ለዓይን ያማረችውን መረጠ
- Mulualem Getachew
- 3 minutes ago
- 4 min read

በየቀኑ ስለ መጪው ግምት እንሰጣለን። በተለይ ሙያተኛ ስትሆኑ ደግሞ ሰዎችም ስለ መጪው ይጠይቋችዋል። አላውቅም ካላችሁ ወይ እየዋሻቹ ነው የሚመስላቸው ወይም እውቀት የሌላቹ። ግን ደግሞ ሁላችንም ስለ መጪው ገምተን ውሳኔ እንሰጣለን።
ሕይወቴ እንዲሰምር ማንን ላግባ?
ምን ባጠና ይሻላል?
ምን ሙያ ልምረጥ ወደፊት የሚያበላ?
ብሰደድ ወይስ ሀገሬ ብቀር?
ዓብይ አህመድ ለሚቀጥሉት ዓምስት አመታት ይቀጥላል ወይስ ይወድቃል?
ዲሞክራቶች ይመረጣሉ ወይስ የአሁኑ አስተዳደር ይቀጥላል?
የመሳሰሉት መጪው ጊዜ ላይ ያተኮሩ ትንበያዎችን በየቀኑ እንሰጣለን። ያን ተመስርተን ሕይወታችንን በዛ መንገድ እንመራለን።
ግን ከዚህ በፊት ያደረግናቸውን ትንበያዎች ብንመለከት ብዙዎቹ አሰቃቂ ናቸው። በአንድ ወቅት የDepartment of Homeland Security ምክትል የነበረ አንድ የሕግ ፕሮፌሰር ነበረኝ። ፕሬዝዳንት ትረምፕ ሲመረጥ ትረምፕ የሚሰራቸውን ታሪኮች፣ ስለሚገነባው አዲስ የፌዴራል ከተማ፣ ስለሚቀነሱ በጀቶች እና የአሜሪካ የበጀት ጉድለትን እንዴት እንደሚፈታ በማብራራት በኢሜል ያልጻፈልኝ ጉድ የለም። እኔም የእርሱን እምነት ሳይ ትረምፕ ሊያደርገው ይችላል ብዬ አስቤ ነበር።
ከሁለት ዓመት በኋላስ ምን ሆነ? በቅርብ ኢሜል አደረኩለት። ትረምፕ ክዶናል አለኝ። ጦርነት ጀመረ። የፌዴራል በጀት ጉድለት በጥቂት ወራት ውስጥ 39 ትሪሊዮን ዶላር ደረሰ። አሜሪካ በዓመት ከምትሰበስበው በላይ ለዕዳ የምትከፍለው በለጠ። የተገነባ የፌዴራል ከተማ የለም። ትረምፕ በብዙ ሙስና እየታማ ነው። ያ ሁሉ ግምት ውሃ በላው። ያ ሁሉ ትንበያ (በጣም አዋቂ በሚባል ሰው የተሰጠ) የተገላቢጦሽ ሆነ።
ዛሬ ከአጎቴ ጋር ስናወራ፣ ስለ ኢትዮጵያ ምርጫ አነሳን። ከዛ ዓብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጣ የተናገራቸውን ንግግሮች፣ ስለዲሞክራሲ የገባቸውን ቃሎች፣ ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ የገለጸልን ተስፋዎችን እና እኛ ደግሞ በምን ደረጃ አምነን ኢትዮጵያችን ተቀየረች ፥ ትንሣኤዋ ደረሰ ብለን ተቀብለን እንደነበረ ራሳችንን ገመገምን። ከስምንት ዓመት በኋላ ከአዲስ አበባ ልዩ ማማር በቀር ሀገራችን እንዳልነበረች ሆና አገኘናት። የቱንም አልገመትንም ነበር። የቱም አልታየንም ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገ ለምርጫ የቀረበለትን ዓብይ አህመድን ብቻ ሊመርጥ እየወጣ ነው። ይሄን ማየት አልቻልንም ነበር።
ነገስ? ከዛሬ ስምንት ዓመት በኋላስ ምን ይሆናል? ከዛሬ ሁለት ዓመት በኋላስ? AI በሁሉም ቦታ እየመጣ ነው። ምንድነው የሚሆነው ነገር?
