚሊዮን ተከታዮች እና ላይኮችን መቁጠር ነው።
አላን ዶ ቦቶን ይሄን ነው የጥሩ አስተዳደግ ማሳያው ልጆቻችሁ ታዋቂ መሆንን ሳይፈልጉ ሲቀር ነው ያለው። ወላጅ ታዋቂ ለመሆን በሚጥርበት ዓለም ውስጥ፣ ልጆች አይፓድ እና ስልክ በሚያሳድጋቸው ዓለም ውስጥ ምን ዓይነት ትውልድ ነው የሚፈጠረው? ይሄን እንጠይቅ። አላን ዶ ቦቶን የጥሩ አስተዳደግ አለ እንጂ የትኛው ወላጅ ነው ከዚህ ደዌ የተፈወሰው ቀድሞስ?
የአላን ዶ ቦቶንን ንግግር እየሰማው በተመሳሳይ በጣም ቀዝቃዛ በሆነው የሚሲሲፒ ወንዝ ሥር ረጅም የእግር ዋክ (walk) እያደረኩኝ ነበር። ሁለት ነገሮች መጡልኝ። የመጀመሪያው ሰላማዊ እና ጸጥ ያለ ሕይወት ያለውን ደስታ። የምር በዛ ወንዝ ዳር ያለው የዝምታ ውበት ወደር አልነበረውም። በዛ ውስጥ ምንም ዋክ የሚያደርግም ሰው አልነበረም። ያ እራሱ ገረመኝ። ከዚህ ዝምታ በላይ ውበት የት ኖሮ ነው ሰው የጠፋው? ይሄን የመሰለ ኦርዲነሪ (ተራ) ሕይወት። ማንም የማይሻማችሁ ሕይወት። ተራ ሰው ሆኖ የመኖር ውበት። በዚህ ተፈጥሮ ውስጥ፣ በዚህ ዝምታ ውስጥ ፥ ምንም ሆኖ የመኖር ሕይወት። ግን በሕይወት ሚሊዮን ሰዎች ተክትለዋችሁ ፥ የውስጥ ሰላም ከሌላችሁ ምንድነው? ለጉድ ፈምሳችሁ ፥ ውስጣችሁ ግን ርጋታ ከሌላው፣ የቁስ ክምችት እንዲያፍናችሁ አሁንም አሁንም የምትጥሩ ከሆነ ፥ ምንድነው ረቡ? የሆነ ቀን አሁን ያደነቃችሁ ሰው ሁሉ ሟች ነው። የተደነቃችሁት እናንተም ማንም የማያስታውሳችሁ ቀን ይመጣል። ከዛስ? ፥ ለዚህ ነበር? ያ ሁሉ ትግል!
ሁለተኛው ሀሳብ ሃይማኖት ነው። ምንድነው ሰዎች በሃይማኖት ውስጥ የሚያገኙት? በሃይማኖት ውስጥ ሰዎች የሚያገኙት ፍቅርን ነው። አንድ እስከ ሁለመናቸው የሚወዳቸው አምላክ እንዳለ ነው የሚያውቁት። አንድ ምንም ቢሆኑ፣ ምንም በኃጢአት ቢቆሽሹ፣ መልከ ጥፉ ቢሆኑ፣ ወይም ሰዎች ገበናቸውን ቢያውቁ መቀበሪያ የሚያጡ የሚመስላቸው ሰዎች ሳይቀር ፥ “ፈጣሪ ግን ይወደኛል!” ፣ የሚል ስሜትን ነው የሚያገኙት።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች የእርሱ መሆናችንን እንዴት እንዲያውቁ እንደፈለገ ሲናገር ሰምታችሁታል? “በመጨረሻም ካሸነፋችሁ የእኔ መሆናችሁ ይታወቃል” አላለም። “የእኔ መሆናችሁ የሚታወቀው በዓለም ዙሪያ ተበትናችሁ፣ የእኔ ወንጌል መቀበር ካልቻለ እና አሸናፊ ከሆነ ነው እውነተኛ መሆናችሁ የሚታወቀው” አላለም። "ለብዙ ዘመናት ወንጌሌ ከቀጠለ የዛኔ እውነተኛ እንደሆነ እወቁም" አላለም። ይሄ የአይሁዱ ገማልያል ትምህርት እንጂ የክርስቶስ ትምህርት አይደለም። እውነትን ልክ እንደ "ሽል ከሆነ ይገፋል ቦርጭ ከሆነ ይጠፋል" በሚል ንግግር የለካው ገማልያል እንጂ ክርስቶስ አልነበረም። ክርስቶስ እውነትን የለካው በፍቅር ነው።
የክርስቶስ ትምህርት ይሄ ነው “እርስ በእርስ ከተፋቀራችሁ የዛኔ የእኔ መሆናችሁ ይታወቃል።” ይሄ ነው ሃይማኖት የሰጠን። የፈጣሪያችን የፍቅር ዓይን በኛ ላይ እንዳረፈ ማመን። የአላን ዶ ቦቶንን የጥሩ አስተዳደግ መለኪያ የሚያሟላ ወላጅ ማግኘት በጣም ከባድ ነው። በሰው መደነቅ እና የሰው ዓይንን መናፈቅ አዶናያዊ ናፍቆት የሌለበት ሰው ማግኘት ከባድ ነው። ምክንያቱም የእውነተኛ ፍቅር እጦት ስላለብን።
የተርዕዮን ኃይል ያሸነፉ ሰዎች በፈጣሪያቸው የፍቅር ዓይን እንደታዩ የገባቸው ወይም ያንን የዝምታ ውበት ፥ ያን ኦርዲነሪ ሆኖ የመኖርን ፥ የሰው ኳኳታ እና ጋጋታ የሌለበትን የውበት ዓለም የተረዱ ሰዎች ብቻ ናቸው።
ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳስብ እኔ ከማንም በላይ የምትመጣብኝ ያቺ ከወንዝ ዳር ውሃ ልትቀዳ የመጣችው የሰማርያዋ ሴት ነች። የዝች ሴት ታሪክ የምር የገባው ፍጹም የፍቅር ሰው የነበረው ዮሐንስ ነበር። ሕዝብ ሊያስተምር ነው የመጣው ብለው ያሰቡት ደቀመዛሙርቱ ይሄ ታሪክ ወዲያው አልገባቸውም። እርሱ ግን የአንዲት ሴት ሕይወት ግድ አለው።
“በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት።” ይላል ታሪኩ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት ሲጀምር። የአንዲት ሴት ሕይወት ግድ አለው። የአንዲት። በጠራራ ፀሐይ ለሰዓታት ጠበቀ። ለእርሱ፣ ለዚህ ጌታ እርሷ ልጁ ናትና። ዓለሙ ናት። ሁሉመናው ናት። ስለዚህ ግድ አለው። ፍቅሩ።
ከአንዲት በኃጢአት ከደከመች ግን ደግሞ የውስጧን ድክመት ከዓለሙ ሁሉ ከሰወረች ሴት ጋር ንግግር አደረገ። ብቻዋን አገኛት። “እኔ የምሰጥሽ ውሃ” አላት። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለላይክ ቆጠራ የማያመላልስ፣ ለሰብስክሪፕሽን ልመና የማያንቆራጥጥ፣ ለወደዱልኝ እና ምን ተባልኩ ስጋት እዚህም እዛም የማያስብል ፥ “እኔ የምሰጥሽ ውሃ" አላት። አልገባትም። ከዚህ ጥማት፣ ከዚህ የመወደድ ፍላጎት ራብ፣ ከዚህ የመታየት ናፍቆት ውጣውረድ የሚገላግላት የሚያናግራት ፥ ውዷ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ አልገባትም።
“መቅጃ የለህም እኮ አለችው።” የእርሱ ውሃ ዘወትር መቀዳት የሚያስፈልገው መስሏት። ይሄን ውሃ ግን አንዴ እስከምትጠጪው ነው ከዛ በኋላ አይጠማሽም። እንደዚህ ዓለም ውሃ በጠጣሽው መጠን የበለጠ የሚያስመኝሽ አይደለም። ከጠጣሽው በኋላ እስከ ዘላለም የምትረኪበት እንጂ።
በዛ ወንዝ ብቻዬን እየሄድኩኝ ነበር። ስለ ሰማርያዊቷ ሴት እና ስለ ጌታዋ ሳስብ እና ያ ስሜት የፈጠረብኝ የውስጥ አስገራሚ ንዳድ ከየትም ቦታ ያላገኘውት ረፍት ነበር የሰጠኝ። በዛ ሰዓት ልክ ሐዋርያው ጴጥሮስ “እባክህ ከዚህ ተራራ አንውረድ” እንዳለው ከዚህ የመገለጥ ፍንጣቂ ወደ ፈምስ ጨለማ እንዳልወርድ ተማጸንኩኝ። ግን ባህሪዬ እዛ ለመርጋት የሚያስችለው ልምምድ አልነበረውም።
የምርጥ አስተዳደግ መለኪያ ልጆቻችን ታዋቂ የመሆን ምኞት ሳይኖራቸው ሲቀር ነው። ላይክ የሚናፍቅ እና የእርሱን እና የሰውን (value) በላይክ ብዛት የሚመዝን ልጅ ካሳደግን ፥ አዎ እንደ ሰማራዊቷ ሴት ከዚህ ድካም ፈጣሪያችን እንዲገላግለን እመኛለሁ። ይሄን ውሃ የቀመስን ቀን ቅንጣት ታክል በሰው መወደድ እና መጠላት ለኛ ግድ አይሰጠንም። ይሄን በጥቂት፣ እጅግ በጥቂት ሰዎች ሕይወት አይቸዋለሁ።






ዘመድኩንን በምን አግባብ ነው ከነዚህ ጋጠ ወጦች ጋር ያጃመልከው?ምንም እንኳን በንፅፅር በዚህ ሶሻልና ሚዲያ ከምናውቃቸው በሀቀኝነቱ ብትጠላውም እንኳን በሀሰት መክሰስ የለብህም።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ ወንድሜ፤ የእውነት ትልቅ ትምህርት ነው። በተለይ እንዲህ ያለ ተግሣጽና ምክር ለዚህ ዘመን ሰዎች በእጅጉ ያስፈልገናል። ተባረክ።
ቁም ነገር ያልሆነውን ቁም ነገር እምታደርጉት እናንተው ናችሁ .. በየተውልዱ አዶናይን የመስለ ብዙ አለ ... የአዶናይ የተለየው ሶሻል ሚዲያው ነው
Melkam Amelekaket!
" በሰማሪያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት "
ልቤን የሚያሳርፍ ሃሳብ ስላካፈሉኝ አመሰግናለሁ እግዚአብሄር ይስጥልኝ