ጠቢብ ነቀፋን ይወዳል
- Mulualem Getachew

- 7 hours ago
- 1 min read
እውነተኛ ርጋታ እና ጠንካራ መሠረት ሲኖርህ ትችት የበለጠ ይጠቅምሃል።
መቶ ፐርሰንት ልክ ብትሆን እንኳን ወደ አስር ፐርሰንት የሚሆን ሰው ከአንተ ተቃራኒ ይቆማል። ወደ አምስት ፐርሰንት የሚሆን ሰው ደግሞ ሊጠላክ ይችላል። በምክንያትም ያለምክንያትም።
ተረድቶ እና አውቆ የሚደግፍህ እንዳለ ሁሉ፤ ምንም ሳይረዳህ እና ሳይገባው የሚወድህ እና የሚደግፍህ አለ።
ዝም ብዬ ሳየው ወደዋለሁ የሚልን ሰው ከተቀበልከው እና በእርሱ ደስ ከተሰኘህ፣ ዝም ብዬ ሳየው ያስጠላኛል የሚልንም ሰው መታገስ እና በእርሱም አለማዘን ይኖርብሃል።
በተለይ የሀገር መሪ፣ የተቋም አመራር ወይም አንዳች ማህበራዊ ኃላፊነት ላይ ስትሆን ፥ ሁሉም ይደግፈኝ የሚል ፍላጎት እብደት ነው።
ከትልቅነት መለኪያዎች አንዱ ትችቶችን፣ ነቀፋዎችን እና ጥላቻዎችን የምናስተናግድበት መንገድ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለ ሰቀሉት ሰዎች በንዴት እነዚህን አጥፋቸው ቢል፤ በግራው ከተሰቀለው ወንበዴ ለይተን ላናየው እንችል ነበር። ከሁሉም የማረክን፣ መሞቱ የምርም ለኛ እንደሆነ ያወቅነው ለሰቀሉት ሰዎች ባሳያቸው ምህረት ነው።
ደካማ መንግስት የሚነቅፉትን እና የሚተቹትን ያስራል።
ለምን?
ምክንያቱም የሚደብቀው፣ የሚሸሽገው ብዙ ክፋቶች አሉት።
ጥፋቱ እንዲታረም፣ እንከኑ እንዲሻሻል የሚፈልግ ማንም ግን ትክክል ቢሆን እንኳ ለትችቶች ክፍት ነው። በሚነቅፉት አይረበሽም። ጠቢብ ነቀፋን ይወዳል እንደሚል መጽሐፍ።



Comments