አላውቅም።
ግን ስለ አንድ መሳጭ ታሪክ ልንገራቹ። ዓለምን ስለወረሰ ሰው። እንዲሁም ለዓለም ጥፋት ምሳሌ ስለሆነ ሰው።
ዘፍጥረት ምክራፍ 13 ላይ ነው ያለው።
የወንድማማች ጦርነት። የታላቅ እና የታናሽ ወንድሞች ጥል።
የአብርሃም እና የሎጥ የእረኛ ሠራዊት በግጦሽ መሬቶች ተጣሉ። ጥንታዊ ጦርነትም ሆነ ዘመናዊ ጦርነት በሪሶርስ መቆጣጠር ላይ ያለ ነው።
አብርሃም ይሄ የእረኞች ጥል ወደ እርሱ እና ወንድሙ ሎጥ ጋር መምጣቱ እንደማይቀር አወቀ። ስለዚህ ወደ ሎጥ ሄዶ እንዲህ አለው። "እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ። ምድር ሁሉ በፊት ህ አይደለችምን፧ ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።" ዘፍ ምዕ 13፥8።
አብርሃም ምን ያህል የወደፊቱን መገመት የሚችል ሰው መሆኑን እወቁ። ሁሉን ነገር ግን አይደለም። የሰውን ባህሪ ነው የገመተው። ሰው ይጣላል። ጻድቅ ነን ስለዚህ ከጥል ነጻ ነን አላለም። ሁለት ሰዎች ተመሳሳይ ነገር የሚፈልጉ ከሆነ መጣላታቸው አይቀርም። አንዳች በመኃላቸው ይሄን የሚያስቆም ጠንካራ ሥርዓት ከሌለ በቀር። አቻዎች ይጣላሉ። አብርሃም ታላቅ ቢሆንም ሎጥን ግን በትህትና እና በልመና ቀረበው። እንለያይ ብሎ ለመነው። አሁንም ታላቅ ቢሆንም የመምረጥን ቅድሚያ ለሎጥ ሰጠው። አንተ ምረጥ እኔ እከተላለሁ አለው።
ሎጥ የእርሱ እና የአብርሃም እረኞች ጥል ሰላም እንደነሳው የሚገልጽ ምንም ነገር የለም። ምንአልባትም ሁልጊዜ አሁን ያለው የወንድማማች ፍቅር ይቀጥላል የሚል የዋህ እይታ አለው ማለት ነው። ምክንያቱም ይሄ ነገር አሳስቦት የመጣው አብርሃም እንጂ ሎጥ አይደለም። አብርሃም ጠብን ከሩቅ አይቶ መጪውን ተነበያ። ለዛም መጠበቂያ ሊያደርግ ተነሳ።
መጠበቂያውንም ሲዘረጋ የእኔ የሚለውን እና የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ቅድሚያ አልሰጠም። ግን መልካም የሆነውን ለወንድሙ፣ ለታናሽ ወንድሙ በማስቀደም አንተ ምረጥ አለው። በስግብግብነት የሚጸና ዘላቂ ሰላም እንደሌለ አውቋልና። ሎጥ አሁንም "አንተ ታላቅ ነህ። አንተን መከተል ነው ያለብኝ" አላለውም።
እሺ ብሎ የወደፊቱን መኖሪያውን ለመምረጥ ተነሳ። የምርጫ መስፈርቱንም ዓይኑን አደረገ። መጽሐፉ ቅዱስ ሎጥ ዓይኑን አነሳ። ለዓይኑም እንደ እግዚአብሔር ገነት የምትመስለውን፣ በግብጽ አምሳያ የተሰራችውን ሰዶምን መረጠ ይለናል። ውበት። እርሱም የዓይን ውበት ነበር መለኪያው።
የወደፊቱን ተነበየ። በትንበያውም መሰረት መረጠ። የዛ ትንበያ ፎርሙላ የዓይን ውበት ነበር። ሳየው ደስ ይለኛል። ሳየው ያምራል። የሚል።
አብርሃም ወደ ምርጫ እና የወደፊቱን መኖሪያ ለመምረጥ አልተጣደፈም። ተረጋጋ። ሎጥ ግን በፍጥነት ተለየው። ይልቁንስ አብርሃም እግዚአብሔር መጥቶ ዓይኑን እስኪያበራለት ድረስ ታገሰ። በመጨረሻም የመረጠው ቦታ ድንጋያማውን ኬብሮን ነበር። ግን ጸሎት እንዳደረገ እና በእምነትም በመደገፍ ያን ምርጫ እንዳደረገ እናነባለን። ግን የዓይን ውበት አልነበረውም ፥ ቤተሰብ ለመመስረት፣ ተረጋግቶ ለመኖር፣ አምላኩን ለማምለክ የሚያስችል ስፍራ ግን ነበር።
