አጭሩ ረዥም መንገድ
- Mulualem Getachew
- 11 hours ago
- 2 min read

አመጽ አንድን ነገር የማሳኪያው አጭሩ መንገድ ሊመስለን ይችላል። በሕይወት ውስጥ ወለፈንዲ (paradox) ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ ስኬትን በአጭር ማግኘት እና በረጅሙ እና እውነተኛው መንገድ ማግኘት ነው። በየቀን ሕይወታችን ውስጥ በጣም ትልቁ ግፊት የምንፈልገው ነገር ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ የሚለው ስሜት ነው። ሕይወት አጭር ናት ግን ከተሳሳትን ደግሞ የዛ ስህተትን ፍሬ የማጨዲያው ወራት ከሕይወት ርዝማኔ በላይ ረዥም ነው የሚሆንብን። ሁላችንም በሃያዎቹ መጀመሪያ ይሄ አብዮታዊ የመሆን ፍላጎታችን እና ለውጥን በቶሎ የማምጣት መሻታችን ጅል የሆኑ ስህተቶችን አሰርቶናል። ማምጣት የምንፈልገው ለውጥ የግድ ሀገራዊ ብቻ ላይሆን ይችላል። በሕይወታችንም ሊሆን ይችላል።
ለብዙ ዘመን ስለመታገስ ሰምቻለሁ። ግን ትግስት ሲባል ቃሉን እንደመጥራት ቀላል አይደለም። መታገስ ምንአልባትም ከትህትና ቀጥሎ በጣም ከባዱ ባህሪ ሊሆን ይችላል። መታገስ የምንፈልገውን ነገር መርሳት እና በመጣ ጊዜ ይምጣ ማለት አይደለም። መታገስ የምንፈልገው ነገር እንዲሆን በመስራት ግን ያንን ነገር ሕጋዊ ባልሆነ ሁኔታ እና ብዙዎችን በሚጎዳ መልኩ ላለማግኘት መስራት ነው። መታገስ የምንፈልገውን ነገር ባለመርሳት ፥ መሻታችን በራሱ ብቻ የመጠበቅ ጊዜውን እንዳያሳጥረው መጠንቀቅ ነው።
ለምሳሌ ፕሬዝዳንቱ እንዲቀየር የሚፈልግ ሰው ብዙ ሕጋዊ መንገዶች አሉት። ለዛ መስራት ይችላል። ሕጋዊ መንገዶች ተጓዳኝ ጉዳቶችን ለመቀነስ የተቀመጡ ናቸው። እንደ አሜሪካ ባለ ሀገር ውስጥ ደግሞ ፕሬዝዳንቶች በዓመታት ይቀያየራሉ። ሕዝብ አንድን ፕሬዝዳንት ሲመርጥ እኛ ላንስማማ ብንችል እንኳ የሌሎችን መራጮች መብት ግን ማክበር አንዱ የትግስት መገለጫ ነው። ከዛም በላይ ትህትና ነው። እነሱም በአመክንዮ ሂደት (reasoning process) አስበው እና አውጥተው አውርደው እንዳደረጉት ማመን ያስፈልጋል። ሕጋዊ መንገዶችን የሚከተል ማንም እነዛን የማሳመን ሸከም ስለሚኖርበት ፥ እነሱን ለመረዳት ብዙ ርቀት ይሄዳል። በዚህ መኃል እርስ በእርስ መነጋገር፣ የልዩነትን ክፍተቶች የማጥበብ ሥራዎች ይሰራሉ። ትግስት ባላንስድ (balanced) የሆነ ውጤት እንድናገኝ የሚያደርገን ለዛ ነው። በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ እውነት ማናችንም ጋር ተጠቅልላ የለችም። የምንጠላው ወይም የምንቃወመው ቡድን ጋርም እውነት አለ። ለዚህ ነው በትግስት የሚራመድ ማንም ብዙ እውነቶችን ገንዘብ ማድረግ የሚችለው።
በጣም መጋፋት ካሉብን ፍላጎቶች ትልቁ ለውጥን በፍጥነት የማየት ውሳጣዊ ስሜትን ነው። ስንዴ ዘርታችሁ ይሄ ነገር እየበቀለ ነው እንዴ ብላችሁ ቆፍራችሁ አውጥታችሁ አታዩትም። አፈሩን አለስልሳችሁ፣ ወቅቱን ጠብቃችሁ እስከዘራችሁ ድረስ ያ ዘር አፈሩን ፈልቅቆ ቡቃያ ሆኖ እስኪወጣ መጠበቅ (መታገስ) ይኖርባችዋል። የብዙ ድንቅ ለውጦች ቁልፍ ያለው በመታገስ ላይ ነው።
አመጽ የትግስት እጦት ነው። አመጽ የምንፈልገው ነገር ጋር በአጭር የመድረስ ስሜታዊ ኃይል ነው። ውጤቱም የምንፈልገውን ነገር የበለጠ ማርዘም ነው። ጸጸት አንድን ነገር በአጭሩ የማግኘት ሩጫ ሽልማት ነው።
የምንፈልገው ነገር ላይ ውጤቱ ላይ ብቻ ዓይናችንን ከማድረግ ያን ለማግኘት የምንሄድበት ርቀት፣ ጉዞ ጭምር እንዲያስደስተን እና ያ ሂደት (process) የራሱ የሆነ ደስታ እንዳለው ማሰብ ትግስት እንዲኖረን ይረዳል። አቋራጮችን የሚጠቀም ማንም የሚፈልገው ነገር ጋር ቢደርስ ራሱ ያገኘው ነገር ምን እንደሆነ እና ዋጋው የቱን ያህል እንደሆነ አይገነዘብም። ያገኘውን የማጣት ዕድሉ እንደ መጣበት መንገድ ፈጣን ነው። የጥድፊያ ስሜት ከስንፍና ከሚመጣ የመዘግየት ስሜት በላይ አደገኛ ነው። የዘገየ ሰው ያለውን ላያጣ ይችላል። የሚጣደፍ ግን ያለውንም ያጣል። ትግስት ግን ማንቀላፋትም አይደለም። ትግስት ወደ ምትፈልጉበት ቦታ በየቀኑ መሄድ ማለት ነው። ትግስት የማያቋረጥ ፥ ጨርግዶም እንደማይሄድ ወንዝ ነው። ትግስት የሚፈልገውን ነገር ብቻ ሳይሆን ወደ ሚፈልገው ቦታ የመሄጃው መንገድንም የሚፈልገውን ነገር በመጨረሻ እንዲደሰትበት የማድረግ አቅም እንዳለው ይገነዘባል። የትግስት ዕጦት ውጤቱንም ይቀይረዋል።