በአብርሃም የወደፊት ትንበያ ውስጥ የምንማራቸው በጣም አስገራሚ እውቀቶች አሉ።
የመጀመሪያው ስግብግብነት የለበትም። ለራሱ ቅድሚያ ያልሰጠ ምርጫ ነበር። ታናሽ ወንድሙን አስቀደመ። ምን አልባት ሌሎችን መስማት፣ ታናሽ ቢሆኑ እንኳን ሌሎችን ለማድመጥ መሞከር ስለ ወደፊቱ ለመገመት ይረዳል። ከሁሉ በላይ ሰው ስግብግብ በሆነበት ነገሮች ላይ ጥራት ያለው እይታ አይኖረውም። የቸኮላችሁበት፣ የተስገበገባችሁበት ነገሮች ላይ ግልጽ እና ጥርት ያለው እይታ የላችሁም። ስለዚህ ተረጋጉ። ሌሎች ሊቀሟቹ ከመሰላቹ ተውሏቸው። ይውሰዱት።
ሁለተኛ አብርሃም ዓይኑን አላመነም። ዓይናችን እውነትን የመግለጥ ተልዕኮ ብቻ የለውም። የመጋረድም እንጂ። ሎጥ መጥፊያውን ከተማ መረጠ። ሚስቱን አጣበት። ልጆቹ አስነወሩት። ሎጥ የብዙ መጥፎ ምስሌ እንዲሆን አደረገው ዓይኑ። ፍጻሜውም ጉስቁልና ሆነ። የእርሱ ንጽህና ነፍሱን ቢታደግለትም ደስታ እና ርካታ ግን አልሰጠውም። ምክንያቱም የወደፊቱን በዓይኑ ብቻ መርጧልና።
አብርሃም በእምነት እና በጸሎት ጭምር ተደገፈ። መሰረታዊ የሆኑ የወደፊት ሕይወታችን ላይ ልዩነት የሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ እንረጋጋ። ጸሎት ማድረግ ከቻልን እናድርግ። የማናምን ካለን ደግሞ ቢያንስ የተረጋጉ እና የሰከኑ፣ ታማኝ ሰዎችን እናውራ። ከዛም በእምነት ይሁን ምርጫችን።
አብርሃም የመሬቱ ውበት ሳይሆን የእምነቱ ጥንካሬን መሠረት አደረገ። ብዙ ሰዎች ነገ የሚያበላው ምንድነው ብለው ሙያ እና ትምህርታቸውን ይመርጣሉ። ከዛ ይልቅ ጠንካራ የሆንበትን፣ ጎበዝ የሆንበትን ነገር የምርጫ መሠረታችን ብናደርግ ስኬት ይቀርበናል።
ሎጥ የምርጫውን አካባቢ እና ሁኔታ ለማጥናት ጊዜ አልወሰደም። ቢወስድም በዛ ያሉት ሕዝቦች ምን እንደሚመስሉ፣ ለልጆቹ እንዴት ያለ አካባቢ መሆኑ፣ ሰው አነዋወሩ እንዴት እንደሆነ ግድ አልሰጠውም። አንድን ነገር ስንመርጥ እና የወደፊቱን ስንተነብይ ይሄ ዓለም ውስብስብ መሆኑን አንርሳ። ምርጫችን እና ትንበያችን በብዙ ዙሪያው ባሉ ጉዳዮች ይጠቃል። በብዙ የተያያዙ ጉዳዮች ተጽዕኖ ውስጥ ይወድቃል። ለምሳሌ ይሄን ግለሰብ አምነዋለሁ ብለን ልንመርጠው እንችላለን። ግን ግለሰቡ ምን ዓይነት ጓደኞች አሉት፣ የት ያዘወትራል፣ አብረው እነማን ይሰራሉ፣ ቤተሰቡ ምን ይመስላል እና የመሰሉ ሁኔታዎች ያ ግለሰብ መልካም ቢሆን እንኳ ሊቀይሩት ይችላሉ። ስለዚህ ብዙ ጉዳዮችን ትንታኔያችን ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው።
በመጨረሻም ለምርጫችን ጊዜ እንስጠው። የሎጥ ምርጫ መጥፎ እንደሆነ የአብርሃም ምርጫ ደግሞ ትክክል እንደነበረ ለማየት ጊዜ አስፈልጎታል።